የዘርፈ ብዙ ሙያዎች ባለቤት

ብዙዎች እንደሚሉት፤ በዚች ዓለም ውስጥ ስኬታማ ሆኖ ለመኖር ራስን ማጠናከርም ሆነ ማዳከም የሚፈጠረው በአእምሮ አጠቃቀማችን ልክ ነው:: ያለውን አቅም በአግባቡ የማይጠቀም ሰው ደካማ ነው ሊባል ይችላል። የሚሆነውንና የሚችለውን ፈልጎ የማግኘት ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ደካማ ሆኖ የተፈጠረ ሰው የለም:: ወጣቶችም ይህን በውል መረዳት አለባቸው :: ተስፋ መሰነቅ ለወጣቶች ትልቅ ጉልበት ይሆናል:: ጉልበት የሚሆንለት ግን በዕውቀት ሲመራ ነው። አንድ ወጣት ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ራሱን መፈተሽ ይኖርበታል። ምንድነው የምችለው ? ምንድነው የማልችለው ? ብሎ አቅሙን መለካት አለበት::

ወጣቶች ስኬታማ ለመሆን በመጀመሪያ የራእይ ሰው መሆን እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ያነሳሉ:: ራእይ የለሽ ሰው ካለበትና ከደረሰበት አልፎ ለመሄድ አይፈልግም :: ይህ የሚሆነው ዓይኑ የተተከለው በገሃድ በሚታየው ላይ ብቻ በመሆኑና በዓይነ ህሊናው የሚያየው እይታ ስለሌለው ነው:: ባለ ራእይ ሰው ባለበት ሳይወሰን ወደ አዲስ ነገር ለመግባት ይገሰግሳል :: ራእይ የለሽ ሰው አይነ ስጋው ብቻ የተከፈተና በፊቱ ያለውን ብቻ እንዲያይ የሚገደድ ሰው ነው:: ባለ ራእይ ሰው ግን አይነ ህሊናው የተከፈተ በመሆኑ በፊቱ ካሉት በእጁ ከጨበጣቸው እውነታዎች ባሻገር በማየት ያልማል።

ሕልም ተስፋ እና ትጋት በአንድ መንፈስ ከሄዱ መጨረሻቸው ድልና ስኬት ነው የሚባለው እንዲሁ ዚም ተብሎ አይደለም ሕልማቸውን ሰንቀው በትጋት የተራመዱ እና የስኬት ማማ ላይ የተቀመጡ ብዙዎቹ ስላሉ እንጂ። ዛሬ ስለ ስኬት ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም። የዚህ ሳምንት የወጣቶች አምድ እንግዳችን የዘርፈ ብዙ ሙያዎች ባለቤት ሐኪም ደራሲና ሰዓሊ የሆነው ወጣት ሚካኤል አርጋው በመሆኑ አንጂ።

ዶክተር ሚካኤል አርጋው ውልደቱ በመዲናችን አዲስ አበባ ሲሆን ቤተሰቦቹ በሥራ ምክንያት ወደ ሀዋሳ በማቅናታቸው የልጅነት ግዜውን ያሳለፈው በሀዋሳ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሀዋሳ ኤስ ኦ ኤስ (SOS) ትምህርት ቤት መከታተል ችሏል። በትምህርት አቀባበሉ ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል የነበረው ሚካኤል በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በህክምና ትምህርት በዶክትሬት ድግሪ ተመርቋል። በአሁኑ ወቅትም በቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ሀገሩን እያገለገለ ይገኛል።

አስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት መጥቶ የዩኒቨርሲቲ ምደባ እስኪደረግ ድረስ የሕክምና ትምህርት የመማር ከልጅነት ጀምሮ የነበረ ህልምም ሆነ ፍላጐት እንዳልነበረው የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ ከልጅነት ጀምሮ የነበረው ሕልም አርክቴክት የመሆን እንደነበር ነገር በመጨረሻ ሰዓት ከራሱና ከቤተሰቡ ጋር በመመካከር የሕክምና ትምህርት ለመከታተል ወስኖ ትምህርቱን እንደቀጠለ ይናገራል።

ዶክተር ሚካኤል የአስተዳደግ ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር ሲናገር፤ የሚፈልገውን ነገር ምክንያታዊ ሆኖ ማስረዳት እስከቻለ ድረስ የሚፈልገው ነገር ሁሉ እየተደረገለት እንዳደገ ይናገራል። ይህም በትምህርት ውጤታማ ሆኖ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በጎ ተፅዕኖ እንደነበረው ያስረዳል።

ወጣቱ ዶክተር ሚካኤል አርጋው ሕክምና ባለሙያ ብቻ አይደለም ሰዓሊ ጭምር እንጂ፤ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ ሙሉ ትኩረት በሚፈልገው የሕክምና ትምህርት ዘርፍ ላይ ሆኖ የስዕል ሥራውን እንዴት መቀጠል እንደቻለ ሲናገር፤ ከልጅነት ጀምሮ በትምህርት ቤት እንደ የቤት ሥራ የሚሰጡ የስዕል ሥራዎችን እንደ ትልቅ ፕሮጀክት ወስዶ ይሰራ እንደነበር ተናግሮ፤ ነገር ግን ለስዕል ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም ሰዓሊ እሆናለሁ የሚል እምነት እንዳልነበረው ይገልጻል።

ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲደርስ መሠረታዊ የስዕል ትምህርት (technical drawing) ይሰጥ ነበር የሚለው ዶክተር ሚካኤል፤ በዚህን ወቅት ለስዕል የነበረው ፍቅር ይበልጥ እንደጨመረ ይናገራል። በወቅቱ የጓደኞቹን ጨምሮ የተለያዩ የማስመሪያ ስዕሎችን በመሥራት ይሰጥ እንደነበር ይህም ለስዕል ያለው ፍቅር ይበልጥ እንዲጨምር እንዳደረገው የልጅነት ግዜውን አስታውሶ ይናገራል።

በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የሕክምና ትምህርት ተቋርጦ ለዘጠኝ ወራት ቤት በተቀመጠበት ወቅት በልጅነት ይሰራ የነበራቸውን የስዕል ሥራዎች ደግም በመጀመር የሰራቸውን የስዕል ሥራዎች በማህበራዊ ሚድያ በመጋራት ከተመልካች ባገኘው በጎ ምላሸ ያገኘው ዶክተር ሚካኤል፤ በዚህ የተመልካች አስተያየት በመነሳት የስዕል ሥራውን አጠናክሮ ስለመቀጠሉ ይናገራል።

ከዚህ በተጨማሪ ወደ ፅሑፍ ሥራው ወይም ወደ ደራሲነት ስለመጣበት አጋጣሚ ሲናገር፤ “የሕክምና ትምህርት ብዙ ግዜ የሚወስድ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት የሚሆን ሰዓት የማይገኝበት ቢሆንም ከልጅነቱ ጀምሮ ሁለገብነትን በጣም ስለሚወድ በአንድ ሙያ ተገድቦ የመኖር ዓላማም ሆነ ፍላጐት አልነበረኝም የተለያዩ ነገሮችን መሞከር አዲስ ነገር ማየት ያስደስተኛል በዚህም ምክንያት አዲስ ነገር ለማወቅና ለመማር ግዜ አላጣም ነበር” ይላል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሶስተኛ ዓመት ተማሪ ከነበረበት ግዜ ጀምሮ ወደፊት ለሕትመት ይሆናሉ በሚል የተለያዩ ፅሑፎችን መፃፍ እንደጀመረ የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ መፅሐፍ እንደ መዝናኛው ሆኖ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በማስኬድ ሥራዎቹን ከቆይታ በኋላ ለህትመት እንዳበቃቸው ይናገራል።

ዶክተር ሚካኤል በመጀመሪያ ለህትመት ስለበቃውና በሁለት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛና በእንግሊዝኛ ስለተዘጋጀው (የተሸሹ ድምጾች) ስለተሰኘው መፅሐፉ ሲናገር፤ የስነልቦና ወይም የስነ አዕምሮ ጤና ላይ ትኩረት ያደረገ ይዘት ያለው መፅሐፍ መሆኑን ገልፆ፤ በተጨማሪም የፍልስፍና ዕይታዎችን ያካተተ የልብወለድ ዓለምን የሚዘክር መፅሐፍ መሆኑን ይናገራል።

በሌላ በኩል አንድ የሕክምና ባለሙያ የራሱን ሕመም ደብቆ ወይም ችላ እያለ በየዕለቱ የስነልቦና ሕመም የገጠማቸው ስዎች እያስተናገደ ስላለበት ሁኔታ መፅሐፉ እንደሚዳስስ የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ ይህም የሕክምና ባለሙያው የሚከፍለውን መስዋዕትነት ዋጋ ለመስጠት በማሰብ የተደረገ ስለመሆኑ ይናገራል።

ማህበራዊ ጉዳይ፣ የገቢ ሁኔታ፣ ጥሩ ያልሆኑ የልጅነት ልምዶች፣ አፈጣጠርና መሰረታዊ የጤና ሁኔታዎች የአንድን ሰው የአእምሮ ጤንነትና ስነልቦና ሁኔታ ሊወስኑ እንደሚችሉ የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ መፅሐፉ በመላው ዓለም ሆነ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከወረርሽኝ በላይ ወጣቱን እየተፈታተነው ያለውን የስነ አዕምሮ መታወክ (mental health burden) በተመለከተ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት በመስጠት የሚተርክ እንደሆ ያስረዳል።

ዶክተር ሚካኤል እንደሚናገረው፤ የሕክምና ትምህርት ቤት ብዙ ነገር የሚታይበት ነው። በአዕምሮ ፈተና ያለበት ብዙ ወጣቶች ለተለያዩ የአዕምሮና የስነልቦና ችግሮች ሲጋለጡ የምንመለከትበት ነው። የዚህ ምክንያት የሕክምና ትምህርት ከባድ ኃላፊነት መሸከም የሚጠይቅ ስለሆነ ነው። በዚህ ሁሉ ፈተናዎች ይገጥማሉ፤ በተጨማሪም ሕመም ገጥሞት የሚመጣ ሰው ማከም ወይም ደግሞ አድምጦ ምላሽ መስጠት በራሱ የሚፈጥረው ከፍተኛ የአዕምሮ መጨናነቅ አለ፤ መፅሐፉ እነዚህን ጉዳዮች በማንሳት ትምህርት ለመስጠት የተዘጋጀ ነው ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ የሕክምና ትምህርት ውስጥ ያሉ ወጣቶች እንደ ሌሎች ጓደኞቻቸው በመጨዋወት በተለመደው መልኩ የወጣትነት ግዜያትን ለማሰለፍ ዕድል የማይሰጥ እንደሆነ የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ በዚህ ምክንያት ብዙ የሕክምና ተማሪዎች የአዕምሮ መታወክ ውስጥ ይገባሉ ስለዚህ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለሚያጋጥማቸው ፈተና የስነልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ በሚረዳ መልኩ የተዘጋጀ መፅሐፍ መሆኑን ይገልጻል።

በሌላ በኩል ወጣቱን ጨምሮ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ በተለያየ የሕይወት መስክ የተሰማሩ ግለሰቦች በስነ አዕምሮ ችግር በጣም እየተሰቃዩ እንዳለ የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ ያለ አዕምሮ ጤና የሌለ በመሆኑ ይህንን ከግምት በመውሰድ ሁሉም ሰው በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢ ችግር ስለሆነው የአዕምሮ ጤና ግንዛቤ እንዲኖረው በማሰብ ለሕትመት እንዳበቃው ይናገራል።

ሌሎች በአካል ላይ የሚያጋጥሙ ሕመሞችን በመድሀኒት ወይም በቀዶ ሕክምና ማከም ይቻላል የሚለው ዶክተር ሚካኤል፤ የስነ አዕምሮ ችግር ግን ውስብስብና በቀላሉ የሚታከም ባለመሆኑ ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ነው ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልገው፤ ከዚህ አንፃር መፅሐፉ የስነልቦናና የስነ አዕምሮ ጉዳዮችን በተመለከተ በዝርዝር የሚተነትን በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል።

በአዕምሮ ጤና ቀውስ ማሻሻያ ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ በማሰብ ይህንን መፅሐፍ ለአንባቢያን ለማቅረብ እንደተነሳሳ የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ የአዕምሮ ጤና ሲቃወስ የግለሰብ የየዕለት ተግባር፣ ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት እና የሰውነት ሁኔታ ላይም ተጽዕኖ አለው:: ዕድሜ፣ ጾታን፣ የገቢ ሁኔታን ወይም ዘር ሳይለይ ሁሉም ሰው ለአእምሮ ጤና መታወክ በሽታ የመጋለጥ ዕድል አለው ከዚህ ለመዳን ትክክለኛው አማራጭ ቅድመ ጥንቃቄ ነው ይላል።

የስነ አዕምሮ ተፅዕኖ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ የሚለው ዶክተር ሚካኤል፤ ከዓለም የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞ ዲጂታል ሚዲያው በአዕምሮ ጤና ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። ከዚህ አኳያ መፅሐፉ ችግሩን ለማቅለል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይናገራል።

ዶክተር ሚካኤል እንደሚናገረው፤ በአሁኑ ወቅት መፅሐፉ በዓለም አቀፍ ዲጂታል መገበያያ በሆነው አማዞን (Amazon) የተለያዩ ግምገማና መመዘኛዎችን አልፎ ሽያጭ ላይ ይገኛል። በዚህ ዓለም አቀፍ ከሆኑ አንባቢዎች አበረታች የሆኑ አስተያየቶች እንዳደረሱት ይናገራል።

መፅሐፉ ለሀገር ውስጥ አንባቢያን በተለያዩ አመራጮች ቀርቧል የሚለው ዶክተር ሚካኤል፤ ዲጂታል በሆነ መንገድ በፅሁፍ አፍሮድ በተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ (Afroread mobile app) እንዲሁም በድምፅ ተራኪ በተሰኘ (Teraki Mobile app) መተግበሪያ ላይ ይገኛል። በሀገር ውስጥም ጥሩ ተቀባይነት አግኝቶ እየተነበበ እንደሚገኝ ይናገራል።

ወደፊት ይህንን መፅሐፍ ወደ ምስል በመለወጥ በፊልም የማምጣት ሀሳብ እንዳለው የሚናገረው ዶክተር ሚካኤል፤ በጥሩ ባለሙያ መፅሐፉ ወደ ፊልም ፅሑፍ ተቀይሮ ሰዎች በሚረዱት መልኩ በምስል እንዲመጣ የማድረግ ከፍተኛ ፍላጐትና እንዳለው ይገልጻል።

የሶስት ሙያዎች ባለቤት የሆነው ዶክተር ሚካኤል፤ ስለወደፊት እቅዱ ሲናገር፤ የያዛቸውን የሙያ ዘርፎች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግ ያስረዳል። በስዕል ሙያው የራሱን የስዕል ማሳያ የመክፈት፣ በሕክምና ትምህርቱም ቢሆን በሁለት መስኮች የስፔሻሊት ትምህርት የመውሰድ፣ በድርሰቱ እንዲሁ የተለያዩ መፅሐፍትን በተለይ የአዕምሮ ጤና ላይ ያተኮሩ የፅሑፍ ሥራዎችን በስፋት የመሥራት እቅድ እንዳለው ተናግሯል።

ዶክተር ሚካኤል በመጨረሻም ለወጣቶች ባስተላለፈው መልዕክት፤ ነገ ቃል አልተገባልንም ምን እንደሚፈጠር አናውቅም መኖር ያለብን ዛሬን ነው። ስለዚህ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ሕይወትን ቀለል አድርጎ መምራት ያስፈልጋል። ወጣቶች የስነ አዕምሮ ጤናቸውን ጉዳት ላይ ከሚጥል ነገር ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው። በተጨማሪም ባላቸው ነገር ደስተኛ በመሆን ግዜው ላመጣው የታይታ ዓለም ባለመገዛት ኑሯቸውን መምራት እንደሚገባቸው ተናግሯል።

ክብረአብ በላቸው

 አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You