ጎል አልባው የዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ

የ2026 ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የአፍሪካ ዞን የተለያዩ ጨዋታዎች በየምድቡ ተከናውነዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሦስተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን ጊኒ ቢሳውን ከሜዳው ውጪ በስታዲዮ ናሲዮናል 24 ደሴተምብሮ ስታዲየም የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

በምድብ አንድ የተደለደሉት ዋልያዎቹ ከትናንት በስቲያ ምሽት ጊኒ ቢሳውን በገጠሙበት ጨዋታው በርካታ የግብ አጋጣሚ መፍጠር ቢችሉም ያገኙትን እድል በአግባቡ ተጠቅመው ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው ጨዋታውን 0ለ0 አጠናቀዋል። ዋልያዎቹ አቡበከር ናስርና ዳዋ ሆጤሳን የመሳሰሉ ጨራሽ አጥቂዎችን በጉዳት ምክንያት ማሰለፍ እንዳልቻሉ ይታወቃል። በዚህም በሦስቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች አንድም ጊዜ ኳስና መረብ ማገናኘት ሳይችሉ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዟቸው ቀጥሏል፡፡

ዋልያዎቹ ሦስት የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርገዋል፡ ፡ ይህም ሞሮኮ ላይ ከሴራሊዮን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ዜሮ ለዜሮ መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በቡርኪናፋሶ ደግሞ 3 ለ 0 መሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡ በዚህም መሠረት ዋሊያዎቹ በሁለት ነጥብ እና በሦስት የግብ ዕዳ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡

ከወራት እረፍት በኋላም ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ቢሳው እና ጅቡቲ ጋር ለሚያደርጋቸው የምድብ ጨዋታዎች አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በብዛት ለወጣት ተጫዋቾች እድል ሰጥተዋል። ያም ሆኖ በሦስቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከሦስት ነጥብ ጋር መገናኘት አልቻሉም። ዋልያዎቹ ምናልባትም በዚህ ማጣሪያ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ማሳካት ካለባቸው በመጪው እሁድ የምድቡን ዝቅተኛ ተገማች ቡድን ጅቡቲን በገለልተኛ ሜዳ ሞሮኮ ላይ ማሸነፍ ይሆናል።

የዋልያዎቹ የሦስተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ተጋጣሚ የጊኒ ቢሳው ቡድን ባለፈው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ደካማ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የተሻለ ነጥብ በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። ለዚህም የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ባሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ ምክንያት አሠልጣኝ ከባሲሮ ካንዴን በማሰናበት የቀድሞ የፉልሃም አሠልጣኝ ሉዊስ ቦአ ሞርቴን ተተኪ አድርገው መሾማቸው አንዱ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል።

ጊኒ ቢሳው በሕዳር 2016 ዓ.ም ከጅቡቲ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 1 ለ 0 አሸንፏል። የማሸነፊያ ግቧንም በሲዊዝ ሱፐር ሊግ የሚጫወተው ሰባት ቁጥሩ ማዑሩ ሮደሪገስ ማስቆጠሩ አይዘነጋም፡፡ የጊኒ ቢሳው ብሔራዊ ቡድን ከቡርኪና ፋሶ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ደግሞ በአንድ አቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ግቧን ያስቆጠረውም በፈረንሳዩ ሊዮን የሚጫወተው ማማ ሳምባ ባላዴ ነበር። ጊኒ ቢሳው በሦስት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ እና አንድ ንጹህ ግብ በመያዝ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጊኒ ቢሳው የሚገኙበትን ምድብ አንድ ግብጽ ከትናንት በስቲያ በሜዳዋ ቡርኪናፋሶን 2ለ1 ማሸነፏን ተከትሎ በዘጠኝ ነጥብ ትመራለች፡፡ ቡርኪና ፋሶ መሸነፏን ተከትሎ በአራት ነጥብና ሁለት ንፁህ ግብ ሶስተኛ፣ ሴራሊዮን በግብ ክፍያ በልጣ በአራት ነጥብ ትከተላለች። አንድም ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ዋልያዎቹ በሁለት ነጥብ አምስተኛ ላይ ይገኛሉ። በስምንት የግብ እዳና በዜሮ ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችው ደግሞ ጅቡቲ ናት።

ሴራሊዮን ነጥቧን አራት ያደረሰችው ከትናንት በስቲያ ጅቡቲን 2ለ1 ማሸነፋን ተከትሎ ነው። ኢትዮጵያ ነገ ጅቡቲን ስትገጥም ሴራሊዮን ደግሞ ሰኞ ከሜዳዋ ውጪ ቡርኪናፋሶን ትገጥማለች።

ከዋልያዎቹ ግብ አልባ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ ጎን ለጎን ብሔራዊ ቡድኑ ነገ በሜዳው ጅቡቲን መግጠም ሲገባው በገለልተኛ ሜዳ ለመጫወት መገደዱ ዛሬም አነጋጋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም የካፍና የፊፋን ጨዋታዎች ለማስተናገድ መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም ማግኘት አልቻለችም፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት እድሳቱ የተጀመረው የአዲስ አበባ ስታድየም በእነዚህ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ብሔራዊ ቡድኑን ከስደት ይታደጋል ተብሎ ተስፋ ቢደረግበትም አልተሳካም፡፡ ይህም ዋልያዎቹ በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታዎችን ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉና እንደ ሀገርም ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን መቼ እንደሚያቆም በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጥያቄ ማስነሳቱን ቀጥሏል፡፡

ቦጋለ አበበ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You