በዓለም አቀፍ መጠሪያው “ግሪጎሪያን ካላንደር” ይባላል። በኢትዮጵያ ግን በተለምዶ “በፈረንጆች አቆጣጠር” ሲባል በመደበኛ አገላለጽ ደግሞ “እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር” ይባላል። ሁለቱም ግን አይገልጹትም። ዓለም አቀፍ የቀን አቆጣጠር ስለሆነ በአውሮፓውያን አይወሰንም። ዳሩ ግን የፈለሰፉትና የጀመሩት አውሮፓውያን ስለሆኑ በእነርሱ ስም መጥራታችን ስህተት አይሆንም። አውሮፓውን ነጮችን “ፈረንጅ” እያልን ስለምንጠራ በተለምዶ “የፈረንጆች አቆጣጠር” እያልን እንጠቀመዋለን። ይህ ሁሉ የሆነው ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አቆጣጠር ስላላት ያን ያህልም የአውሮፓውያኑ ላይ ትኩረት ስለማይደረግ ነው።
ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አቆጣጠር ቢኖራትም ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና በዕለት ከዕለት ክንውኖቻችን ውስጥ የአውሮፓውያኑን የዘመን አቆጣጠር ለመጠቀም እንገደዳለን። ዛሬ ላይ ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ‹‹ስማርት›› ስልክ የሚጠቀም ሁሉ ቀን እና ሰዓቱን የሚሞላው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነው። በተለይ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ እየተረጎምን ነው የምንጠቀመው። ለምሳሌ፦ ጠዋት 9፡00 (AM) ከሆነ 3፡00 ብለን እንናገራለን ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ከዘመናት በኋላ የኢትዮጵያው አቆጣጠር የመረሳት ዕጣ ፋንታ እንደሚገጥመው ለመገመት ቀላል ነው።
ለጊዜው ግን አንድ ልብ ያልተባለ የሚመስለኝ ነገር በፈረንጆቹ አቆጣጠር የሚዛቡ መረጃዎች ናቸው። መረጃዎቹ የሚዛቡት የፈረንጆች ስለሆነ ወይም አቆጣጠሩ ችግር ኖሮበት ሳይሆን ከአጠቃቀም ችግር ነው። በተለይም በማሽን በሚሰሩ መረጃዎች ሰዎች በግደለሽነት በሚሰሯቸው ስህተቶች ነው። ቀላል ምሳሌ ላንሳ።
ቀን፣ ወር እና ዓመተ ምህረት በቁጥር ሲቀመጡ በብዛት ከትንሹ ወደ ትልቁ ነው። ይሄ ማለት መጀመሪያ ቀን፣ ከዚያ እዝባር ተደርጎ ወር፣ እዝባር ይዘጋና ዓመተ ምህረቱ ይቀመጣል። ወር በእዝባር ውስጥ ይሆናል ማለት ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ ከትልቁ ወደ ትንሹ ሊደረግ ይችላል። ይሄ ማለት ዓመተ ምህረት፣ ከዚያ ወር፣ መጨረሻ ላይ ቀን ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን መረሳት የሌለበት ነገር በቅደም ተከተል መሆኑን ነው።
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ስህተቶች የሚፈጸሙት። አንዳንድ መረጃዎች ላይ ተዘበራርቆ ይቀመጣል። ይህ የሚያጋጥመው በቁጥር ሲቀመጥ ነው። የወሩን ስም በመጻፍ ከሆነ ችግር የለውም። በቁጥር ሲቀመጥ ግን ስህተቶች የሚፈጠሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ለምሳሌ፤ በትልልቅ የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች (ሱፐር ማርኬት) እና በብዙ የግብይት ቦታዎች ላይ ደረሰኝ ሲቆረጥ ቀኑ ተዘበራርቆ ይጻፋል። የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት።
07/06/2024 ይህን መረጃ የተመለከተ ሰው ጁን (ሰኔ) 7 ቀን 2024 ብሎ ነው የሚረዳው። ምክንያቱም በብዛት የተለመደው ከትንሹ ወደ ትልቁ ነው፤ ከቀን ወደ ወር፣ ከወር ወደ ዓመተ ምህረት ማለት ነው። አልፎ አልፎ ከትልቅ ወደ ትንሽ ይደረጋል፤ እንደዚያ እንዳይገምት ደግሞ ዓመተ ምህረቱ መጨረሻ ላይ ይታያል። ዓመተ ምህረቱ ባለ ብዙ ዲጂት ስለሆነ ከቀን እና ወሩ ጋር አያምታታም። ለማሳጠር 24 ተብሎ ከተቀመጠ ግን እሱም ከቀን ጋር ሊያምታታ ይችላል። ለምሳሌ ከዓመታት በፊት 11/10/12 ተደርጎ የተቀመጠ መረጃ ብናገኝ የትኛው ቀን፣ የትኛው ወር፣ የትኛው ዓመተ ምህረት እንደሆነ አይታወቅም።
ይህ መረጃ በብዙ ዓይነት አማራጭ ሊያሳስተን ይችላል። ኦክቶበር (ጥቅምት) 11 ቀን 2012 መሆን ይችላል። ወሩን አስቀድመው ከጻፉት ዴሴምበር (ታህሳስ) 10 ቀን 2012 መሆን ይችላል። ዓመተ ምህረቱን አስቀድመው ከጻፉት ጥቅምት 2011 ወይም ታህሳስ 2011 መሆን ይችላል። ዓመተ ምህረት መሃል ላይ ማድረግ አልፎ አልፎም ቢሆን የተለመደ ስላልሆነ ቢያንስ እሱን እንለፈው።
ስለዚህ ከላይ የገለጽኩት 07/06/2024 የሚለው መረጃ ቀኑን አስቀድመው ከጻፉት ጁን (ሰኔ) 7 ቀን 2024 መሆን ይችላል። ወሩን አስቀድመው ከጻፉት ጁላይ (ሐምሌ) 6 ቀን 2024 መሆን ይችላል።
ይህ የመደናገር ችግር የሚፈጠረው ከወራት ወይም ከዓመታት በኋላ ስናየው ነው። ለምሳሌ፤ ደረሰኝ ከሆነ በተጻፈበት ቀን ካየነው የዕለቱን ቀንና ወር ስለምናውቀው አንቸገርም። ከወራት በኋላ ካየነው ግን ተዘበራረቀ ማለት ነው። መረጃው የግድ አስፈላጊ ቢሆን ተቸገርን ማለት ነው። ከደረሰኝ ያለፈ ሌሎች የታሪክና የሌሎች ሰነዶች መረጃዎች ቢሆኑ የተሳሳተ ሁነት ተመዘገበ ማለት ነው።
ይህ ሁሉ እንዳይሆን ወጥ የሆነ ልማድ ቢኖር ጥሩ ነበር። በማሽኖች ላይ ለማሳጠር ሲባል በቁጥር ይቀመጣል፤ በሌሎች ሰነዶች ግን ወሩ በስም ቢጻፍ ይሻል ነበር። ለምሳሌ ዛሬ በአውሮፓውያኑ ቀኑ ጁን (ሰኔ) 15 ነው። ጁን 15 ቀን 2024 ተብሎ ቢቀመጥ ግልጽ ይሆናል ማለት ነው። ከ15 እና 24 ወር ስለማይሆኑ ይህኛው ቀላል ሊሆን ይችላል። ከጁን 13 በፊት በነበሩት ቀናት ቢሆን ግን 12/06/24 ተብሎ የተጻፈው ያሳስታል ማለት ነው።
ስለዚህ ቢቻል ወሩ በስም ቢጻፍ፤ ቦታ ለመቆጠብ ሲባል በቁጥር ሲጻፍ ግን ብዙዎች በሚገምቱት ቅደም ተከተል (ከትንሹ ወደ ትልቁ ማለት ነው) ቢጻፍ መረጃ እንዳይዛባ ያደርጋል። ይሄ ማለት መጀመሪያ ቀኑን፣ በእዝባር ውስጥ ወሩን ማድረግ ማለት ነው።
የፈረንጆች አቆጣጠር ላይ ያተኮርኩት በተለይም እንደ ደረሰኝ ማሽን አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚሰሩት በዚህኛው ስለሆነ ነው። የኢትዮጵያ አቆጣጠር የሚያገለግለው በሰው በሚጻፉ ነገሮች (በኮምፒተርም ቢሆን) ስለሆነ አስቦ ለመጻፍ ዕድል አለው። ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያው አቆጣጠር ላይም የዚሁ አይነት ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ደብዳቤዎች ላይ “ቀን” ተብሎ እዝባር እየተደረገ ይጻፋል። የዛሬ ደብዳቤዎች ከዓመታት በኋላ የታሪክ ሰነዶች ናቸውና ቀን እና ወር ሊዘበራረቅ ይችላል ማለት ነው።
ለምሳሌ ዛሬ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ነው። ይህ ቀን በደብዳቤ አናት ላይ ወይም በሌላ ሰነድ ላይ 08/10/16 ተብሎ ተጻፈ እንበል። የኢትዮጵያ አቆጣጠር ላይ ብዙ ጊዜ ከቀን ወደ ወር እና ወደ ዓመተ ምህረት የሚጻፈው በቅደም ተከተል ነው። በማሽን የፈረንጆቹ አቆጣጠር ላይ የለመደ ሰው ግን ከላይ እንደገለጽው ወሩን ወይም ዓመተ ምህረቱን እያስቀደመ በብዙ መንገድ ሊደናገር ይችላል ማለት ነው። ስለዚህ ቢቻል ወሩ በስም ቢጻፍ፣ ዓመቱ ምህረቱም ሙሉውን ቢቀመጥ (2016 ተብሎ) ይሻላል። የሁለት ዲጂት መቅረት የሚቆጥበው ጊዜና ቦታ የት ያደርሳል?
በአጠቃላይ የዛሬ ሁነቶች የነገ ሰነዶች ናቸውና ነገ በማያስቸግር መንገድ ቢቀመጡ እንላለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም