ጦቢያው የጥበብ ሁዳዴ

ለጥበብ ቤት ሰደቃ ሆነው ለኪነ ጥበብ ቤዛ ከሆኑ የመድረክ ጦቢያዎች መሀከል አብራር አብዶን ሳንጠቅስ ማለፍ አንችልም። አብራር አብዶ ካሉማ…ከአዲስ አበባ ወልቂጤ፣ ከወልቂጤ ሆለታ…በፍቅር ተጸንሶ፣ በሸጋዎቹ ኢማን ተወልዶ፣ በአላህ ሂጅራ መንገድ ታንጾ፣ ከሀዲስ ቁርአን ቀርቶና በሥራ ባህል ተቀርጾ ሲያድግ፤ ለሕይወት ምስጢሩ የኑሮ ሀጃ የእርሱ የታላቅነት ዓቂቃው ፍቅር ብቻ ነው። ስለ ጦቢያው እያነሱ ስለ እርሱ ካወሩማ ሩብ ጨረቃ ጆሮዋን አንጠልጥላ፣ ዛፎቹም ቅጠላቸውን አዝምመው ቁልቁል እያንጋደዱ ልስማ ማለታቸው አይቀርም። በጀነት አፈር ላይ እንደወደቀች ፍሬ ሀድራው የጎመራ ነውና “የዝነኞች”ም ዝናውን ሊያወሳ ይወዳል።

በሀገራችን የቲያትር ፊልምና ሙዚቃ እንዲሁም በውዝዋዜ መድረኮች ላይ ምን ቀረሽ የማይባል ሁለገብ የጥበብ ማቶት፣ የጉብዝናው አፎት ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ደጅ ብቅ ብላችሁ አብራር አብዶ ብትሉ እንኳንስ ሰውና የግቢው ዛፍ ተክሉም ስለ እርሱ ይነግራችኋል። በቲያትሩ ብቻ ከ67 በላይ በሆኑ ቲያትሮች ውስጥ ቀልብን በሚሰልበው የትወና ብቃቱ ታይቷል። ፊልሙን ማን ይቁጠረው…ያ የሚያስገመግመው ብራቅ ድምጹ እንኳንስ የሰውን የአንበሳን ቁጣ ያበርዳል። ውስጡ ገራገር ሆደ ቡቡ ነው። ሲፈልግ ግን የፈለገውን ሆኖ በመተወን እሳትም ውሀም መሆኑን ይችልበታል።

በቲያትር መድረኮች ላይ ብቻም ሳይሆን በእንግድነት በሚቀርብባቸው መድረኮች ላይም ማስደመሙን አያቆምም። በብዙ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተመልክተነዋል። እራሱን ለጥበብ ሰደቃ አድርጎ ሲቀርብ የእርሷም እዝነት ከችሮታው አልሰሰተችበትም። ደግሞ ውዝዋዜውም የግሉ ነው። በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ለረዥም ዘመናት በባህላዊ ውዝዋዜ ሲያሰለጥን ቆይቷል። በእንቅስቃሴያዊ የጥበብ ስልት፤ በኬሮግራፊውም ክህሎቱ የዳበረ ነው። ሁልጊዜም ባይሆን ከነሸጠው ግን በግጥምና ዜማውም ዓልሞ ተኳሽ ነው።

የዓባይ ዳር እንኮይ፣ የሙዚቃውን መዲና ማህሙድ አህሙድን ከሁሉም በፊት ቀርቦ ከጅረት ቅላጼው ፏፏቴ ውስጥ የተስፋ እርስቅነቱን ተመልክቷል። “አልሙ ሌሌ” ማህሙድ ከመነሻው እጅግ የተወደደባት የጉራጊኛ ሙዚቃ ናት። ይህችን ሙዚቃ ግጥምና ዜማዋን ሠርቶ፣ በካሴትም አስቀድቶ እንዲያጠናት የሰጠው አብራር አብዶ ነበር። ፒያሳ ማሕሙድ ሰፈር “ሳባው” ሙዚቃ ቤት እየተመላለሱ አብራርም ማሕሙድን ያስጠናዋል። ተሠርቶም በካሴት ወጣ። ሙዚቃው እጅግ ተወደደና ገጠር ከተማውን አጥለቀለቀው። ታላላቆች በሕይወታቸው ውስጥ የሚሠሩት ሌላ አንድ ታላቅ ሰው ይኖራል። የአብራር አብዶ የታላቅነት ጀማ ፍሬው እንዲህ ከራሱ አልፎ በሌሎቹም ላይ የተንዠረገገም ጭምር ነው።

በውብ ቀለማት ያሸበረቀው ኢትዮጵያዊ ጉራጌነትና የፍቅር ሁዳዴ ኢትዮጵያዊ እስላማዊነት ማደሪያቸው የእርሱ ልብ ነው። የጥበብን ኩታ ለብሶ ከመድረክ ላይ ሲቆም የጥበብ ጥላው በጣራ ግርግዳው ላይ ሁሉ ስዕል ሠርቶ ይታያል። በሀይማኖታዊ ቦታና ጊዜ ሽርጡን አሸርጦ በዱአና በሶላቱ ቀናኢ መንፈሳዊነቱ ከልቡ አልፎ ከፊቱ ላይ ይረብባል። ከአንዱም ሳያጎድልና ሳይጎድል፣ ከሁሉም ሁሉንም እርስቁ ያደረገ ግሩም ኢትዮጵያዊ የጥበብ ልጅ ነው። የእርሱ መታወቂያ ሕዝባዊ ሀገር ወዳድነትና ባህል ሀይማኖቱን አክባሪነቱ ነው። ሕብራዊ ልቦናው የሁሉንም ብሔር ቋንቋ ባህል ወግና እሴት ለማወቅ ሁሌም ያኮበኩባል። በበጎ አድራጎት ሥራዎች ውስጥም ከፊት ከምናሰልፋቸው የጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ እርሱ ነው።

የሰው መውደድን ይስጥህ ብለው ከመረቁ አይቀር እንደ አብራር አብዶ ማለት ነው አንጂ…ማንም ስሙን በክፉ አያነሳውም። ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ስላበረከተው ትልቅ አበርክቶ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖር ኢትዮጵያዊ የሚመሰክረለት ሰው ነው። በ2007 ዓ.ም በፍራንክፈርት ከተማ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከአንድ የጥበብ አዳራሽ ውስጥ ሰብሰብ ብለዋል። ምክንያቱ ደግሞ በዚያ የሚገኘው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኪነ ጥበብ ማዕከል” ለሀገር ባለውለታ የኪነ ጥበብ ልፋተኞች እውቅናና ሽልማት ሊያበረክት መሆኑ ነው። በዕለቱ አብራር አብዶም ከዚያው ተገኝቷል።

በዝግጅቱ መሀል ግን ከመድረኩ ላይ ወጣ። “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” የተሰኘችውን የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንን ድንቅ ተውኔት መተወን ጀመረ። አብራር ያቺን ሰዓት ፈጽሞ አብራርን አነበረም። ሎሬቱ እርሱን እየተመለከተ የጻፈው ይመስላል። አቤት የትወና ብቃት! አብራር ያቺን ሰዓት ተመልካቹን ሁሉ ቁጭ ብድግ አደረገ። በዕለቱም በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ለ42 ዓመታት ያህል ላበረከተው የጎላ ሚና የክብር ሽልማትና ዕውቅና አበረከቱለት።

ሀገር ፍቅርና አብራር አብዶ ውሀና ጀልባ እንደማለት ናቸው። ጀልባ ያለውሀ ባዶ ገንዳ ብቻ ነው። ለአብራር የቅርቡ የሆኑት ድንገት እርሱን ከቤት ከሰፈሩ ፈልገው ያጡት እንደሆነ የት ሊገኝ እንደሚችል ያውቁታል። የሕይወቱ ጀልባ ያለ ሀገር ፍቅር አትቀዝፍም። በግቢና በዙሪያዋ ተገኝቶ አየሯን ካልማገ በስተቀር ሳንባው ሌላ አየር የሚቀበል መስሎ አይሰማውም። ነዳጅ ጨርሳ ወደ ማደያ እንደምትሮጥ መኪና እርሱም ወደ ሀገር ፍቅር ይገሰግሳል። ማሕሙድ ጋር ቅጠሪኝን እንደሚወደው እንደ ጥንቱ አራዳ ፍቅር እርሱም ቀጠሮው ሁሉ ሀገር ፍቅር ቲያትር ነው። ለጨዋታ ቁም ነገሩ ሁሉ ከወዳጆቹ ጋር ለመቀጣጠር ደስ የሚለው ከዚያ ሲሆን ብቻ ነው። “ሀገር ፍቅር ከእናቴ በላይ የኖርኩባት ቤቴ ናት።

እዛ ባልቀጥራቸውና ከሌላ ቦታ ቢሆን እንኳን ታክሲ ይዤ መጀመሪያ የምሄደው ወደ ሀገር ፍቅር ነው። እዚያ ሳልደርስ ሌላ ቦታ መሄድ አልችልም። ሁሉም ነገር ይጠፋብኛል። በመኪናዬ ሆኜ እንኳን ይዛኝ የምትሄደው ወደዚያ ነው። በሀገር ፍቅር ጀምሬ የጨረስኩትም በሀገር ፍቅር ነው።” በማለት በየአጋጣሚው ሁሉ ከቲያትር ቤቱ ጋር ስላለው ተጋምዶ በሀሴት ይናገረዋል። አብራር ኪነ ጥበብን በሀገር ፍቅር ከተዋወቃት ጀምሮ ጡረታ ለመውጣት ጥቂት ዓመታት ብቻ እስኪቀሩት ድረስ ከዚያ ወደየትም ውልፍት ብሎ አያውቅም።

57 ዓመት ሲሞላው በአንድ የግል ጉዳይ ሳቢያ ቀደም ብሎ ከሥራው ለቀቀ። ሥራውን እንጂ ሀገር ፍቅርን ግን ሊለቃት አልቻለም፤ በተቻለው መጠን ሁሉ ወደዚያው ለማቅናት ይቸኩላል። የሚገርመው ደግሞ ገና በጠዋቱ መደበኛ ሠራተኞች እንኳን ሳይገቡ ቀድሟቸው ከስፍራው የሚገኝ መሆኑ ነው። ሀገር ፍቅር የጥበብ ጡቷን ያጠባችው እናቱ፣ ያለእርሷ የማይታየው ሱሱ ናት።

ጊዜው 1970ዓ.ም፤ ወቅቱም የአብዮታዊው የቀይ ሽብር መጋረጃ ተገልጦ ቲያትር መሳይ ገሀዶች የሚታዩበት ነበር። በዚያን ጊዜ አብራር በሀገር ፍቅር ቲያትር ይሠራ ነበር። በዚያን ሰሞንም አንዱ የመንግሥት ካድሬ ከመሬት ተነስቶ እርሱንና አራት ባልደረቦቹን ጥምድ አድርጎ ያዛቸው። የጎሪጥ እያየ በልቡ ያሴርባቸው ጀመረ። ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን የውሸት ካባውን ደርቦና የጠነሰሰውን በኪሱ ሸጉጦ አምስቱንም አስቀፈደዳቸው። እህ…ሲባል “ሀገር ፍቅርን ሊያፈርሱ አሲረው የተነሱ ናቸው” አለ። የውሸት ተንኮል ካባውንም አውልቆ ደረበባቸው። ነገሩ ግን ሳይሳካላት ቀረ። ለሁለት ቀን ያህል ብቻ ታስረው በነጻ ተለቀቁ።

በጡረታ እስከተገለለበት ቀን ድረስ የሠራቸውን ቲያትሮችም ሆኑ ፊልሞች ጠቅሰን የምንደርስበት አይደለም። ከሀገር ውስጥ አማርኛ ኦሮሚኛና ጉራጊኛ እንዲሁም ደግሞ ከውጭ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛና አረብኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ መናገር የሚችለው አብራር አብዶ ጣሊያንኛን ግን አይችላትም። ታዲያ በአንድ የቲያትር መድረክ ላይ ጣሊያናዊ ሆኖ ጣሊያንኛን ከተንጋደዱ የአማርኛ ቃላት ጋር ቀይጦ ሲናገር ተመልክተነው ይሆን…ትወናው ብቻም ሳይሆን ሜካፕ ከተጨመረበት መልኩ ጋር ተደማምሮ ባራቴሪን መሰለ። “የምርም ጣሊያናዊ መስያቸው ከመድረክ ሆኜ ሊጎዱኝ ሙከራ ያደረጉብኝ ሰዎች ነበሩ” በማለት ለበርካታ ጊዜያት ስለታየው ትዕይትና አጋጣሚው ያወሳል።

“ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” አብራር እንደ አቡነ ጴጥሮስ መስቀሉን ከአንገቱ አጥልቆ፣ ቆቡን ደፍቶ ሲተውን ተመልካቹን አስደምሞ በየመድረኩ አፍዝዟቸዋል። ከሰባት ዓመታት በፊት የጊዜው ምርጥ ፊልም ብለን ባጨበጨብንለት “ፍቅር ሲፈርድ” በተሰኘው ፊልም ውስጥ አብራር አይረሳም። ወጋየው ንጋቱ (ወጊሾ) ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዳይሬክት አድርጎ በተወነበት “ትዝብት” በሚለው ቲያትሩ ከአብራር ጋር አብረው ተውነውበታል። የዚያን ሰሞን ወጋየው ሕመሙ ጠንቶበት ነበርና ከዚህች ቲያትር በኋላ በመድረክ ሳይታይ በዚያው አሸለበ። ስለ ጦቢያው አብራር አብዶ ሥራዎች ካነሳን ”ሌተር ፍሮም ዘ ሬድ ሲ” የሚታለፍ አይደለም።

የትወና ችሎታው ባህር ተሻግሯል። የፊልሙ ታሪክ በአንድ ፈረንሳዊ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን፤ መቼቱ ደግሞ በሐረርጌና በጅቡቲ ነበር። ሀገራችንን ጨምሮ በፈረንሳይ ቀኝ ግዛት ስር በነበሩ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ለእይታ ቀርቧል። እንግዲህ እርሱ ያልጀመረውና ጀምሮም ያልጨረሰው የጥበብ ሁዳዴ የለም። በውዝዋዜ፣ ትወና አልፎም እስከ ግጥምና ዜማ ያልደረሰበት፤ ገብቶም ውሀ ያልጠጣብት ቤተ ጥበብ የት አለና…

አብራር አብዶና የመናዊቷ ሴት…በአንደኛው የወጣትነቱ ሰሞን እንዲህ ሆነ፤ አብራር በሚኖርበት ሰፈር ውስጥ ከምትኖር የመናዊት ኮረዳ ጋር ፍቅር ቢጤ ይጀምራል። ሁለቱም እፍ ጥብስ ከማለት አልፈው በፍቅር ክንፍ ወደማለት ገቡ። የትዳር ጎጆ ቀልሰው ከአንድ ጣራ በታች የፍቅር ቄጤማቸውን ለመቁረጥ አስመኛቸው። ድል ያለ ሠርግ ባይሆንም በትንሹ ለኒካ (ለቀለበት ሥነ ሥርዓት) የምትሆን ዝግጅት ማሰናዳት ጀመሩ። የተቆረጠው ቀን ደርሶም ከአባቷ ፊት ቆሙ። አባቷ ግን የሚገባውን ጥሎሽ ካልሰጣችሁ በስተቀር ልጄን አሳልፌ አልሰጥም አሉ።

ምን ችግር አለው በማለት፤ ምን ያህል ነው የምንጥለው? ሲሉ ይጠይቃሉ። አባትም “40 ሺህ ብር” ይላሉ ቆፍጠን ብለው። ይኼኔ ነው መሸሽ…ሰውየው ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ወዲህ ቢሏቸው ወዲያ አሻፈረኝ እንዳሉ በአቋማቸው ጸኑ። በደስታ ልጃችሁን… ብለው ሄደው በተስፋ መቁረጥ እጃቸውን አጣምረው ተመለሱ። መካሪ አያሳጣን…ከፍቅሩ ነጥለው በ40 ሺህ ብር ያስቆዘሙትን አብራር፤ ከወዳጆቹ አንዲት ምክር ብልጭ ተደረገለት። “እርሷም ብትሆን ትወድሃለችና ጠልፈህ አግባት” ይሉታል። የጨነቀ ዕለት ሀረግም መንጠልጠያ ነውና በሀሳቡ ተስማማ።

አንድ ቀን አሳቻውን ጊዜ ጠብቀው በጓደኛው ቮልስዋገን መኪና ቱር! ብለው ከልጅቷ ሰፈር ደረሱ። ጠልፈውም ይዘዋት መጡ እሷም ትወደዋለችና በጠለፋው ተስማምታ ነበር። ተደፈርኩ ብለው የሚያስቡት አባቷ ከሄደች በኋላም አላስቆም አላስቀምጥ አሉት። አብራርና ባለቤቱ ግን በግፊያው እየተወተረተሩም ሦስት ልጆችን ወልደው ሳሙ። በኋላ ተስፋ የማይቆርጡት የአባቷ ንዝነዛ አየለና እሷም አመሏ ከፋ። ከፍቺ መልስ ሁለት ልጆች ለእሷ አንድ ልጅ ደግሞ ለሱ ተከፋፈሉ።

ብዙም ሳትቆይ ጥላ ወደ የመን ሄደችና የቀሩትንም ልጆቹን አምጥቶ ለ15 ዓመታት ያህል እናትም አባትም እየሆነ ለብቻው አሳደጋቸው። ሁሉንም በትምህርት ቦታ ቦታ አሲዞም 1991 ዓ.ም ዳግም በትዳር ተጣመረ። ሁለተኛዋ ሚስቱ እሷም አንድ ልጅ ነበራትና በጋራ አንድ አክለው የአምስት ልጆች አባት ለመሆን በቃ። “ከልጆቼ በላይ አስበልጬ የምወደው ልጄ ነው” ይለዋል ባለቤቱ ከሌላ ስለወለደችው ልጅ ሲናገር። አሁን በአምስት ልጆችና በ8 ያህል የልጅ ልጆች ተከቦ አባትም አያትም ሆኗል።

አርቲስት አብራር አብዶ ባደገበት ቀዬውም ተወዳጅነትና ዝናን የተጎናጸፈ ምርጡና ፈርጡ የጉራጌ ልጅ ኢትዮጵያዊ ነው። እንደ ሀገር በታላላቅ የጥበብ መድረኮች ቆሞ ሲያስደምመን ተመልክተነዋል። ለባህሉ ያለው ውስጣዊ አክብሮት እጅግ የተለየ ነው። ታይቶ የማይጠገበውን ተልሶ የማይሰለቸውን የጉራጌን ባህል በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ከሆኑት መሀከል የሚታየው እርሱው እራሱ ነው። “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” ነውና የትም እንሁን ከወዴት ዞረን የተነሳንበትን ማኅበረሰብ መመልከት ስንችል ያኔ ታላቅነታችን ይጎመራል። በአበርክቶዋችን ከሁሉም ላሳደገን ማኅበረሰብ ብናደላ ውለታውን መለስን እንጂ ዘረኛ ሆንን ማለት አይደለም። አብራርን በተመለከተ ከጉራጌዎቹ መንደር ውስጥ አንድ መማር ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል።

እነርሱ አክብረው ስለተቀበሉት እርሱም በሄደበትና በቀረበበት ሚዲያ ሁሉ ባህላቸውን አጉልቶ ያሳያል፤ ስለ እነርሱም ይጠየቃል ብዙ ጉዳዮችንም ያነሳል። ታዲያ እንደ ሀገር ሁላችንም ባለውለታዎቻችን አክብረን ብንቀበልና የሚገባቸውን ትኩረት ብንሰጣቸው ኖሮ እንዲሁ በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ከሀገራቸው ጋር ከፍ ባሉ ነበር። ማኅበረሰቡን በተመለከተ በሚካሄድ በየትኛውም ኪነ ጥበባዊ ጉዳይ ቸል ብሎ አያውቅም። ለአብነትም በብሔራዊ ቲያትር በተዘጋጀውና በጉራጌ ማኅበረሰብ ውስጥ የሴቶች መብት ተሟጋች በሆነችው “የቃቄ ውርድወት” ትውፊታዊና ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ ከተሳተፉ አንጋፋ የቲያትር ተዋንያን መሀከል አንዱ አብራር አብዶ ነው።

በኪነ ጥበቡም ሆነ በበጎ እንቅስቃሴዎቹ ለሚያደርገው ሁሉ ውለታውን እነርሱም ቢሆኑ አይዘነጉትም። በዚህ ብሩክ እንቅስቃሴው ላደረገላቸው ነገር ከፊቱ ቆመው በምስጋና ሸልመውታል። “አብራር…” ሲሉ በወልቂጤ ከተማ 2 መቶ ካሬ ሜትር መሬት እና 1 መቶ ሺህ ብር አበርክተውለታል። ከሁለት ዓመታት በፊትም ጉራጌዎቹ ባለውለታዎቻቸውን በሚሸልሙበት በ”ኬር” የእውቅናና የሽልማት ሥነ ሥርዓት በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተውታል። ገራገሮቹ ሲወዱት እኮ ወሰን የላቸውም። እንደ ኢትዮጵያዊ ባህላቸው፤ በየመድረኩ ጋቢውን እያለበሱ ያጌጡታል። እርሱም በአጸፋው ከፊታቸው ጎንበስ ብሎ ክብረቱን ፍቅር ባልተለየው ፈገግታ ያጎናጽፋቸዋል።

የቅርቦቹ የሆኑት ሁሉ በተጨዋወቱ ቁጥር የሚቀልዱበት አንድ ቀልድ አለ። የጉራጌ ልጅ መቼስ ሥራ ልማዱ አርማው ንግዱ ነውና “ለማንስ ብለህ ከኪነ ጥበብ ሥራ ጋር ትታሻለህ ለምን አትነግድም” ይሉታል። እርሱም በመልስ ምት “ጉራጌነቱ በዘር አንጂ በሙያ አይደለማ” ሲል ፈገግ ብሎ ይመልስላቸዋል።

ከፍቅራቸው የተቀዳው ፍቅር በሀገሩ የኪነ ጥበብ ደብር ታውሶ ያስታውሳቸዋል። አረፋን ከመስቀል እስልምናውን ከክርስትና በፍቅር አድባር አጣምረው በአንድነት ይመጅኑታል። አረፋውም በረካውን አስከትሎ መጥቷልና ይኼኔ እሱም ከዚያው ደርሷል። በዓመት አንዴ ልጅ ቢመጣ በአረፋው፤ መቼስ ከሕጻን ከአዛውንቱ “የተንቢ!…የተንቢ!” እንኳን በደህና መጣህ፤ ይምጣብኝ! ይምጣብኝ! “…ኔሁ! ኔሁ! አዶድ ከስ” እያሉ በናፍቆት ፌሽታ እየተቀባበሉ ግጥም አድርገው ሲስሙት… በእነርሱው ምርቃት “ኬር ይኹን አረፋ! ኬር ይኹን ኢትዮጵያ! ኬር ይኹን ጉራጌ!” ብዬ ላብቃ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You