የአትሌቲክስ ስፖርት ቤተሰብ የነገውን የረጅም ርቀት ድንቅ ፉክክር ሊመለከት፤ የአትሌቶቹንም ብቃት ሊመሰክር ቀጠሮውን ኖርዌይ ኦስሎ ላይ አድርጓል:: የዳመንድሊግ ሰባተኛዋ መዳረሻ በሆነችው ኖርዌይ የሚደረገው ይህ ውድድር በሜዳ ተግባራትና በተለያዩ ርቀቶች ከሚደረጉ ሩጫዎች መካከል የተለየ ግምት የተሰጠውና ቀልብ ሳቢ ትዕይንት ይስተናገድበታል ተብሎ የሚጠበቀው የወንዶች 5ሺ ሜትር ነው:: ይህ ውድድር የላቀ ትኩረት ያሰጠው ደግሞ በምስራቅ አፍሪካውያኑ ሀገራት ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የርቀቱን ምርጥ አትሌቶች በማገናኘቱ ነው::
በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ስኬታማ የሆኑት የሁለቱ ሀገራት አትሌቶች የሚፎካከሩባቸው መድረኮች ከፍተኛ የአሸናፊነት ፍልሚያ ማስተናገዳቸው አይቀርም:: የፓሪሱ ኦሊምፒክ ደግሞ ሁለት ወራት ብቻ የቀሩት መሆኑን ተከትሎ አትሌቶቹ ያሉበትን ብቃትና ዝግጅታቸውን ለመመዘን ከማስቻሉ ባለፈ አትሌቶቹ በኦሊምፒክ የሚካፈሉባቸውን ርቀቶች በሚመለከትም ፍንጭ የሚሰጥ ነው የሚሆነው:: ተጠባቂው የነገ ውድድርም እንደ በሪሁ አረጋዊ፣ ዮሚፍ ቀጄላ፣ ሃጎስ ገብረሕይወት፣ ጥላሁን ኃይሌ፣ ጆሹዋ ቺፕቴጊ፣ ጃኮብ ጂፕሊሞ፣… በመሳሰሉት የአትሌቲክስ ጀግኖች መካከል የሚደረግ ነው::
በኦሊምፒክም ሆነ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክ በዚህ ርቀት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪና ውጤታማ መሆናቸው ይታወቃል:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኬንያ አትሌቶች ስኬት እያነሰ የአውሮፓዊቷ ኖርዌይ እየጨረ ቢመጣም የኢትዮጵያውያን እና ዩጋንዳውያን ፍልሚያ ግን በይበልጥ ሳቢ እየሆነ ይገኛል:: ዩጋንዳዊው ጆሹዋ ቺፕቴጊ ደግሞ በርቀቱ የኦሊምፒክ ቻምፒዮና ከመሆን ባለፈ በጀግናው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን ክብረወሰን በመስበር ውጤታማነቱን አስመስክሯል:: በፓሪሱ ኦሊምፒክም ይህንኑ ስኬቱን ለመድገም ያለመ ስለመሆኑ ትኩረታቸውን በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ያደረጉ የመገናና ብዙሃን ይጠቁማሉ:: ይሁንና በዳይመንድ ሊጉም ሆነ በኦሊምፒኩ ከወጣቶቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚገጥመው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ነው የሚገመተው::
ባለፈው ዓመት ሉዛን ላይ አሸናፊ የነበረውና በሞናኮ ሁለተኛ የወጣው ወጣቱ አትሌት በሪሁ አረጋዊም በውድድሩ አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ዋነኛው ነው:: በጠንካራ አቋም የተያዘውን የውድድር ዓመት የጀመረው አትሌቱ በሰርቢያው የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና እንዲሁም ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ላይ በተሳተፈበት የ5ሺ ሜትር ርቀት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው:: የነገው ዳመንድ ሊግ ተሳትፎውም የመጀመሪያው ሲሆን ለፓሪሱ ኦሊምፒክ እያደረገ ያለውን ዝግጅት የሚያስመሰክርበት ሩጫ በመሆኑ ለአሸናፊነት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል::
ከዩጋንዳውያን አትሌቶች ጋር ሲፎካከር ይህ የመጀመሪያው ያልሆነው በሪሁ ፈተና እንደሚሆንባቸውም ነው የሚጠበቀው:: በተለይም በነገው ውድድር ከሚሳተፉት መካከል አንዱ ከሆነው ጃኮብ ኪፕሊሞ ጋር በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና ያሳዩት የትከሻ ለትከሻ ፉክክር የሚዘነጋ አይደለም:: በእኩል የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኙት አትሌቶቹ በሰከንዶች ብቻ የተበላለጡ ሲሆን፤ ዛሬም በመካከላቸው የአሸናፊ ተሸናፊ ፍልሚያ እንደሚስተናገድ ይገመታል::
አምና በኦስሎ ዳይመንድ ሊግ አሸናፊ የነበረው ዮሚፍ ቀጄልቻ በዚህ ውድድር ተሳታፊ መሆኑ የተረጋገጠና በድጋሚ ባለድል ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ይገኛል:: ከሁለት ወር በፊት ስፔን ላይ በ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊ የነበረው አትሌቱ በሌሎች ውድድሮች ላይ አልታየም:: ይኸውም ትኩረቱን በዝግጅት ላይ አድርጎ መቆየቱን የሚያመላክት ሲሆን፤ የዓምናውን ድል ለማደስ ነገ እንደሚሮጥም ነው የሚጠበቀው:: ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሃጎስ ገብረሕይወትም ከተፎካካሪ አትሌቶች መካከል ይገኛል:: የ5ሺ ሜትር ርቀት አትሌቱ እአአ 2013ቱ የሞስኮ ዓለም ቻምፒዮና የብር፣ በቀጣዩ ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ፤ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ነበር:: ተስፈኛው አትሌት ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ተደጋጋሚ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት ብቃቱን ለማሳየት ባይችልም በፓሪስ ኦሊምፒክ ግን ሀገሩን መወከል በሚችልበት ብቃት ለመመለስ በጥረት ላይ ይገኛል::
በዚህ ርቀት አራተኛው የዓለም ፈጣን አትሌት የሆነው ወጣቱ አትሌት ጥላሁን ኃይሌም ውድድሩን ከሚያደምቁት መካከል ተሰልፏል:: በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከብሄራዊ ቡድን ምርጫ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ቅሬታ የነበረው አትሌቱ በተያዘው ዓመት ብቃቱን በማስመስከር ፓሪስ ላይ ሀገሩን ለመወከልም ይሮጣል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም