መሥራት የሚከብዳቸው መተቸት ይቀላቸዋል!

ከነገራችን በፊት፤ ‹‹የሥራ ትንሸ የለውም›› የሚባል ነገር በበኩሌ አያሳምነኝም። አተያየቱ እንዴት ቢሆን ነው ግን? እንደ አባባሉ ከሆነ እኮ በወር የመቶ ምናምን ሺህ ብር ደሞዝተኛ እና የማይሸጥ ዕቃ ይዞ ጎዳና ለጎዳና ሲዞር የሚውል እኩል ናቸው ማለት ነው። ለምን እንደሚባል ግልጽ ነው። የሚያስገኘው ገቢ ማነስና መብዛት አይደለም፤ ሥራው ግን ያው ሥራ ነው ሊባል ይችላል።

የምርምር የሥራ ትልቅ እና ትንሽ የለውም። ትልቅ እና ትንሽ የሚያደርገው ራሱ ባለቤቱ ነው። አንድ የሪልስቴት ባለቤት ከማስቲካ አዟሪነት የተነሳ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ማስቲካ ማዞርን ቀላል ሥራ አንለውም ማለት ነው። አንድ የሪልስቴት ባለቤት ካላወቀበት የዕለት ጉርሱን እስከሚያጣ ድረስ ወደ ድህነት ሊወርድ ይችላል፤ ስለዚህ የሪልስቴት ሥራም ትልቅ አይደለም ማለት ነው። ትልቅ እና ትንሽ የሚያደርገው ባለቤቱ ነው።

ከሥራ ይልቅ ‹‹ሰው እኩል አይደለም!›› ማለት ሳይቀል አይቀርም። ሰው እኩል የሚሆነው በመብት እንጂ በትጋት ግን ይለያያል። አንዱ ሰነፍ አንዱ ጎበዝ የሆነው በልዩነት ነው። ስለዚህ የሥራ ትልቅነትና ትንሽነት በሰውየው ጥንካሬ ላይ ይወሰናል ማለት ነው።

ለማንኛውም አንድ የዓለማችን ቀላል ሥራ አለ፤ እሱም ‹‹ትችት!›› ነው። ትችት የዓለማችን ቀላሉ ሥራ ነው ብንል በፍፁም ማጋነን አይሆንም። በተለምዶ ቀላል ናቸው ከምንላቸው ሥራዎች ሁሉ ቀላል ነው። ትችት ማለት እኮ አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ ሌሎች የሰሩትን መተቸት ማለት ነው።

ትችት ሲባል ምክንያታዊ የሆነ ትችት እንዳለ አምናለሁ። ያ ማለት የተሰራው ሥራ በትክክልም የሚያስተች ሲሆን ማለት ነው። በሌላ በኩል የሚተቸው ሰው ያንን ድርጊት ራሱ የማያደርገው መሆን አለበት። አለበለዚያ ግን ውስጤ አምኖት አይቀበለውም።

ለምሳሌ ቆሻሻ በየመንገዱ መጣልን፣ መጥፎ ሥነ ምግባርን፣ ዝሙትን፣ ሱስን… ብዙ ሰው ይተቻል። የሚያናድደው ግን ራሱ የሚያደርገውን ነገር ነው። ራሳቸው የሚያደርጉትን ነገር ሬዲዮ ላይ ወጥተው ያንኑ ድርጊት ሲኮንኑ ይሰማል። ያንን ድርጊት ይፈጽሙታልና ማበረታታት አለባቸው ወይም ዝም ማለት አለባቸው ማለት አይደለም። ዳሩ ግን መተቸት እንደመተው ቀላል አለመሆኑን ለማሳየት ነው። ያ ስለዝሙትና ስለስካር ሲያወግዝ የነበረው ጋዜጠኛ ራስህ ተወው ቢባል አይተወውም፤ መተቸቱ ግን ቀላል ስለሆነ በየዕለቱ መተቸት ይችላል።

ብዙ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያም ሆነ ዋናዎቹ ሚዲያዎች ላይ የምንታዘበው ነገር አለ። በተለይም በአርቲስቶች ጎራ (ብዙ ጊዜ ወጣ ያለ ነገር የሚታየው ከዚያ አካባቢ ስለሆነ) አንድ ነገር ሲፈጠር ሰዎች ጎራ ፈጥረው ይከራከራሉ። ለምሳሌ ድርጊቱ ነውር ከሚባሉ ነገሮች (ዝሙት፣ ራቁት) ቢሆን፤ ድርጊቱን የሚኮንኑ እንዳሉ ሁሉ ‹‹ደግ አደረገች ወይም ደግ አደረገ የሚሉም አሉ።

‹‹ደግ አደረገች›› የሚሉ ሰዎች ምክንያታቸው፤ ‹‹ሁላችንም ስላልተያዝን ነው እንጂ እናደርገዋለን›› በማለት ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ነውረኝነቷን ከቁጣ ጋር ያወግዙታል።

ይህ የሆነው እንግዲህ፤ ሁሉም የመሰለውን የተናገረ መተቸት ቀላል ስለሆነ ነው። እነዚያ ሲያወግዟት የነበሩት ሰዎች በትዳራቸው ላይ የሚወሰልቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ያወገዟት ዕለት ማታ ራሱ ከትዳራቸው ውጭ ሊወሰልቱ ይችላሉ።

አንድ ነገር ግን ያስማማናል! በማህበረሰቡ ዘንድ ነውር የሆነ ነገር ሲከሰት ‹‹እኔም አድርጌዋለሁና አልተችም›› አይባላም። ባንተች እንኳን የድርጊቱን ባለቤት የተቹትን ልናወግዝም አይገባም።

የትችት ነገር ሲነሳ፤ ብዙ ጊዜ በቀልድም ይሁን በቁም ነገር አንድ የሚጠቀስ ማሳያ አለ። ሲጋራ የሚያጨስ መምህር ስለሲጋራ ጉዳት ቢያስተምር ተማሪዎች እንዴት ይቀበሉታል የሚል ነገር ይነሳል።

ራሱ መተው ያልቻለውን እንዴት ለሌሎች ጎጂ ነው ብሎ ያስተምራል ለማለት ተፈልጎ ነው።

ሲጋራ የሚያጨስ መምህር ስለሲጋራ ጎጂነት ድብን አድርጎ ማስተማርና መምከር ይችላል! እሱ መተው አልቻለም ማለት ሌሎችም አይችሉም ማለት አይደለም። እሱ መተው ባለመቻሉ ደካማነቱን እየገለጸ ያለውን አስከፊ ጉዳት መናገሩ ግን እንዲያውም ከማያጨሱት የተሻለ አሳማኝ ይሆናል። ይሄ ሰው እኔ እያጨስኩ እንዴት ስለሲጋራ ጎጂነት እመክራለሁ ማለት የለበትም! ቢችል መተው፤ ካልቻለ ግን ሌሎች እንዳያጨሱ መምከር!

ስለዚህ ይህን መምህር መተቸት የለብንም ማለት ነው። መተቸት ቀላል ስለሆነ ነው የተቸነው። ይሄኔ እኛም ከእሱ የባሰ መተው ያልቻልነው መጥፎ ልማድ ይኖር ይሆናል። ትችት የሚገነባውና የሚያንጸው ነገር እንዳለ ሁሉ ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበ ከሆነ ግን ተቺውን ራሱን ትችት ላይ ይጥለዋል።

ገጠር ውስጥ ቤተክርስቲያን ቄሶች ሲሰብኩ አንድ የምሰመው ነገር ነበር። ‹‹ቄስ ሲሰክር አየን ብላችሁ አትስከሩ፣ ቄስ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ሲወሰልት አየን ብላችሁ አትወስልቱ፤ በምድርም በሰማይም የሚዋረደው ራሱ ነው›› ይሉ ነበር።

ርግጥ ነው አርዓያ ሆኖ መገኘት ምንም አያከራክርም! ያ ካልሆነ ግን ያ ሰው መምከር የለበትም ማለት አይደለም። በራስ መተማመን ካለን ከሰውየው የምንወስደው ሳይንሳዊ እውነታውን ነው። በነገራችን ላይ ‹‹እገሌ ራሱ ያደርገው የለ እንዴ!›› የምንለውም ትችት ቀላል ስለሆነ ነው። እኛ ልናደርገው ስንፈልግ ነው በእሱ የምናሳብብ።

እደግመዋለሁ! ትችት አያስፈልግም እያልኩ አይደለም። ዳሩ ግን እኛው ራሳችን የምናጠፋውን ጥፋት ሰዎች ላይ ሲሆን ንፁህ መስለን መተቸት ስንፍና ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከመተቸታችን በፊት የነገሩን ነባራዊ ሁኔታ ማጤን ይጠበቅብናል።

ከምንም በላይ ትችት ቀላል መሆኑን የምናረጋግጠው ግን በየመድረኩ የሚነገሩ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ አንዱ የሚገርመኝ የሰዓት አጠቃቀም ነው። ሁለት ሰዓት ተኩል የተባለ ስብሰባ ሦስት ወይም አራት ሰዓት ይመጣና ከእሱ በኋላ የመጡ ሰዎችን ይተቻል። ‹‹ሐበሻ ስንባል መቼ ይሆን የምንሰለጥን!›› እያለ ይናደዳል። ይሄንን ማለት ቀላል ነው፤ ልክ በተባለው ሰዓት መድረስ ግን ከባድ ነው።

ቆሻሻ በየመንገዱ የሚጥሉ ሰዎችን መስደብና መውቀስ ቀላል ነው፤ ቆሻሻ ማጽዳት ግን ከባድ ነው። ማጽዳት ቀርቶ አለመጣል ራሱ በተገባ ነበር፤ ግን እየጣልን ነው የጣሉትን የምንተች።

በተቻለን መጠን እንዳይደረጉ የምንፈልጋቸውንና የምንመክራቸውን ነገሮች ራሳችንም ባናደርግ! ከዚያ ውጭ ደግሞ የምንተቻቸውን ነገሮች መሠረታዊ ምክንያታቸውን ብናጤን! አለበለዚያ ልማዳቸው ነው እየተባልን ነው የምንታለፍ!

ምክንያታዊ እንሁን! እንዲደረጉ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ራሳችን እናድርግ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You