ወረዳው የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለማከናወን ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል

ጊምቦ ወረዳ:- በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ስድስተኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ::

በክረምቱ ለሚከናወነው አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እየተደረገ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ለማየት በሥፍራው ለተገኘው የጋዜጠኞች ቡድን የወረዳው አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሽባባው እንደገለጹት፤ በወረዳው አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን በሦስት ዙሮች እቅድ ተይዞ ሲሠራ የቆየ ሲሆን፤ በዚሁ መሠረትም በበጋ የተለያየ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ የፍራፍሬ ልማት ሥራዎችና በአንድ ጀንበር ከ300ሺ በላይ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች ተከላ መርሀ ግብር ነው::

በሦስተኛው ዙር ደግሞ በክረምት ወይንም በመኸር እየተደረገ ለሚከናወነው መርሀ ግብር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል::

በአጠቃላይ ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ ለሚከናወነው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በወረዳው ከአራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል በእቅድ መያዙን የጠቆሙት አቶ ተሾመ፤ ከእቅዱ ውስጥም በበጋው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ መከናወኑንና ጽድቀቱ በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን አስረድተዋል:: በቀሪው ጊዜ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች ተከላ እንደሚከናወንም ገልጸዋል::

ወረዳው ካሉት 35 ቀበሌዎች በ30ዎቹ የአየር ላይ ካርታ (ጂፒኤስ) በመጠቀም ከ300 ሄክታር መሬት በላይ ለተከላው መለየቱን አመልክተዋል::

የጉድጓድ ዝግጅቱም ጎን ለጎን እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በክረምቱ ለደን የሚሆኑ ጥድ፣ ግራቪሊ፣ አኬሺያ፣ የተባለ ዝርያ ያላቸው ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመዋል::

በዚህ መልኩ ለመርሀ ግብሩ ከተዘጋጁት አካባቢዎች አንዱ የሆነውን ገሬ ቀበሌ ለጋዜጠኞች ቡድን አስጎብኝተዋል:: የክረምቱ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም ከያዝነው ሰኔ ወር ጀምሮ እንደሚከናወን አስታውቀዋል::

የወረዳው ዓመታዊ ዝናብ ጥሩ የሚባል መሆኑንና ይህም ለሚከናወኑት የፍራፍሬና የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብሮች ተስማሚ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ተሾመ፤ ዝናቡ በበጋ የተተከሉት ፍራፍሬዎች ጽድቀት ጥሩ እንዲሆን እንዳስቻለም አመልክተዋል::

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You