ኢትዮጵያውያን የነገሱበት የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ

ስድስተኛው የዳይመንድ ሊግ መዳረሻ በሆነው ኦስሎ ከተካሄዱ ውድድሮች መካከል በተለይ የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ የያዘው የ5ሺ ሜትር ሩጫ እንደተጠበቀው ድንቅ ፉክክር አስተናግዷል። ባለድሉ አትሌት ሃጎስ ገብረህይወት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ያደረገው ጥረትም በሁለት ሰከንዶች ባይሳካም የኢትዮጵያን ክብረወሰን ግን ሰብሯል። ይኸውም የአትሌቱን ችሎታ በኦሊምፒክ መድረክ ላይ በድጋሚ ለማየት ዓለም በይበልጥ እንዲጓጓ ያደረገ ሆኗል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርቀቱ ነግሰው የቆዩት ዩጋንዳውያን አትሌቶችም ኦስሎ ላይ ለኢትዮጵያውያኑ እጅ መስጠታቸው የርቀቱ ክብር ወደ ሀገሩ ሊመለስ እንደሚችል አመላካች ነው። እንደሚታወቀው እአአ ከ1990ዎቹ አጋማሽ አንስቶ ለረጅም ዓመታት የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን በሁለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነው ተይዞ የቆየው። በእርግጥ ሁለት ኬንያዊያን አትሌቶች የክብረወሰን ባለቤቶቹን ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለን ሰዓት ለማሻሻል ሞክረዋል፤ ይሁንና ከወራት የዘለለ እድሜ ሳይኖራቸው በራሳቸው በኢትዮጵያውያኑ በድጋሚ ተወስደዋል። እአአ ከ2020 አንስቶ ግን የርቀቱ ክብረወሰን በኡጋንዳዊው ጆሽዋ ቺፕቴጊ እጅ ገብቶ ይገኛል። በዚህ ርቀት ተፎካካሪዎች እነዚሁ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች መሆናቸውም ክብረወሰኑ ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች እንዳይጠበቅ አድርጓል።

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የርቀቱ የቀድሞው ክብረወሰን በጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሄንግሎ ላይ የተመዘገበው ልክ በዕለቱ ከ20 ዓመት በፊት 2004 ላይ ሲሆን፤ ሰአቱም 12:37.35 ነበር። ከዓመታት በኋላም ኡጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቺፕቴጊ 12:35.36 በሆነ ሰዓት በማሻሻል ክብረወሰኑን የግሉ አድርጎት ቆይቷል። ከትናንት በስቲያ ምሽት በተደረገው የዳይመንድሊግ ውድድርም ሃጎስ አስደናቂ ብቃት ቢያሳይም 12:36.73 በሆነ ሰዓት በመሮጥ ለጥቂት ክብረወሰኑን ሳይሰብር ቀርተል። ነገር ግን በርቀቱ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ሲመዘገብ ሁለት ወር ብቻ ለሚቀረው የፓሪሱ ኦሊምፒክም በርቀቱ ቅድሚያ ተጠባቂ ከሆኑ አትሌቶች መካከል እንዲሰለፍ አድርጎታል።

በ5ሺ ሜትር ርቀት በመሮጥ የሚታወቀው አትሌቱ እአአ 2013ቱ የሞስኮ ዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ሲያገኝ፤ በቀጣዩ የቤጂንግ ቻምፒዮና ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቋል። በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን የወከለው አትሌቱ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት እንደነበር ይታወሳል። ተስፈኛው አትሌት ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ተደጋጋሚ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት ብቃቱን ለማሳየት ባይችልም፤ ባለፈው ዓመት ሪጋ ላይ በተደረገ የጎዳና ላይ ቻምፒዮና የ5ኪሎ ሜትር አሸናፊ በመሆን ወደ አቋሙ መመለሱን አስመስክሮ ነበር። የተያዘውን የውድድር ዓመት ደግሞ በአፍሪካ ጨዋታዎች የጀመረ ሲሆን፤ የ5ሺ ሜትር ቻምፒዮናም ነበር። በዳይመንድ ሊጉ የመጀመሪያ ተሳትፎው ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡን ያስደነቀ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ውድድሩን ተከትሎ አትሌቱ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበረው ቆይታ ‹‹ባስመዘገብኩት ሰዓት እጅግ ደስተኛ ነኝ። ከዚህ ቀደም ኦስሎ ላይ የግሌን ምርጥ ሰዓት ሮጬ ነበር፤ ይሄኛው ግን የተሻለው ነው። በውድድሩ ስፍራ የነበረው የአየር ሁኔታ እና የስፖርት ቤተሰቡ ድጋፍ ጥሩ ነበር። ፈጣኑ ሩጫ ቢፈትነኝም መጨረሻው መልካም ሆኗል። አሁን በፓሪስ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር ለመሳተፍ የሚያስችለኝን ጥረት አደርጋለሁ›› ሲልም ፍላጎቱን አሳይቷል።

አምና በኦስሎ ዳይመንድ ሊግ አሸናፊ የነበረው ዮሚፍ ቀጄልቻ ድጋሚ ባለድል ባይሆንም በጠንካራ ፉክክር ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችሏል። ከሁለት ወር በፊት ስፔን ላይ በ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊ የነበረው አትሌቱ በሌሎች ውድድሮች ላይ አልታየም። ይኸውም ትኩረቱን በዝግጅት ላይ አድርጎ መቆየቱን የሚያመላክት ሲሆን፤ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት በታየበት ውድድር የራሱን ምርጥ ሰዓት በ12:38:95 በማስመዝገብ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ኡጋንዳዊው የርቀቱ የቀድሞ የዓለም ቻምፒዮን ጃኮብ ኪፕሊሞ 12:40:96 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የርቀቱ የሪከርድ ባለቤትና የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ ጆሹዋ ቺፕቴጌ በ12:51:94 ሰዓት ዘጠነኛ ሆኖ ፈጽሟል። ይህም ከሁለት ወራት በኋላ በሚካሄደው የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ የቀነኒሳ ድል በኋላ የወርቅ ሜዳሊያ ተስፋ እንዲጣልባቸው አድርጓል።

ብርሃን ፈይሳ

 አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You