በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙና የመሮጫ መምን (ትራክን) አካተው ከተገነቡ ስታዲየሞች መካከል የአሰላ አረንጓዴ ስታድየም አንዱ ነው። ስታድየሙ ከተገነባ 20 ዓመት ሲሆነው፤ የመሮጫ መሙ (ትራኩ) ደግሞ ከ13 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። የመሮጫ መሙ ከእድሜ እና ከአገልግሎት ብዛት ጋር ተያይዞ ከጥቅም ውጪ ወደሚሆንበት መንገድ ላይ ቢሆንም ለእድሳቱ ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው የአሰላ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ስታድየሙን በበላይነት የሚያስተዳድረው ጽህፈት ቤቱ በአገልግሎት ብዛት የተጎዳውን የመሮጫ መም፣ ክቡር ትሪቡን እና አጥሩን አድሶ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል። የመሮጫ መሙ በየወቅቱ የሚካሄዱትን የክልል እና ሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችን እንዲሁም ልምምዶችን የሚያስተናግድ በመሆኑ፣ በሚደርስበት ጫና ምክንያት ከጥቅም ውጪ ወደ መሆን እየሄደ ይገኛል። ስፍራው በርካታ አትሌቶች የሚፈሩበት በመሆኑ ለልምምድ በርካቶችን ሲያስተናግድ ከተለያዩ የክልሉና የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ አትሌቶች፣ ፕሮጀክቶች እና ክለቦችም ይጠቀሙበታል። በዚሁ የአገልግሎት ብዛትና ከእድሜ ጋር የተያያዙ ጫናዎች ቢኖሩም እስከ አሁን ድረስ እድሳት አልተደረገለትም፡፡
የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት የተጎዳውን የመሮጫ መም (ትራክ) ለማደስ፣ ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ንግግሮችን ቢያደርግም በሚፈለገው ልክ ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል። ታድሶ የተለመደውን አገልግሎት እንዲቀጥል የህዝብና መንግሥትን አፋጣኝ እገዛ እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል። በርካቶች ውጤታማ የሆኑበትና ለተተኪ አትሌቶች መፈጠርም ምክንያት የሆነውን የመሮጫ መም እድሳት እገዛ እንዲያደርጉ ለአትሌቶችም ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ የተሰጠ ምላሽ ግን የለም። መሙ ትኩረት እንዲያገኝ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ተሰጥቶት ቢዘገብም ምላሹ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡
የአሰላ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዶ ዳባ፤ የስታድየሙ የመሮጫ መም ብዙ ጫናዎችን እያስተናገደ ያለ እድሳት በጽሕፈት ቤቱ ጥበቃና እንክብካቤ እስከ አሁን መቆየቱን ይገልጻሉ። ዓመታትን አስቆጥሮ እድሳት ያልተደረገለት ብቸኛ ስታድየም በመሆኑ በፍጥነት ጥገና ሊደረግለት ይገባል። ለክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮና እና ጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውን አካላት እንዲሁም ከስፍራው የወጡ አትሌቶች ለእድሳቱ እገዛ የተጠየቁ ቢሆንም ምላሽ የሰጠ አካል አልተገኘም፡፡
ስታድየሙን ለማደስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ባለሙያዎችን መድቦ የእድሳቱን ዋጋ አስጠንቶ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በአሁኑ የገበያ ዋጋ 18 ሚሊዮን ብር ተገምቷል። ይህንንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እና የክልሉን ወጣቶችና ስፖርት ቢሮን በደብዳቤ በመጠየቅ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እና የቢሮ ኃላፊው መሙ ያለበትን ደረጃ መመልከታቸውን ጠቁመዋል። ሁሉም ስታድየሙንና መሙን (ትራኩን) ለማደስ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ግን የስታድየሙን እና የመሙን እድሳት ለማከናወን ባስጠናው የዋጋ ተመን መሰረት ለ2017 ዓ.ም እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አቶ በዶ ጠቁመዋል።
የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ የስታድየሙን የዙሪያ አጥር ከባዛር በተሰበሰበ ገቢ አማካኝነት፣ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ ሱቆችና የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት እንዲችል ተደርጎ እያሰራ ይገኛል። በዚህም መሰረት ፕሮጀክቱን በሶስት ወራት ለማጠናቀቅ ከተቋራጭ ጋር ውል የተገባ ሲሆን፣ 10 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሰራም ነው። የስታድየሙ እድሳት በሁለት ምዕራፍ የሚከናወንና ከአጥር እንዲሁም ከመሮጫ መም ውጪ የክቡር ትሪቡን ወንበሮች እድሳት ይገኝበታል።
አንገብጋቢውና ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ መታደስ የሚገባው የመሮጫ መም ግን በፍጥነት ታድሶ ወደ አገልግሎት መግባት እንደሚኖርበት ጽህፈት ቤት ኃላፊው አክለዋል። ለዚህም የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮና ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈዴሬሽን ጋር በትብብር የሚሰሩ ከሆነ በፍጥነት ታድሶ የተለመደውን አገልግሎት መስጠት ይችላል። ጽህፈት ቤቱም የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ በመሆኑ ሌሎች ባለድርሻዎችም የበኩላቸውን እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የክልል ሀብት የሀገርም ሀብት በመሆኑ እድሳትና እንክብካቤው በአፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡
በስታድየሙ አስተዳደር ስር የሚሰሩ የተወሰኑ የሜዳ ተንከባካቢዎች ያሉ ሲሆን፤ እድሳት ከተደረገለት በኋላ እንክብካቤውን እና ጥበቃውን አጠናክረው እንደሚሰሩም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም