መቻል 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራል

በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ አንጋፋ ከሆኑ የስፖርት ክለቦች መካከል አንዱ መቻል ነው። ክለቡ ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት ለመጠበቅ እና ዳር ድንበርን ለማስከበር ደምና አጥንታቸውን በሚገብሩ የሠራዊቱ ክፍል የተመሰረተ ነው። ዘመናት ያስቆጠረው ክለብ አሁን ካለበት ደረጃ እንዲደርስ ዋጋ የከፈሉ በርካታ የሠራዊቱ አመራሮችና አባላት ጥቂት አይደሉም። አንድ ክፍለ ዘመን ለመድፈን ሁለት አስርት ዓመታት በቀሩት ጉዞ የስም ለውጥን ጨምሮ በርካታ መሰናክሎችን በማለፍ፤ አሁንም ከሀገር አልፎ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፍ ትልቅ የስፖርት ክለብ ለመሆን ወጥኖ እየሠራ ይገኛል።

ንጉስ አጼ ኃይለስላሴ በ1916ዓ.ም ለጉብኝት ወደ አውሮፓ ባቀኑበት ወቅት የተመለከቱት ስፖርታዊ ውድድር ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ሠራዊቱን በአዳዲስ ወጣቶች በማደራጀት የውስጥ ውድድሮች እንዲካሄዱ በማድረግ እስከ 1936ዓ.ም በስፖርት እንቅስቃሴ መቆየቱን ታሪክ ያወሳል። በሠራዊቱ ክፍሎች ውስጥ የሚካሄዱት የስፖርት ውድድሮች ዳብረውና አድገው ከአስራ አንድ ዓመት በኋላ መቻል ስፖርት ክለብ ተብሎ በ1938ዓ.ም በስፖርት ማህበርነት ተመዝግቦ እስከ አሁን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ታሪካዊውና አንጋፋው የስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ የስፖርት መሰረት ከጣሉት ውስጥ ቀዳሚ ነው። እንደ ቀደምትነቱና ለስፖርቱ እንዳበረከተው አስተዋጽኦም በሀገርና አህጉር አቀፍ ደረጃ ትልቅና ዘመናዊ የስፖርት ክለብ ለመሆን የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከጀመረም ሰነባብቷል። ውጥኑን እውን ለማድረግ ደግሞ እንደ መልካም አጋጣሚ ዘንድሮ የ80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን ኢላማ አድርጓል። ክብረ በዓሉም ታሪካዊነቱንና ትልቅነቱን በሚያሳይ እንዲሁም ለውጤታማነት መሠረት በሚጥሉ ክንውኖች እንደሚሆንም ተነግሯል።

የጀግኖች መፍለቂያ የሆነው የስፖርት ክለብ የ80ኛ ዓመቱን ክብረ በዓል ‹‹መቻል ለኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ሃሳብ ከሰኔ 1 እስከ 30/2016 ዓ.ም ድረስ አሁን ካለበት አንድ እርምጃ ወደ ፊት ማሻገር የሚችል አላማን አንግቦ በተለየዩ ክንውኖች ይካሄዳል። ከተግባራቱም መካከል የክለቡን ታሪክ የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም እና መጽሄት ማዘጋጀት፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር፣ የፓናል ውይይት፣ ክለቡን የማስተዋወቅ ሥራ፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የድጋፍ ስምምነቶችን መፈጸም፣ ለክለቡ መዝሙር በማውጣት፣ በእውቅና ፕሮግራም እንዲሁም ስፖርታዊ ውድድሮችን በማድረግ በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቱንም የቦርዱ አመራር ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚገኙበት ትልቅ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራምም ተዘጋጅቷል። በተጨማሪም ከተቋማት ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ ከባለሀብቶች፣ ከድጋፍ አድራጊ አካላት እና ከማሊያ ሽያጭ ገቢ ለመሰብሰብም ታቅዷል።

የስፖርት ክለቡ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቮሊቦል፣ እጅ ኳስ እና ቅርጫት ኳስን የመሳሰሉ ስፖርቶችን በማቀፍ እየተወዳደረ ሲሆን፤ አጠናክሮ ለማስቀጠል ብዙ ሥራዎች እንደሚያከናውንም ቦርዱ ገልጿል። በአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያንና አፍሪካን ማኩራት ከቻሉት ከሻምበል አበበ ቢቂላ እና ማሞ ወልዴ አንስቶ በርካቶችን በማፍራት እስካሁን ዘልቋል። በቦክስ ስፖርትም ትልልቅና ሀገርን መወከል የቻሉ ቦክሰኞችን አፍርቷል። በእግር ኳስም ጠንካራ የሴቶችና ወንዶች ክለብን በመገንባት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ተፎካካሪ ክለብ ሆኖ እየተወዳደረ ይገኛል።

የስፖርት ክለቡ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጸሃይ ሽፈራው፣ ክለቡ በአዲስ መልክ ሲደራጅ ዋና ዓላመው ታሪኩን በማስቀጠል ትልቅ ክለብ ማድረግ ሲሆን፤ ቦርዱ ስብሰባዎችን በማድረግ የክለቡን ቁመና መገምገሙን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት የክለቡን የ5 ዓመት እቅድ በመንደፍ ከየት ተነስቶ የት መድረስ አለበት የሚለው ግብ መቀመጥ ችሏል። መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት በሚችል መልኩ የክለቡን አደረጃጀት በመፈተሽ ባለሙያዎች የሚመሩትና እውቀት ያለበት የስፖርት ክለብ እንዲሆን መሠራቱንም ጠቁመዋል።

ክለቡ 80ኛ ዓመቱን ሲያከብር በፋይናንስ ራሱን የሚችልና ጠንካራ ክለብ የሚያደርገውን ሥራ እንደሚያከናውንና የራሱን ስታድየም እና ዘመናዊ አደረጃጀትን የሚከተል ለማድረግ ሰፊ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ምክትል ሰብሳቢው አክለዋል። የቦርዱ ዓላማም ክለቡን ወደ ነበረበት ታላቅነት መመለስና ከራሱ አልፎ የኢትዮጵያን ስፖርት መቀየር እንዲችል ማድረግ ነው። በአንድ ወር የክብረ በዓሉ ክንውን ውስጥ ክለቡን የማገዝ፣ የማደራጀት፣ ከሠራዊቱ ጋር የማቆራኘት ሥራዎችም ይከናወናሉ።

የዚሁ እንቅስቃሴ አንድ አካል የሆነው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት ትልቅ የሩጫ ውድድር የተዘጋጀ ሲሆን፤ ሰኔ 23/2016ዓም ይካሄዳል። የወንዶች እግር ኳስ ክለቡ ደግሞ ከዩጋንዳው ክለብ ኪታራ ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን እንደሚያደርግ ተጠቅሷል። በተጨማሪም አንድ በዓለም ላይ ታዋቂ የሆነ ስፖርተኛ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ልምዱን እንዲያካፍል ይደረጋል። ታዋቂ አርቲስቶች ከቀድሞ የመቻል እና ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች እንዲሁም፣ ባለሀብቶች ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም በመርሀ ግብሩ መካተቱ ተነግሯል።

ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You