መንግሥት ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ በመሆን ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ከድህነት እንዲያወጡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ትምህርታቸውን አጠናቀው ያለ ሥራ የተቀመጡ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከስልጠና ጀምሮ የፋይናንስ አቅርቦት፤ የማምረቻና መሸጫ ቦታ እንዲሁም የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
ወጣቶች ተደራጅተው እየሰሩ ካሉባቸው የሥራ መስኮች መካከልም የከተማ ግብርና ሥራ ዋነኛው ነው፡፡ ክልሎች በተለይም በከተሞች አካባቢ ትምህርታቸውን አጠናቀው ያለ ሥራ የተቀመጡ ወጣቶች ወተት፤ በንብ ማነብና በዶሮ እርባታ ላይ በማሰማራት ረገድ ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ ነው ያሉት፡፡
ከእነዚህም ክልሎች መካከል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ የጋዜጠኞች ቡድንም በቅርቡ በክልሉ እየተሰሩ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎች የመስክ ምልከታ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ከእነዚህም የክልሉ አካባቢዎች መካከል የቡታጅራ ከተማ አንዱ ሲሆን በከተማዋ ወጣቶች ተደራጅተው በተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎች ላይ እያደረጉት ያለው የሥራ እንቅስቃሴ ምልከታ አድርጎ እንደሚከተለው ይዞ ቀርቧል፡፡
ወጣት አቤል ሙሉጌታ ቀሽት የንብ ማህበር መስራችና ሊቀ መንበር ነው፡፡ ተማሪ በነበረበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከግብርና ባለሙያዎች ጋር ስለነበር ለግብርና ሥራ የተለየ ፍላጎት እንደነበረው ያስታውሳል፡፡ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም የሚቀርባቸው የግብርና ባለሙያዎች እሱና ጓደኞቹ በንብ ማነብ ሥራ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይነግሯቸዋል፡፡ ወጣት አቤል አዋጭነቱን ካጠና በኋላ ምክረ-ሃሳቡን ተቀበለና አራት ጓደኞቹን በማሰባሰብ ማህበር መሰረተ፡፡ እናም በቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት እገዛ በከተማ በሚገኘው ሆስፒታል ባዶ ስፍራ ላይ አስር ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎችን በማዘጋጀት የንብ ማነብ ሥራ መጀመራቸውን ይገልፃል፡፡
ወጣት አቤል እንዳሰበውም ሥራው ውጤታማ እየሆነና የሚያመርቱት ምርት በከተማው ነዋሪ ተወዳጅ እየሆነ ሲመጣ 200 ዘመናዊና ከ150 በላይ ባሕላዊ ቀፎ ማድረስ ቻሉ፡፡ ማር የማምረት አቅማቸው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ1ሺ 500 ኪሎ ግራም በላይ ደርሷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከግብርና ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለማህበሩ የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው መሆኑን የሚጠቅሰው ወጣት አቤል በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ወለላ ማር እስከ 600 ብር ድረስ ፤ እንጀራ ማር ደግሞ 500 ብር የሚሸጡ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ማህበሩ በንብ ማነብ ሥራ ብቻ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 13 ለሚሆኑ የከተማዋ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ያመለክታል፡፡
ወጣት አቤል እንደሚለው፤ በአሁኑ ወቅት ማህበሩ የንብ ማነብ ሥራውን እየሰራ ያለው በተለመደውና በባሕላዊ መንገድ ነው፡፡ ይሁንና በቀጣይ ዓመት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አሰራራቸውን የማዘመን እቅድ ይዘው እየሰሩ ነው፡፡ ከከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር እስከ አንድ ሺ ዘመናዊ ቀፎ ለማድረስ አልመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቡታጅራን የምስራቅ አፍሪካ የንብ ማዕከል ለማድረግ እየሰሩ ነው፡፡
ለዚህ ግባቸው መሳካት ግን የቦታ እጥረት ተግዳሮት ይሆንብናል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ወጣት አቤል ተናግሮ ፤ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ማቅረባቸውንና በቅርቡ ምላሽ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳለውም ያመለክታል። ‹‹አስፍተን ለመሥራት የፋይናንስ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ፕሮፖዛል ነድፈን ብድር ለመጠየቅ አቅደናል›› ሲልም ያክላል፡፡
በቡታጅራ ከተማ በንብ ማነብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ማህበራት መኖራቸውን የሚናገረው ወጣት አቤል የእነሱ ማህበር ለሌሎቹ ማህበራት ስልጠና በመስጠትና ተሞክሮ በማካፈል እገዛ እያደረገ መሆኑንም ያስረዳል፡፡ ‹‹ህብረ ንብም በመስጠት የምናግዛቸውም አሉ›› በማለት ተናግሮ ወደፊት ዘመናዊ ማር የማቀነባበሪያ ማሽን የመትከል አላማ ስላላቸው ከእነዚህ ማህበራት ማር በመረከብ እና እሴት በመጨመር ወደ ውጭ የመላክ እቅድ እንዳላቸው ነው ያብራራው፡፡
ሥራውን ሲጀመር 12ኛ ክፍል ገና እንዳጠናቀቀ እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣት አቤል በአሁኑ ወቅት በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን እያጠና መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህም አሁን ለጀመረው የንብ ማነብ ሥራ ከፍተኛ ድጋፍ ያበረክትልኛል የሚል እምነት እንዳለው ይጠቅሳል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎቹም የማህበሩ አባላት ለማህበሩ በሚጠቅሙ ዘርፎች ላይ ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን አመልክቶ፤ ይህም ግላዊ የሆነ ክህሎትና አቅማቸውን ከማሳደግ ባሻገር ከተማዋን በንብ ማነብ በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ለማድረግ ለወጠኑት እቅድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ያስረዳል፡፡
ፋሲል አሕመድ /ዶክተር/ የቡታጅራ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት የግብርና ባለሙያ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው፤ ጽሕፈት ቤቱ ወጣቶችን የሥራ ፈጣሪ ከማድረግ አኳያ በንብ ማነብ ብቻ ሳይሆን፤ በእንስሳት እርባታ፣ በዶሮ እርባታ መንደሮች ተመስርተው ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዋነኝነት በንብ ማነብ ሥራ ከተማዋ የልሕቀት ማዕከል የሚያደርጋት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ በከተማ ደረጃ ወደ 12 የንብ መንደሮች ያሉ ሲሆን፤ ቀሽት የንብ ማነብ ማህበር ደግሞ በከተማውም ሆነ በክልል ደረጃ በንብ ማነብ ሥራ ሞዴል ሆኖ የተመረጠ ነው፡፡
‹‹ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ገና የጀመረ ቢሆንም በዓመት እስከ አንድ ሺ ኪሎ ግራም ማር የማምረት አቅም ላይ የደረሰ ሲሆን በቀጣይ ግን ከሶስትና አራት ሺ ኪሎ ግራም በላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል›› የሚለው ዶክተር ፋሲል፤ ማህበሩ በሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ከመንደሮቹ አልፎ የከተማው ነዋሪም በጊቢው ላይ አንድና ሁለት ቀፎ በመስቀል በንብ ማነብ ሥራ ላይ እየገባ መሆኑንም ያስረዳል፡፡
በተመሳሳይም ቡታጅራ በወተት ልማት ስሟ ገኖ እየወጣ መሆኑን የሚያነሳው ባለሙያው በአቅራቢያ ካሉ ዞኖች ባሻገር ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ለሚመጡ አካላት ሞዴል በመሆንና ተሞክሮ በማካፈል ረገድ የላቀ ሥራ መሰራቱን ይጠቁማል፡፡ ‹‹32 ማህበራት በአንድ አካባቢ ላይ ተደራጅተው በከፍተኛ መጠን ወተት እየተመረተ ነው፤ በእነዚህ ማህበራት ደግሞ የሚሰሩት አብዛኞቹ የከተማዋ ወጣቶች ናቸው›› ሲል ያመለክታል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በከተማ ግብርና ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ወጣቶች የሙያ፤ የቴክሎጂ፤ የሕክምና እና የስልጠና ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አስታውሰው፤ የብድር አቅርቦት እንዲያገኙም ከባንክ ጋር የማስተሳሰር ሥራም ጭምር በኃላፊነት እያከናወነ መሆኑን ነው የሚያብራራው፡፡
እነወጣት አቤል ከቦታ አቅርቦት ጋር የሚያነሱትን ጥያቄ በሚመለከት ዶክተር ፋሲል ተጠይቆ ‹‹የከተማ አስተዳደሩ ማህበሩን ከማደራጀት ጀምሮ አሁን እያመረተ ያለበትን ቦታ በመስጠት ድጋፍ አድርጓል፤ በተለየ መልኩ ለዓመታት ባዶ ቦታ አጥረው ያለ ሥራ ያስቀመጡ የመንግሥት ተቋማት መሬት ለተደራጁ ወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ እንዲውል ተደርጓል›› ሲል ያስረዳል፡፡ አክሎም ‹‹ማህበሩ በቀጣይ ለአቀደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት መሳካት የከተማ አስተዳደሩ የተለመደ ትብብሩን ያደርጋል›› ብሏል፡፡ ይሁንና ከተማ እንደመሆኑ የመሬት አቅርቦት ውስን በመሆኑ ሰፊ ጥናት የሚፈልግ መሆኑን ከግንዛቤ ማስገባት ተገቢ ነው ባይ ነው፡፡
ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘም ‹‹አበዳሪ ተቋማት ለተደራጁ ወጣቶች አፋጣኝ የብድር አገልግሎት እንዲሰጧቸው ከማድረግ በዘለለ በተለይ በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩላችንን ድጋፍ እያደረግን ነው›› በማለት ይናገራል፡፡ በሌላ በኩል ማህበራቱ የገበያ ትስስር እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር የተመረቱ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ተለያዩ ሀገራት ለመላክና ለሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የክልሉ መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ፋሲል ያብራራል፡፡
በዚህ ረገድ በከተማዋ በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ጠቅሶ፤ ‹‹በተለይም ሶሲ የተሰኘው አግሮ ኢንዱስትሪ ከማህበራቱ ወተት ተረክቦ የማቀነባበር ሥራ በስፋት እየሠራ ነው፤ ይህም ወጣቶቹ የሚያመርቱት ምርት እንዳይባክን ከማድረግ ባለፈ ለሌሎች በርካታ የከተማዋ ወጣቶች ሥራ እድል በመፍጠር ረገድ አወንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው›› ሲልም ይገልፃል፡፡
በተመሳሳይ በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ማር ለማቀነባበር እቅድ ላላቸው እንደ እነአቤል ያሉ ወጣቶችን የብድርና የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ እገዛ እንደሚያደርግ ያመለክታል። ‹‹በተለይ ቀሽት የንብ ማነብ ማህበር አሁን ካለው አያያዝ በመነሳት ከተማችንን በስፋት ያስተዋውቅልናል ብለን እናስባለን፤ እንዳውም የቡታጅራ ብራንድ ማር በማምረት የጎላ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለን›› ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ማህበሩ ማር በማቀነባበር ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችለውን አቅም በማጎልበት ረገድ ከማህበሩ አባላት ጋር ምክክር እያደረገ ስለመሆኑም ዶክተር ፋሲል የጠቆመው፡፡
እንደ ግብርና ባለሙያው ማብራሪያ፤ በከተማዋ መኖ አቀነባብሮ በከተማዋ ላሉ ማህበራት የሚያሰራጭ ወልታ የተሰኘ ዩኒየን አለ፡፡ ይሁንና ካለው ሰፊ ፍላጎት አንፃር አቅርቦቱ ዝቅተኛ በመሆኑ በአምራቾች ቅሬታ በተደጋጋሚ እየቀረበበት በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ በርከት ያሉ የመኖ ማቀነባበሪያዎችን እንዲቋቋሙ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ለመኖ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪው የሚውሉ የግብርና ውጤቶችንም በከተማ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች በስፋት የማምረት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በተለይም ‹‹አልፋ አልፋ›› የተሰኘው መኖ እንዲሁም ለንብ ማነብ ጠቃሚ የሆኑና ማዓዛማ የሆኑ አባባና ሌሎች እፅዋቶችን ሁሉም በየጊቢው ላይ እንዲያመርት እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ድጋፍ እየተደረገ ነው ያለው፡፡
በንብ ማነብ ላይ የተሰማሩ ማህበራት አቅማቸውን በማሳደግ ሰም የማተም፤ ንግስት ንብ እያባዙ ለሌሎች አዳዲስ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የማሰራጨት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ዶክተር ፋሲል ያነሳል። በተጨማሪ ማር መጭመቂያ ማሽን እንዲያገኙ የከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በከተማዋ ያሉ ወጣቶች በግብርናም ሆነ በሌሎች የሥራ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውንም ሆነ ሀገርን ከድህነት ለማውጣት እያደረጉ ያሉትን ብርቱ ጥረት ለመታዘብ ችሏል፡፡ ወጣቶቹ የተደረገላቸውን ውስን ድጋፍ ተጠቅመው ለሌሎች ምሳሌ የሆነ ተግባር በመፈፀምም አበው ‹‹ወጣት የነብር ጣት›› የሚሉትን የብርታትና የጥረት ቢሂል በተጨባጭም እያስመሰከሩ መሆኑን እኛም በተጨባጭ አረጋግጠናል፡፡ ወጣቶቹ በአግሮ ኢንዱስትሪውም ሆነ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ሁነኛ ምንጭ ለመሆን ላለሙት የልማት ግብ መሳካት የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍ በወቅቱ እንዲያደርግላቸው ለማስገነዝብ እንወዳለን፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም