ወርቃማው ነበልባል

እሳት የወለደው ወርቃማው የእሳት ነበልባል አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አርማዊ ቀስተደመና ሠርቶ ከሰማያዊው የሙዚቃ ሰማይ ላይ ሲወርድ የተመለከተው ማነው…ውሃ የወለደው እሳት መብረቅ ይሆናል፡፡ የመብረቁ ነበልባልም በረዶውን ከዝናብ ጋር ቀላቅሎ ድምጹን እያስገመገመ እንደሚመጣው ሁሉ ግጥሙን ከዜማው ጋር ቀላቅለው ዧ! እያሉ ወርደው ሁለት ሳሉ አንድ ሆነዋል፡፡ በመሀል ከተማ ላይ የጎሞራ ባህር ሠርተዋል፡፡ እሳትም ውሃም የጥበብ ማዕበል የሙዚቃ መርበብት ናቸው፡፡

ከ1960ዎቹ ተነስተው በ70 እና 80ዎቹ ሙዚቃዎች ውስጥ ሲንበለበሉ ቆይተው ይሄው ዛሬም ድረስ አሉ። ውቅያኖሱ የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ይልማ ገብረአብ እና ዋኖሱ የዜማ ደራሲ አበበ መለሰ የሙዚቃ መርከብ ያረፈባቸው ጠሊቃን ናቸው፡፡ ያለ ግጥም ያለ ዜማ ያለ ሁለቱ ሙዚቃ አይቆምም፡፡ ጣምራዎቹም አንዱ ከአንዱ የማይነጣጠሉ ዘውድና ጎፈር ናቸው፡፡ ለዛሬው ግን ግድ ብሎን አንዱን ብቻ ነጥለን ልንተርከው ነው፡፡ ስለ አንደኛው ሲወራ የምንሰማው ግን ስለ ሌላኛው ነው፡፡

ነበልባሉ የእሳት ጎሞራን ይመስላል፡፡ ከጎሞራው በፊት ከብልጭታው ልንጀምር ስንል ለመጀመሪያ ጊዜ ፈንጥቆ ወደታየበት መነሻው ይወስደናል፡፡ በአራት ኪሎ በሰባ ደረጃ ቆመው አሻግረው ፒያሳን የተመለከቱ እንደሆነ በዓይን ጥቅሻ ወደዚያው ያመለክተናል፡፡ በዶሮ ማነቂያ ግንባር ቁልቁል እየተምዘገዘግን ወርደን በሠራተኛ ሰፈር ወገብ ላይ አረፍ ስንል ደግሞ ያንን ነበልባል ከብልጭታው ጋር እንመለከታለን፡፡ ያ የምንመለከተው የእሳት ብልጭታም ትንሹ ይልማ ገብረአብ ነው፡፡

በዚያ ሠራተኛ ሰፈር ውስጥ በወርሀ ነሀሴ 1953ዓ.ም ከእናቱ ማህጸን ብልጭ ብሎ ለጎመራው ጥበብ በቃ፡፡ ልጅነቱን ከጥበብ ጋር ሲሯሯጥ ነበልባሉ ቀድሞ አበሰለው፡፡ የባላባቱ የቀኝ አዝማች ገብረአብ ልጅ ነውና ለመቦረቂያው እርስቱም አይጠበውም፡፡ አርሾን ቀጥሎ ከነበረው የመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ ከተሠራው የቄስ ትምህርት ቤት ጀመረ፡፡ ዳዊቱንም ደገመ፡፡ አስኳላን ፍለጋ ወደ ብርሃን ትምህርት ቤት ሄዶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለሁለተኛው መሰናዶ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት አመራ፡፡ ገና ብዙም ሳይርቅ ወላጅ አባቱን በሞት አጥቶ ነበርና ቀጣዩ እጣፈንታው ከእናቱና ከእንጀራ አባቱ ጋር ሆነ፡፡ ቢሆንም ግን ጥሩ እንጀራ አገኘበት እንጂ መጥፎ አልነበረም፡፡ በሙዚቃ ህይወቱም የበኩር ምስጋናውን የሚያቀርበውም ለእኚሁ የእንጀራ አባቱ ነው፡፡

በ1966ዓ.ም በዋዜማው ዕለት የተከፈተው የባህል ምሽት ቤት ባለውለታው ነው፡፡ አባቱን (የእንጀራ አባቱን) ተከትሎም ወደዚያው ይሄድ ነበር፡፡ ምናልባትም ሙዚቃን በአካል የተመለከተውና የተዋወቀው ከዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዚህን ጊዜም ገና ልጅ ነው፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ ባገኘ ቁጥር አርፎ መቀመጥን አያውቅም፡፡ ጊታሩንም ክራሩንም ብቻ ያገኘውን የሙዚቃ መሳሪያ ሁሉ መነካካቱ የልጅነት ነብሲያውን ታጠግበዋለች፡፡ አባቱም ቢሆኑ ተው! እያሉ አያስቆሙትም፡፡

የነገውን ይልማን ተመልክተው ሙዚቀኛ ይሆናል ባይሉም፤ ግን ደግሞ እራሱን ለልጅነት ደስታው ትተውለታል፡፡ የ11ና 12 ዓመት ልጅ ሆኖ ሙዚቀኝነት ይነሽጠዋል፡፡ ከቤት ክራሩን እያነሳ ከቤተሰቡ ፊት ቆሞ የተሾመ ደምሴ “አዳራሹ ቤቴ”ን ይጫወት ነበር፡፡ ከቤቱ ውስጥ ነጻነትና ጆሮ አልተነፈገውም፡፡ ከዚያን የትንሽነቱ ወራት ጀምሮ ከቀበሌው የኪነት ደጃፍ አይጠፋም ነበር፡፡ ሥራ ሰጥተውም ቤተኛ አደረጉት፡፡ የቀበሌው ሊቀመንበር በየስብሰባው የሚያቀረቡትንም ጽሁፍ ማዘጋጀቱን ተያያዘው፡፡ እንግዲህ እያጠፋም እያለማም ብቻ ግን እዚያ አካባቢ ያሉ ሹመኞችም ቢሆኑ ከልጅነቱ ጋር የሚንቦራጨቀውን ሙዚቃ ሊሰሙለት ይወዱ ነበር፡፡

ከቀበሌው ጋር ያለው ቁርኝት አድጎና ችሎታውም ዳብሮ ሲመለከቱ ወደ ኪነት ቡድኑ እንዲቀላቀል አደረጉት። በአንድ ወቅት የቀበሌውን ጊታር አውጥተው ሰጡት፡፡ እርሱ እንደሆን ሲፈጥረውም ቸር አድርጎ ነውና የሰጡትን ጊታር መልሶ ለሌላ ሰው አዋሰው። ከዕለታት በአንዱ ቀን ታዲያ ያዋሰው ወዳጁ ጊታሩን ተሸክሞ በቀበሌው ደጅ ሲንጎማለል ያልፋል፡፡ በቀበሌው ሰዎች ዓይን ውስጥም ገባ፡፡ ሌሊት ወደ ሰባት ሰዓት ገደማ የይልማ በር ተንኳኳ፡፡ ከገባበት የእንቅልፍ ዓለም ተመልሶ ዓይኑን እያሸሸ በሩን ከፈተ፡፡ ከውጭ የደርግ ወታደሮች ቆመዋል፡፡

ሊቀመንበሩ ሊያናግሩት እንደሚፈልጉ ሲነግሩት አዲስ ሥራ ቢመጣ ነው ብሎ በማሰብ ተከትሏቸው ሄደ። ድግሱ ግን ሌላ ነበር፡፡ የጊታሩ ጉዳይ ያልጠበቀውን መዘዝ ይዞለት መጣ፡፡ ደግነቱ እዳን አስከትሎ ዘብጥያ አወረደው፡፡ ለ6 ወራት ያህልም በእስር እንዲቀጣ ሆነ፡፡

ይልማ ከቤቱ ውስጥ ከጣራው በታች አልጋው ላይ ሆኖ ድንገት ቀጭ ቋ! መሳይ የግጥም ኮቴ “ይረገም!…ይረገም!” ሲል ከምናቡ ላይ አቃጨለበት፡፡ የሀሳቡንም በር ወለል አድርጎ ገባ፡፡ ይሄኔ ብዕሩን ለመጀመሪያው ታሪክ አንስቶ በብጣሽ ወረቀት ላይ አሳረፋት፡፡ ግጥሟ ሙዚቃ ለመሆን ትችላለች ብሎ አሰበ፡፡ እና ማንስ አሳምሮ በድምጹ ያስረቅርቃት? ግጥሟን ይዞ ሙሉቀን መለሰን ፍለጋ ወጣ፡፡

ገጽ ለገጽ ፊቱ ቆሞ እርሱን ለመመልከት በመቻሉ ይልማ ለደስታው ወደር አነበረውም፡፡ ሙሉቀን መለሰም ከፊቱ የቆመውን ታዳጊ አየት አድርጎ ወረቀቱን ተቀብሎ ግጥሙን ተመለከተው፡፡ የወደደው ቢመስልም ይሁን ብሎ ሊያልፈው ግን አልፈለገም፡፡ በደንብ እንዲያበስላት መልሶ ሰጠው፡፡ ተቀብሎም ዳግም በሌላኛው ቀን ተመለሰ፡፡ አሁንም ትንሽ መብሰል ይቀረዋል ሲል እንደገና ሦስተኛ ቀጠሮ ሰጥቶ ሸኘው፡፡ ልቡ ቆማ የጉጉት ክንፍ ልታበቅል ብትደርስም ይልማ አስተያየቱን በክብር ተቀብሎ ከመሄድ ውጪ አንዳችም ቅር አላለውም ነበር፡፡

ለዚህ አስተማሪነቱም ሙሉቀንን ያመሰግነዋል፡፡ ሦስተኛውን ቀጠሮ ሲጠባበቅ ግን ሌላ አጋጣሚ ተፈጠረ። በጭንቅላቱ የዞረው የግጥም ዛር ሲያንከላውስ ወስዶ ከኤፍሬም ታምሩ ደጅ ላይ ጣለው፡፡ የበኩር ብስራቴ ይሆናል ያለውን ሙሉቀን መለሰን ቀድሞ ኤፍሬም ታምሩ ተገኘ፡፡ “ሸግዬ” የሚለውን ግጥሙን ሰጠው፡፡ ኤፍሬም ይህን ሥራ ጨምሮ አልበሙን ባወጣ በሁለተኛው ሳምንት ሙሉቀንም “ይረገም”ን አክሎ መጣ፡፡ ይሄኔ ነው ደስታ! ይሄኔ ነው ተድላ! ይልማ ድል በድል ሆኖ ደስታና ልጅነቱ እንደ ፈንዲሻ ፈካ፡፡ የዓይኔ ነገርማ…

ከዚሁ በኋላ ይልማን ማንስ ያቁመው፤ በተራራማው የሙዚቃ አናት ላይ ወጥቶ እንደ ጎበዝ የጦር ጄነራል ወደፊት እየገፋ አጧጧፈው፡፡ እንዲህም ይቻላል እንዴ እስኪባል ድረስ አንድ ሺህ 2 መቶ ሃምሳ የሙዚቃ ምርኮ ተቆጣጠረ፡፡ ሙሉቀን መለሰ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ አስቴር አወቀ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ማህሙድ አህመድ፣አረጋኸኝ ወራሽ ቴውድሮስ ታደሰ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ቴዲ አፍሮ…የይልማን የግጥም መረቅ በሰፊው ከጠጡት መሀከል በጥቂቱ እኚህ አንጋፋ ጃግሬዎች ይገኙበታል፡፡

እንደ አርጋኖን ከደመናው በላይ በውብ ፍቅር በውብ የብርሃን ግላጭ እየቀዘፈ፤ ሌላ ጊዜም እንደ መብረቅ እያስገመገመ በግጥሞቹ ነበልባል ታላላቆቹንም ታላቅ ወላፈን አድርጎ ሠርቷል፡፡

«አለወይ አለወይ፤

ውብ እንዳንቺ፤

ጸባየ ሰናይ፤”

ቴዲ አፍሮ አዚሞ ተዛዚሞበታል፡፡ ይልማ እኮ ግጥምን ከመድረስ አልፎ ቅኔ ማልበስም ተክኖበታል። እንዴት ያለ ግጥም አዋቂ ነው ለማለትም አስቀድሞ የማወቅ ብቃትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ከእርሱ ሙዚቃዎች ሙዳይ ውስጥ ያለውን ወርቅ ለመረዳት መስማት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከላይ የሚነግረን ፍቅር ሰም እንጂ ወርቁ አይደለም፡፡ የዚህን ጎበዝ ግጥሞች መርምረው ወርቁን የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡

ከበስተጀርባው ታሪክ፣ ሰው፣ ሚስጥር…አንዳች ነገር አይጠፋም፡፡ ተመስጦው ምናቡን ብቻም ሳይሆን ነብሱንም ትሰውረዋለች፡፡ በመብረቅ የታጀበ የሙዚቃ ጎሞራ ከውስጡ ይፈነዳል፡፡

አብዛኛዎቹ ሥራዎቹ አንዳችም ባልጠበቅነው መንገድ ለአንዱ የተጻፉ ስውር መልዕክቶችን እናገኝባቸዋለን፡፡ በ1970 በቀይ ሽብሩ ሰሞን ይልማ አንድ የሙዚቃ ግጥም ጻፈ፡፡ ዜማውንም አበበ መለሰ ሰፍሮ አስቀመጠው። ስምንት ያህል ዓመታትን ቆይቶ 1979ዓ.ም ኤፍሬም ታምሩ ተጫወተው፡፡

«የናፍቆት ጥፋቱ የበደሉ በደል፤

ሲመሽ ነብስ ይዘራል ስፍራ ሲደለደል፤

ለመፈራረጃው ሰፊ ቤት ሳለሽ፤

ምነው ባደባባይ ትቀጪኛለሽ፤»

ስንሰማው ለከዳተኛዋ ፍቅሩ የሚያንጎራጉር ይመስለን ይሆናል፤ የዜማ ደብዳቤው ግን ለደርግ መንግሥት የተሰናዳ መልዕክት ነበር፡፡ የቀይ ሽብር አፈሳ ፊሽካው የሚነፋው ቀን ሳይሆን ማታ ተደላድለው ከተኙ በኋላ ከየበሩ እየተንኳኳና ከጦፈ እንቅልፍ መሀል ከህልም እየነጠሉ ነበርና ሲመሽ ነብስ ይዘራል ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ ጠዋት ማልደው ሀገር ሰላም ብለው ሲነሱ አደባባዩ ሁሉ በሬሳ ተሞልቶ በደም ተጨማልቆ ይታያል። ለቅጣቱ የሚሆን ስፍራ ሳይጠፋ ምነው በአደባባዩ መገደላችን ለማለት ቅኔው በሰም ተለብጦ ቀርቧል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ለመዘርዘር እንጀምር ይሆናል እንጂ አንጨርሳቸውምና አንዲቷን ብቻ እናክላት፡፡

«ይረገም ይህ ልቤ አልፎ የሄደበት፤

ይረገም ይህ ልቤ ሌላ ያሰበበት፤

«የዓይኔ ነገርማ ገና ብዙ አለበት፤»

ሙሉቀን መለሰ ይህን ዜማ ሲያንጎራጉር “የዓይኔ ነገርማ…” ይልማ ለሙሉቀን የሰጠው የራሱን ታሪክ ነበር፡፡ ከእንግልት መልስ ከአልጋው ላይ ጋደም ብሎ የጻፋት “ይረገም” መነሻው ይሄ ነበር፡፡ “የዓይኔ ነገርማ ገና ብዙ አለበት” ሲል ስለሚመለከትበት ዓይኑ እንጂ ስለሚያፈቅራት ጸባየ ሰናይዋ፤ ስለ አይናለም መሆኑን እንዴትስ ልናውቅ እንችልና…በጣም የሚወዳት ፍቅሩ ነበረች፡፡ ያኔ ወህኒ ሲወርድ የአይንዬ ወንድም በስፍራው ነበር፡፡

በአይንዬ ጦስ ወደፊት ገና ብዙ ነገር እንደሚጠብቀው ለማሰብ አላረፈደም፡፡ ምን ሲል እንዳሰበው የዚህን ወታደር እህት በፍቅር መመኘቱ፡፡ የዚያን ምሽት ከፖሊስ መኪና ውስጥ ሆኖ ወንድሟ መኖሩን ተመለከተ። አይንዬ ደግሞ ከበሩ ላይ ቆማ ታለቅሳለች፡፡ እነዚህን ሁለት ነገሮች ሲመለከት የተያዘው በአይንዬ ጉዳይ መሰለው። ወንድሟም የእጁን ሊሰጠው እንደሆነ አመነ። ምን ሲያቀብጠኝ ይሆን እህቱን ማፍቀሬ ሲልም አሰበ፡፡ በቀበሌው ውስጥ እንግልቱ በዛበት፡፡ ይህን የተመለከቱት የከፍተኛ ኪነትም ከዚያ አስወጥተው ወደራሳቸው ወሰዱት፡፡

በሥራ አብሯቸው ወደ ክፍለ ሀገሮች መንቀሳቀስም ጀመረ፡፡ በአንደኛው ቀን ወደ አሥመራ ለሚደረገው ጉዞ ሲሰናዳ አይኔ ለመጨረሻ ጊዜ የዚያኔ ተመለከታት። ያሳየችው ፊት ዳግም እንደማይገናኙ የሚናገር ነበር። በውስጣቸው ፍም እሳት የሆነ ፍቅር ቢቀጣጠልም ተቀያይመው ተኮራርፈዋል፡፡ ሁለቱም በልባቸው ከያዙት ፍቅር ሌላ አይንዬ በሆዷ ጽንስ ነበር፡፡ ልጅነቱ ግን ተናነቃቸውና ቃል አውጥተው ሳይተነፍሱ በዚያው ተለያዩ፡፡

«የሀገር ቤቷ ዓይናማ አንቺ ለግላጋ፤

አንቺ የገጠር መለሎ የገጠር ሎጋ፤

ልቤን ሆዴን ሰወርሽው ሳይመሽ ሳይነጋ፤»

(ማህሙድ አህመድ)

ከዚያ መለያየት በኋላ ግን ሌላ አዲስ የፍቅር ህይወት ጀመረ፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተጣመራትን ባለቤቱንም አገኘ፡፡ በሚሠራበት ኪነት ውስጥ የነበረችና ውበቱን ያለስስት የደፋባት የደም ገንቦ አንዲት ቆንጆ ነበረች።

በልጅነቷ ላይ ቀበጥነቷ ተደማምሮ ልቡን ረታችውና ከጀላት፡፡ ልጃቸው በውበቷ ምክንያት ከዓይን ገብታ የጅብ እራት እንዳትሆን የሚሰጉት እናቷ ጸጉሯ በደረሰ ቁጥር ሁሉ በምላጭ ይሸልቱት ነበር፡፡ እርሱም ሊያገባት ቆርጦ እናቷን ተዋወቃቸው፡፡

ለእፎይታው በትዳር መጠቅለሏን ሲጠብቁት የነበረ ምኞታቸውም ነበርና በቶሎ ይሁን አሉ፡፡ የእርሱ ዘመዶች ግን ተቃወሙት፡፡ የእርሷ እናት ግን ግድ የለህም ሁለታችሁንም እኔው እድራችኋለሁ በማለት ሃሳብ እንዳይገባው ገፋፉት። ጊዜው ደርሶም ሠርጉ እንደነገ በአንደኛው ቅዳሜ ማዘጋጃ ተፈራርመው ምሽቱን ከእናቷ ቤት ሲመጡ አሳዛኙን መርዶ አረዱት፡፡ እንዴት ለወንድ አንቺ ትደግሺያለሽ በማለት ሰፈርተኛው ሁሉ ሰደበኝ፤ ስለዚህ አዝናለሁ እሷን እንጂ አንተን ለመዳር አልችልም አሉት፡፡

ይህን ጊዜ ትርምሱ ሌላ ሆነ ለነገ ሠርግ የሚደርስ ድግስ ለማዘጋጀት ሁሉም በየፊናው ተሯሯጠ፡፡ ሙሉቀን መለስ እንጀራውን ከቤቱ አስጋግሮ አስላከ። በጠዋቱ ጄሪካን አሲዞ ጠላ ፍለጋ የወጣው ይልማ፤ ተክለሃይማኖት ሰፈር ገብቶ የማርያም ጠላ በርሜሉ ፈንድቶብን ነው እባካችሁን ተባበሩን በማለት ጠላውን በየጄሪካኑ አስሞላ። ወዛደር ሆኖ የጠላ ጄሪካኑን ተሸክሞ ሲገባ አጃቢና ሚዜው ከቤት ቁጭ ብሎ እርሱን ሲጠባበቅ ደረሰ፡፡ የኤፍሬም ታምሩ ሚስት ግን ተአምር በሚመስል መልኩ በአንድ ምሽት ሁሉንም አሰናዳችው፡፡

ይህ የሆነው በጥር ወር ላይ ነበር፡፡ ከሠርጉ 15 ቀናት ቀደም ብሎ የአልበም ሥራውን የለቀቀው ኤፍሬም ታምሩ ደግሞ በአድናቆት ሲዘመርለት የነበረበት ሰዓት ነው። የማይሆነው ሆኖ እንዳልጠበቁት ተከሰተ፡፡ የዚያን የሠርጉ እለት በሰፈሩ መቆሚያ መቀመጫ ታጣ፡፡ ከልጅ እስከ አዛውንቱ ኤፍሬምን ለማየት ሲገፋፋ የቤቱ አጥር ሳይቀር ፈረሰ፡፡ የኪነት ቡድኑ ከነ ሙዚቃ መሳሪያው ተገኝቶ አጃኢብ! የተባለለት ሠርግ ሆነ፡፡ የታሰበው መሽቶ ያልታሰበው አጋጣሚ ነጋ፡፡

በጣት ለሚቆጠሩት ግጥሞቹ ካልሆነ በስተቀር ይልማ እራሱ ዜማ አይሰራላቸውም ነበር፡፡ “እርግብ” የተሰኘውን ሙዚቃ ከሽኖ ለመስፍን አበበ ሲሰጠው ግን ከነዜማው ነበር። እርሱም በጊታሩ ጭምር በውብ ድምጹ ብሉኝ ብሉኝ እንደሚል ትርንጎ ዓይነት አድርጎ ሠራው፡፡ የተዜመላት ልጅ ከዘመናት በኋላ አባቷን ፍለጋ የመጣችው የአይንዬ ልጅ፤ እርግቤ ነበረች፡፡ “የዓይኔ ነገርማ ገና ብዙ አለበት” ሲል ታውቆት ነበር፡፡ ያኔ ሲለያት የእርሱን ልጅ በሆዷ እንደተሸከመች ታውቆት ነበር፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ልጁን ፍለጋ ወደ እርሷ ቢሄድም አይንዬ ግን ልትሰማው አልፈቀደችም፡፡ ትንሿ እርግብ የይልማ ልጅ ስለመሆኗ ሁሉም የሚያውቀው እውነት የነበረ ቢሆንም፤ ከኔ ምንም ልጅ የለህም በማለት ከአባቷ ሸሽጋ አሳደገቻት፡፡ እርግቤ አድጋ ትልቅ ልጅ ስትሆን ግን አባቴን ስትል አፈላልጋ መጣችለት፡፡

«እዚያ ማዶ ጋራ ያለሽው እርግብ፤

ምን ረሀብ አገኘሽ የሚያንገበግብ፤»

ወርቃማው ነበልባል፤ ይልማ ገ/አብ እስከዛሬ ድረስም አንድ ሺህ 2 መቶ ሃምሳ የሙዚቃ ግጥሞችን በማበርከት እሳትና ውሃ የወለደው መብረቅ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ከባህሩ ቀኜ እስከ ቴዲ አፍሮ ድረስ 104 ያህል ሙዚቀኞች የእርሱን የግጥም ሥራዎች ተቋድሰዋል፡፡ በህይወት ዘመኑ የሙሉ ጊዜ ሥራውን የሰጠው ለሙዚቃው ነውና በ2011ዓ.ም የህይወት ዘመን ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ የወርቃማው ነበልባል እሳተ ጎሞራ ከሌላ የአልማዝ ወላፈን ጋር እንመለከተው ይሆናል፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You