በጠንካራ ፉክክር የደመቀው ታላቁ ሩጫ በበቆጂ

ዓለም ያከበራቸው፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክም የገዘፈ ስም ያላቸው አትሌቶችን ያፈለቀችው በቆጂ ለኢትዮጵያ ስፖርት ባለውለታ ነች። ይህ ድንቅ መልከዓ ምድር እና የአየር ሁኔታን የታደለ ስፍራ ለስፖርት ምቹ በመሆኑ ለዘመናት እጅግ በርካታ አትሌቶች ፈልቀውባታል። ይህንን ስፍራ የአትሌቶችና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመሆን የሩጫ ውድድር በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ከሰሞኑም ታላቁ ሩጫ በበቆጂ ለ3ኛ ጊዜ በሕፃናት፣ ታዳጊ እና በአዋቂ ዘርፍ የ12 ኪሎ ሜትር የአትሌቶችና ሕዝባዊ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል። መነሻና መድረሻቸውን በበቆጂ ስታዲየም በማድረግ በተከናወነው ውድድርም በወንዶች አምና የቦታውና በዱባይ ማራቶን አሸናፊ የሆነው አትሌት አዲሱ ጎበና በድጋሚ አሸናፊ ሆኗል። እጅግ ጠንካራ ፉክክር ባስተናገደው በዚህ ሩጫም ብርሀኑ ፈዬ እና አማን ከድር ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። በሴቶች ደግሞ ትዕግስት ደጀኔ፣ መስከረም አሰፋ እና አዳነች መስፍን ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው ገብተዋል። ከውድድሩ ለመታዘብ እንደተቻለው ታላቁ ሩጫ በበቆጂ በየዓመቱ እየደመቀና በፈታኝ ፉክክር ታጅቦ ትልቅ ተቀባይነት ማግኘት እየቻለ ይገኛል።

በቆጂ የምርጥ አትሌቶች መፍለቂያ ብቻ ሳትሆን ነዋሪዋ ሁሉ ሯጭ የሆነባት ስፍራ መሆኑን የምትገልጸው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ፤ታላቁ ሩጫ ከዚህ ቀደም በከፍታ ስፍራ ላይ በሚገኝ ቦታ በዚህ ርቀት ውድድር አካሂዶ አያውቅም፤ በዓመቱ ሌሎች ስፍራዎች ላይ የሚደረጉ ውድድሮች አጭር ርቀቶች (ከሃዋሳ ሀይቅ ግማሽ ማራቶን ውጪ ያሉት) ናቸው። በቆጂ ላይ ከአትሌቶች ባለፈ ሕዝቡንም የሚያሳተፍበት የረጅም ርቀት ሩጫ በመሆኑ በእርግጥም የሯጮች መፍለቂያ ለመሆኑ ማሳያ ነው። ድጋፍ የሚሰጠው ተመልካች ቁጥርና ስሜትም ምስክር እንደሆነም ታብራራለች።

በበቆጂ አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች ከዚህ ቀደም በኤልዶሬት በሚደረገው ውድድር የመካፈል እድል ያገኙ ነበር፤ የዘንድሮው ውድድር ግን አስቀድሞ በመካሄዱ ማሳተፍ አልተቻለም። የዘንድሮ አሸናፊዎች በቀጣይ በሚካሄደው ውድድር የሚሳተፉ ሲሆን፤ በታዳጊ ዘርፍ በተካሄደው ሩጫ የላቀ ብቃት ያሳዩት ደግሞ የበቆጂ እና የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላትን ይቀላቀላሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጓል። ከዚህ ባለፈ ግን ታላቁ ሩጫ በበቆጂ እና የኤልዶሬትን ውድድር አትሌቶችን በማቀያየር እንዲሁም ሌሎች የልምድ ልውውጦችን በማድረግ ለማሳደግ ታቅዷል።

የአዲስ አበባ ድምቀት የሆነው ታላቁ ሩጫ በሚካሄድበት ወቅት ከተለያዩ ዓለማት የዓለም እና የኦሊምፒክ ቻምፒዮን የሆኑ ዝነኛ አትሌቶች ይጋበዛሉ። ይሁንና በርካቶችን ለድል ያበቃችው በቆጂ መሰል ውድድር እያስተናገደችም ከጉያዋ የወጡ አትሌቶች ሊገኙ አለመቻላቸው የበርካቶች ጥያቄ ነው። የውድድሩ አዘጋጆች በበኩላቸው፤ ለእነዚህ አትሌቶች ጥሪ ቢያቀርቡም በአካል ስፍራው ላይ መገኘት አለመቻላቸውን ነው የሚጠቁሙት። ከዚህ ባለፈ በስፖርት ቱሪዝም ላይ አተኩሮ የሚሰራው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓመት ውስጥ እንደሚያካሂዳቸው ትልልቅ የሩጫ ውድድሮች ሁሉ የአትሌቶች ምንጭ የሆነችው በቆጂንም የቱሪስቶች ማዕከል ለማድረግ በተጠናከረ ሥራ እንደሚቀጥሉም ሥራ አስኪያጇ ጠቁማለች።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ ይህ ሩጫ አንግቦ የተነሳው ዓላማ የስፖርት ቱሪዝምን ማስፋት እንደመሆኑ ለአትሌቲክስ ስፖርት እጅግ ምቹና የአትሌቶች ምንጭ የሆነው በቆጂ ተመራጭ መሆኑን ጠቁመዋል። ረጅም ጉዞ የሚጀምረው ከአንድ እርምጃ ነው፤ እንደሚታወቀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያም በትንሽ ቁጥር የጀመረውን ሩጫ በሺዎች በማሳደግ የውጪ ሀገራት ዜጎችንም በስፋት በማካተት ይደረጋል። በመሆኑም ይህንን ሩጫም በማሳደግ በርካታ ቁጥር ያለው ሯጮችንና ቱሪስቶችን ለማሳተፍ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል። ከሩጫ ባለፈ ተራራ ለመውጣት እንዲሁም ለብስክሌት ስፖርትም የተመቸ እንደመሆኑ በቀጣይ ሁነቱን በማስፋት የቱሪስቶችን ቆይታ ለመጨመር ይሠራል።

ይሁንና ዓላማው ግብ እንዲመታ ለአትሌቶች የሚሆን የስልጠና ስፍራዎችንና ለቱሪስቶች የሚሆኑ መሰረተ ልማትን ማሟላትም አስፈላጊ ነው። እንደ በቆጂ ሁሉ በርካታ አትሌቶች የፈለቁባት የኬንያዋ ኤልዶሬት ከተማ ዋነኛ ገቢዋ ከተለያዩ ዓለማት ወደስፍራው በሚጓዙ አትሌቶች ስልጠና የሚገኝ ነው። ይህንን ሁኔታ በቆጂም ላይ እንዲንጸባረቅ ለማድረግ ደግሞ የባለሀብቶች፣ የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት ተሳትፎ አስፈላጊ ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ውድድሩን ከማካሄድ ባለፈ አካባቢውን የማነቃቃት ሥራ በማከናወኑ የተወሰኑ ለውጦች ተስተውለዋል። በቆጂ ያፈራቸው ስመጥር አትሌቶች ግን በተለየ ሁኔታ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። አትሌቶቹ ተወልደው ያደጉበት አካባቢ እንዲታወቅ፣ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንና ሕዝቡም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚገባቸውም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You