በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖችን በመገጣጠም ስራ የተሰማሩት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች

መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትና ተሳታፊነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ ይታወቃል:: አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ በመሆን ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት እንዲችሉ በሚደረገው ጥረት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል::

ከዚህም ባለፈ መንግሥት በ2022 ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርጉ የተለያዩ ዕቅዶችን በማውጣት እየሠራ ይገኛል:: ይህም አምራች ኢንዱስትሪውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችል ዕቅድ እንደሆነ ይታመናል::

እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መነቃቃት እንዲፈጠርባቸው አድርገዋል:: በተለይ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ተነቃቅተው ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም:: በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ ይበል የሚያሰኝ ነው::

አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ባለው በዚህ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች መካከልም ሀገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣው የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀሩትን፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑትን የኤሌክትሪክ መኪኖችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ ያሉ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሃብቶች ይገኙበታል::

በአገር ውስጥ ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል በቡና ምርትና ኤክስፖርት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚታወቀው ቀርጫንሼ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አንዱ ነው::

የድርጅቱ መስራችና ባለቤት አቶ እስራኤል ደገፋ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪናን መጠቀም የሚያስችል ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረጓን ጠቅሰው፣ በማኅበረሰቡም ዘንድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ፍላጎት ከፍ እያለ መምጣቱን ጠቅሰዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ የተለያዩ ድርጅቶች ፖሊሲውን መሰረት በማድረግ እንዲሁም ይህን የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት የኤሌክትሪክ መኪኖች በአገር ውስጥ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ እየተሠራ ነው:: የኤሌክትሪክ መኪኖቹን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት ይልቅ በአገር ውስጥ ገጣጥሞ ለተጠቃሚዎች ማቅረብ የበለጠ አዋጭና ተመራጭ ሲሆን፤ በተለይም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ለምትፈተን አገር የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል::

በአሁኑ ወቅት በነዳጅ ከሚሰሩ መኪኖች ይልቅ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቀሱት አቶ እስራኤል፤ የኤሌክትሪክ መኪኖቹ አዋጭና ተመራጭ መሆናቸውንም ይናገራሉ፤ ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ መኪኖችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ወደ ገበያው ለመግባት እየተንደረደረ መሆኑን አመላክተዋል:: የኤሌክትሪክ መኪኖቹን በአገር ውስጥ የመገጣጠሙን ሥራ ከውጭ ድርጅት ጋር እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ይህም በመገጣጠሙ ስራ ውጤታማ ለመሆን የተሻለ መንገድ መሆኑን አስታውቀዋል::

‹‹አምራች ድርጅቶች አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገበያ ይዘው በመምጣት የአገሪቷን የማምረት አቅም ማሳደግ አለባቸው›› የሚሉት አቶ እስራኤል፤ ኢትዮጵያ እስካሁን የዓለም ሸቀጥ ማራገፊያ ሆና ቆይታለች:: ይህንን ለመቀየር ደግሞ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል:: አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራት ያላቸውና ተወዳዳሪ ምርቶችን በማምረት ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ ገበያ ተደራሽ ለመሆን መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል:: ይህን በማድረግ በግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ብቻ የምትታወቀው ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ተሳታፊ መሆን አለባት፤ ለዚህም የመንግሥት ድጋፍና ክትትል ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ በርካታ ሀገራት የኤሌክትሪክ መኪኖችን ምርጫቸው በማድረግ ተጠቃሚ ሆነዋል:: እንደ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈትናቸው አገራትም ቢሆኑ የኤሌክትሪክ መኪኖችን መጠቀማቸው አዋጭነቱ አያጠያይቅም:: ድርጅቱ በአገር ውስጥ የሚገጣጥማቸውን የኤሌክትሪክ መኪኖች ወደ ገበያው ከማስገባቱ አስቀድሞ ይጠቀምባቸዋል:: በቀጣዩ ዓመት ድርጅቱ እንደ ድርጅት ሙሉ ለሙሉ የኤሌክትሪክ መኪኖችን የሚጠቀም ይሆናል:: በዚህም ከነዳጅ ጋር ተያይዘው ያለአግባብ የሚመጡ ከፍተኛ ወጪዎችን መቀነስ ይቻላል::

‹‹ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለነዳጅ ታወጣለች›› ያሉት አቶ እስራኤል፤ ይህን ከፍተኛ የአገሪቷ ወጪ መቀነስ እንደሚገባም ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅት በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ ለመቀየር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እጅግ የሚበረታታና ውጤታማ እንደሆነ ጠቅሰዋል:: በተያያዘም ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ለሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲውል በማድረግ የአገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል::

የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቻርጅ ለማድረግ ቢበዛ 30 ደቂቃ እንደሚወስድ አቶ እስራኤል አስታውቀው፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዳጅ ለመቅዳት በየማደያው ከሶስት ሰዓታት በላይ መቆም የግድ የሚሆንበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል:: ማንም ሰው የኤሌክትሪክ መኪኖቹን በቤቱ ሆኖ በፈጣን ቻርጀር ለ30 ደቂቃ ቻርጅ በማድረግ ከ800 እስከ 1000 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚችልም አመልክተዋል:: ይህን በተግባር ማየት ችያለሁ ሲሉ ጠቅሰው፣ መኪናቸውን በሳምንት አንድ ጊዜ ለ30 ደቂቃ በፈጣን ቻርጀር ቻርጅ እንደሚያደርጉና በቀላሉ የሚያልቅ እንዳልሆነም ተናግረዋል:: የነዳጅ ወጪያቸውን በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻላቸውንም አስታውቀዋል::

አቶ እስራኤል እንዳብራሩት፤ የኤሌክትሪክ መኪኖች ወጪ ከመቀነሳቸው ባለፈ ጩኸት ወይም ድምጽ እና ጭስ የሌላቸው በመሆኑ ከተማን አይበክሉም:: ንጹህ አየር መተንፈስ ያስችላሉ:: ቴክኖሎጂው እጅግ አስፈላጊና ተስማሚ ስለመሆኑ እስካሁን በሚገባ አላየንም፤ አሁን ግን አይናችንን ከፍተን ልናየው የሚገባ ትልቅና ዘርፈ ብዙ አበርክቶ ያለው ነው::

የኤሌክትሪክ መኪኖቹ በዋናነት የሚፈልጉት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደመሆኑ የኤሌክትሪክ መኪኖቹን ቻርጅ ለማድረግ ብዙ ቦታ አይፈልግም፤ በትንሽ ቦታ ላይ እንደ ሞባይል ስልክ ቻርጅ ማድረግ ይቻላል:: በከተማ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት ሊኖሩ ይገባል:: ለዚህም ድርጅታቸውም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየተነጋገረ ይገኛል:: ከተማ አስተዳደሩም ፈጣን ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላትን በቅርቡ ያመቻቻል የሚል ዕምነት አለ::

ቀርጫንሼ ትሬዲንግ አሁን እየገጣጠማቸው ከሚገኙት የኤሌክትሪክ መኪኖች መካከል የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ጨምሮ የቤት አውቶሞቢሎች ይገኙበታል:: በአሁኑ ወቅትም የመገጣጠም ስራቸው የተጠናቀቀ ለገበያ ሊቀርቡ የተዘጋጁ 100 የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች አሉ:: እነዚህ አውቶሞቢሎችም ለሜትር ታክሲ ወይም ለራይድ አገልግሎት መዋል የሚችሉ ናቸው:: ተሽከርካሪዎቹ ወጪ ከመቆጠብና የአየር ብክለትን ከመከላከል ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራም የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የላቀ ነው::

ሌላኛው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እየገጣጠመ ያለው የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ እንግዳው እንዳሉት፤ ኩባንያው የኤሌክትሪክ መኪኖቹን በአገር ውስጥ መገጣጠም የጀመረው ከ2015 መገባደጃ አንስቶ ነው::

እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ የኤሌክትሪክ መኪኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል:: በአሁኑ ወቅትም ከ25 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ዓለም ላይ ይገኛሉ:: እነዚህን መኪኖች በመያዝ ትልቁን ድርሻ የምትይዘው ቻይና ናት፤ 60 በመቶ ያህሎቹ የኤሌክትሪክ መኪኖች እየተመረቱ ያሉትም በቻይና ነው::

ኢትዮጵያ ውስጥ በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የሚገጣጠሙት የኤሌክትሪክ መኪኖችም ቻይና ውስጥ ባሉ የጎልደን ድራገን ብራንድ የሚመረቱ መሆናቸውን አቶ ሰጠኝ ጠቅሰው፣ ኩባንያው በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው መካከል የጎልደን ድራገን ብራንዶችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት እየተገጣጠመ ይገኛል ብለዋል:: በ2015 ዓ.ም መገባደጃ የመጀመሪያዎቹን 216 የኤሌክትሪክ መኪኖችን በተለይም 15 ሰዎችን የሚጭኑ ሚኒባሶችን ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል::

‹‹የኤሌክትሪክ መኪና ፍላጎት በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ እያደገ የመጣበት የራሱ ምክንያት አለው›› ያሉት አቶ ሰጠኝ፤ ይህም ከከባቢ አየር ብክለት ነጻ የሆነን አካባቢ ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ይላሉ:: ሌላው በነዳጅ ተጽዕኖ ሥር ያለውን ዓለም ከነዳጅ ተጽዕኖ ማላቀቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ከታዳሽ ኃይል ኤሌክትሪክን ማምረት በሚችሉ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የኤሌክትሪክ መኪኖች ቢስፋፉ አዋጭ ነው:: በተለይም አገሪቷ ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የምታወጣውን ከ40 በመቶ በላይ ወጪም መቀነስ ያስችላታል:: በዚህ ሁለት ዓመታት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እየናረ መጥቷል:: በየነዳጅ ማደያዎች የሚታዩ ሰልፎችም ከነዳጅ ጋር ያለንን ጥገኝነት ያመለክታሉ::

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በኤሌክትሪክ መኪና ፍላጎት ከቀዳሚዎቹ አገራት ተርታ የምትገኝ መሆኗን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አመልክተው፣ መኪና መገጣጠሚያም በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ አገር የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቀዋል፤ ለዚህም የመኪና መገጣጠሚያዎቹ ምቹ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መኪና መገጣጠሚያው በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው ብለዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ትልቅ የኤሌክትሪክ አቅም ያላት አገር እንደመሆኗ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች አሏት:: እነዚህም አገሪቷ ምትፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው:: የኤሌክትሪክ ኃይል ለመኪኖች ብቻ ሳይሆን ለፋብሪካዎችና ለአጠቃላይ ኑሮ ያስፈልጋል:: ስለዚህ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቻርጅ እየተደረጉ የሚሰሩ አንደመሆናቸውና በቀጣይም በብዛት መኪኖቹ የበለጠ ወደ ስራ ሲገቡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ የተሻለ መሆን ይኖርበታል::

አቶ ሰጠኝ እንዳብራሩት፤ የኤሌክትሪክ መኪኖቹ በሁለት አይነት መንገድ ቻርጅ ይደረጋሉ:: አንደኛው ፋስት ቻርጅ የሚባለው ሲሆን፣ ይህም በፍጥነት ወይም ከ30 እስከ 45 ደቂቃ ቻርጅ ማድረግ የሚችል ነው:: ሁለተኛው በቤት ውስጥ ቻርጅ የሚደረግና እንደ ሞባይል ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል ነው:: ስለዚህ መኪኖቹ በሚቆሙበት ቦታ ቻርጅ መደረግ አለባቸው:: ለዚህም የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ተደራሽ መሆን ይኖርበታል:: መጠቀሙ በነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነን አገር በኤሌክትሪክ ወደሚሰሩ መኪኖችን ስናሸጋግር ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል፤ ሊወጣ ይችል የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለሌሎች አገልግሎቶች በማዋል ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል::

ኩባንያው የሚያቀርባቸው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው:: ሌሎች በግለሰብ ደረጃ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች አሉ::

ከ80 ሺ በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደገቡ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ መረጃን ጠቅሰው ያብራሩት አቶ ሰጠኝ፤ እነዚህ መኪኖች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስፈልጋቸው እንደመሆኑ መንግሥት መኪኖቹ ኃይል የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለበት አስገንዝበዋል::

በላይነህ ክንዴ ግሩፕ የሚያቀርባቸው መኪኖች ከነቻርጀራቸው እንደሚቀርቡ የገለጹት አቶ ሰጠኝ፤ በአማካኝ ለአስር መኪኖች አንድ ቻርጀር እንደሚቀርብም አስታውቋል:: ለአብነትም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለገዛቸው 150 በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ለአስር መኪኖች አንድ ቻርጀር በድምሩ ከ15 ቻርጀሮች በላይ ከመኪኖቹ ጋር አብሮ ተሰጥቷል ሲሉ አብራተዋል:: የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽንም እንዲሁ አስር መኪኖችን ገዝቶ አንድ ቻርጀር ወስዷል ያለው ዳይሬክተሩ፣ እነዚህ አስር መኪኖች ቢሮ ውስጥ ቻርጅ መደረግ የሚችሉ መሆናቸውን ነው ያስታውቁት::

ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ ድርጅቱ መኪናውን ብቻ ሳይሆን የቻርጅ ችግር እንዳይፈጠር ጭምር ቻርጀሮችንም ያስመጣል:: በተለይም በርካታ ቁጥር ያላቸውን የኤሌክትሪክ መኪኖች ለሚገዙ ድርጅቶች ቻርጀሮችን በመኪናው ዋጋ እንዲያገኙ ይደርጋል::

የኤሌክትሪክ መኪኖቹ ያለ ቻርጀር የሚሰሩ ባለመሆናቸው በየአካባቢው የኤሌክትሪክ መኪኖቹ ቻርጅ የሚያደርጉበት ቦታ ሊኖር ይገባል ያሉት አቶ ሰጠኝ፤ አሁን ላይ በ50 ኪሎ ሜትር ውስጥ ቻርጀሮች እንዲኖሩ፣ ነዳጅ ማደያዎች ቻርጀር እንዲኖራቸውና የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ተቋማት አካባቢም እንዲሁ ቻርጀሩ እንዲኖር አስገዳጅ ሕጎች እየወጡ እንደሆነም አስታውቀዋል::

ለዚህም ድርጅቱ የኤሌክትሪክ መኪና አቅራቢ እንደመሆኑ በከተማዋ የኤሌክትሪክ ቻርጀር እጥረት እንዳይፈጠር እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባባር ስታዲየም አካባቢ አምስት ቻርጀሮችን ለመትከል በራስ ተነሳሽነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል::

መኪኖቹ በአገር ውስጥ መገጣጠማቸው መለዋወጫቸውን በቀላሉ ለማግኘት ይረዳል ያሉት አቶ ሰጠኝ፣ በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች እንደ አገር ካላቸው ፋይዳ አንጻር በመንግስት ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል::

ድርጅቱ ሥራ ሲጀምር ከባድ የደረቅና ፈሳሽ የጭነት መኪኖችን ይገጣጥም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰጠኝ፤ ከዚህ ባለፈም በአሁኑ ወቅት የመኪና አካላትን በአገር ውስጥ ማምረት መጀመሩን ነው የገለጹት:: አዳዲስ የኤሌክትሪክ መኪኖችንም እንዲሁ በአገር ውስጥ ገላን እና ደብረብርሃን በሚገኙ ሁለት መገጣጠሚያ ፋብሪካዎቹ እየተገጣጠመ መሆኑን አስታውቀዋል:: በቀጣይም ከዚህ በተሻለ መንገድ የተለያዩ የመኪና አካላትን በአገር ውስጥ አምርቶ ከሕዝብ ትራንስፖርት በተጨማሪ በግለሰብ ደረጃ የሚያዙትን አውቶሞቢል መኪኖችንም በአገር ውስጥ የመገጣጠም ዕቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል::

ኩባንያው በደብረ ብርሃን የገነባውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሰሞኑን ማስመረቁም ይታወቃል::

ፍሬሕይወት አወቀ

 አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You