መልካም የኢድ አል አድሃ (አረፋ ) በዓል!

የኢድ አል አድሃ (አረፋ ) በዓል በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው። በዓሉ በእምነቱ አስተምህሮ መሠረት ነብዩ ኢብራሂም የአላህ ትዕዛዝን ለመፈጸም በፍጹም ትህትና እና ታዛዥነት ልጃቸው እስማኤልን ለመስዋዕትነት ያቀረቡበት ነው።

የአረፋ በዓል በቅድስቲቱ ምድር መካ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የእምነቱ ተከታዮች ቋንቋ ሳይገድባቸው፣ የቆዳ ቀለም ሳይለያቸው ፣ስፍራና ማንነት ሳያግዳቸው በአንድ አይነት አለባበስ በአንድነት በመሰባሰብ ጥያቄያቸውን ለፈጣሪ የሚያቀርቡበት ነው።

በዓል በሁለት አይነት መልኩ ይከበራል፤ አንደኛው ሃይማኖታዊ መስፈርቶችን ጠብቆ ወደ መካ በመሄድ የሚደረግ የጸሎት ሥነሥርዓት ነው። የሃጂ ተጓዦች ከሚከውኗቸው አበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱና ዋንኛው የአራፋት ተራራን መውጣት ነው። የጤናና የገንዘብ አቅማቸው የፈቀደላቸው ሙስሊሞች ቢያንስ በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ቅድስቲቱን ምድር መካን በሐጅ ሥርዓት መካፈል ይጠበቅባቸዋል።

ከመካ በስተምሥራቅ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘውን ቅዱስ ተራራ መመልከትና ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቶችን በዚያው መፈጸም እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ያዛል። በዚያም ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስም ቅዱስ ቁርአን እያነበቡ፣ ፈጣሪን እያወደሱና እና የምህረት እጁን እንዲዘረጋ እየለመኑ ይቆያሉ። የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ቀን ከብት የማረድ ግዴታም አለበት።

ሁለተኛው ወደ መካ ለመሄድ ዕድልን ያላገኙ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሙስሊሞች የዒድ ሶላት ሥርዓትን በአንድነት በአደባባይ በደመቀ ሁኔታ ያከብራሉ። ከሶላት በኋላ አቅም ያላቸው ሰዎች በግና ሌሎች እንስሳትን በማረድ አቅም ለሌላቸው ጎረቤቶቻቸው በማካፈል በዓሉን በጋራ ያሳልፋሉ።

በየቤቱ አቅም እንደፈቀደ ምግብ አዘጋጅቶ ከዘመድ ወዳጅ ከጎረቤት ጋር መብላት መጠጣትም በዚህ በዓል የተለመደ ነው። ለኢድ አል አድሃ አንድ ሰው ከሚያርደው ከብት ሲሶውን ብቻ እንዲወስድ፤ ሲሶውን ለችግረኞች፣ የተቀረውን ሲሶ ለጐረቤት እንዲሰጥ የሃይማኖቱ አስተምሮ ያዛል።

የአረፋ በዓል የጋራ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች የሚበለጽጉበት፣ አብሮነት፣ መደጋገፍ፣ መረዳዳትና መተሳሰብ የሚጎለብቱበት ነው፤ በእለቱም እነዚህ ሃይማኖታዊ እሴቶች ጎልተው የሚስተዋሉበት ነው፤ አቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን በማገዝ የሚከበር ነው። የመረዳዳት በዓል በመሆኑም በእለቱ ያለው ለሌለው ያካፍላል በዚህም የፈጣሪውን ትዕዛዝ ይፈጽማል።

በዓሉ ከዚህም ባለፈ፤ የእምነቱ ተከታዮች ጥፋት ካለባቸው ለጥፋቱ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ትክክለኛ መንገድ የሚመጡበት ነው። እርስ በእርሱ በመተዛዘን ለችግሮች መፍትሔ የሚሰጥበት ትልቅ ሃይማኖታዊ መድረክ ነው ። የሐጅ ጉዞ ተንኮልን በመጸየፍ የመተዛዘን፣ የመደጋገፍ ትምህርት የሚቀሰምበት ሃይማኖታዊ ጉዞ ነው።

በዚህ ወቅት የሚስተዋለው ሃይማኖታዊ ተግባራት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚከናወን ተግባር ሊሆን ይገባል። ደካሞችን በሁለንተናዊ መንገድ መርዳት ፣ ለጦም አዳሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን ማቅረብ ፣የታረዙትን ማልበስና ወላጅ አልባዎችን መጎብኘት በኢድ አል አድሃ የሚወደድ ተግባር ቢሆንም በሌሎችም ቀናት እነዚህን በጎ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ።

የእምነቱ ተከታዮች መረዳዳትን በዓል ሲመጣ ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ባህል ሊያደርጉት ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ወደታች ወርደው ምእመኑን ማስተማር ለሁለንተናዊ በጎነት የሚሆን ዝግጁነት እንዲፈጥሩ ማነቃቃት ይጠበቅባቸዋል። ለራሳቸውም ሆነ ለወገኖቻቸው የአብሮነት፣ የመደጋገፍ፣ የመረዳዳት እና የበጎነት ተምሳሌት እንዲሆኑ አበክረው መሥራት ይኖርባቸዋል።

መልካም የኢድ አል አድሃ (አረፋ ) በዓል!

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You