“የአረፋ ኹጥባ” አማርኛን ጨምሮ በ20 ቋንቋዎች እንደሚተረጎም ተገለጸ

– የ1445ኛው የሃጅ ሥነ ሥርዓት ትናንት በይፋ ተጀምሯል

“የአረፋ ኹጥባ” አማርኛን ጨምሮ በ20 ቋንቋዎች እንደሚተረጎም ተገልጿል፡፡ የ1445ኛው የሃጅ ሥነ ሥርዓት በትናንትናው ዕለት በሳዑዲ አረቢያ መካ በይፋ ተጀም ሯል።

በዳሁል ሂጃህ ወር ከሚከናወነው የሃጅ ሥነ ሥርዓት ውስጥ በ9ኛው ቀን የሚፈጸመው “የአረፋ” ሥነ ሥርዓት አንዱ ነው።

ታዲያ ይህ “የአረፋ ኹጥባ” “ሥነ ሥርዓት ዘንድሮ በመላው ዓለም ብዙ ተናጋሪ ባላቸው 20 ቋንቋዎች እንደሚተረጎም የሁለቱ ቁዱሳን መስጊዶች አስተዳደር ሃራማይን ሸሪፈይን አስታውቋል።

በአረብኛ ቋንቋ የሚከናወነው የአረፋ ኹጥባ በመላው ዓለም ብዙ ተናጋሪ ባላቸው 20 ቋንቋዎች በመተርጎምም በዓለም ዙሪያ ለ1 ቢሊዮን ሰዎች እንዲደርስ እንደሚደረግም ተገልጿል።

የአረፋ ኹጥባ ተተርጉሞ ከሚተላለፍባቸው ቋንቋዎች መካከል አማርኛ ቋንቋ አንዱ እንደሆነም ተነግሯል።

በተጨማሪም የአረፋ ኹጥባ በእንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይና፣ ማላይ፣ ኡርዱ፣ ፋርሲ፣ ቻይኒዝ (ማናዳሪን)፣ ቱርኪሽ፣ እና የሩሲያኛ ቋንቋዎች እንደሚተረጎም ታውቋል።

እንዲሁም፣ ሃውሳ፣ ቤንጋሊ፣ ስዊድሽ፣ ስፓኒሽ፣ ሳዋሂሊ፣ ጣሊያንኛ፣ ፖርጉጋልኛ፣ ቦስኒያን፣ ማላያላም፣ ፍሊፒኖ እና ጀርመንኛ ቋንቋዎችን ይተረጉማል ነው የተባለው።

ከ7 ዓመት በፊት የተጀመረውና በአረብኛ ቋንቋ የሚከነወነው የአረፋ ኹጥባ በመላው ዓለም ብዙ ተናጋሪ ባላቸው ቋንቋዎች ተተርጉሞ እንዲተላለፍ ሲደረግ ይፍ ለሰባተኛ ጊዜ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

የ1445ኛው የሃጅ ሥነ ሥርዓት በትናንትናው ዕለት በሳዑዲ አረቢያ መካ በይፋ ተጀምሯል። ትናንት ምሽት ላይም ሀጃጆች ወደ ሚና ጉዞ ይጀምራሉ ተብሏል።

ዓመታዊውን የሀጅ የጸሎት ሥነሥርዓት ለመታደም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሀጃጆች መካ ከትመዋል። በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ሙስሊሞች የሚታደሙት ዓመታዊ ሥነሥርዓት በሃይማኖቱ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

እስልምና ከሚያዛቸው 5ቱ መሰረታዊ ሃይማኖታዊ ግዴታዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ይነገራል።

የአረፋ ኹጥባ ብዙ ተናጋሪ ባላቸው 20 ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለ1 ቢሊዮን ሰዎች እንዲደርስ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You