ወደኋላ እንዳንመለስ?

ባለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት ከፍተኛ እመርታ ከታየባቸው ነገሮች መሐከል አንዱ የሴቶች መብት ጉዳይ ነው። ሴቶችን ልጅ ከመውለድ እና ምግብ ከማብሰል ጋር ብቻ አስተሳስሮ የኖረውን ዘልማዳዊ አስተሳሰብ አስተካክሎ ሴት ልጅ ቦታዋ ማዕድቤት እና መኝታ ቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤት እና ቢሮም ውስጥ እንደሆነ ለማስተማር ብዙ ተጥሯል። በርካታ ስኬትም ተገኝቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደርጓል። በሥራው ዘርፍም ለወትሮው ለሴቶች አይደፈሩም ተብለው የሚገመቱ የሥራ መስኮች ሴቶች በከፍተኛ ቁጥር የሚሳተፉባቸው እየሆኑ መጥተዋል፡፡

በምክር ቤቶች በከፍተኛ ቁጥር እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት ካቢኔም እስከ 50 በመቶ በሚደርስ መጠን ሴቶች ድርሻ እንዲይዙ መደረጉ የዚህ እመርታ መገለጫ ነበር። የጠለፋ ጋብቻን፣ ግርዛትን እና መሰል ጎጂ ባሕልን እንዲቀንስ ማድረግ መቻሉም ከብዙዎቹ ስኬቶች መሐከል ተጠቃሽ ነበር፡፡

በቅርብ ጊዜያት ግን እነዚህን ስኬቶች ሁሉ አደጋ ውስጥ የሚከት ዝንባሌ እየታየ ነው። የት ከተባለም በማኅበራዊ ሚዲያ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያው የሴቶች መብት የማስከበር ትግሉን የሚጋፉ ትርክቶች እየተበራከቱ ይመስላል። ሴትን ወደኋላ የሚመልሱ፣ አባታዊ (patriarchal) ሥርዓትን መመለስ የሚፈልጉ አስተሳሰቦች በየቦታው ብቅ እያሉ ነው። አንዳንዶቹ ክርክሮች የፌሚኒዝምን እንቅስቃሴ በመቃወም የሚደረጉ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ባሕላችንን እናስከብራለንም የሚሉ ናቸው።

እርግጥ ነው ባሕላችን መከበር አለበት። ቤተሰብን አስኳል ያደረገ ማኅበራዊ መዋቅራችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ከምዕራባውያን እሴት የሚቀዱ እና ኢትዮጵያዊውን ማኅበራዊ አኗኗር የሚጋፉ ንቅናቄዎች አይጠቅሙም። ይህ ማለት ግን ፌሚኒዝም መጥፎ ነው ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፌሚኒዝም (አለ የሚባል ከሆነ እንኳን) አደገኛ ነው ማለት አይደለም። ወደኋላ ተንሸራትተን ሴትን ልጅ ወደ ማድቤት ባለቤት እና ወደ መኝታ ቤት ጌጥነት እንመልሳለን ማለትም አይደለም። በቅርብ ጊዜ የሚታዩ የሶሻል ሚዲያ ክርክሮች ግን መንፈሳቸው ወደዚያ የተቃረቡ ናቸው፡፡

ፌሚኒዝምን አለቅጥ ማራከስ፥ የወንድ ልጅን የበላይነት የሚሰብኩ ቅስቀሳዎችን ማብዛት (ሲግማ ወንድ እና መሰል አይነት የሰሞኑ ፌስቡክ እና የቲክቶክ ዘመቻ)፣ ሴት ልጅ እንዲህ ስትሆንና እንደዚያ ስትሆን ብቻ ነው የሚያምርባት የሚል ፍረጃ ፣ መብታቸውን የሚጠይቁ ሴቶችን በአካላዊ ገጽታቸው ማራከስ፣ በየቦታው የሚታይ የሴት ልጅ እገታ እና መሰል እንቅስቃሴዎች ጤናማ አይደሉም፣ ውጤታቸውም የሚያምር እንደማይሆን እርግጥ ነው። ይሄ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚታይ ጤናማ የማይመስል ውይይት ለጊዜው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ ስለሚታይ ተራ የፌስቡክ ወሬ እና የቲክቶክ ማድመቂያ ቢመስልም በጊዜ ሂደት ግን ወደ መደበኛው ሚዲያም ሆነ ወደ እለታዊ ኑሮ የሚሻገር ችግር መሆኑ አይቀርም። በእርግጥ እስካሁን በሴቶች ጉዳይ ከመንግሥት በኩል አዲስ የተያዘ አሉታዊ አቋም ባይኖርም ነገር ግን መንግሥት በሴቶች መብት ዙሪያ አሁንም አቋሙ ጠንካራ እንደሆነ ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡

እዚህ ጋር የሚነሳ ጥያቄ ይኖራል። ጥያቄውም መንግሥት የሰዎችን ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲያግድ ነው ወይ ጥያቄው? ሊባል ይችላል፣ መልሱም አይደለም የሚል ነው። የሴቶች መብት መከበር ያለበትን ያህል ሀሳብን የመግለጽ መብትም ሊከበር ይገባል። አንድ ሰው ሴት ልጅ ድርሻዋ ሚስት እና እናት መሆን ብቻ ነው ብሎ ሊያስብም ይችላል። ለምን አሰብክም ሆነ ለምን ተናገርክ ሊባል አይቻልም። ነገር ግን እንዲህ አይነት ሀሳብ ያለው ሰው ወይም ቡድን በሚኖርበት ጊዜ መንግሥት ወገንተኝነቱ ለማን እንደሆነ በግልጽ ማሳየት አለበት። አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ውስጥ እንዲህ አይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች አሉ። ስለ ሀሳባቸው የደረሰባቸው በደል የለም። ነገር ግን መንግሥት በንግግርም ይሁን በተግባር በሚያወጣቸው ሕጎች እና ፖሊሲዎች ወገንተኝነቱ ለሴቶች እኩልነት ነው። እዚህም መሆን ያለበት ይሄው ነው፡፡

መንግሥት ይሄን ማድረግ ያለበትም ያለው ብቸኛ አማራጭ ይህ ስለሆነ ነው። ካሁን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ወዳለፈው ዘመን የወንድሞቻቸው የበታች እና የራሳቸው ፍላጎት የሌላቸው የባሎቻቸው ንብረት ማድረግ አይቻልም። ይህ መሆን የማይችልበት ብዙ ምክንያትም አለ። ስለዚህም የማይሆነውን ነገር ለመመለስ መታገል የለብንም። ይልቁንም ከምዕራቡም ይሁን ከየትም ያልተቀዳ ለኢትዮጵያዊት ሴት የሚገባ እና የሚመጥን ሥርዓት ለመፍጠር መሥራት አለብን። በማኅበራዊ ሚዲያ ስለሴቶች የሚሠሩ ይዘቶችን የሚያዘጋጁ ሰዎች ያለንበት ዘመን 21ኛው ክፍለ ዘመን መሆኑን ማስታወስ እና ወዳልኖሩበት ዘመን እያዩ መናፈቅ መተው አለባቸው።

ሚዛን ስሜ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You