መድኃኒቶች በጀርሞች በመለመዳቸው በዓለም በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ

አዲስ አበባ፡- የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች በመለመዳቸው የተነሳ በዓለም ላይ በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እንደሚሞቱ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

12ኛው ሀገር አቀፍ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን “የፀረ-ተህዋስያን በጀርሞች መለመድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን ማጠናከር” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተከብሯል።

በመርሀ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ረጋሳ ባይሳ እንደገለጹት፤ የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በሰውና በእንስሳት ጤና እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ችግር ነው።

በችግሩ ምክንያት በዓለም ላይ በየዓመቱ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ምክንያቶች እንደሚሞቱ የጠቆሙት አቶ ረጋሳ፤ ችግሩን ለመቀነስ አስፈላጊው ርምጃ ካልተወሰደ እ.አ.አ. በ2050 የሟቾች ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ ይገመታል ሲሉ አመላክተዋል።

ችግሩ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እስከ 3 በመቶ ወይም 10 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚያስከትል ገልጸው፤ በታዳጊ ሀገሮችም ከ5 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደሚያደርስ አንስተዋል።

የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ከበሽታው ጋር ከተላመዱ የማዳን አቅም እንደማይኖራቸው አስረድተው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ኅብረተሰቡ የታዘዘለትን መድኃኒት በታዘዘው መጠንና ጊዜ በመውሰድ እንዳለበት ገልጸዋል። መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶችም መድኃኒቶቹን ሲያጓጉዙና ሲያከማቹ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመሥራት በመድኃኒቶች ውጤታማነት ላይ መሥራት እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ ረጋሳ፤ መላው ዜጋ መድኃኒቶችን በጤና ባለሙያዎች ትዕዛዝ ብቻ መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት፣ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ችግሩን ለመቅረፍ የሚረዳ የመከላከያና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂክ እቅድ አውጥተው አባል ሀገራት እንዲተገብሩት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በመንደፍ ሀገራዊና ክልላዊ አማካሪ ኮሚቴ እንዲሁም ቴክኒካል ቡድን በማዋቀር ባለፉት ዓመታት በርካታ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች መሥራቷን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ተወካይ የሆኑት ወይዘሮ አስናቀች አለሙ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ መድኃኒቶችን ለማስቀረት የሚረዳ አሠራር ተግባራዊ ተደርጓል። በቀጣይ የቁጥጥር ሥራዎች ከክልሎች ጋር በመሆን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀኑን የጤና ሚኒስቴር፣ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣንና የግብርና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በጋራ አዘጋጅተውታል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You