አርማወር ሀንሰን በግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞ

የህክምና ምርምር ተቋም የሆነው አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የተቋቋመው በሲውዲንና ኖርዌይ ህፃናት አድን ድርጅትና በበርገን ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተደረገ ትብብር እ.ኤ.አ በ1970 ነበር። ስያሜውንም ያገኘው በእውቁ ሳይንቲስትና ለመጀመሪያ ጊዜ የስጋ ደዌ በሽታ መንስኤ ‹‹ማይክሮባክቴሪየም ሊፕሬ›› መሆኑን ባረጋገጠው ኖርዌያዊ ጄራርድ ሄነሪክ አርማወር ሀንሰን ነው።

ኢንስቲትዩቱ ከሀገር ባለፈ ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፉ በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮችን አድርጎ በዓለም አቀፍ መፅሄቶችና ጋዜጦች ላይ አሳትሟል። ዛሬም ወቅታዊና አንገብጋቢ በሆኑ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ የምርምር አብርክቶዎችን እያደረገ ይገኛል።

የአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደሚናገሩት፣ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ይዘታቸውን፣ መልካቸውንና ዓላማቸውን እየቀየሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የአርማወር ሃንሰን የህክምና ምርምር ኢንስቲትዩት ግን ስያሜውንና ዋናውን ተልእኮውን ሳይቀይር አምስት አስርት ዓመታትን ተሻግሯል። ኢንስቲትዩቱ የስጋ ደዌ በሽታ የሰውነት መከላከል ሃይልን ለመመራመር ተብሎ ለአንድ በሽታ ምርምር ነበር የተቋቋመው። ስሙንም ያገኘው ያንን በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ካሳወቀው ኖርዌያዊ ሳይንቲስት ከሆነው አርማወር ሀንሰን ነበር።

ኢንስቲትዩቱ ይህን ሥራ ሲያከናውን ሌሎች ተግዳሮቶች ወደ ኢትዮጵያ መጡና በስጋ ደዌ የምርምር የተጀመረው መሠረተ ልማት፣ የሰው ሃይል፣ የተቋም የምርምር ባህል ወደሌሎችም በቀላሉ መሄድ ስለቻለ ወደ ቲቢ፣ ኤች አይ ቪ፣ ቁንጭር፣ ወባ፣ ተላላፊ ያልሆኑና ወደሌሎች የአንጀት ትላትል በሽታዎች ምርምር በሂደት መግባት ችሏል። እነዚህ የምርምር ሥራዎች አርማወር ሀንሰን የምርምር ተቋም እንደመሆኑ በታዋቂ የዓለም የምርምር መፅሄቶች ላይ የሚታተሙ ናቸው። መታተማቸው ብቻውን ግን ለኢትዮጵያ ብዙ ጥቅም አይሰጥም።

ብዙ ጥቅም እንዲሰጥ አሁንም የውስጥ አሠራር ሥርዓትን ቀይሮ የምርም ውጤት ምክረ ሃሳቦች የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦች ሆነው ተሰንደው ለፖሊሲ አውጪዎች እንዲደርሱ፣ በጤናው ዘርፍ ሥራ ላይ ላሉ የጤና ባለሙያዎች እንዲደርሱና ተግበራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሎ አደረጃጀት ተፈጥሮ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። እነዚህ ሥራዎችም አድገው ኢንስቲትዩቱን ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ አድርሰውታል። ይህ የሃምሳ አራት ዓመት የአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ትሩፋት በተለይ በበሽታ ምርምርና ጥናት ዙሪያ የተገኙ ውጤቶች ለኢትዮጵያና ለዓለም መታወቅ ስላለባቸው ይህን የማስተዋወቅ ሥራ ኢንስቲትዩቱ ሠርቷል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት፣ አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በሃምሳ አራት ዓመታት ጉዞው በርካታ ነገሮችን አሳክቷል። የመጀመሪያው እውቀትን ማበልፀግ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ በ1962 ዓ.ም ሲመሠረት ከታተመው የመጀመሪያው የስጋ ደዌ በሽታ የሰውነት የመከላከል ሃይል እውቀት ጀምሮ አሁን በቀጣዮቹ ሳምንታት ከሚወጡ የምርምር ህትመቶች ሁሉ ለዓለም የሳይንስ ቋት እውቀትን ማበርከት ችሏል። ብዙ ጊዜ ሳይንሳዊ እውቀቶች የሚወጡት ካደጉት ሀገራት ቢሆንም ኢትዮጵያም እንደ አደጉት ሀገራት በእነርሱ ተርታ የሚሰለፍ እውቀት በልጆቿ ሥራ ከኢትዮጵያ ምድር ታወጣለች የሚለውን ኢንስቲትዩቱ አሳይቷል።

ከ 1 ሺ በላይ የሚሆኑና ኢንስቲትዩቱ የወጡ የምርምር ፅሁፎች በታዋቂ የዓለም የምርምር መፅሄቶች ላይ ታትመዋል። የዛሬ ዓመት የወባ በሽታን በሚመለከት ‹‹ኔቸር ሜዲስን›› በሚባል በዓለም አንቱ በተባለ የምርምር መፅሄት ላይ ማሳተም ተችሏል። ኒዮርክ ታይምስም ይህን ሥራ ጠቅሶ በጋዜጣው የፊት ገፅ ላይ ይዞ ወጥቷል። የኢንስቲትዩቱ መሪ ተመራማሪ በአሜሪካ ኮንግረንስ ላይ ተጠርቶ ንግግር እንዲያደርግ ተደርጓል። በተመሳሳይ የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማም ተመራማሪውን ጠርቶ ንግግር እንዲያደርግ ጋብዟል። ከዚህ አንፃር እውቀትን ማበልፀግና ተደራሽ ማድረግ ትልቁ የምርምር ሥራ ስለሆነ አርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በርካታ በሽታዎች እውቀትን የማበልፀግ ሥራ ሠርቷል።

እነዚህ እውቀቶች ታዲያ እውቀት ብቻ ሆነው አልቀሩም። እውቀቶቹ ወደ ሥራ ተቀይረዋል። የዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ ‹‹ኢሳት ፋይፍ›› የተሰኘና ከኢንስቲትዩቱ የወጣ የምርምር ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለህክምና አገልግሎት ወደ ሥራ ገብቷል። በሌላ በኩል ከሰባት ሀገሮች ጋር በጋራ በመሆን ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያን ወክሎ ከአለርት ሆስፒታልና ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ የሚወስደው የህክምና ጊዜ ከሃያ አራት ወር ወደ ዘጠኝ ወር በምርምር እንዲወርድ አድርጓል።

በቅርቡ ደግሞ በተሠራ ሁለተኛ ዙር ጥናትና ምርምር ሥራ መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ ህክምና ከዘጠኝ ወር ወደ ስድስት ወር መውረድ እንደሚችል አሳይቶ ይህንኑ የምርምር ሥራ በታወቀውና ‹‹ላንሴት›› በተሰኘው የምርምር መፅሔት ላይ አሳትሟል። የዓለም ጤና ድርጅትም ይህን ምክረ ሃሳብ ወስዶ መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ የምርመራ ፕሮቶኮልን ቀይሯል። ቲቢ የሁሉም ሀገር በሽታ እንደመሆኑ ይህ የምርመር ተፅዕኖ ዓለም አቀፋዊ ነው። ኢንትቲትዩቱም በዚህ የምርምር ሥራ ለዓለም ጤና መጠበቅ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በተመሳሳይ በኤች አይ ቪ ዙሪያም በኢንስቲትዩቱ በኩል ትልልቅ የምርምር ውጤቶች ወጥተዋል። በጉበት በሽታም ዙሪያ እንደዚሁ ሰፋፊ የምርምር ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህ በሻገር የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የሀገሪቱን የጤና ልማት ሥራ የሚመራ በመሆኑ በምርምር የሚገኙ ምክረ ሃሳቦች ወደ ፖሊሲ ተቀይረው ፤ ፖሊሲዎቹ ደግሞ ወደ ስትራቴጂ ተለውጠው እንዲተገበሩ በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በኩል ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። ለአብነትም ‹‹አኖፍሊስ ስቴፊንሲያ›› በተሰኘችውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተከሰተችውን አዲስ የወባ ትንኝ ዝርያ ለመከላከል ልዩ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ምክረ ሃሳብ ወጥቶና ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

ይህች አዲስ የወባ ዝርያ ፓራሳይት ባህሪዋን ቀይራ ዘረመልን በማጥፋት ለምርመራ ጥቅም ላይ የሚውለውን አፋጣኝ የምርመራ ዘዴን ታልፈዋለች። አትታይም፤ ትደበቃለች። የዚህ አይነት ችግር በኢትዮጵያ ውስጥ በመታየቱ ትኩረት እንዲደረግ በኢንስቲትዩቱ በኩል ምክር ሃሳብ ቀርቧል። በዚህ መሠረት ጤና ሚኒስቴር ፖሊሲ ቀይሮና ስትራቴጂ ነድፎ አዲስ የመመርመሪያ ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርጓል።

ክትባትን በሚመለከት የማጅራት ገትር ክትባት አይታወቁም ነበር። ይሁንና የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች በሰሯቸው ሥራዎች ‹‹ስትሬን ኤክስ፣ ስትሬን 135›› የተሰኙ የማጅራት ገትር ባክቴሪያ አይነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ታውቆ ከዛ በፊት የነበረው ክትባት የሚሸፍናቸው እነዚህን የሚይዝ እንዳልነበርና እነዚህን እንዲይዝ አድርገዋል። በዚህም ክትባቱ ሥራ ላይ እንዲውል እየተደረገ ይገኛል። ኒሞኒያ ላይ የተሠራው ሥራም ተመሳሳይ ነው። የኒሞኒያ ክትባትም አስር የተለያዩ የክትባት አይነቶችን የሚይዝ ነበር። በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች አማካኝነት በተደረገ ምርምር ክትባቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን እንዲይዝና ክትባቱ ገብቶ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚገልፁት በዓለም ዙሪያ ያሉ የመንግሥት የምርምር ተቋማት በመንግሥት ይደገፋሉ። መሠረተ ልማት በመንግሥት ይሠራል። ግብዓቶች በመንግሥት ይገዛሉ። የሠራተኛ ደሞዝ በመንግሥት ይሸፈናል። ነገር ግን ፕሮጀክቶች በሀገር ሀብት ብቻ አይሸፈኑም። በአሜሪካን ያሉ ትላልቅ ተቋማት ድጋፍ አግኝተው ነው የምርምር ሥራ የሚሠሩት። አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትም ከመንግሥት በሚያገኘው በጀት ሰፋፊ የምርምር ሥራዎችን ይሠራል።

ነገር ግን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እንደልምድ በዓለም ዙሪያ የሚወጡ ማስታወቂያዎችን እየተከታተለ ማስታወቂያዎቹ የእርሱን የምርምር መስክ የሚመለከቱ ከሆኑ የምርምር ፕሮፖዛል መነሻ ሃሳቦች ይዘጋጃሉ። እነዚህ መነሻ ሃሳቦች ሰፊ ፕሮፖዛል ተደርገውና ተፅፈው ለነዚህ አካላት ይላካሉ። ከተገመገሙ በኋላ ሚዛን የሚደፉ ከሆነ ይመረጣሉ። ሲመረቱ ገንዘብ ይገኛል። በውድድር ሚገኙ የምርምር ሥራ ማስኬጂያ ገንዘቦችን ነው ኢንስቲትዩቱ ሲያገኝ የኖረው። ዘንድሮም በርካታ ገንዘብ ከተለያዩ ድርጅቶች አግኝቷል።

ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ለሃምሳ አራት ዓመታት ዘልቋል። ይሁንና የሚያከናወናቸውን ሥራዎች በመገናኛ ብዙሃን ከማስተዋወቅ አንፃር ሰፊ ሥራ አልሠራም። ይህንን እንደ አንድ ክፍተት በማየትም ነው በምርምር፣ ፈጠራ፣ ልማትና ምርት ለሀገርና ለዓለም እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ለመገናኛ ብዙሃንና ለክልል የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ከሰሞኑ ያስተዋወቀው። የምርምር ተቋማት ከሕዝብ ጋር አብረው ሆነው እንደመስራታቸው ሥራቸውን ለሕዝብ ካላስተዋወቁ ሕዝብ መጠራጠሩ አይቀርም። ስለዚህ የኮሚዩኒኬሽን ሥራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል።

ከዚህ ባለፈ አርመማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የገጠሙት በርካታ ተግዳሮቶች አሉት። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ለምርምር አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ እንደልብ አለመገኘት ነው። ስለዚህ በዚህ ዘርፍ ያለውን ክፍተት በማየት ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ማድረግ ይገባል። በርካታ ያደጉ ሀገራት እዛው ቤተ ሙከራቸው ውስጥ ተቀምጠው የሚፈልጉትን ነገር ያዛሉ። አቅራቢ ኩባንያዎች የሚፈልጉትን ግብዓት ያመጡላቸዋል። ኢንስቲትዩቱም ወደዚህ ደረጃ መድረስ ይገባዋል። የጨረታ ሥርዓቱም ጠንካራ ሊሆን ይገባል። የግዢ ሥርዓቱም የምርምር ተቋማትን ተግዳሮት ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። ስለዚህ ኩባንያዎች የምርምር ግብዓቶች ክፍተት መኖሩን ተገንዝበው የምርምር ግብዓቶችን ማሟላት የሚችሉ ከሆነ የምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ይፈታል።

ሌላው የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እየገጠመው ያለው ችግር ገንዘብ ነው። ምርምር ሰፊ ገንዘብ ይፈልጋል። ለምርምር የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በጣም ውድ ናቸው። እነዚህ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ ካልተሟሉ የዘረ መል ትንተና ሥራ መሥራት አይቻልም። የክትባት ምርምር ሥራዎችን ማከናወን አይቻልም። የመድሃኒት ምርምር ሥራ መሥራት አይቻልም። የህክምና መገልገያ መሣሪያ ምርምር ሥራ መሥራት አይቻልም። ከዚህ አንፃር ለየትኛው የህክምና ዘርፍ ምርምር ሥራ በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል።

ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከዓመታዊ የተጣራ ገቢያቸው ላይ እስከ 1 ከመቶ ድረስ ለምርምር ሥራ ይመድባሉ። የኢትዮጵያ መንግሥትም ባለፉት አምስት ዓመት በነበረው መረጃ መሠረት እስከ 0 ነጥብ 6 ከመቶ ያህል ለምርምርና ልማት ሥራ መድቧል። ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እንደመሆኗና በርካታ የከፍተኛ ትምህርትና የምርመር ተቋማት እንደመኖራቸው ገንዘቡ በቂ አይደለም። ከዚህ አኳያ መንግሥት ለምርምር ሥራ የሚመድበውን ገንዘብ ከፍ ቢያደርግ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል።

ከዚህ ባለፈ በዓለም ዙሪያ ያሉ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሠራተኞች ስለ ህክምና ምርምር እንዲያስተዋውቁ ኢንስቲትዩቱ ይፈልጋል። የቢዝነስ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ እንደሚሠሩ ሁሉ ምርምርና የሳይንስ ልማት ሀገርን ስለሚቀይር የኢትዮጵያ የምርምር ተቋማት እነርሱ ካሉባቸው ሀገራት ውስጥ ያሉ ተቋማት ጋር አብረው በትስስር እንዲሠሩ መንገድ የሚከፍቱ ከሆነ በዛ ትስስር ውስጥ ሀብት ይገኛል። እነዚህንና መሰል ተግዳሮቶችን ወደ እድል በመቀየር ሥራዎችን በተጠናከረ መልኩ መሥራት የሚቻል ከሆነ ኢትዮጵያ እንድትቀየር ሳይንስና ምርምር ትልቅ መሠረት ይጥላል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You