የተወለደችው በጎጃም ደብረ ማርቆስ ከተማ ሲሆን፣ ያደገችው ደግሞ በአዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ፣ የከፍተኛ ትምህርቷን በቀድሞ አጠራሩ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ (በአሁኑ ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ) እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከታትላለች።
ወደ ሥራ ለመሰማራትና በሁለት እግሯ ለመቆም ከፍተኛ ፍላጎት ነበራትና የኮሌጅ ትምህርቷን በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ እንዳጠናቀቀች ወዲያውኑ የስራውን ዓለም ተቀላቅላለች። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውራም ሰርታለች።
ዛሬ ደግሞ አልባሳትን የሚያመርተው የኢቲኤም ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናት። የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን የሆነችው ይህች ግለሰብ ወይዘሮ መሰረት አውራሪስ ትባላለች።
የወይዘሮ መሰረት የስራ ጥንካሬ የሚጀምረው እንዲህ ነው። ከኮሌጅ በዲፕሎማ እንደተመረቀች ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወጥታ አሰላ ከተማ ላይ ለሁለት ዓመት፣ በአዳማ ከተማም አንዲሁ ለሁለት ዓመት በድምሩ ለአራት ዓመታት በመምህርትነት አገልግላለች። ከአራት ዓመት የመምህርነት ሥራ በኋላም መንግሥታዊ ባልሆነ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅት የመቀጠር ዕድል ያገኘችው ወይዘሮ መሰረት የመጀመሪያ የውጭ ድርጅት ሥራዋን አሀዱ ያለችው ስልጤ አካባቢ ነበር።
መንግሥታዊ ባልሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ለ15 ዓመታት አገልግላለች። በእነዚህ ድርጅቶች የምታከናውነውን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከአልካን ዩኒቨርሲቲ በሶሺዎሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በልዩ ፍላጎት (special need) አግኝታለች። መሰረት ሁለተኛ ዲግሪዋን በተቀበለች ማግስት ትሰራበት የነበረው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የስራ ጊዜው ያበቃል፤ እሷ ግን ሌላ ድርጅት ፍለጋ አላማተረችም፤ በቀጥታ የግል ሥራዋን ለመስራት ማሰብ ጀመረች።
‹‹ምንጊዜም ቢሆን የራሴን ሥራ መስራት እንዳለብኝ አስብ ነበር›› የምትለው መሰረት፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥራ በምትሰራበት ወቅት የተለያዩ ቢዝነስ ፕላኖችን ታዘጋጅ ነበር። መጠነኛ ክፍያ በማስከፈል ለተለያዩ ሰዎች ትሰራ የነበረው ቢዝነስ ፕላን ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጻለች። በዚህ ጊዜ ነው እርሷም የራሷን ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅታ መስራት እንዳለባት ማሰብ ውስጥ ገባች፤ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት በማሰብ እውን ለማድረግ ማሰብ ጀመረች። ከሰራቻቸው ቢዝነስ ፕላኖች መካከልም የጋርመንት ቢዝነስ ፕላን ውስጧ እንደቀረ ታስታውሳለች።
ትሰራበት የነበረው ድርጅት ሊዘጋ አካባቢ የጋርመንት ሥራ የምትሰራ አንዲት ግለሰብ ለሥራዋ ማስፋፊያ የሚሆን ቢዝነስ ፕላን እንድትሰራላት ትጠይቃታለች። ይህን ጊዜ ነገሮች በልካቸው የተሰፉ ያህል ዕቅድ ተግባር ሊሆን የግድ ሆነ። አጋጣሚው ለመሰረት ምቹና ቀልጣፋ በመሆኑ ቢዝነስ ፕላኑን ስትሰራ የሰበሰበችው መረጃ ዘርፉን ይበልጥ እንድታውቀውና እንድትወደው ዕድል ሰጣት።
መሰረት ብዙ ነገር ለመስራት ያቀደች ቢሆንም፣ ይህን አጋጣሚ ግን ማሳለፍ አልፈለገችም። ውስጧ ስለፈለገው ዕድሉን ለመጠቀም ወስና ዘርፉን ለሚያውቁ ወዳጆቿ አማከረች። ያገኘችው ግብረ መልስም እጅግ አበረታችና ደጋፊ ሆነ፤ የጋርመንት ዘርፉን ለመቀላቀል ማሟላት ያለባትን መስፈርቶች በፍጥነት አሟልታ ጉዞዋን ቀጠለች።
በወቅቱ የስፌት ማሽኖችን ገዝቶ ቤት ተከራይቶ ግብዓቶችን አሟልቶና ሠራተኞችን ቀጥሮ ማሰራት የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ባይኖራትም ከፋይናንስ የበለጠ ወኔና ተነሳሽነት ግን ነበራት።
የጋርመንት ሥራን በፍጹም ፍላጎትና ከውስጥ በመነጨ ተነሳሽነት ለመሥራት የተነሳችው መሰረት፤ መንግሥት አቅም እንደሆናትም አጫውታናለች። ልማት ባንክ ሊዝ ፋይናንስ በሚባል ፕሮጀክት ሥራውን መጀመር የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርላት ተረዳች። ሙሉ አቅሟን አሟጣ ለመጠቀም ከነበራት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ልማት ባንክ የሚጠይቃትን መስፈርት በሙሉ በፍጥነት በማሟላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሽኖችን አግኝታለች።
ሁለት ቤተሰቦቿን ጨምራ ኢቲኤም ጋርመንትን አቋቋመች። ለስራ ፍላጎት እንጂ ሙያው ያልነበራት መሆኑን የተረዳችው መሰረት፣ በኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንስቲትዩት በመግባት ለ15 ቀናት መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ስልጠና አግኝታለች።
ስልጠናውን እንደጨረሰች አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 40 የተለያዩ የስፌት ማሽኖችን ከልማት ባንክ ተረከበች። ማሽኖቹን ይዛ ወደ ሥራ የገባችው መሰረት፤ ‹‹ለሥራው አዲስ እንደመሆኔ ሥራ ውስጥ ለመግባት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፌያለሁ›› ትላለች።
በተለይም ገበያው የሚፈልገውን ከማወቅ ጀምሮ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ገበያ ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። በወቅቱ ለማምረት ያቀደችው የሕጻናት አልባሳት /ማቀፊያ፣ ኮፍያ፣ ካናቴራ፣ ሱሪ፣ ካልሲ/ እና ሌሎችንም በአንድ ጥንድ ለማምረት ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ሥራው ስትገባ ጥሬ ዕቃው ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ሃሳቧን ለመቀየር ተገደደች።
በዚህም ተስፋ ያልቆረጠችው መሰረት፤ ሌሎች የገበያ ፍላጎቶችን ማማተር ጀመረች። በጥናቷም በትልቁ ገበያ መሀል መርካቶ የሴትና የወንድ የውስጥ ሱሪዎች በስፋት ተፈላጊ መሆናቸውን አረጋገጠች።
እነዚህ የውስጥ ሱሪዎች ከአገረ ቻይና በስፋት ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ጠቅሳ፣ ሱሪዎቹን በአገር ውስጥ በተሻለ ጥራት ለማምረት ዝግጅቷን አጠናቅቃ ወደ ማምረቱ ገባች። በዚህ ስራም አንድ ሁለት እያለች 120 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሶስት ፈረቃ እያመረተች ገበያውን መቀላቀል ቻለች።
መሰረት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 ይከሰታል። ይህም አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን በመግታቱ እንደማንኛውም ሰው የመሰረት ሥራና ማሕበራዊ ሕይወት ጭምር ተናጋ።
ይሁንና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኮቪድን ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስን ማምረት የሚችለው ጋርመንት በመሆኑ ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክን ጨምሮ የተለያዩ የሕክምና አልባሳትን በማምረት ሥራዋን ማስቀጠል ችላለች።
‹‹የጋርመንት ዘርፍ በቅብብሎሽ የሚሰራ ነው፤ ኮቪድ 19 ደግሞ ንክኪ አይፈልግም። በመሆኑም በወቅቱ ዘርፉ በጣም እየተጎዳ ነበር።›› ያለችው መሰረት፣ በተመሳሳይ ደግሞ ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ማምረት የግድ ነበር›› ትላለች። በጥንቃቄ የሕክምና አልባሳትን በማምረት ችግሩን ማለፍ መቻሉን አመልክታለች።
በቫይረሱ ምክንያት ድርጅቱ ሲዘጋ እሷ በተለያዩ የጤና ጥበቃ ቢሮዎች በመሄድ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክን ጨምሮ የሕክምና ባለሙያዎች የሚለብሱትን ሙሉ ልብስ ማምረት እንደምትችል አስረድታለች።
በዚህ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎችን ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው የሚሸፍንና ለጥንቃቄ የሚያገለግላቸውን የደህንነት ልብስ ለናሙና ሰርታ አቅርባለች። ልብሱም በየሆስፒታሎቹ በስፋት ተፈለገና 24 ሰዓታት በማምረት ተደራሽ ማድረጉን ተያያዘችው። የአልባሳቱ በከፍተኛ መጠን የመፈለግ አጋጣሚ ችግሩ በተለይም በጋርመንት ዘርፍ ለተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሰፊ የገበያ ዕድል ይዞ የመጣ እንደነበር ነው ያስታወሰችው።
በ2010 ዓ.ም የተቋቋመው ኤቲኤም ጋርመንት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በነበረው ኮቪድ 19 ይበልጥ ተነቃቅቶ አሁንም ድረስ የተለያዩ አልባሳትን እያመረተ ይገኛል። በዋናነት ሲጀምር አንስቶ ያመርት የነበረውን የሴትና የወንዶች ጥራት ያላቸውን የውስጥ ሱሪዎች በስፋት በማምረት ከውጭ የሚገባውን መቀነስ ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ሱፍ ልብሶችን ጨምሮ ቲሸርቶች፣ የአዋቂና የልጆች ቱታዎች፣ ማሊያዎች፣ የጥበቃና የጽዳት ልብሶች፣ የሕክምና፣ የሆቴልና ሌሎች አልባሳቶችንም እንደሚያመርት የጠቀሰችው መሰረት፤ ኢቲኤም ጋርመንት የማያመርተው ምንም አይነት አልባሳት እንደሌሉም ገልጻለች።
ቀደም ሲል ወደ ገበያው በመሄድ ‹‹ምን ይፈልጋል›› በሚል ጥናት በማድረግ ታመርት እንደነበር በማስታወስ፣ በአሁኑ ወቅት ግን በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻሏን ገልጻለች። ገበያው ወደ ጋርመንቱ እንደሚመጣም ነው ያስረዳችው። እሷ እንዳለችው ከደንበኞቿ የሚደርሷትን የተለያዩ ትዕዛዞች መሰረት በማድረግ እንዲሁም ጨረታዎችን በመሳተፍ አልባሳትን እያመረተች ትገኛለች።
ምርቶቹ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ባሉ ክልሎች እየደረሰ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህም መርካቶ አካባቢ በሚገኙ ነጋዴዎች አማካኝነት በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫዎች ተደራሽ እየሆነ ይገኛል። አልባሳቱ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አምስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የኢቲኤም ጋርመንት ሱቅ እንዲሁም በባዛርና ኤግዚቢሽኖችም ለገበያ ይቀርባሉ።
እሷ እንዳለችው፤ ድርጅቱ ለሚያመርታቸው አልባሳት በሙሉ መቶ በመቶ የጥጥ ጨርቆችን ይጠቀማል። ጨርቆቹም አገር ውስጥ ከሚገኙ ጨርቃጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች የሚገኙ ናቸው፤ ሌሎች የጨረታ ሥራዎች ሲመጡም እንደ ትዕዛዙ ከውጭ የሚመጡ ጨርቆችን ከአስመጪዎች እየተረከበች ትሰራለች። ከጨርቆቹ በተጨማሪ ክሮች፣ ማሸጊያዎች፣ ቁልፍ፣ ዚፕና የመሳሰሉት መለዋወጫዎች በሙሉ ከውጭ የሚገቡ ናቸው።
ኢቲኤም ጋርመንት ገበያው የሚፈልገውን ሁሉ የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም፣ በቦታ ጥበት በሙሉ አቅሙ እያመረተ አለመሆኑን ወይዘሮ መሰረት ትናገራለች። በቦታ ጥበት ከሥራ ውጭ የሆኑ ማሽኖች እንዳሉም ጠቅሳ፣ በዚህ የተነሳም የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው 120 ሠራተኞች መካከል ከግማሽ በላይ የሆኑትን ማሰራት እንዳልቻለች አመልክታለች። በአሁኑ ወቅት ለ26 ሴቶችና ለአንድ ወንድ በድምሩ ለ27 ዜጎች ብቻ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሏን ነው ያስረዳችው።
እሷ እንዳለችው፤ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየሰጠ ያለው ትኩረት ጥሩ ነው። ያም ቢሆን የጋርመንት ዘርፉ የበለጠ መበረታታትና መደገፍ ያለበት በመሆኑ ከዚህ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ኢንዱስትሪዎቹ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በስፋት እንዲያመርቱ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ገበያ ጭምር ተደራሽ መሆን የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል።
መንግሥት ላለፉት አምስት ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከገቢ ግብር ነጻ በማድረግ ትልቅ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ያለችው ወይዘሮ መሰረት፣ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንስቲትዩት በበኩሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ እገዛ አድርጓል። አምራች ኢንዱስትሪዎችም በብዙ ተበረታታዋል ብላለች።
የጋርመንት ዘርፍ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል እና በአብዛኛው ሴቶች የሚሳተፍበት እንደመሆኑ ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል ያለችው ወይዘሮ መሰረት፤ እሷም የሥራ ዕድሉን ለሴቶች መስጠቷን ገልጻለች። በተለይ ፋብሪካው በሚገኝበት ሀያት አካባቢ ለሚገኙ ወጣት ሴቶች በሙያው ላይ ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እያሰማራች መሆኗንም ተናግራለች።
ለወጣቶቹ የኪስ ገንዘብ በመስጠት በነጻ ስልጠናውን ትሰጣለች። ወጣቶቹም ባገኙት ስልጠና መሰረት በጋርመንት ውስጥ ከቅንጨባ ጀምሮ እስከ ስፌት ስራ ይደርሳሉ። ይህም አንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን የምትወጣበት መንገድ እንደሆነ በመግለጽ፤ ሌሎች በጎ ተግባራንም አቅሟ በፈቀደላት መጠን እያደረገች እንደሆነ ነው የጠቀሰችው።
እሷ እንዳለችው፤ ኢቲኤም ጋርመንት የመቄዶኒያ ጎረቤት እንደመሆኑ በመቄዶኒያ ለሚገኙ አረጋውያን የተለያዩ አልባሳትን ያቀርባል። ለአብነትም ድርጅቱ በቅርቡ ከሶስት መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አዳዲስ አልባሳትን በመቄዶንያ ለሚገኙ አረጋውያን አበርክቷል። መንግሥታዊ ለሆኑ ማንኛቸውም ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት አጋርነቱን በተግባር ያሳያል።
ኢቲኤም ጋርመንት በቀጣይ ማስፋፊያ በማድረግ ሥራውን በስፋት ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ወይዘሮ መሰረት ጠቁማለች። ከጋርመንት ባለፈ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በማቋቋም ለድርጅቷና ለሌሎች ጋርመንቶች ጨርቆችን አምርታ የማቅረብ ሰፊ ዕቅድም አላት። ይህን ዕቅድ ማሳካት እንዲቻልና ኢንዱስትሪው በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለውን በጎ ተጽዕኖ ከፍ ለማድረግ የሁላችንም ጥረት ይቀጠላል ስትልም አረጋግጣለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም