እኛስ ከከተማዋ ጋር ምን ያህል ዘምነናልን?

አዲስ አበባ በእርጅና ብዛት ጎብጣ መነሳት ከተሳናት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከተሰሩ ዘመናትን የተሻገሩት ደሳሳ ጎጆዎቿ እርጅና ተጭኗቸዋል። በጉያዋ ያሉ ቤቶች ግድግዳዎቻቸው ፈራርሶ፤ ጣራዎቻቸው ወይቦ አዲስ አበባን ከዕድሜዋ በላይ አስረጅተዋታል፡፡

ቤቶቹ ሰዎች ይኖሩባቸዋል እንጂ ከንፋስም ሆነ ከፀሃይ እንዲሁም ከዝናብ ማንንም አያስጥሉም፡፡ በበጋም ሆነ በክረምት በእነዚህ ቤቶች ውስጥ መኖር ስቃይ ነው፡፡ በተለይም በመሃል የከተማዋ ክፍል የሚገኙት ቤቶች ከተማዋ ስትቆረቆር ጀምሮ የነበሩ በመሆናቸው ለመፍረስ አንድ ሀሙስ ብቻ ነበር የቀራቸው፡፡

ፒያሳና እና አራት ኪሎን የመሳሰሉ መሃልኛው የአዲስ አበባ ክፍል ችምችም ብለው በተሰሩ ቤቶች የታጨቀ፤ ከዘመኑ ጋር ያልዘመነ፤ ከ130 ዓመታት በፊት በነበረው የቀጠለ እና በአሁኑ ወቅት ያለውን የአኗኗር ሁኔታ የማይመጥን ነው፡፡

ፒያሳን የመሳሰሉ አካባቢዎች ስማቸው ገናና ቢሆንም በገቢር ግን ስማቸውን የሚመጥን ገጽታ የላቸውም፡፡ ምንም አይነት ዘመናዊነት የማይታይባቸው ኋላቀር አካባቢዎች ከመሆናቸውም በላይ በስመ አራዳ ለዘመናት ድህነት ተጭኗቸው የቆዩ ናቸው፡፡

ዛሬ ግን የ137 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ አዲስ አበባ መልኳን እየለወጠች ነው፡፡ አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደ መሆኗ ይህን የሚመጥን ልማት እየተከወነላት ይገኛል፡፡

ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮች ባማረ መልኩ እየተሰሩ ነው፡፡

በአምስት አቅጣጫዎች እየተከናወነ ያከለው ኮሪደር ልማት ከተማዋን ከመሰረቱ የሚቀይር ነው፡፡ የተሽከርካሪ መሄጃ አስፋልቱን እና የእግረኛ መንገዱን ስፋት ለተመለከተውም ዓለም አቀፍ ደረጃን ባሟላ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ያመላክታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹‹አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ካሉ ዋና ከተማዎች ከኬፕታውን በስተቀር የሚወዳደራት ከተማ እንደማይኖር በተግባር የምናሳያችሁ ጉዳይ ነው፡፡›› ሲሉ አዲስ አበባ እንደስሟ ውብ እና አዲስ የምትሆንበት ጊዜ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ይኸው ጉዳይ አሁን በተግባር እየተገለጸ ነው። ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያሉት መንገዶች እጅግ ባማረ ሁኔታ ተገንብተዋል፡፡ ዛሬ ፒያሳንና አራት ኪሎን የተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን እስኪጠራጠር ድረስ መገረሙ አይቀሬ ነው። የአስፋልቱ ጥራት፤ የእግረኛ መንገዶቹ ስፋትና ጥራት፤ የመናፈሻዎቹ እና አረንጓዴ ስፍራዎቹ ውበትና ድምቀት፤ የዘንባባዎቹ ማራኪነት በሙሉ እጅን አፍ ላይ ለመጫን የሚያስገድዱ ናቸው፡፡

ለወትሮው በአቧራና በእርጅና ብዛት ተጎሳ ቁለው የነበሩ ሕንጻዎችና ፎቆች ዛሬ ታድሰው አዲስ ሙሽራ መስለዋል፡፡ በየስርቻው ተወትፈው የነበሩ ቅራቅንቦዎች ተወግደው የፒያሳና የአራት ኪሎ ውበት ወለል ብሎ እንዲታይ ሆኗል፡፡ ብዙዎች እሪ ይሉበት የነበረው እሪ በከንቱም ዛሬ ስሙን አድሶ ሰላምና ውበት ፈሶበታል፡፡

አፍን በሚሰነፍጥ ሽታው የሚታወቀው ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያለው መንገድም ጽዳቱ ተጠብቆለታል፤ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችም ተገንብተውለታል፡፡ በአጠቃላይ በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ዓለም ከደረሰበት የዘመናዊ ከተማ መስፈርት አንጻር አዲስ አበባም መሰለፍ ጀምራለች፡፡

ሆኖም ከአዲስ አበባ መዘመን ጋር እኛ ነዋሪዎቿ ምን ያህል ዘምነናል ? ወይም ለመዘመን ተዘጋጅተናል? የሚለው ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ነው።ይህንን ጥያቄ ልናነሳ የቻልነው ደግሞ ከልማቱ ጎን ለጎን የታዘብናቸው ጉዳዮች ስላሉ ነው፡፡

የመጀመሪያው ጉዳይ የጽዳት ጉዳይ ነው፡፡ አንዲት ከተማ ዘመናዊ የሚባለው ወይንም ደግሞ ነዋሪዎቿ ዘምነዋል የሚባሉት ለጽዳት ትኩረት ሲሰጡ ነው፡፡ ጽዳት ዘመናዊነት መገለጫ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እየዘመነች ባለችው ከተማ በተቃራኒ ከተማዋን የሚያቆሽሹና ውበቷን የሚያጎድፉ ተግባራት አሁንም ይስተዋላሉ፡፡

ውብ በሆኑት እነዚህ ጎዳናዎች በየቦታው የሚሸኑ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ እንኳን ለመሽናት ቀርቶ ለመራመድም በሚያሳሳው ጎዳና ያለምንም ሀፍረት ቆመው የሚሸኑ ሰዎች ዛሬም አልጠፉም፡፡

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፤ የአፍሪካ መዲናና ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በየሜዳው መጸዳዳት እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ከተሞች ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መቀመጫነት ሊመረጡ የሚችሉት ጽዱና ውብ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ጽዱና ውብ ያልሆኑ ከተሞች ለማንኛውም አገልግሎት ተመራጭ አይሆኑም። ስለዚህም ከ50 ዓመታት በላይ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሆና የቆየችው አዲስ አበባ በጽዳቷ ምክንያት መቀመጫነቷ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ ባዶ ሜዳ ላይ መጸዳዳትና አካባቢን መበከል በርካታ የሆኑ ውስብስብ ችግሮችን የሚያስከትል ነው፡፡ ባዶ ሜዳ ላይ የሚጸዳዳ ማህበረሰብ ክብር የለውም፡፡ የሰው ልጅ ተደብቆ ወይም ተከልሎ ከሚያደርጋቸው ተግባራት መካካል አንዱና ዋነኛው መጸዳዳት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሲሆን ክብርን ያጎድፋል፤ ከሰው ልጅ ተርታ አስወጥቶ ከእንስሳት ተርታ ያሰልፋል፡፡

ቀደም ባለው ጊዜ አብዛኞቹ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች የተቀበሩት ከከተማዋ ምስረታ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ከማርጀታቸውም ባሻገር አሁን ያለውን የሰው ቁጥር የማስተናገድ አቅም ለማስተናገድ የሚያስችሉ መጸዳጃ ቤቶች አልነበሩም፡፡ በዚህም ላይ በየጊዜው በሚሰሩ ግንባታዎች አማካኝነት ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎቹ ለብልሸት ስለተዳረጉ በአግባቡ ፍሳሽን የማስወገድ አቅም አልነበራቸውም፡፡

በዚህም ምክንያት አካባቢዎቹ በየጊዜው በሚፈነዱ መጸዳጃ ቤቶች የሚጥለቀለቁና አፍንጫ በሚሰነፍጥ ጠረናቸውም የሚታወቁ ናቸው። አግባብ ባይሆንም ሰዎች የቆሸሹትን የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለማቆሸሽ ብዙም ሞራል ጥያቄ የሚያነሳባቸው አልነበረም፡፡

ዛሬ ግን ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች እየተገነቡ ነው። ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ባለው ኮሪደር እንኳን ከ20 የማያንሱ መጻዳጃ ቤቶች እየተገነቡ ነውለ። ስለዚህም በየቦታው መጸዳዳት በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ ከአዲስ አበባ ዘመናዊት ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ስለዚህም እየዘመነች ካለችው ከተማ ጋር አብሮ ለመጓዝ እራስን ማስተካከል ይገባል፤ በየቦታው መጻዳዳትም ነውር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ከዚሁ ከጽዳት ጋር በተያያዘም ሶፍት፤ ወረቀት፤ የውሃ መያዣ ፕላስቲክ (በተለምዶ ኃይላንድ) የመሳሰሉትን በየቦታው መጣልም ከእንግዲህ ወዲያ በቃ ሊባል ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ክእንግዲህ ወዲያ አበቦችንና አትክልቶችን እንጂ ቆሻሻዎችን መሸከም አትችልም፡፡ ስለዚህም ቆሻሻዎችን እየተዘጋጁ ባሉ የቆሻሻ ማስቀመጫዎች ውስጥ በመጣል የከተማዋን ጽዳት መጠበቅ የሁሉም ነዋሪ ግዴታ ሊሆን ይገባል፡፡

ሌላው እየዘመነች ያለችውን ከተማ ውበቷ እንዳይጎላና ጎዳናዎቿ እንዳያምሩ እንቅፋት እየሆነ ያለው ተሽከርካሪዎችን በዘፈቀደ ማቆም ነው፡፡ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያለው ሰፊ ጎዳና መኪኖችን እንደልብ የሚያንሸራሽርና ለመኪናዎች መቆሚያም የራሱ የሆነ ፓርኪንግ ታስቦ የተሰራለት ነው፡፡

ሆኖም ከቀድሞው ባህል ያልወጡ አሽከርካሪዎች በየቦታው መኪናቸውን በመገተር የትራፊክ ፍሰቱን ሲያስተጓጉሉና እነሱም ለቅጣት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ከመኪና መቆሚያ ውጭ እንደፈለጉ አቁሞ መሄድ የሚፈቀድ አይደለም፡፡ የእኛዎቹ አሽከርካሪዎች ግን ከዘመናዊነት በተፋታ መልኩ ዛሬም መኪናቸውን በሰፋፊ ጎዳናዎች ላይ ከማቆም ባህል አልተላቀቁም፤ ከዘመናዊነት ጋር አልተዋወቁም፡፡

በእግረኞች በኩል የሚታዩ ክፍተቶች ደግሞ በሰፊው እና ባማረ መልኩ የተሰሩ እግረኛ መንገዶችን ትቶ በመሃል አስፋልት መጓዝ አሁንም ያልተላቀቀን አባዜ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ሲከናወን ለእግረኛ መንገዶች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በርካታ ሰዎችን አዝናንቶ እንዲጓዙ የሚያደርጉ ስፋታቸው ከ10 ሜትር ያላነሱ የእግረኛ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ እነዚህ መንገዶችም በአበቦችና በዘንባባ ዛፎች ያጌጡ ናቸው፡፡ ሆኖም አንዳንድ እግረኞች ይህን ያማረ ቦታ ለቀው አስፋልት ውስጥ ሲጓዙና እራሳቸውንም ለአደጋ ሲያጋልጡ ተመልክተናል፡፡

በትራፊክ አደጋ ዙርያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት እስከ 84 በመቶ የሚደርሱ አደጋዎች የሚከሰቱት ከእግረኞች ጋር በተያያዘ ነው። ይህ ደግሞ እግረኞች የተፈቀደላቸውን መንገድ ትተው የተሽከርካሪ መስመር ውስጥ በመግባታቸው የሚፈጠር ችግር ነው፡፡

በእርግጥ ቀደም ሲል አብዛኞቹ መንገዶች ሲሰሩ የእግረኛ መንገዶችን ታሳቢ አድርገው ስለማይሰሩ በቂ የእግረኛ መንገዶች አልነበሩም፡፡ ስለዚህም እግረኞች አስፋልት ውስጥ ገብተው ለመጓዝ ይገደዱ ነበር፡፡

በእግረኛ መንገዶች አለመኖር ሳቢያ የሚደርሰውን አደጋ የሚተነትን ጥናታዊ ጽሁፍ ይፋ እንዳደረገው በአዲስ አበባ አምስት ሺሕ 784 ኪ.ሜ ርዝመት ያላቸው መንገዶች የተገነቡ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኹለት ሺሕ አምስት መቶ 39 ኪ.ሜ ብቻ የአስፋልት መንገዶች እንደሆኑና ከአስፋልት መንገዶች 35 በመቶ ብቻ የእግረኛ መንገዶች ሲኖራቸው እነርሱም ከፍተኛ ጥገና የሚፈለጉ ናቸው።

የትራፊክ አደጋን ከሚያስከትሉ ጉዳዬች መካከል የእግረኛ መንገድ አለመኖር ከፍተኛውን ሚና እንደሚወስድ በዚህም በተለያዩ ጊዜ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል 84 በመቶ የሚሆነው የሚደርሰው አደጋ እግረኞች ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም በ2010 በተሰበሰበ መረጃ መሰረት ከደረሰ የትራፊክ አደጋ ሦስት ሺሕ አራት መቶ 59 መካከል በእግረኞች ላይ የደረሰ አደጋ ኹለት ሺህ ዘጠኝ መቶ 14 እንደሆነና ከዚህ እግረኞች በእግረኛ መንገድ ላይ ሲጓዙ አራት ነጥብ አራት በመቶ፣ የእግረኛ መንገድ በሌለበት ግራቸውን ይዘው ሲጓዙ 10 በመቶ እንዲሁም የእግረኛ መንገድ በሌለበት የመንገዱን ቀኝ ጠርዝ ይዘው በመጓዛቸው የደረሰ አደጋ 4 አራት ነጥብ ስምንት በመቶ መሆኑንም በጥናቱ አመላክተዋል።

ዛሬ ግን ይህ ችግር ተቀርፏል፤ በቂ የእግረኛ መንገዶች ተሰርተዋል፡፡ ስለዚህም አንድ እግረኛ የተፈቀደለትን መንገድ ለቆ አስፋልት ውስጥ ገብቶ እንዲሄድ የሚያደርገው አስገዳጅ ሁኔታ የለም፤ አያድርገውና አደጋ ከተከሰተም ጥፋቱ የእግረኛው ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

በአጠቃላይ እየዘመነችው ካላችው ከተማ ጋር አብሮ ለመጓዝ ዘመናዊ አስተሳሰብና ተግባራት ያስፈልጋሉ፡፡ በተለይም ከጽዳት፤ ከፓርኪንግ እና ከእግረኛ መንገድ አጠቃቀም ጋር ያሉ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችንና ተግባራትን ማስወገድና ከዘመኑ ጋር አብሮ መጓዝ የግድ ይላል፡፡

እስማኤል አረቦ

 

Recommended For You