እዚህ ከተማ ውስጥ ጠጅን እንደ ጠንክር የሚጠጣት ሠው አለ ቢሏችሁ እንዳታምኑ፡፡ ጠጅ ራሷ ጠንክር ካልጠጣት የተጠጣችም አይመስላት፡፡ ‹‹ልብስ መስቀያውን አገኘ›› እንዲሉ ጠጅም ብርሌዋን አገኘች ከተባለ ጠንክር ሰቦቃ ነው፡፡ ታድያ ጠንክር ጠጅ ብቻውን አይደለም የሚጠጣው፤ ከሳቅና ጨዋታው ጋር እንጂ፡፡
አንድ ቅዳሜ ከጋሽ ምንተስኖት ጋር ቁጭ ብለው የብርሌ አንገት ሲቆጠሩ ጋሽ ምንቴ ጠየቁ …
‹‹እኔ የምልህ ጠንክር፤ ለመሆኑ እኚህ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ እህል የሚበሉ ይመስልሃል?››
‹‹መቼስ መብላትማ ስጋ ያለ እህል፣ ነፍስ ያለ ስጋ አይቆም ይበሉ ይሆናል እንጂ፡፡ ግን ባይሆን ብፁዕ ስለሆኑ እንደ እኔና እንደ ርስዎ ሽንት ቤት አይቀመጡ ይሆናል። ቢቀመጡ እንኳን የወርቅ እንቁላል ቢጥሉ ነው፡፡›› ብሎ ጠንክር ረቂቅ እውቀት ተናገረ፡፡
እንግዲህ ጋሽ ምንተስኖት ‹‹የመንደሩ አድባር›› የተባለላቸው ባለሱቅ ናቸው፡፡ ታድያ የጋሽ ምንቴ ሩብ ያህል የገንዘብ ተቀማጭ ያለው በጠንክር ስም ነው፡፡
‹‹እንዴት?›› ቢሉ፣
ምስክር እንዲሆን የጠንክር የዱቤ ደብተር በሱቃቸው የገንዘብ ካዝና ውስጥ በጥንቃቄ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ጋሽ ምንቴ ሁልጊዜ የድህነት ስጋት ላይ ናቸው። በዚያ ላይ ጠንክር በሱቃቸው በኩል ባለፈ ባገደመ ቁጥር ዛሬ እሞታለሁ፣ ነገ እሞታለሁ እያለ ያስቦካቸዋል፡፡
አንድ ቀን ግን ጠንክር ለይቶለት ጨርቁን ጥሎ አበደ። የእብደቱን ምክንያት የመንደሩ ጠቢባን አዋቂዎች ጤዛ ልሰው፣ ስራ ስር ምሰው፣ ቅጠል በጥሰው ሲመረምሩ ጠንክር በገንዘብ ማጣት የተነሳ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ጠጅ ሳይጠጣ ከርሟል አሉ፡፡ ጊዜው የሁዳዴ ጦም በመሆኑ ሰይጣን የጠንክር ጠጅ ማቆም የጥድቅ ስራ እንጂ የገንዘብ ማጣት ስላልመሰለው አጉል ተተናኩሎት ኖሯል፡፡
ጋሽ ምንተስኖት መቼም የዋዛ ሰው አይደሉም። ዘመድ አዝማድ ሰብስበው ሲመክሩ ጠንክር ዕብደቱ ተስማምቶት ከቀጠለ የዱቤው ደብተር ለቁጭት ይቀመጣል እንጂ የገንዘባቸው ጉዳይ ውሃ እንደሚበላው ተነገራቸው፡፡ በመጨረሻ ሚስትና ልጆቻቸውን ለመንደሩ ሰው አደራ ትተው ርቀው ተሰደዱ፡፡ ጠንክርን ሶስት ሰባት አስጠምቀው ከነሙሉ ጤንነቱ ይዘውት ሲመለሱ ‹‹ሹልክ ብዬ ቅምስ›› ጠጅ ቤት ጥለውት በድል አድራጊነት ወደ ቤታቸው ገቡ። ያን ቀን ማታ ሚስታቸው እትዬ ምንተስኖሽ የጀግና አቀባበል አደረገችላቸውና እንዴት ያለ ሌሊት አለፈ፡፡ አይ ሌሊት፣ ሌሊት ብሎ ዝም ነው!
‹‹ምናለ ለኔ ሲል አስራ ሶስት ወር ሌሊት በምድሪቱ ላይ በነገሰ። ያኔ ነበር የአስራ ሶስት ወር ፀጋ እያሉ መሸለል›› አሉ በማግስቱ ለጋሽ ደጀኔ ሲያወሯቸው፡፡ እንግዲህ ጋሽ ደጀኔ ስልብ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ጠንክር በጋሽ ምንቴ ታጋይነት እብደቱን በሶስት ሰንበት ጠበል ድል ነስቶ ከተመለሰ በኋላ ግን እርምም ሳይቆይ ሞት ያሳድደው ጀመር፡፡ ለጋሽ ምንቴ ሲነግራቸው በመጀመሪያ የተለመደው ቀልድ መስሏቸው…
‹‹የምንተስኖትን ብድር ሳትከፍል እሞታለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ብትሞት እንኳን መቃብር ፈንቅየ አወጣሃለሁ›› ብለው ቀለዱበት፡፡
ኋላ ግን ነገሩ ሲደጋገም እውነትም ሞት የጠንክር አፍንጫ ስር እያነፈነፈ መሆኑን ተረዱ፡፡ በዚህ ጊዜ የአፍላነት ጀብደኝነታቸው ሽው አለባቸውና …
‹‹የማን ወንድ ነው ጫፍህን ንክት የሚያደርግህ?›› ብለው ሸለሉ፡፡
‹‹ኧረ የዘንድሮስ ቁርጥ ነው ጋሽ ምንቴ፣ ሞቱማ በነፍስ ነው የሚፈልገኝ፡፡›› አላቸው፡፡
አንድ ሰሞን ጥበቃው አስቸገራቸው፡፡ ሱቃቸውን ጥርቅም አድርገው ዘግተው ጠንክር በወጣ በገባበት፣ ባለፈ ባገደመበት ሁሉ እየተከተሉ ሲጠብቁት ሰነበቱ፡፡ ኋላ ግን በአንድ በኩል ሞቱንማ በቀላሉ ታግለው የማይጥሉት ጠላት መሆኑ ሲገባቸው፣ በሌላ በኩል ጥበቃው ምርር ሲላቸው ጊዜ ጠንክር ገና በህይወት እያለ ብድሩን ከፍሎ ካለጨረሰ ሲሞት ልብና ኩላሊቱን የመውረስ መብት እንዲሰጣቸው የከተማውን ማዘጋጃ ቤት በማመልከቻ ጠየቁ፡፡
ማዘጋጃ ቤቱም በከተማው ውስጥ በተፈጠረው የመቃብር ቦታ እጥረት የተነሳ ጋሽ ምንቴ አስከሬኑን ጓሯቸው የሚቀብሩ ከሆነ አይደለም ልብና ኩላሊቱን፤ አይንና ጆሮውን፣ እጅና እግሩን፣ ሳንባና ፈርሱን ሳይቀር የመውሰድ እና ለውሻቸው ከመስጠት ጀምሮ ለፈለጉት አላማ ማዋል እንደሚችሉ አስረግጦ ቃል ገባላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ጋሽ ምንተስኖት ህይወታቸው የተረጋጋና የሰከነ ሆነ፡፡ ታድያ ይሄ ወሬ በከተማው ሲነዛ ሁሉም ሰው የገረመው አንድ ነገር፣ ለካ ጠንክርን እንደ ሰው መንግሥት ያውቀዋል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሄንን ሞት ግጦ የተፋው የሰው ጡር ማን በከተማው ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ስሙ በመዝገብ ሰፍሮ ይገኛል ብሎ ገመተ፡፡
‹‹ዘመን ዘመንን እየወለደ›› እንዲሉ ከጋሽ ምንተስኖት እና ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ፊርማ በኋላ እንደ ዘበት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ጋሽ ምንቴ ከጠንክር እዳ ይልቅ ልብና ኩላሊቱ ቢሸጥ የበለጠ ዋጋ እንደሚያወጣላቸው አምነዋልና የጠንክር ሞት እንደ ምፅአት ቀን ራቀባቸው፡፡ ከጎጃም ደብተራ ጀምረው እስከ ወሎ ቃልቻ ድረስ በመተተኛ ቢያስደግሙ፣ ጠጠር ቢያስጥሉ፣ ሞራ ቢያስነብቡ ወይ ፍንክች ጠንክር የአባ ቢላዋ ልጅ፡፡ ጭራሽ እድሜው እንደ አብርሃም ረዘመ፡፡ ጡር ካልፈራ ክርስቶስ ዳግም ለፍርድ እስኪመጣ ድረስ ጠጅ እየጠጣ ሳይጠብቀውም አይቀር፡፡
ታድያ በዚህ ሁሉ መሃል ጋሽ ምንቴ ያልተገለጠላቸው አንድ የተፈጥሮ ረቂቅ ምስጢር ነበር፡፡ ለካ ባለ እዳው ጠንክር ብቻ ሳይሆን ቀጠሮ ቀናቸው ከደረሰ እርሳቸው ራሳቸው ቀድመው ሊጠናቀቁም ይችላሉ፡፡ ግን ጋሽ ምንቴ ይሄ ረቂቅ የተፈጥሮ ምስጢር ሲገባቸው በጣም ዘግይተው ኖሯል፡፡
አንድ ምሽት ከጋሽ ደጄኔ ጋር ጠጅ ሲጠጡ ቆይተው ለሽንት ቀዬ በተዛወሩበት እብድ ውሻ ነከሳቸው፡፡ ከጠንክር ቀድመው አበዱ፣ ከጠንክር ቀድመው ተፈጠሙ!
እንግዲህ ጋሽ ምንቴ በህይወት እያሉ የትም በከንቱ በትነው ሳይሰበስቡት ስለቀረባቸው ጥሪት ሲያሰላስሉ ንስሃ መግባቱንም ዘንግተውት ሞት ደርሶ አይናቸውን ከደነ፡፡
አንድ ቀን ታድያ ስልቡ ጋሽ ደጄኔ ሞተው ቤተ-ዘመድ ቀብሯቸው በተመለሰ በሶስተኛው ቀን አፈራቸውን አራግፈው ተነሱ፡፡ ኋላ ‹‹ሹልክ ብዬ ቅምስ›› ጠጅ ቤት ቁጭ ብለው በላይኛው ሀገር ስላዩአቸው ተዓምራት ሲያወሩ ጋሽ ምንቴን በገነት ምን የመሰለ ሱቅ ከፍተው ገበያቸው ደርቶ እንዳገኟቸው ተናገሩ፡፡
የጋሽ ምንቴ ገነት የመግባት ጉዳይ እንቆቅልሹ ቢመረመር፣ ቢብጠረጠር ማን ሊቅ ማን ረቂቅ ይፍታው። አንድ ቀን ጠንክር በስካር ምስጢሩን ይፋ እስኪያወጣው ድረስ፡፡
ጋሽ ምንቴ በተቀበሩ በሶስተኛው ቀን የትንሳኤ መለከት ከመነፋቱ ቀደም ብሎ እኒያ አቡነ ጳውሎስ ለጉዳያቸው ወደ ጓሮ ዞሩ አሉ፡፡ በዚያም የጋሽ ምንቴ ትኩስ የመቃብር አፈር ሸተታቸው፡፡ እንግዲህ ምን ቅን መልዓክ እንዳማከራቸው እንጃ እንደ ጃንሜዳ ከተንጣለለው የሙታን ሀገር መካከል መርጠው የጋሽ ምንቴ መቃብር ላይ የወርቅ እንቁላላቸውን ጣሉ፡፡ የጋሽ ምንቴ ትኩስ የመቃብር አፈር ላይ ያረፈው የወርቅ እንቁላል ወዙ ከአፈሩ አልፎ፣ ገላቸውን ዘልቆ ነፍሳቸውን አረጠባትና እነሆ በመንግስተ ሰማይ ሱቃቸውን ከፈቱ፡፡
አሁንም ጠንክር ሲመጣ እዳየን ይከፍለኛል የሚል ተስፋ አላቸው ይባላል፡፡
‹‹ችርስ ለአቡናችን የወርቅ እንቁላል!›› አለ ጠንክር ብርሌውን ከፍ አድርጎ።
እዩኤል ወርቁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም