ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ጥሩ አድርገው ከተናገሩና ድንቅ አድርገው ከጻፉ ጸሀፍያንና ሀሳብያን መካከል የሆመር ‹ኢትዮጵያ የገነት ሀገር ሕዝቦች› የሚለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ይሄን ለመነሻነት ላንሳ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን፣ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ኢትዮጵያን አጉልተው ያሳዩን ጥንታዊ ጸሀፍቶች ጥቂቶች አይደሉም። ከዚህ ምልከታ አንጻር ጥንታዊ የግሪክ ጸሀፍቶች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።
ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚያወድሱ ሌሎቹ ጸሀፍቶች ከማለፌ በፊት ግን ለመነሻ ርዕሴ የሆመርን እውነታ መንካት ይጠበቅብኛል። ከክርስቶም ልደት በራቀ ዓመታት ውስጥ ሰውነትን ያገኘ ይሄ ሰው ከዓለም ሀገራትና ሕዝቦች ልቀንበት ሀሳቡንና ብዕሩን ወደ እኛ ያነጣጠረበት ጉምቱ ምክንያት እንዳለው የማያሻማ ጉዳይ ቢሆንም ስለ ሰላምና ፍትህ፣ ስለ ነጻነትና እኩልነት በቆሙ ነፍሶች ተማርኮ ኢትዮጵያዊነትን በዚህ ልክ መግለጹ ባሰብኩት ቁጥር ኩራትን የሚያላብሰኝ እውነታ ነው።
ይሄ ደራሲ ለሰላምና ለፍቅር፣ ለአንድነትና ለኅብረብሄራዊነት በምንሰጠው የላቀ ዋጋ ብዕሩን ባደማ ቁጥር ኢትዮጵያዊ ትካዜ የሚወድቅበት ጸሀፊ ነበር። ከልደተ ክርስቶስ በፊት በጻፈው ‹ወዲሴ› ድርሰቱ ላይ ‹በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕዝቦች እጅግ የተራቀቁ፣ እጅግም ኃያላን፣ የሚያማምሩና የተከበሩ ሕዝቦች ናቸው› ሲል ስለ ጥቋቁሮች ሀበሾች ዘመን ተሻጋሪ እውነታን አጋርቷል።
ግሪካዊው ጸሀፍት አኪለስ በበኩሉ ..ፕሮሚስስ ባውንድ በተባለ መጽሀፉ ላይ አይኦ የተባለችን ገጸባህሪ ወደጥቁር ሕዝቦች ሀገር ሄደች..አይቶፕስ ከተባለ ወንዝ አጠገብ ወደሚኖርበት ኢትዮጵያ ተሻግራ ሄደች ሲል ጽፏል። ፍራንሲስ ቤከንም ‹አዲሲቷ አትላንቲስ› ሲል ዛሬም ድረስ በኩራት የምንናገረውን የቁልምጫ ቃል በብዕሩ ከትቦልናል። ስለጥንተ ኢትዮጵያ ሲነሳ ይሄ ሰውና አባባሉ ቀድሞ በመነሳት የዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ገላጭ እውነታ ሆኖ አብሮን በመጓዝ ላይ ነው።
በሀሳቡ፣ በጽሁፉ ያወሳት ሌላኛው አቴንሳዊ ሰው ዴዎድረስ ነው። በሩቅ ሆኖ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ ስብዕናና ተፈጥሮ ካጠኑና ከተረዱ ጥቂት ሀሳባውያን አንዱ ነው። ሲኮሎስ፣ ሄርኮለስና የወይን አምላክ ባኬስ ሶስቱም አማልዕክት በኢትዮጵያውያን አማኝነትና ቸርነት፣ ደግነትና ርህራሄ እጅጉን ይደነቁ እንደነበር ያወጋ ደራሲ ነው። በነገራችን ላይ ከላይ የዘረዘርኩላችሁንም ሆኑ ስለኢትዮጵያ የተነገሩ ሌሎች ታሪኮችን ለማረጋገጥ አሁኑኑ ታሪክ መዳሰስ ትችላላችሁ። አንዳቸውም ፈጠራ አይደሉም። እንደ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በግሪክ ጸሀፍት አብዝተው የተጠቀሱና በድርሰቶቻቸው የተወደሱ ሀገርና ሕዝብ የለም።
ሌላው የቬዛንታይኑ ጸሀፊ ፕላስደስ ነው። ኢትዮጵያውያን በፍትሀዊነታቸው በአማልዕክት ይወደዳሉ፣ ይወደሳሉ፣ ይከበራሉ ሲል ጠቅሶናል። ፕሮክለስ የተባለው ፈላስፋ በበኩሉ ..‹ይቺ ፍጹማይት ሀገር በልቦለድ የተፈጠረች ሳትሆን በእውነት የነበረች የልባሞች ሀገር ናት፣ ይህም የኢትዮጵያ ሀገር ግዛት ነው› ሲል መስክሯል።
የእስልምና መስራች ነብዩ መሀመድም በእውነትና በፍትሀዊነት የጸናች አንድ ሀገር ሲሹ ኢትዮጵያን ነው ያገኙት። ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ፣ በዛ እውነትና ፍትህ አለ፣ ሰውን የማይበድል እርሱም የማይበደልባት ንጉስ አለ› ሲሉ ዛሬም ድረስ በኩራት የምናወጋውን ወግ ተናግረውልናል። ዓለም ላይ እጅግ በርካታ ሀገራትን በኃይል በመቆጣጠርና በስሙ በመቀየር ተወዳዳሪ የሌለው ታላቁ እስክንድር እንኳን ስለ ኢትዮጵያ ሲያስብ አቅም ያጣበትን ታሪክ እናገኛለን።
‹እነሆሜር፣ እነፕላስደስ፣ እነዴዎድረስ የመላዕክት መቀመጫ ያሏትን ሀገር በምርኮ መያዝ እንደምን ይቻለኛል? ሲል የተናገረበትን ጥንተ ታሪክ ማስታወስ ይቻላል። ከሁሉም ታላቁ መጻፍ ቅዱስ ‹ኢትዮጵያ መልኩን ነበር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይቀይር በማያልፍ ቃሉ መስክሯል።
ከላይ በሰማናቸው ታሪኮች ስር እናድፍጥና እስኪ ከራሳችን በራሳችን ለራሳችን ጥያቄ እናንሳ። መልካችን ምን አይነት ነበር? የባዕድ ሀገር ሕዝቦችን ለትካዜ ጥለን ስለፍቅርና ስለእውነት ብዙዎችን ያናገረ ኢትዮጵያዊነት ወዙ የት ገባ? ከቅድስናና ከጨዋነት ጋር የተመሳሰለ ጥንተ ታሪካችንን ምን በረዘው? የስርዐት መነሻ፣ ለሕግ ፍጻሜ የሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነት በማንና እንዴት ተበላሸ? ብዙዎች ሸሽተው የሚሸሸጉብን፣ ደፋሮች በፊታችን ስር ስለፍቅር የሚዝሉልን፣. ክፉዎች ስለእኛ ጽድቅን የሚማሩብን ሕዝቦች ምን አግኝቶን ከሰስን?
ብዙዎችን ያጠራ ስማችን፣ እልፎችን ከባርነት የታደገ ክንዳችን፣ በፍቅር ካልሆነ በምንም የማይሸነፍ ማንነታችን ስለምን ጥላቻና ብሄርተኝነት ገባበት? ስለሰላም የዘመሩ አፎቻችን፣ ስለጽድቅ፣ ስለሰብዐዊነት፣ ስለፍትህና እኩልነት ያወጉ አንደበቶቻችን ስለምን በእብለትና በማስመሰል ጎለመሱ? የገነት ሀገር ሕዝቦች ተብለን ስም የወጣልን፣ ማንንም የማይነኩ ማንም የማይነካቸው ስንባል የተወደስን፣ ጥንተግሪካውያን ከእኛ ውጪ ታሪክ የሌላቸው እስኪመስል ድረስ በድርሰቶቻችን ያከበሩን ሕዝቦች ምን ገባብን? የሀይማኖት መሪዎች ሂዱ ወደእዛ ሲሉ በመተማመን የሚሉኩብን፣ ከፍቅር ውጪ፣ ከእውነት ውጪ፣ ከሰላም ውጪ እውቀት የሌለን እኛ ማን አበላሸን?
ብዙዎችን በምክክር ያስታረቅን፣ ለብዙሀን የሰብዐዊነት ዋጋን የከፈልን እኛ ማን በየት በኩል ጭካኔንና አለመግባባትን ነዛብን? በብሄርና በዘር፣ በቋንቋና በርስት ተቧድነን በአንድነቷ የተዘመረላትን ሀገር ስለምን ተመሳጠርንባት? ማንስ ነው የሚያድነን? ማንስ ነው ወደቀድሞ ከፍታችን የሚመልሰን? ዛሬ ላይ ስለድህነታችን፣ ስለኋላቀርነታችን፣ ስለሞትና ጉስቁልናችን ካልሆነ ማንም አያወራልንም። ሰላም ስለማጣታችን፣ እርስበርስ ስለመለያየታችን፣ ስለመገፋፋታችንና ስለፖለቲካ ሹኩቻችን ካልሆነ ማንም ስለክብርና ታላቅነታችን አይጽፍም። ውብ ታሪክ በአዳፋ ታሪክ ሲቀየር እንደማየት የሚያም ነገር የለም።
ትላንት ላይ በዓለም ሊህቃን ዘንድ የሚጻፍላት፣ የሚወራላት ሀገራችን ዛሬ በድህነትና በእርስ በርስ ጥላቻ የሚወራላት ሆናለች። ለምን በሉ! ለምን እንበል! ራሳችንን ነጻ እስካላወጣን ድረስ ማንም ስለእኛ ግድ የሚሰጠው የለም። የጥንት ጸሀፍት መነሻ ሀሳብ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያቆነጎሉ የሰብዐዊነት ውሀ ልኮች ነበሩ። ስለሌላው ግድ ማለት፣ ስለሰው ልጅ መጨነቅ፣ ስለአንድነትና ስለፍቅር ማደማችን ነበር። ስለነጻነትና እኩልነት፣ ስለፍትህና ሚዛናዊነት ዋጋ መክፈላችን ነበር። ዛሬ ላይ የብዙሀኑን ብዕር ያነቃቁ፣ ብዙዎችን ያናገሩ ተዳሎቻችን በእኛው ራስወዳድነት ደብዝዘዋል።
ስለፍቅር አቧራ የለበሰ የክብርና የፊተኝነት ታሪካችንን ከወደቀበት አንስተን እንደአዲስ እናብሰው። ምንድነው የጣለን? ማንስ ነው ከከፍታችን ያወረደን? ብለን የጠየቅን ሰሞን በራስወዳድነትና በብሄር ሽኩቻ ደምሳሽ አጥተው እንደተራራ የተቆለሉ የጥላቻና የዘረኝነት እድፎችን እናገኛለን። በንቀትና በቂም ነገን እንዳናይ፣ ተስፋ እንዳናደርግ የሚያደርግ የጥላቻ ቁልል በመሀከላችን አለ። በጥላቻና በትርክት እርስበርስ እንድንፈራራና እንድንሰጋጋ የሚያደርግ አንዱን ከሌላው ጋር የለየ የፍርሀት ተራራ አለ።
አለመደማመጥ ወልዶ ያሳደገው፣ እኔነት አምጦ የወለደው፣ በዘረኝነት ካባ እሽሩሩ የሚባል የኢትዮጵያዊነት ዲያቢሎስ መሀከላችን አለ። በፍቅር ስም ቀራኒዮ ላይ የተሰቀለውን ሕገ ክርስቶስ እንዳናይ፣ እናዳናስብ፣ በጲላጦሳዊ ከደሙ ንጹህ ነኝ እሳቤ ታጥበን የጸዳን እንዲመስለን አዚም የጫነብን ራስን ከጥፋት የማራቅ አባዜ በሁላችንም መሀል አለ። ተነጋገርን እንዳንግባባ፣ ተግባብተን አብረን እንዳንቆም፣ አብረን ቆመን ታሪክ እንዳናድስ፣ ታሪክ አድሰን የጥላቻ ተራራዎችን እንዳንድ ያደረገ የእልህ ፖለቲካ ውስጥ ነን። አንዳቸውም ግን አልጠቀሙንም። ፊተኝነትን ቀምተው ማንም ካልቆመው ኋለኝነት አቁመውናል።
ሁሉም ነገር መጨረሻ እንዳለው የገባኝ መረዳት አለ። የእኛ መጨረሻ ግን ራቀብኝ። መቼ ነው ነቅተንና በቅተን አብረን የምንቆመው? መቼ ነው ምንም ካላመጣልን የብሄር ፖለቲካ፣ የማንነት ጥያቄ ርቀን ኢትዮጵያዊነትን የምናቀነቅነው? መቼ ነው ከአባቶቻችን የታሪክ ዳና ተምረን ትውልዱ ከጥላቻ ወጥቶ በአባቶቹ የፍቅር ዳና ላይ የሚቆመው? ስል እጠይቃለው። ቢጨንቀው አይደል አዝማሪውስ በእንባ ተለብሶ መምጫዋ የራቀበትን ሀገሩን አንጋጦ እያየ ‹ባክሽ ቶሎ ነይ ኢትዮጵያ› ሲል ያቀነቀነው።
አሁን ይጽፉብናል እንጂ ማንም አይጽፍልንም። አብዛኛው የዚህ ትውልድ ታሪኮች የጥላቻ ተራራን መቆለል እየሆነ ነው። ፖለቲካው፣ ፖለቲከኛው፣ አስታራቂው፣ አክቲቪስቱ፣ የሚመለከተው፣ የማይመለከተው ሁሉ ታሪክ አጋጣማሚ እውነት አዛናፊ እየሆነ ነው። የጥላቻ ተራራዎቻችን በፍቅር እስካልተናዱ ድረስ የሚታደገን አይኖርም። ተራውን በፍቅር ስንንድ ያን ጊዜ የእውነት ማየት እንችላለን። ያን ጊዜ ከተራራው ኋላ የተደበቁ የክብርና የፊተኝነት ከፍታዎቻችን ይታዩናል። ማንም እንዳያየን፣ ከማንም ጋር እንዳንተያይ በራሳችን ላይ የጥላቻ አጥር አጥረን እንዴት ነው ሀገር የምንገነባው? እንዴት ነው ተነጋግረን የምንገነባው?
ራሳችንን በራሳችን የደበቅነው እኛ ነን። ማንም አልደበቀንም..ቢደብቁን እንኳን ለመውጣት እስከተንፈራገጥን ደረስ መውጣት እንችላለን። የጥንቱ ዘመን ራሳችንን ያልደበቅንበት ፍቅርን ብሄራዊ መዝሙር፣ አንድነትን ሀገራዊ ወግ አድርገን የኖርንበት ጊዜ ነው። ያሁሉ አቴንሳዊ ውዳሴና መዝሙር፣ ያሁሉ ዓለም አቀፍ የክብር፣ የጀግንነት ፣ይሁንታ እና ፍቅርን ተመርኩዘን የኖርንበት ጊዜያችን ነው። አድዋ ብትሉ፣ ጥንተ ክብሮቻችን ብትሉ ራሳችንን ባልደበቅን ሰሞን የዋጁን ቀለሞቻችን ናቸው። ስለሰውነት ግድ የሚሰጠውን አካልና አእምሮ ባለክብር አድርጎን ዘልቋል። አሁን ደግሞ ክብራችንን ለማስመለስ የጥላቻ ተራራዎችን እናፍርስ።
በውጪ ሀገር አፍቅሮተ ነዋይ ለሚባዝኑ አሁናዊ ትውልድ ጥሩ አስተማሪ መሆን ስለሚችል ፍሬድሪክ ቦልተን ስለኢትዮጵያ የተናገረውን ለማንሳት እገደዳለሁ። ፍሬድሪክ ቦልተንን ፕላንተ ኤንድ ፕላኔት በተሰኘ መጽሀፉ ላይ የኤቶርን ሀገር ኢትዮጵያን ሲገልጻት ይሄን ነበር ያለው ‹ኢትዮጵያውያን ገነት የምትባለው የራሳቸው ሀገር መሆኗን አያምኑም፣ ደግሞም የሩቅ ሀገር ሰው ጽሁፍ ይጠብቃሉ፣ በዚያ ላይ ስለራሳቸው ማውራት አይወዱም። ሀጢዐት ነው ይላሉ› ሲል ከትቧል። ከዚህ ጸሀፊ ገለጻ ውስጥ ‹ኢትዮጵያውያን ገነት የምትባለው የራሳቸው ሀገር መሆኗን አያምኑም› የምትለዋን መዘዝኩ። እውነት ነው አናውቅም ብዙዎች በሚመኙት ተፈጥሮ መሀል ቆመን፣ ሌሎች በሌላቸው ታሪክና ባህል፣ ወግና ስርዐት በኩል ሰው ሆነን የሌላን ናፋቂ ነን። የራሳችንን ንቀን የሌሎችን አወድሰን የቆምን ብዙ ነን።
ሀገረ ገነት፣ ታሪከ ቀለም፣ ሕዝበ እግዚአብሄር መሆናችን በተለያየ መንገድ የሚጠቀስ እውነታ ቢሆንም ለራሳችን እየሰጠን ያለነው ዋጋና ክብር ግን የሚመጥነን አይደለም። የፍቅር ቤታችንን አፍርሰን የጥላቻ ተራራ ቆልንበታል። በአንድ ወቅት የሰላም ጮራን የፈነጠቀ ሰማይ፣ የነጻነትንና የእኩልነትን ፍኖት ያቀና አድማስ የሞትና የጦርነት አረር እየፈነጨበት ይገኛል። የጥላቻና የመፈራራት አውሊያ ነግሶበት ይገኛል።
ሄሮዱተስም ዝም አላለም ከቅድመ ክርስቶስ ልደት በ490 ይቺን ምድር ተቀላቅሎ ስለኢትዮጵያዊነት ይሄን ብሎ ታሪክ አስቀምጧል ‹ኢትዮጵያውያን ከሰዎች ሁሉ የተዋቡና ታላላቆች፣ ቁመናቸውም ያማረ ሀያላን ናቸው› ሲል ብዕሩን አድምቷል። በ6ኛው መቶ ከ/ዘመን በነበረው ባማረና በሸጋ ገለጻ ስለኢትዮጵያ ባወጋው በሄሮዱት ድርሰት ማብቂያዬን ላድርግ..እርሱ እንዲህ አለ ‹ኢትዮጵያውያን ታላላቆች መልካቸው ያማረ፣ የሰውነታቸው ቅርጽ የተዋበ፣ ጻድቅና በጎ አድራጊዎች፣ ለስራ የማይደክሙ፣ ጥበበኞች፣ አማልዕክት የሚወዷቸው፣ በአንደበታቸው ሀሰት የማይገባ፣ በጦርነትና በእርጅና ካልሆነ በበሽታ የማይሞቱ ናቸው› ሲል ቃሉን አስቀምጧል። ቶማስ ሞር ‹ዮቶጵያ› ሲላት ፕሊቶ ደግሞ ‹የአትላስ ደሴት› ሲል አሞካሽቷታል።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም