ህልምን የማወቅ መንገዶች

ህልሙን ያወቀ ሰው የቱ ጋር እንዳለ ያውቃል። ወዴት እንደሚሄድ ይረዳል። የሆነ ቀን ተነስቶ ‹‹እኔ በቃ እድሜዬ ዝም ብሎ አለፈ! ጊዚዬ ዝም ብሎ ነጎደ!›› አይልም። ወዴት እንደሚሄድ ያውቃል። መድረሻና መነሻውን ያውቃል። መንገዱን ጀምሮታል። ህልም አለዋ! ለምሳሌ በልጅነታችን በጣም ደስ የሚለን የማንረሳው ጊዜ የበዓል ሰሞን ነው። በዓል ሲደርስ ጨዋታው፣ ደስታው ወደር የለውም። ልብስ ይገዛልናል፣ የምንፈልገው ነገር ይደረግልናል። አንረሳውም። ካደግን በኋላ ግን በዓል ትዝም አይለንም። አናጣጥመውም።

ለምሳሌ የዛሬ ዓመት ያከበራችሁት በዓል ትዝ ይላችኋል? ምንም ትዝ አይላችሁም። የዛሬ ሃያና ሰላሳ ዓመት ያከበራችሁትን በዓል ግን በደንብ ታስታውሱታላችሁ። ትልቅ ስትሆኑ በዓል ትርጉም አይኖረውም። ከበዓል በላይ ግን ትርጉም የሚሰጣችሁ ህልም ነው። ለልጅነት ትርጉም የሚሰጠው በዓል ነው፤ ለትልቅነት ደግሞ ህልም ነው።

ህልም ሲኖርህ ብዙ ነገርህ ይቀየራል። ለምሳሌ ማንነትህ ይቀየራል። ህልም ጥቅሙ ህልሙን አሳደህ እንድትይዘው አይደለም። አንተ እንድትቀየር ነው። ለህልሙ ስትል የሆነ የምትለውጠው ማንነት አለ። ውስጥህ የሆነ ነገር ይገነባል። ሚሊየር መሆን እኮ ጥቅሙ ሚሊዮን ብሩ አይደለም። ሚሊየን ብርማ ሎተሪ የደረሰው ሰውም ያገኘዋል። ከዓመታት በኋላ ግን ከስሮ ከጨዋታ ውጭ ይሆናል። ግን ሚሊየነር መሆን ጥቅሙ አንተ ሚሊየነር ለመሆን ስትል የጊዜ አጠቃቀምህ፣ የገንዘብ አያያዝህ፣ ከሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ይቀየራል።

ለምሳሌ አይታችሁ ከሆነ የከሰረ ነጋዴ እንደምንም ብሎ ወደ ገንዘቡና ወደ ቢዝነሱ ይመለሳል። ለምን? የረገጠውን ደረጃ ያውቀዋል። ዝም ብሎ አየር ላይ ፊጥ ብሎ አልወጣም። ደረጃውን ወጥቷል። መንገዱን ተጉዞታል። ህልም ሲኖርህ አንተ ትቀየራለህ። ማንነትህ ይቀየራል። አመለካከትህ፤ ለነገሮች ያሉህ እይታ ይቀየራል። ህልም አለሃ! የሰው ልጅ ለህልሙ ሲል ራሱን መቀየሩ አይቀርም።

ህልም ሲኖርህ ደስ የሚለው ነገር አንተ ትቀየራለህ። ህልም አቅማችንን እንድንጠቀም ያደርገናል። ከውስጣችን የሚወጣ የሆነ ኃይል አለ። ዓላማና ህልም ሲኖርህ ትባንናለህ፤ ትነቃለህ። የምትንቀውና የምትበልጠው ሰው በጣም እየተቀየረ ከሆነ የሆነ የሚያሮጥ አላማ ይዟል ማለት ነው። የሆነች ህልም ይዟል ማለት ነው። ሌላውን ተውትና ቋንቋ መልመድ ትፈልጋላችሁ እንበል። አረበኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ… ወዘተ ሊሆን ይችላል። ግን የቋንቋ ትምህርት ቤት ገብታችኋል አልቻላችሁም። ሞክራችኋል፤ ብዙ ነገር አልተሳካላችሁም። ‹‹እኔ ለምንድን ነው ግን ቋንቋ የማይገባኝ›› ልትሉ ትችላላችሁ። ህልም የላችሁም።

ለምሳሌ ግን ‹‹አስር ሺ ዶላር ይከፈልሃል ቶሎ ቋንቋውን ቻልና ትቀጠራለህ›› ብንባል ደሞዛችን 1 ሺ ዶላር ወይም ከዛም ያነሰ ከሆነ ለዛ ገንዘብ ስንል እንባንናለን። በአንድ ጊዜ ከአልበርት አንስታይን በላይ አይምሯችን ይመጥቃል ቋንቋዋን ለመቻል። ለምን? ደሞዝ አላታ! ህልም አለና! አንዳንድ ጊዜ አይታችሁ ከሆነ አረብ ሀገር ሳይሄዱ ኢትዮጵያ ተቀምጠው የአረብኛ ፊልም ለማየት ሲሉ አረብኛ ቋንቋ የቻሉ ሰዎች የሉም? በርግጠኝነት ብዙ ሰው ታውቃላችሁ። አብዛኛዎቹ ሰዎች እንግሊዘኛ ቋንቋስ የሚችሉት እንዴት ነው? ዘፈን ለመስማት ሲሉ፣ የሚወዱትን ፊልም ለማየት ሲሉ ነው።

አያችሁ! በትንሽ ነገር እንኳን ህልምና አላማ ሲኖረን አቅማችንን እንጠቀማለን። ስለዚህ ወዳጄ! ከማንም አንሰህ አይደለም፤ ህልም ስላላስቀመጥክ ነው። ጥልቅ መሻት ሲኖርህ አቅምህን የምትጠቀመው ወደህ ሳይሆን ተገደህ ነው። ምክንያቱም ልሞክር አትልም። ማሳካት አለብኝ ነው የምትለው። ውሃ ቢጠማህ ‹‹እንደው ካገኘው ልሞክር ካላገኘው ችግር የለውም›› አትልም። ‹‹መጠጣት አለብኝ›› ትላለህ ለመኖር ስትል። ህልም እንደዛ ነው። ጥልቅ መሻት እንደዛ ነው። አቅሜን መጠቀም አለብኝ ትላለህ። ህልማችንን ለማወቅ የሆነ ደረጃ ድረስ ለመምጣት ግን እነዚህ ተከታዮቹ ሶስት ነጥቦች ላንተ ወሳኞች ናቸው።

የመጀመሪያው ደስታ የሚሰጥ፣ ጥሩ ስሜት የሚፈጥርና የሆነ ጊዜ አድጎ ሞያ ሊሆን የሚችል ተግባር/passion/ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ ሰው በቤቱ የሆነ ምግብ ሰርቶ፣ ኬክ አዘጋጅቶ ‹‹አንተ እንዴት ይጣፍጣል፤ አንተማ የሆነ ሬስቶራንት ብትከፍት፣ ምግብ ቤት ብትከፍት›› የምትሏቸው ሰዎች አሉ። በቃ ማብሰል ለነዚህ ሰዎች ደስታ የሚሰጣቸው ነገር ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰው ደግሞ የሂሳብ ጥያቄ ሲሰራ የሆነ ጨዋታ የሚጫወት ይመስላል። በጣም ያስደስታል። አንዳንዱ ደግሞ ሲናገር አፍ የሚያስከፍት አለ። ይህም ፓሽን ነው። አያችሁ ይህ ደስ ብሏሁ የምታደርጉትና በፍቅር የምትሰሩት ነገር ነገ አድጎ ሞያ ልታደርጉት የምትችሉት ነገር ይሆናል።

ሁለተኛው ደስ ብሏችሁ የምታደርጉት ነገር ትንሽ አደግ ብሎ ገንዘብ ማምጣት ሲጀምር ሞያ /profession/ ይሆናል። ለምሳሌ ያ ምግቡ በጣም ቆንጆ ነው የምትሉት ሰው ወይም የምትሏት ሴት ተቀጥራ ሼፍ ብትሆን፣ ምግብ አብሳይ ብትሆን አሁን ሞያዋ ገንዘብ እያመጣላት ነው። ስለዚህ ሞያ ሆነ ማለት ነው። ያ ሒሳብ በጣም የሚሰራው ልጅ የሒሳብ መምህር ቢሆን ወይም ተመርቆ ኢንጂነር ቢሆን አሁን ሞያተኛ ሆነ ማለት ነው። አያችሁ! በነፃ ብትሰሩት እንኳን የሚያስደስታችሁ ነገር ገንዘብ ሲያመጣ ሞያ ይሆናል።

ሶስተኛውና በጣም ወሳኙ የመኖር አላማ/purpose/ ነው። አሁን ከገንዘብ ከፍ ያለ ነገር ሲያመጣላችሁ ነው የመኖር አላማ የሚባለው። ያቺ ምግብ የምታበስለዋ ሴት ‹‹እኔ የከተማው ሕዝብ ሁሉ መመገብ እፈልጋለሁ በሬስቶራንቴ›› ብትል ትልቁ አላማዋ ነው። ግዙፍ የመኖር አላማ ሆነ። ያ የሒሳብ መምህር ወይም ኢንጂነር ‹‹አብዛኛውን ሰው ሒሳብ እንዲወድ አደርገዋለሁ›› ካለ ከገንዘብ በላይ ትልቅ ህልም አስቀመጠ። ትልቅ አላማ አስቀመጠ። በነገራችን ላይ ዓለምን የቀየሩ ሰዎች ተለቅና ገዘፍ ያለ ህልም ስላላቸው ነው።

ህልም እንዲኖርን የግድ ሞያዬን አላወኩትም ብለን መጨነቅ የለብንም። ትልቁ ቦታ አልተያዘም። ሁሉም ሰው የሚሻማው መሃል ላይ ላለው ነው። አይታችሁ ከሆነ እታች ያለውን ሁሉም ይንቀዋል። መሃሉን ሁሉም ይፈልገዋል። ትልቁን ይፈሩታል። ለምሳሌ አካውንታንት ለመሆን፣ ሽያጭ ሠራተኛ ለመሆን ወይም ደግሞ የሆነ ቦታ ለመቀጠርና ፀሐፊ ለመሆን የሚፈልገው ሰው በጣም ብዙ ነው። ብዙ ሺ ሰው ተሰልፎ ታያላችሁ። ሥራ አስኪያጅ ለመሆን የሚወዳደረው ግን በጣት የሚቆጠር ነው። ለምን መሰላችሁ? አብዛኛው ሰው ትልቁን ነገር ማሰብ ይፈራል። ደስ የሚለው ግን ትልቁ ቦታ አልተያዘም።

ስለዚህ ወዳጄ! ለሰማዩ ትወረውራለህ፤ ቢያንስ እኮ ጣራውን ትነካለህ። ህልም አሩጠን የምንይዘው ሊሆን ይችላል። ወይ ደግሞ እየኖርን የምንገልጠውም ህልም አለ። ምን መሰላችሁ፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ ወይ ኢንጂነር መሆን እፈልጋለሁ ወይም ደግሞ የሆነ ነገር ማሳካት እፈልጋለሁ፣ የካምፓኒ ሥራ አስኪያጅ መሆን እፈልጋለሁ ካለ የሆነ ቀን የሚያሳካው፣ አሩጦ የሚይዘው እንደሆነ ያስባል። አንዳንድ ሰው እንደዚህ ዓይነት ህልም ያወጡና ልክ ሲያሳኩት የሕይወት ትርጉም ይጠፋባቸዋል። ‹‹ሃብታም መሆን እፈልግ ነበር ሆንኩ፣ ማግባት እፈልግ ነበር አገባሁ፣ ዶክተር መሆን እፈልግ ነበር ሆንኩ ግን ትርጉም አጣሁ›› ይላሉ።

ህልም ደግሞ የምትኖረውን ማድረግ ነው። በቃ እኔ የምደሰተው ሰዎችን ስረዳ ነው፣ የሰዎችን ሕይወት ስቀይር ነው፣ የማይቆም ህልም አለኝ ስትል ደግሞ የምታሮጠው ብቻ ሳይሆን የምትኖረው ህልም ይኖርሃል። በመጨረሻ ‹‹ህልም የለኝም እኮ፣ ግራ ግብት ብሎኛል፣ እንደው ህልሜን ባውቀው›› የሚሉም አሉ። ህልም የለኝም የሚል ሰው እነዚህን ሶስት ጠቃሚ ነገሮች ቢያደርግ ህልሙን የማግኘት እድሉን ያሰፋል።

የመጀመሪያው እጅህ ላይ ላለው መታመን ነው። አሁን እየተማርክ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ወጥረህ በደንብ ተማር። ሥራ እየሰራህ ሊሆን ይችላል። አሁን ያለህበት የተቀጠርክብት ቦታ ላይ በትጋት ሥራ። ህልም ለጠንካሮች የሚሰጥ የፈጣሪ ፀጋ ነው። በጣም ስትጠነክር፣ ስትበረታ አሁን እንዲህ ደግሞ ባደርገው ብሎ አይምሮህ ራሱ ይነግርሃል። ፈጣሪህ ራሱ መንገድ ይጠቁምሃል። ለምን? እጅህ ላይ ላለው ታምነሃላ! አያችሁ በጣም ስንጠነክር ሕይወት ትገባናለች፤ አዲስ ነገር እንረዳልን። በቃ አሁን እየበረታሁ ነው እንዲህ ባደርግ እንላለን።

ሁለተኛው የራስን ሪከርድ ለመስበር መጣር ነው። መቼም ሁላችንም የራሳችን ሪከርድ አለን። ገንዘብ የማስቀመጥ ሪከርድ ሊኖረን ይችላል። ለምሳሌ 10 ሺ ብር የማስቀመጥ ሪከርድ ያለው ሰው 100 ሺ ብር ለመድረስ መሞከር፣ 100 ሺ ያስቀመጠ ሚሊዮን ለመድረስ፣ ሚሊዮን ያስቀመጠ መቶ ሚሊዮን፣ ቢሊዮን…፣እያለ የራሱን ሪከርድ ለማሻሻል መጣር። በእውቀትም ሪከርድህን መስበር ትችላለህ። እኔ የተማርኩት ዲፕሎማ ነው ካልክ እስከ ዲግሪ ማስኬድ፣ ህልምህ ከትምህርት ጋር የሚገናኝ ከሆነ ለምን ማስተርስ አልይዝም፣ ለምን ዶክትሬት ዲግሪ አልይዝም፣ ለምን ፕሮፌሰር አልሆንም፣ ለምን እንዲህ አላደርግም እያልክ የራስህን ሪከርድ ማሻሻል መጨመር አለብህ።

በቃ አሁን ተቀጥሬ የምሰራበት ቦታ ላይ ዝም ብዬ አካውንታንት ልሆን እችላለሁ ከዛ ግን ሱፐርቫይዘር እሆናለሁ፣ ቀጥሎ የብራንች ማናጀር፣ ከዛ በኋላ የአጠቃላይ ማናጀር እሆናለሁ ማለት አለብህ። አየህ! የራስህን ሪከርድ እየሰበርክ ህልምህን ማሳደግ ትችላለህ። ኃይሌ ገብረስላሴ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ የደረሰው እኮ ሪከርዱን እያሻሻለ ነው። እንዴት? ከላችሁ መጀመሪያ ወንድሜን መቅደም አለብኝ ብሎ ተነሳ። ሁሌም በጠዋት እየተነሳ የመሄደው ጉዞ ረጅም ነው። ወንድሜን መቅደም አለብኝ ብሎ ሲቀድመው፣ ከትምህርት ቤቴ፣ ከአካባቢዬ፣ ከክልሌ፣ ከሀገሬ፣ ከዓለም ሲል የራሱን ሪከርድ እየበጣጠሰ ምን ያህል ስኬታማ እንደሆነ ታውቃላችሁ። አንተም ሪከርድህን መስበር የምትጀምረው ከራስህ ነው። ስለዚህ የራስህን ሪከርድ አሻሽል። የእውቀት፣ የገንዘብ፣ የሥራ ሪከርድህን አሻሽል። ያኔ ህልም ይኖርሃል።

ሶስተኛውና የመጨረሻው ሁሌም ራስን መጠየቅ ነው። ‹‹የኔ ትልቁ ህልም ምንድን ነው?›› በል። በነገራችን ላይ በዚህ ዓለም የትኛውንም ጥያቄ ከጠየቅን መልስ አለው። ግን ሳንሰለች ደጋግመን መጠየቅ አለብን። እኛ ጥያቄውን ከጠየቅን በኋላ እጃችን ላይ ላለው መታመን ስንጀምር አይምሯን በራሱ ሰዓት ማሰብ ይጀምራል። አንተ ተኝተህ እሱ ያስባል። ያንተን ህልም እሱ ይጨነቅበታል። ከየትም ቆፍሮ ህልምህ እንዲህ ነው ሊልህም ይችላል።

ስለዚህ ህልሜ ምንድን ነው፣ እኔ ምንድን ነው የምሆነው ብለህ መጨነቅ የለብህም። እጅህ ላይ ላለው ታመን። መሥራት ያለብህን ነገር ወጥረህ ሥራ። የራስህን ሪከርድ አሻሽል። በመጨረሻ ደግሞ አይምሮህን ደጋግመህ ጠይቀው። ህልምህ ምንም ሊሆን ይችላል። አሁን ስታወራው አጠገብህ ያሉ ሰዎች ሊስቁብህም ይችላሉ። እንደውም ጥሩ ህልመኛ ነህ ማለት ነው ሰው ከሳቀብህ። ለምን? አይቻልም የሚባለውን ነገር ለማድረግ ራሱ አቅምህን እንድትጠቀም ያደርግሃል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You