ሚዲያው የስፖርት ተቋማት አሰራርን ሊፈትሽ ይገባል

ስፖርት አሁን ከደረሰበት የእድገትና ዘመናዊነት ደረጃ ላይ እንዲገኝ መሰረታዊ ለውጥ ካመጡ ጉዳዮች መካከል የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል:: እአአ 1990ዎቹ አጋማሽ አንስቶ የመገናኛ ብዙሃን ለስፖርት የሚሰጡት ሽፋን መጨመርን ተከትሎ፤ ተደራሽነትን ብቻ ሳይሆን ስፖርት ራሱን የቻለ ግዙፍ ዘርፍ እንዲሆን አስችሏል:: ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያም የሚስተዋል ሲሆን ትኩረታቸውን በስፖርት ላይ ያደረጉ የኅትመት፣ የብሮድካስት እንዲሁም ድረ-ገጾች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ነው:: ለዘርፉ ያላቸው አበርክቶም የላቀ ነው::

ለሀገራት የስፖርት እንቅስቃሴ ማደግ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን በስፖርት ሜዳ ላይ የሚመዘገበው ውጤት ብቻውን ዋጋ አይኖረውም:: በመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ሽፋን አግኝቶ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ መሆን ይኖርበታል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው ከሆነም ካሉት የመገናኛ ብዙኃን ብዛት አኳያ በሀገር ውስጥ የስፖርት ጉዳይ ሽፋን በመስጠት የሚሰሩት በጣት የሚቆጠሩት ናቸው:: ስፖርትና መገናኛ ብዙኃን የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሆነው ሳለ የሃገር ውስር ስፖርት ትኩረት ማጣቱ አስገራሚ ቢሆንም፤ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ግን ሊነሱ ይችላሉ::

የሀገር ውስጥ ስፖርትን በማስተዋወቅና ታሪክን በመሰነድ ረገድ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የቆየው የኅትመት ውጤቶች መዳከምና መመናመን ተጠቃሽ ነው:: በስፖርት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚሰሩ ጋዜጦች በርካታ ቢሆኑም ከኅትመት ዋጋ ውድነት እና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች የተነሳ የተዘጉ ጋዜጦች ቁጥር ጥቂት አይደለም:: በእርግጥ የብሮድካስትና የድረ-ገጾች መፈጠር ለስፖርቱ ትልቅ ትንሳኤን ማምጣት ችሏል:: ነገር ግን በኢትዮጵያ ስፖርቱ በሚገባው ልክ ትኩረት አግኝቶ እንዲያድግ አሰራሮችን በመፈተሽ የተሰራው ስራ አጥጋቢ አይደለም::

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በስሩ ከሚገኙ ጣቢያዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የኤፍ ኤም አዲስ 97ነጥብ1 የምስረታ (24 ዓመት) ክብረ በዓልን በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ውይይት በማድረግ ያከበረ ሲሆን፤ ለውይይት ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል የስፖርትና የመገናኛ ብዙኃን ግንኙነትን ይመለከታል:: የኢትዮጵያ መገናኛ በዙኃን (ሚዲያ) ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት አበርክቶ፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ ጉዞዎች በሚል የመነሻ ሃሳብ ጽሁፎች ቀርበው በስፖርት ጋዜጠኞች፣ የስፖርት ፌዴሬሽን ኃላፊዎች እና አሰልጣኞች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል::

በኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ውስጥ የኅትመት፣ የብሮድካስትና የበይነ መረብ የመገናኛ ብዙኃን አብረክቶ ትልቅ እንደሆነና ስፖርቱን አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲጓዝ ማድረጉን በቀረበው ጽሑፍና እና የውይይቱ ተሳታፊዎች ሃሳብ ተነስቷል:: ስፖርቱን በማስተዋወቅ፣ ታሪክን በማነጽ እና በማስተማር ረገድ አስተዋጽኦ አላቸው:: በዓለም መድረክ በስፖርቱ የተፈጠሩ ጀግኖች፣ ድሎች እና ለሀገር የተደረጉ ተጋድሎዎች በጋዜጦች ታትመው፣ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ተዘግበው የጋራ ታሪክ በመሆን እንዲዘከሩ ማድረግ ተችሏል:: ኢትዮጵያን በስፖርት በዓለም ደረጃ በውጤታማነት እንድትታወቅና ገጽታዋ እንዲቀየርም አድርገዋል::

ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃኑ የዘርፉን አሰራር በመፈተሽ ረገድም መስራት እንደሚኖርባቸውም ነው የተጠቀሰው:: ስፖርት በዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት የሚመራ እንደመሆኑ መንግስት የተቋማቱን አሰራር ለመፈተሽ የሚያስችል ኃላፊነት የለውም:: ስለሆነም አሰራሩን በመፈተሽ እንዲስተካከል የማድረጉ መብትና ኃላፊነት የመገናኛ ብዙሃን ይሆናል:: ለዚህም ተገቢውን ትኩረት እና ቦታ በመስጠት የስፖርት ማኅበራትን፣ ክለቦችን፣ ተቋማትን እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ተደራሽ በማድረግ መስራት ይገባል::

የስፖርት ፖሊሲ ማነቆዎች፣ የምርመራ ዘገባ እና የግልጸኝነት ችግር የመገናኛ ብዙሃኑ ለስፖርቱ በትክክል ሽፋን እንዳይሰጡና አሰራራቸውን በተገቢ ሁኔታ እንዳይፈትሹ ተግዳሮቶች የሆኑ ጉዳዮች ተደርገው ተነስተዋል:: አጀንዳ ቀረጻ፣ በቂ ሽፋን፣ የይዘት ጉዳይ እና በተለያዩ አካላት የሚደርሱት ጫናዎችም ስፖርቱ ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ ከሚያደርጉት ውስጥ ናቸው:: ሚዛናዊነትን ያልጠበቁ ስራዎች፣ አንዳንድ ጋዜጠኞች ሙያው የሚፈልገውን ባህሪ አለመላበስ፣ ሙያ ብቃት ማነስ፣ የስፖርት ባህልን መሸርሸር፣ … ደግሞ ስፖርቱ እንዳያድግ ማድረጉን ከተሳተፊዎች የተነሱ ነጥቦች ናቸው::

የሃገር ውስጥ ስፖርት ተገቢውን ሽፋን እንዲያገኝና ወደ ፊት ጉዞውን የተሻለ ለማድረግ መሰራት ይገባቸዋል በሚልም በተሳታፊዎች የመፍትሄ ሃሳቦች ቀርበዋል:: ከእነዚህ መካከል ለሙያው የሚታመን ጋዜጠኛን መፍጠር፣ ሚዛናዊ ዘገባ፣ አውደ ጥናትና የፓናል ውይይቶችን ማዘጋጀት፣ የመገናኛ ብዙኃን በአዋጅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ፣ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነትን መፍጠር፣ ከሰለጠኑት ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ ጠቃሚ እውቀቶችን በመቅሰም ስፖርቱን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ የሚሉትም ይገኙበታል::

ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You