በራፋ ስምንት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን ጦሩ አስታወቀ

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ባለችው የራፋ ከተማ ውስጥ እና ዙሪያ የሚያደርገውን ጥቃት እያጠናከረ ባለበት ወቅት ስምንት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን ጦሩ አስታውቋል።

ጦሩ እንደገለጸው፤ የተገደሉት ወታደሮች የኢንጂነሪንግ ቡድን አባላት መሆናቸውን እና በተሳፈሩበት ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ላይ ተጭኖ የነበረው ቁስ ሲመታ ፍንዳታ ተፈጥሮ ነው።

በምዕራብ ራፋ ቴል አል ሱልጣን የተፈጠረው ክስተት እየተመረመረ ነው ብሏል ጦሩ።

የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ወታራዊ ክንፍ ተሽከርካሪው የተጠመደ ፈንጅ ውስጥ መግባቱን እና ፍንዳታው መፈጠሩን ገልጿል።

የእስራኤል ታንኮች በቴል አል ሱልጣን እየገፉ እና ለበርካታ ጊዜ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን የተጠለሉበትን ጠረፋማ ቦታዎች እየደበደቡ ናቸው።

ስምንት ወራትን ያስቆጠረው የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ወደ ተኩስ አቁም እንዲያመራ ዓለም አቀፍ ጫና ቢደረግም እስካሁን አልተሳካም።

በቀጠለው የእስራኤል ጥቃት በጋዛ ከተማ ዳርቻዎች ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ተጨማሪ አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ሮይተርስ የጤና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።

እስራኤል ባለፈው ቅዳሜ እለት ጦሯ በግብጽ ድንበር በምትገኘው ራፋ በመሬት ላይ እና በሃማሴን በተሰሩ ቱቦዎች ውስጥ ተደብቀው የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጦር መሳሪያዎች መያዙን አስታውቃለች።

ጦሩ የሀማስ ታጣቂዎች የሰብአዊ አገልግሎት ቀጣና ከሆነው የማዕከላዊ ጋዛ ክፍል አምስት ሮኬቶችን ባለፈው ሳምንት ዓርብ እንደተኮሱበትም ገልጿል።

ጦሩ ይህ ሀማስ የሰብአዊ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን ለመበዝበዝ እና ንጹሐንን እንደ ጋሻ ለመጠቀም ያለውን ሴራ የሚያሳይ ነው ሲል ከሷል።

የስምንቱ ወታደሮች ሞት የሀመል ፖለቲካ አራማጁ የቀድሞ ጀነራል ቤን ጋንዝ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ያጋጠማቸውን የፖለቲካ ቀውስ ያባብሳል ተብሏል።

ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፍቶ 153 ሰዎች ካገተ እና 1200 የሚሆኑትን ከገደለ በኋላ እስራኤል እየወሰደች ባለው የአጸፋ እርምጃ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ37 ሺህ ማለፉን የጋዛ ጤና ባለስልጣናት ይገልጻሉ።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You