ችሎት ውስጥ ዳኛ ላይ ተኩስ የከፈተው ፖሊስ ተገደለ

አንድ ከፍተኛ የኬንያ ፖሊስ በኬንያ ዋና ከተማ ናይኖቢ በሚገኝ ፍርድ ቤት ውስጥ ዳኛ ላይ ከተኮሰ በኋላ መገደሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

እንደዘገባው ከሆነ ዋና ኢንስፔክተሩ የማካድራ ዋና ዳኛ በሆኑት ሞኒካ ኪቩቲ ላይ የተኮሱት ዳኛዋ የፖሊሱ ባለቤት በተከሰሱበት ጉዳይ ውሳኔ ካሳለፉ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ነው።

እኝህ ፖሊስ የተናደዱት ዳኛዋ የባለቤታቸውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረጋቸው ነው ተብሏል።

በምዕራብ ኬንያ ሎንዲያኒ ውስጥ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ የሆኑት ሳምሶን ኪፕቺርቺር ኪፕሩቶ የተባሉት ፖሊስ ጠብመንጃ በማውጣት ወደ ዳኛዋ ተኩሰው እግራቸውን አቁስለዋል።

በችሎቱ ውስጥ ያሉት ሌሎች ፖሊሶች ወዲያውኑ የአጸፋ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ ከፖሊሶቹ ውስጥ አንደኛው ጥቃት አድራሹን ተኩሶ ገድሏል።

በዚህ ግጭት ሶስት ፖሊሶች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ፖሊስ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

ዳኛዋ እና የቆሰሉት ፖሊሶች ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ተስጥቶት ለቀረ እና ለቀረበት ምክንያት በቂ ማብራሪያ ማቅረብ ያልቻለ ግለሰብን ዋስተና ይሰርዛል ብሏል።

ፍርድ ቤቱ “ይህ ውሳኔ ይፋ እንደተደረገ ሰውየው (ፖሊሱ) ወደ ዳኛዋ ተኩሶ ጭኗን አቁስሏል”ብሏል በመግለጫው።

መጀመሪያ ላይ በወጣው ሪፖርት “ተኩስ የከፈተው ተጠርጣሪዋን ያገባው የፖሊስ ባልደረባ ነው” ሲል አመልክቷል።

የብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት እንደገለጸው፤ ፖሊሱ “ባልታወቀ ምክንያት” ወደ ችሎት ገብቷል። ተኩስ እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ሁነቶችን ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አገልግሎቱ ጨምሮ ገልጿል።

በችሎት ውስጥ የተፈጸመው ይህ ክስተት እንዴት ሊሆን ቻለ በሚል ብዙ ኬንያውያን አስደንግጧል።

ፖሊስ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የሆነ ግድያ በመፈጸም ቢከሰሰም ፍርድ ቤት ውስጥ እንዲህ አይነት ክስተት እስካሁን አላጋጠጠም። ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ቤቱን ሠራተኞች ደህንነት ለማስጠበቅ ጥበቃዎችን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጿል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You