ዘንድሮ በ130 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች በዚህ ዓመት ብቻ የሚተከሉ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ተዘጋጅተዋል። ከሌላ ጊዜው በተለየ መልኩ ችግኞቹ የሚተከሉባቸው ሥፍራዎች ቀድመው ተለይተዋል። ችግኞች የሚተከሉባቸውን ቦታዎች ከመለየት ባሻገር፤ የመሬቱን ትክክለኛ መረጃ በቴክኖሎጂ በመለየት የትኛውም አካል በየትኛው ቦታ ምን ዓይነት ችግኝ እንደተተከለ ሊያረጋግጥ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ለአረንጓዴ ዐሻራ ትኩረት ሰጥታ ከ32ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተክላለች።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩትም ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በቂ ትኩረት የተሰጠውና በቴክኖሎጂም የተደገፈ መሆኑን ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ባለሞያ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሔደውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ ዶ/ር እንደሚናገሩት፤ ደን ልማት ውስጥ በኢትዮጵያ የሚተከለውን የችግኝ መጠን የሚለካ፣ ሪፖርት የሚያደርግ እና ሪፖርቱን የሚተነትን ትልቅ ክፍል (ዲፓርትመንት) ተገንብቷል።
ክፍሉ አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ታጥቋል። በቀጣይም የሰው ኃይል የማሰልጠን እና ተጨማሪ ማሽኖችን እና ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም መረጃ የመሰብሰብ፤ የመተንተን እና ሪፖርት የማድረግ ተግባራት ይከናወናል፤ ለውሳኔ ሰጪ አካላትም ይላካል ሲሉ ባለሙያው ይናገራሉ።
የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች የሚሰሩት በደን ልማት ብቻ ሳይሆን በግብርና ሚኒስቴር፣ በሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር እንዲሁም በሌሎችም ተቋሞች መሆኑ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ከቀበሌ ጀምሮ መሬት የመለየት ሥራ ይከናወናል። በአንድ ቀበሌ ውስጥ በጣም የተጎዳ መሬትን ለተፋሰስ ልማት የሚለየው እዛው ቀበሌ ውስጥ ያለ ባለሞያ ነው ይላሉ።
እዛው እታች ያሉ የቀበሌ ባለሞያዎች፤ ወረዳዎች፣ ዞን እና ክልል ላይ ካሉ ባለሞያዎች ጋር በመሆን ከግምት ባለፈ መሬትን ወደ ቁጥር የመለየት ሥራ ይሠራል። በፌዴራል ደረጃም በደን ልማት ድጋፍ ይደረጋል። የቴክኒክ ኮሚቴውም ድጋፍ ያደርጋል። የክልሉም እስከ ቀበሌ ወርዶ እንደሚደግፍ ይናገራሉ።
አደፍርስ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት የሚታወቅ የተለካ ጥቅም ለማግኘት የመሬት ልየታውን ብቻ ሳይሆን ችግኝ የሚተከልባቸውን ሥፍራዎች መለየት ሥራው በደንብ ታስቦበት እየተሠራ ነው። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል የመሬት ልየታን የሚያከናውኑ ከቀበሌ እና ከዞን የተመለመሉ 2ሺህ ወጣቶች ተለይተው ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንዲሰለጥኑ ተደርጓል።
ሰልጣኙም የተሰጠውን ስልጠና ይዞ የመሬት ልየታ እና የጂኦ ሪፈረንሲንግ ሥራውን ሲሠራ ቆይቷል። ስለዚህ የችግኝ ጣቢያዎቻችን የት ይገኛሉ? ስንት ሔክታር ይሸፍናሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስም ሆነ የመትከያ ቦታውን ለማወቅ እየተሠራ ነው። ዛሬ በዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች (በስማርት ፎን) መረጃ ወደ ማዕከል እየተላከ ነው። በተለያዩ መተግበሪያዎች (አፕልኬሽኖች) የተለዩትን መሬቶች አውቀው ልኬቱን እና ኤክስ ዋይ ኮርድኔት አስቀምጠው ይልካሉ። ልኬቱ ሲገባ እና ኤክስ ዋይ ኮርድኔት ሲገባ፤ የስፔስ ሳይንስ ቋት ውስጥ መረጃው ይገባል። በጂፒኤስ እና በሞባይል ሥራው እየተሠራ ትልቅ መሻሻል እየታየ መሆኑን ያስረዳሉ።
ይህ የተቆጠረ ሥራን በአግባቡ ለመለየት እንደሚያስችል አመልክተው፤ ለአብነት ያህል እዚህ ቦታ ላይ በ10 ሄክታር ላይ አቮካዶ ተተክሏል ከተባለ እና መረጃው ካለ ቦታው ስለሚታወቅ በአግባቡ ለገበያ ለማዘጋጀት ዕድል ይሠጣል። ይህ በሌለበት ጠንካራ የመሬት ፕላን ማዘጋጀትም አይቻልም ይላሉ።
የአቮካዶ ዛፍ መተከሉ ቀድሞ ከታወቀ ፍራፍሬው ሲደርስ ከገበያው ጋር ለማቆራኘትም ችግር እንደማይኖር ያመለክታሉ። ከዛሬው ከታወቀና እና ቀድሞ የለማ ከሆነ፤ ከአራት ዓመት በኋላ መሬት ላይ ምን ያህል ማምረት እንደሚቻል መገመት ይቻላል። ከገበያ ጋር ለማስተሳሰርም ይረዳል።
ባለሙያው ልኬት በጣም አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ በርግጥ አቅም እና መሠረተ ልማት የሚፈልግ መሆኑ የቴክኒክ እና ዓብይ ኮሚቴው በሚፈልገው ልክ የመሬት ልየታው ተካሄዷል ማለት እንደማይቻል ያመለክታሉ።
መረጃ የሚሰበሰብበትም ሆነ ሪፖርት የሚተነተንበት ቦታ ላይ አቅም እየተገነባ መሔድ ይኖርበታል የሚሉት አደፍርስ (ዶ/ር) ዘንድሮ የተለያዩ ባለሙያዎችን የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ። ለምሳሌ የጂ አይ ኤስ ባለሞያዎች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተበትነዋል። እነዛን ወደ አንድ እንዲመጡ ታስቦ እየተሠራ መሆኑንም ያመለክታሉ።
አስተባባሪው እንደሚያስረዱት፤ የሚተከለው ደን የሸፈነው መሬት እና ቀደም ሲል የነበረው መሬት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተባበረ ካርታ እንዲያዘጋጅ ለኢትዮጵያ ደን ልማት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ካርታ ሥራዎች ደግሞ የደን መሬትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የግጦሽ መሬትን፣ የእርሻ መሬትን፣ የከተማ መሬትንም ካርታ ይሠራል። ስለሆነም እነዚህን የጂ አይ ኤስ ባለሞያዎችን አንድ ቦታ በማሰባሰብ የመረጃ አቅርቦቱ የተሻለ ሆኖ መሄድ እንዲችል ሙከራ እያደረግን ነው ይላሉ።
ከፋይናንስ፣ ከሰው ኃይል አደረጃጀት እና አቅርቦት ጋር ተያይዞ፣ እንዲሁም ከመሠረተ ልማት ጀምሮ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ በጣም ሰፊ በመሆኑ በየቦታው ክፍተቶች ይታያሉ ይላሉ። አንዳንዶቹን ክፍተቶች በየዓመቱ ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደፊት ደግሞ በጣም የተዋጣለት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
አደረጃጀቱን ከማዘመን እና ከማጠናከር እንዲሁም በፋይናንስ ለመደገፍ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ከማሳመንም ጋር ተያይዞም እንዲሁም ጂኦሪፈረንሱ ጠቃሚ መሆኑን አስታውሰው፤ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታትም ሌላው ቢቀር የግል ዘርፉም ሆነ ሀገር ውስጥ ያሉ ድርጅቶች እንዲደግፉት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አደፍርስ (ዶ/ር)ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተገልጋይ ገንዘብ ይሰበስባል። ዋናው እና አንደኛው የአረንጓዴ ዐሻራ ተጠቃሚ ይሄ ድርጅት ነው የሚሉት አደፍርስ (ዶ/ር)፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅቱ የአረንጓዴ ዐሻራን በዚህ መጠን መደገፍ አለብኝ ብሎ መምጣቱ በጣም ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ እዚህ መምጣት አለበት፡፤ ሌሎች ሐይቅ ዳር ያሉ ሆቴሎችም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ በመሆናቸው ድጋፍ ማድረግ አለባቸው።
እነዚህ ተጠቃሚዎች ወደፊት ጥቅሙን ሲያገኙ ሳይሆን፤ ዛሬውኑ ወደፊት እንደሚጠቀሙ አስበው መሥራት አለባቸው። እንደዛ ሲሆን የጋራ ሀገር እና ጥቅም ይኖራል ይላሉ።
ወደ 700 ሺህ ሄክታር ጂኦ ሪፈረንሲንግ ለማድረግ ታቅዶ፤ 624ሺህ ሔክታር ኤክስ ዋይ ኮርድኔት ተለይቶ በእጃቸው መግባቱን አስታውሰው፤ በቀጣይ ተከላው እስከሚጀመር ማለትም እስከ ሰኔ አጋማሽ አካባቢ ድረስ 700ሺህ ሄክታር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል ብለዋል። ከአምስት ሄክታር በላይ ያለውን አሁንም የጂኦ ሪፈረንሲንግ ሥራው እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየቀኑ ቁጥሩ እንደሚጨምርም ተናግረዋል።
ይህ ሥራ ቀበሌ፣ ዞኑን ጨምሮ እስከ ክልል የትኛው ቦታ ለማ የሚለውን ለማወቅ እና ለመከታተል ይረዳል። በፌዴራል ደረጃም፤ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ ክልል፣ በአፋር ክልል፣ በአማራ ክልል እያልን በዚህ አካባቢ የፍራፍሬ፣ በዚህ አካባቢ ደግሞ የደን ዛፎች ተተክለዋል ብሎ ለመለየት እንደሚያግዝም ያስረዳሉ። የተሠሩትን የሥነ ምሕዳር ማሻሻያ ሥራዎችን ለመለየት እና በቅድሚያ ቦታውን፣ ከዛ የማኔጅመንት፣ የሰው ኃይል የመመደብም ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያግዝ አመልክተው፤ ይሄ በሌለበት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ያመለክታሉ።
አንድ ክልል ላይ 20 ሄክታር ላይ ቀርከሃ ተተክሏል ቢባል፤ ቦታው ተለይቶ ካልታወቀ ይተከል አይተከል አይታወቅም። ፀደቀ አልፀደቀ የሚለውን ማወቅ አይቻልም። አሁን ግን የት ቦታ ላይ እንደሆነ ስለሚታወቅ ማረጋገጥም ይቻላል። ይሄ በራሱ የአረንጓዴ ዐሻራ ውጤት መሆኑን ያመለክታሉ።
በየቦታው ክላስተር አቮካዶ ተተክሏል። እነማን እና የቱ ጋር እንደተከሉ ስለማይታወቅ መደገፍም አዳጋች ነው። ነገር ግን ቦታው ከታወቀ እና አርሶ አደሮቹ ከታወቁ መንግሥትም ለመደገፍ ይመቸዋል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታቸውን ወደ ውጭ እስከሚልኩ ለማገዝ የተቻለበት አጋጣሚ መኖሩን አመልክተዋል።
እንደ አደፍርስ ዶ/ር ገለፃ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ብዙ ቀዳዳን የሚደፍን ነው። ሀገር እንድትታወቅ፣ ኢኮኖሚያዋ እንዲያድግ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት አልፎ ተርፎ ለሰላም ግንባታም ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በችግኝ ጣቢያዎች ማዳበሪያ በማምረት የግብርና ግብዓትም እየተገኘ ነው። በየችግኝ ጣቢያዎችም የንብ ማነብ ሥራም ተሰርቷል፤ ፍግ የማዘጋጀት ሥራም ተከናውኗል። በዚህም ምክንያት ዛፍ ሲተከል እና የአፈር እና የውሃ ጥበቃ ሥራ ሲሠራ ትናንት የደረቁ ምንጮች ውሃ እያመነጩ ነው። የዝናብ መጠኑ ከፍ ብሏል። አየሩም ተስተካክሏል።
የአረንጓዴ መርሃ ግብሩ ግድቦች በቂ ውሃ እንዲያገኙ ያደርጋል። በተጨማሪም ጎርፉ ይቀንሳል። በአረንጓዴ ዐሻራ የተወሰነውን ውሃ እዚሁ አቆይቶ መሬቱን አለስልሶ ገብርናችንም ምርታማ እንዲሆን አስችሎናል። ከሆሳዕና በቅርብ ርቀት በ2 ዓመት ከስድስት ወር ከዛፋቸው አቮካዶ ያገኙ አሉ። ይህ ትልቅ ትሩፋት ነው።
ከክልሎች ጋር በጋራ በመሥራት መሬት በመለየት፤ የችግኝ ማፍላት ሥራም መሠራቱን እና ችግኞች በቂ ጊዜን አሳልፈው ለተከላ እንዲዘጋጁ መደረጉን የሚናገሩት ደግሞ የደን ልማት ባለሞያው አቶ ተስፋዬ ጋሻው ናቸው። በኢትዮጵያ ደን ልማት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፤ በቀላሉ መፅደቅ የሚችሉ ችግኞች እንዲተከሉ ጥንቃቄ ተደርጎ ተሠርቷል። የስብጥር ሥራም በመሠራቱ የደን ችግኝ ብቻ ሳይሆን የአትክልት እና ፍራፍሬ ዝርያ ያላቸውንም ተክሎች ተዘጋጅተዋል።
ስለዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለሌማት ትሩፋት ሊደግፍ በሚያስችል መልኩ እና የሀገሪቱንም ደን ልማት ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል ይላሉ። በተከላ ወቅት እና ከተከላ በኋላ መደረግ ስላለባቸው ዝግጅቶች ከወዲሁ ገለጻ እየተደረገ ነው።
የፅድቀት መጠኑ እንዲጨምር እያንዳንዱ የተከለው ሰው ኃላፊነቱን ወስዶ መትከልና መንከባከብ ይኖርበታልም ብለዋል።
በየአካባቢው ያለው የግብርና ቢሮ ከተከለው ማህበረሰብ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን አስታውሰው፤ ማህበረሰቡ ‹‹ተንከባክቤ አሳድጋለሁ›› ብሎ በገባው ቃል መሠረት ቃሉን መፈጸሙን ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ኃላፊው ይናገራሉ።
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ፤ የአረንጓዴ ዐሻራን በተመለከተ የሚሠራው ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየታየበት ነው። ጥቅምም እየተገኘበት ነው። በቀጣይ ደግሞ የሚያስገኘው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም