
-የ12ኛ ሀገር አቀፍ ፈተናን ለመፈተን ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፡- የ12ኛ ሀገር አቀፍ ፈተናን በብይነመረብ ለመስጠት መታሰቡ ኩረጃንና የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት ዘላቂ መፍትሔ ነው ሲል የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ፡፡ የ2016 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በብይነ መረብና በወረቀት ለመፈተን ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲልም ተናግሯል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ከበደ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በብይነመረብ ለመስጠት መታቀዱ ኩረጃንና የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት ዘላቂ መፍትሔ ነው፡፡
በ2016 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በብይነመረብና በወረቀት በመፈተን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የ12ኛ ሀገር አቀፍ ፈተናን በብይነመረብ መስጠት ኩረጃንና ስርቆት በዘላቂነት ለመፍታት አስፈላጊ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ፈተናውን ለተወሰኑ ተማሪዎች በብይነመረብ የመፈተን ሥራ በተያዘው ዓመት ይጀመራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ኤጀንሲ የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ትልቁና የረጅም ጊዜ ችግሩ ሆኖ ቆይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ፈተናውን በብይነመረብ የመስጠት ሥራ ተጀምሯል፤ በሂደትም ሙሉ ለሙሉ የወረቀት ፈተናው ይቀራል ብለዋል፡፡
የ2016ዓ.ም የ12ኛ ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና በብይነመረብ መሰጠት መጀመሩ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ተጋዳሮቶች ይገጥሙታል ተብሎ መታሰቡን አመልክተው፤ የሚገጥሙ ችግሮችን ፈትቶ ያለምንም ችግር ፈተናውን ለመስጠት ከወዲሁ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፈተናውን በሚወስዱ ተማሪዎችና ፈተናውን በሚሰጡ ፈታኞች ያለው የብይነመረብ ክህሎት ክፍተት፤ የኤሌክትሪክ ኃይልና የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት እጥረትና ድጋፍ የሚያደርጉ የሰው ኃይል በቂ አለመሆን ያጋጥማሉ ተብለው የተለዩ ችግሮች ናቸው ያሉት ዶክተር እሸቱ፤ ችግሮችን ለመፍታት ተፈታኞችንና ፈታኞችን የማለማመድ፤ ጀኔረተሮችን የማዘጋጀት፤ ከቴሌ ጋር የመሥራት፣ ለድጋፍ ሰጪዎች ስልጠና በመስጠት ቁጥራቸውን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የብይነመረብ ፈተናው ቀድሞ ኮምፒውተሮችና መሠረተ ልማቶች በተዘረጉባቸው ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ ተማሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው በመመላለስ ፈተናውን ይወስዳሉ ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር እሸቱ ገለጻ፤ የ2016 የ12ኛ ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና በወረቀትና በብይነመረብ ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ስለፈተናውና ስለፈተና አሰጣጡ ለተማሪዎች መረጃ ተደራሽ ማድረግ፤ ክልሎች ያላቸውን የተፈታኝ ብዛት እንዲለዩና አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ፤ ለብይነመረብ ተፈታኞችና ፈታኞች ስልጠና መስጠትና ግብአት ማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከፍተኛ ዝግጅትም እየተደረገ ነው፡፡
ኩረጃንና ፈተና ስርቆትን የትምህርት ጥራት ከመጉዳት ባለፈ የተማሪዎችን የመመራመር ፣ በራስ የመተማመን፣ የማብሰልሰል፣ በትምህርት ውስጥ መማር የሚባለውን የባህሪ ለውጥ እንዳያዳብሩ የሚያደርግ ትልቅ እንቅፋት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን በመሻገር የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም