ለአራተኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በአሰላ አረንጓዴ ስቴድየም የተካሄደው የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት ቻምፒዮና በጠንካራ ፉክክሮች ታጅቦ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተጠናቋል። የውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት ተስፋ የተጣለባቸውን ያህል ከዕድሜ ጋር የተያያዙ ችግሮችን አሁንም ድረስ መቅረፍ እንዳልቻሉ ታይቷል፡፡ በዕድሜ ገደብ የሚደረጉ የአትሌቲክስ ውድድሮች የእድሜ ተገቢነት ችግር ተደጋግሞ የሚነሳ ርዕሰ ጉዳይ ቢሆንም አሁንም ድረስ ሊቀረፍ ግን አልቻለም፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዓመታዊ የውድድር መርሃ ግብሩ መሠረት ከሚያካሂዳቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል የሥልጠና ማዕከላት ቻምፒዮናም የዚሁ ችግር አካል ነው፡፡ ውድድሩ ታዳጊ አትሌቶችን ያሳትፋል፣ ሠልጣኞች የወሰዱትን ዘመናዊና በሳይንሳዊ መንገድ የተደገፈ ሥልጠና በውድድር በመለካት፤ በክለብ፣ በማናጀሮችና አሠልጣኞች የመመረጥ እድላቸውን የሚያሰፉበት ትልቅ መድረክም ነው።
ማዕከላቱ ሀገርን የሚወክሉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ድርሻቸው የጎላ መሆኑ አያከራክርም። በነዚህ ማዕከላት መካከል የሚደረገው ዓመታዊ ውድድር ታዳጊዎቹ የወሰዱትን ሥልጠና የሚመዝኑበትና መጻኢ ዕድላቸውን የሚወስኑበት ብቻም ሳይሆን የውድድር ልምድ የሚያሳድጉበትም መድረክ እንደሆነም ይታመናል። ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደው የማሠልጠኛ ማዕከላት ውድድር ድንቅና በተገቢው ዕድሜ ላይ የሚገኙ አትሌቶችን ከማስመልከቱ በተቃራኒ የተጋነኑ የዕድሜ ማጭበርበሮች ተስተውሎበታል።
ከግንቦት 15 እስከ 18/2016 ዓ.ም በተካሄደው ውድድር በሀገሪቱ ከሚገኙ ሰባት የማሠልጠኛ ማዕከላት የተውጣጡት ታዳጊዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች በማዕከላቱ ቢበዛ በአራት ዓመት ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ክለቦች ይቀላቀላሉ። በሂደቱ በመተካካት፣ ማዕከላት አዳዲስ ሠልጣኞችን በመቀበል በውድድሮች ላይ በማሳተፍና የመታየት ዕድል በመፍጠር ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ይደግፋሉ። በዚህ ውድድርም ይህን ጥረት የማስቀጠል ነገር ቢኖርም አንዳንድ ማዕከላት ግን የክለብ አትሌት የሚመስሉ ተወዳዳሪዎችን ይዘው ሲቀርቡ ታይቷል፡፡
ውድድሩ ላይ መሳተፍ የሚችሉት በትክክለኛና ተቀራራቢ የዕድሜ ደረጃ ላይ ያሉ ታዳጊ አትሌቶች ቢሆኑም፣ በትልቅ ደረጃ መወዳደር የሚችሉና አትሌቶች ሲወዳደሩ ታይተዋል። ይህም ማዕከላት በታዳጊ ምልመላ ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው እንዲሁም በውድድሮች ውጤትን ብቻ መሠረት ያደረገ ተሳትፎ በመፈለግ የሚፈጠር ችግር መሆኑን አሠልጣኞች ይገልጻሉ፡፡
የሀገረሰላም አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ እና አሠልጣኝ ደሳለኝ አመጦ፤ ማዕከላት በተገቢው የእድሜ ደረጃ የሚገኙትን ሠልጣኞች ይዘው መቅረብ እንደሚኖርባቸው እና በእኩል እድሜና አቅም ላይ የሚገኙ ሠልጣኞች ሲኖሩም በተሻለ ፉክክር ተተኪዎችን ማፍራት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ ለማእከላት የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል በማጠናከር ችግሩን መቅረፍ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
አትሌቶቹ በውድድሩ ላይ በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀት እንዲሁም የሜዳ ተግባራት ድንቅ ፉክክርና ተተኪን ማፍራት የሚያስችል አቋምን ማስመልከት ችለዋል። ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸው አንዳንድ ርቀቶች ወደ ፊት ሀገርን ማስጠራት የሚችሉ ብዙ ታዳጊዎች መንገዳቸውን ለማቅናት ለክለቦች የፈረሙበትም ውድድር መሆን ችሏል። ከዚህ ጎን ለጎን ግን ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ባለመወዳደራቸው እና ተገቢውን መድረክ ማግኘት ባለመቻላቸው የተበደሉ ታዳጊዎችም በርካታ ናቸው። ይህም ታዳጊዎች ተስፋ እንዲቆርጡና በስራቸው ጠንክረው እንዳይዘልቁ በማድረግ እንደ ሀገር ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡
የዕድሜ ማጭበርበሩ ስር የሰደደ ችግር እና ፌዴሬሽኑም አምኖ ተቀብሎ ከዚህ ቀደም ለመፍትሔው የሁሉንም ርብርብ የጠየቀበት ጉዳይም ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ውድድሮች በየጊዜው ችግሩ እየተነሳ መፍትሔ ከማጣቱም በላይ በወጣት ውድድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ የሆነበት ጊዜም አለ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሃንስ እንግዳ፣ ማሠልጠኛ ማዕከላት ላይ የሚገኙ አትሌቶች ሀገርን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን ለማፍራት፣ የውድድር እድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ አበረታች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሀገር ደረጃ በቂ የሚባል የማሠልጠኛ ማዕከል አለ ተብሎ ባይታሰብም፣ ከዚህ ቀደም ብዙ ሀገርን መወከል የቻሉ አትሌቶችን ማፍራት ችለዋል፡፡
ከዕድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍም ፌዴሬሽኑ የተቻለውን ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ ማዕከላት ላይ አትሌቶቹ በትክክለኛ እድሜያቸው ተመልምለው እንዲገቡ ማድረግ እና ሥልጠና መስጠት፣ በውድድሮች ላይ የሚታዩትን የእድሜ ተገቢነት ጥያቄ በሚገባ ይቀረፋል ብለዋል፡፡ ምልመላው ላይም ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባውና በቀጣይ ፕሮጀክቶችና ማዕከላት ሠልጣኞችን የሚመለምሉበትንና የሚመጋገቡበትን አሠራር በመፈተሽ ሠልጣኞች በዕድሜያቸው ተገቢውን ሥልጠና ወስደው የሚወጡበትን አሠራር ለመፍጠር ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ማእከላት ፌዴሬሽኑ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ቢሆንም ባለቤትነታቸው የመንግስት በመሆኑ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ዓላማ በማድረግ እንዲሠሩና ውጤትን መሠረት ያደረገ እና ከአጉል ፉክክር መውጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም