ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጊኒ ቢሳውን ይገጥማሉ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የ2026 ዓለም ዋንጫ ማሪያ የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎችን በዚህ ሳምንት በማካሄድ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አንድ ዛሬ እና ነገ ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን፤ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላም የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ይቀጥላሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም (ዋሊያዎቹ) ከጊኒ ቢሳው እና ከጅቡቲ አቻዎቹ ጋር ከሜዳው ውጪ ይገናኛል።

ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና አሜሪካ በጋራ በመሆን ለሚያዘጋጁት የ2026 ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ አህጉራት በመካሄድ ላይ ይገኛል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንም 52 አባል ሀገራትን በዘጠኝ ምድቦች ከፋፍሎ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎችን እያከናወነ ነው። በዚህም መሰረት በተያዘውና በመጪው ሳምንት ጥቂት ቀናት የየምድቡ የመጀመሪያ ዙር ቀሪ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ሴራሊዮን እና ጅቡቲ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሴራሊዮን ጋር በማድረግ ያለምንም ግብ መለያየቷ የሚታወስ ነው። ቀጣዩን ጨዋታ ደግሞ በቡርኪና ፋሶ የ3 ለምንም ሽንፈት ደርሶባት አንድ ነጥብ ብቻ ይዛ ከምድቡ ግርጌ ተቀምጣለች።

ዋልያዎቹ የምድቡን ሶስተኛ ጨዋታም ነገ ከጊኒ ቢሳው ጋር በቢሳው ስታዲየም የሚያደርጉ ሲሆን፤ ባለፈው ሰኞም ወደ ስፍራው ተጉዘዋል። በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በመመራት ላይ የሚገኙት ዋሊያዎቹ ለዚህ ጨዋታ የሚሆናቸውን ዝግጅት ከሁለት ሳምንታት በፊት የጀመሩ ሲሆን፤ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ስታዲየም የነበራቸውን ልምምድ አጠቃለው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ደርሰዋል። ቡድኑ ወደዚያው ከማቅናቱ በፊት በዋና አሰልጣኙ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በዚህም ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጎ ወደ ዝግጅት ቢገባም ወሳኞቹ ተጫዋቾች ያሬድ ባዬ፣ ቸርነት ጉግሳ እና ሄኖክ አዱኛ በጉዳት ምክንያት ቡድኑን መቀላቀል እንዳልቻሉ ተጠቁማል። በመሆኑም በቡድኑ ውስጥ ሽግሽግ በማድረግ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ የነገውን ጨዋታ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ከኢትዮጵያ እና ከግብጽ ጋር ላሉበት ጨዋታ ሲዘጋጅ የቆየው የጊኒ ቢሳው ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ፤ በጠንካራ ስብስብ የተደራጀ ቡድን ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ወሳኝ ለሆኑት ጨዋታዎች የአውሮፓ ሊጎችን ጨምሮ በሌላ ሀገራት የሚጫወቱ ተጫዋቾች እንዲሁም አሰልጣኝ ጥሪ በማድረግ ሲዘጋጅ ቆይቷል። ይህንን ተከትሎም አሰልጣኝ ገብረመድህን በቡድናቸው ስነልቦና ላይ የሚፈጥረው ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል። ቡድኑ በአውሮፓ ክለቦች በሚጫወቱ ተጫዋቾች መደራጀቱ በተጫዋቾቻቸው ላይ ጫና የሚፈጥር ከሆነ ሴራሊዮንም ሆነ ቡርኪና ፋሶ በተመሳሳይ የሚጠቀሱ እንደመሆኑ መላመዱ አስፈላጊ ነው።

ተጫዋቾች የአሸናፊነት ስሜት እንዲያድግ እየተሰራ ሲሆን፤ ፕሮፌሽናል አስተሳሰብን ማዳበር ተገቢ ነው ተብሏል። ጨዋታው በተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ መሆኑ የተወሰነ እገዛ ቢኖረውም በተቻለ መጠን ለመቀየር ቡድናቸው ጥረት እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

በምድቡ የጨዋታ መርሀ ግብር መሠረት ትናንት ሴራሊዮን እና ጅቡቲ ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ ኢትዮጵያ ከጊኒ ቢሳው እንዲሁም ግብጽ ከቡርኪና ፋሶ ይገናኛሉ። ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ደግሞ ሌላኛዎቹ የምድብ ጨዋታዎች ተከናውነው የ2016 የዓመቱ መርሀ ግብር የሚዘጋ ይሆናል። በዚህም በመጪው እሁድ ሰኔ 2/2016ዓ.ም ሞሮኮ ላይ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ይጫወታሉ። በቀጣዩ ቀንም ግብጽ ከጊኒ ቢሳው እንዲሁም ሴራሊዮን ከቡርኪና ፋሶ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You