ቴክኖሎጂና አዲስ የፈጠራ ሥራ የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ አሻሽሏል፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂ ፋይዳ ከምንለው በላይ ትልቅ ነው።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በሁሉም መስክ ማለትም የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ በምግብ እራስን ለመቻል፣ ለጤና ብሎም ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ መታገዝ የግድ ሆኗል።
እንደ ሀገር ለቴክኖሎጂ ልማት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ በመንግሥት ይገለፃል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው “ሳይንስ በር ይከፍታል፤ ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፤ ፈጠራ ወደ ፊት ያራምዳል” በሚል መሪ ኃሳብ የተዘጋጀው ኤክስፖ በሳይንስ ሙዚየም ከግንቦት 11 እስከ 18 ተካሂዷል። ትኩረቱን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና ዲጂታላይዜሽን ላይ ያደረገው “ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ 2024” በርካታ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ተቋማትና ግለሰቦችን ያሳተፈ ነበር።
በኤክስፖው ላይ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘርፉ የደረሰችበትን ደረጃ ለማጉላት የሚያግዝ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡ ትኩረታቸውን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ላይ ያደረጉ ኤክስፖዎች በሀገራችን መዘጋጀታቸው የዘርፉን ተዋናዮች በማቀራረብና ትስስር በመፍጠር ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬት ትልቅ ሚናን እንደሚጫወቱ በወቅቱ ተገልጿል።
ወጣት ደሳለኝ ተስፋው በዚህ ዓውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ወጣቶች አንዱ ነው። (የቀለም ሜዳ ቴክኖሎጂ) መስራች የሆነው ደሳለኝ፤ ስለ ድርጅቱ ሥራዎች ስናገር፤ በዋናነት በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሶፍትዌሮችን የማበልፀግ ሥራዎችን እንደሚሠራ ይናገራል። ለአብነት በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ ቴሌኮም እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፍ ላይ ሶፍትዌር በማበልፀግ አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚያደርግ ኩባንያ እንደሆነ ይናገራል።
<<እ ማክስ>> የሚል ስያሜ የተሰጠውና በትምህርት ዘርፉ ላይ ትኩረት በማድረግ የተሰራው ሶፍትዌር ይዞ የቀረበው ወጣት ደሳለኝ ስለዚህ የፈጠራ ሥራ ምንነት ሲናገር፤ “እ ማክስ” (exam management and correction system) ለተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የሚሰጡት ፈተናዎችን ማለትም ከስድስተኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሚሰጠውን የፈተና ሲይስተም ማስተዳደርና መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ይናገራል።
ይህም በሁለት መንገድ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚናገረው ደሳለኝ፤ የመጀመሪያው በወረቀት የሚሰጥ ፈተና ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰጠውን ፈተና አጠቃላይ ሂደት ከመነሻው ጀምሮ መቆጣጠር ማስተዳደርና ከስጋት ነፃ ማድረግ ማስቻሉ ነው ይላል።
ይህንን የፈተና አስተዳደር ሲስተም ሥራ ማስጀመር የተቻለው ከሶስት ዓመት በፊት በስምንተኛ ክፍል ፈተና ላይ እንደሆነ የተነገረው ደሳለኝ፤ አሁን ከሶስት ዓመት በኋላ በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ላይ አስራ አንድ ክልሎች ይህንን ሲስተም እየተጠቀሙ ይገኛሉ። በተጨማሪም ከአራት ነጥብ ሁለት ሚሊየን በላይ ተማሪዎች በዚህ ሲስተም ፈተናቸው እየታረመ እንደሚገኝ ይገልጻል።
ተማሪዎች ለፈተና ምዝገባ ከሚያካሄዱበት ጊዜ ጀምሮ የፈተና ውጤታቸውን የያዘው ሰርተፍኬት ፕሪንት ሆነ እስከሚጠናቀቅበት ያለውን ሂደት የክልል ትምህርት ቢሮዎች ይህንን አሰራር በመጠቀም ማስተዳደር እንደሚችሉ የፈጠራ ባለሙያው ወጣት ደሳለኝ ይናገራል።
እንደ ወጣቱ ገለፃ፤ በሀገራችን በተለይ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የእርማት ሂደቱ የሚከናወነው በወረቀት በእጅ እንደመሆኑ የሚፈጥረው ስህተት ከፍተኛ ነው። ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ በቀላል ወጪ ከዚህ ቀደም የነበረውን ኋላቀር አሰራር የሚያስወግድ ነው።
እንደ ሀገር የዚህ ቴክኖሎጂ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገረው ደሳለኝ፤ የብሔራዊ ፈተና ስርዓት ከውጭ የመጣ ሲስተም ነው። ከውጭ ኢምፖርት ተደርጎ የሚመጣ አሰራር ነው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስወጣ ነው። የአድሚሽን ካርድ፣ የመልስ መስጫ ወረቀት፣ የውጤት ሰርተፍኬት መስፈሪያ ሁሉ በከፍተኛ ወጪ ተገዝቶ የሚመጣ ነው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አለው ይህንን ማስቀረት መቻል ትልቅ እምርታ ነው ይላል።
በሁለተኛ ደረጃ እንደ ሀገር የቴክኖሎጂ ጥገኛ እየሆንን ነው። የቴክኖሎጂ አቅምን በራስ መዘርጋት የማይቻል ከሆነ ሌሎች አካለት በመማፀን ነው አገልግሎት ማግኘት የምንችለው፤ ይህ ደግሞ ዘመናዊ ባርነት ነው። ከዛ ባለፈ የሀገሪቱን የዳታ ሲስተም ከመጠበቅ አንፃር በውጭ የፈተና እርማት ሲከናወን ማሽኑ የሚቀበለው የመልስ ወረቀት ሂደቱን የሚመሩ አካላት ዲዛይን ያደረጉትን ብቻ ነው። ማሽናቸው ከወረቀታቸው ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ምክንያት የዳታ ደህንነት ጉዳይ ከእጅ ይወጣል ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። በአዲሱ ቴክኖሎጂ ግን ይህንን ማስቀረት እንደሚችል ይናገራል።
በዚህ ዘመን ንቁ ለሆነ ማኅበረሰብ ትልቁ ማሰሪያ (ዳታ) እንደሆነ የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው፤ ከዚህ አኳያ በመመልከት መንግሥት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንዲከታተለው ከፖሊሲ አንፃርም እንደዚህ አይነት አሰራር በሀገር ውስጥ በማልማት መጠቀም ይቻላል የሚል እምነት ተወስዶ ተግባራዊ እንዲደረግ ሥራዎቹን ይዞ እንደቀረበ ገልፇል።
ይህ የቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ ከሚሰጠው አገልግሎት ባለፈ ወደ ውጭ ኤክስፐርት የማደርግ አቅም እንዳለው የሚናገረው ደሳለኝ፤ በሀገር ውስጥ ከሁለት ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልላዊ ፈተናዎች ላይ ተግባራዊ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ይህ የሚያሳየው በብሔራዊ ደረጃ ጥቅም ላይ የመዋል አቅም እንዳለው ነው። ከዚህ አንፃር መንግሥት በፌዴራል ደረጃ ቴክኖሎጂውን አስገምግሞ እውቅና መስጠት መቻል አለበት፤ ይህ ቴክኖሎጂውን ኤክስፐርት ማድረግ እንዲቻል መደላድል እንደሚፈጥር ያስረዳል።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የብሔራዊ ፈተናቸውን ስርዓት ለማስተዳደር ቴክኖሎጂውን ከውጭ ኢምፖርት አድርገው እንደሚጠቀሙ የሚናገረው ደሳለኝ፤ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ይህንን የቴክኖሎጂ ውጤት ኤክስፐርት ማድረግ ብትችል ሶፍትዌር መሸጥ ብትጀምር ከገፅታ ግንባታ አኳያ የሚፈጥረው በጎ ተፅዕኖና እንዳለ ሆኖ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባው የውጭ ምንዛሬ ቀላል አይደለም እንደማይሆን ይናገራል።
አንድን ነገር ችግር ነው ብለን እስከወሰድን ድረስ ይህ ችግር መፈታት አለበት፤ ይህ ችግር ካልተፈታ ሀገር እያጣች ያለችው ነገር ይሄ ነው ብለን መለየት እስከቻልን ድረስ በተጨማሪም ለዚህ ችግር መፍትሔ መስጠት ከተቻለ ደግሞ የሚገኘው ፋይዳ ይህ ነው ብለን መለየት ከቻልን ምንም ነገር መስራት እንችላለን የሚለው ደሳለኝ፤ ከውጭ አስመጥተን የምንጠቀመውን ቴክኖሎጂ የሰሩት ሰዎች እስከሆኑ ድረስ እኛም በሀገር ውስጥ መሥራት እንችላለን፤ ትልቁ ነገር ችግሩን በአግባቡ መረዳት መቻል ነው። ይህ ቴክኖሎጂም ከዚህ አኳያ በመረዳት የተሰራ ነው ይላል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ለቴክኖሎጂና ፈጠራ የተሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚለው ወጣት ደሳለኝ፤ ከዚህ አንፃር በሀገር ውስጥ የተመረተ የቴክኖሎጂ ውጤት ከመጠቀም አኳያ የተወሰነ የእምነት ማጣት ጉዳይ ሊኖር ይችላል፤ ሆኖም የትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ በተዋረድ ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካለት በቂ ጥናት በማድረግ አብሮ ከመስራት ወደኋላ አይሉም የሚል እምነት እንዳለው ይናገራል።
“መንግሥት ሁሉንም ነገር መሥራት አለበት ብለን አናምንም” የሚለው ወጣት ደሳለኝ፤ መንግሥት መዋቅሩን መዘርጋት ለቴክኖሎጂ ሥራ አመቺ ሁኔታን መፍጠር ነው ያለበት እንጂ ሁሉንም ነገር መንግሥት እንዲሰራ አይጠበቅም፤ ስለዚህ ከመንግሥት የሚጠበቀው መሥራት የሚችሉ ስዎች መበረታታት፣ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ማስቻል ነው መሆን ያለበት ይላል።
ይህንን ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት የአስራ አንድ ክልሎች ትምህርት ቢሮዎች እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው፤ በፌዴራል ደረጃም አንድ ቀን በር ተከፍቶ አብረን እንስራ፤ በቴክኖሎጂው ላይ የሚጨመሩ ወይም የሚቀነሱ ነገሮች ላይ ከመግባባት ተደርሶ በብሔራዊ ደረጃ ጥቅም ላይ የሚውልበት ግዜ እሩቅ አይሆንም ይላል።
በሀገር ልጆች የተመረተ የተሻለ ነገር እስከመጣ ድረስ በኩራት መጠቀም እንጂ ወደኋላ የምንልበት ምክንያት አይኖርም በሂደት ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የፈተናዎች ኤጀንሲ ጥቅም ላይ የሚያውሉት ግኝት እንደሚሆን እምነት እንዳለው ይገልጻል።
የፈተና አሰጣጥ ሂደት ምስጢራዊና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆን ያለበት በመሆኑ ከዚህ አኳያ ሶፍትዌሩ ምን ያህል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው የሚለውን በተመለከተ የፈጠራ ባለሙያ ሲናገር፤ “ፈተናዎችን የሚያወጣው በቀጥታ ይህንን ሥራ እንዲሰራ ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት ተቋም ነው። እኛ ምንም አይነት ግንኙነት ከፈተና ጋር አይኖረንም እኛ የምናቀርበው የሶፍትዌር አገልግሎት ነው። ሶፍትዌሩን የሚያስተዳድሩት የፈተናዎች ኤጀንሲ ወይም ትምህርት ሚኒስቴር ናቸው”። ከዚህ አንፃር የደህንነት ሁኔታ አሳሳቢነት የሌለው ነው ይላል።
ወጣት ደሳለኝ እንደሚናገረው፤ በኢትዮጵያ ደረጃ ትልቁ የደህንነት ፍተሻ የሚያካሂደው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በየስድስት ወሩ ይህንን ሲይስተም እየፈተሸ የደህንነት ስጋት እንደሌለበት ማረጋገጫ እየሰጠ ጥቅም ላይ እንዲውል ምክረ ሀሳብ እየሰጠ ነው። በዚህ አግባብ ከደህንነቱ ስጋት ነፃ የሆነ ስርዓት ስለመሆኑ እውቅና እንዳለው ይናገራል።
መንግሥት በተለይ ለቴክኖሎጂ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ የሚናገረው ደሳለኝ፤ ነገር ግን ዓለም ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃርና ሌሎች ሀገራት በዘርፉ ከደረሱበት ልህቀት አኳያ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቃል። በተለይ የመንግሥት ተቋማት ላይ ያለው የቴክኖሎጂ ፍላጐት አሁንም ገና እንደሆነ ይገልጻል።
ተቋማት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያዘምኑ በፖሊሲ ደረጃ አቅጣጫዎች ቢኖሩም በተግባራዊነቱ ላይ አሁንም ክፍተት አለ ተቋማት ከለመዱት አሰራር ተላቀው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አሁንም በትኩረት መሥራት አስፈላጊ ነው ይላል።
ይህ ቴክኖሎጂ ለፈተና ሥርዓት አስተዳደርና ተያያዥ ለሆኑ ወጪዎች የሚወጣውን ከስድስት ነጥብ ስምንት ሚልየን ፓውንድ በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት የሚችል ቴክኖሎጂ እንደሆነ የሚናገረው ደሳለኝ፤ ይህም የውጭ ምንዛሬ ከማዳን አኳያ ብሎም በቴክኖሎጂ እራስን ከማብቃት አንፃር ብዙ ትርጉም ያለው እንደሆነ ይናገራል።
በመጨረሻም የፈጠራ ባለሙያው ወጣት ደሳለኝ፤ ባስተላለፈው መልዕክት ትውልድ የአሁኑንና ሊመጣ የሚችለውን ዘመን መዋጀት አለበት፤ ወጣቱ አሁን ያለንበት ዘመን ምንድነው? ምን ይፈልጋል? የወደፊቱስ ዘመን ምን አይነት ሊሆን ይችላ? የሚለውን በመለየት ዘመኑ ለሚፈልገው ነገር ዝግጁ መሆን አለበት።
አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ ዘርፉን መቀላቀል ተገቢ ነው። ከዚህ አኳያ ወጣቶች በዘርፉ ፍላጐት ኖሯቸው መሥራት አለባቸው፤ ነገሮች አልጋ በአልጋ ስለማይሆኑ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ በሁሉም ረገድ እራሳቸውን ብቁ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግሯል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም