ኢትዮጵያውያን ምዕራቡን ከምስራቅ፣ ሰሜኑን ደግሞ ከደቡብ የሚያገናኙ እንደሀገር ዘመናትን የተሻገርንባቸው፤ ጠንካራ ሀገር የተገነባባቸው፤ በዓለም አደባባይም በበጎ የምንነሳባቸው ትርክቶች አሉን። እነዚህ ትርክቶችም በሕብር የደመቀ አብሮነታችንን መጠበቂያ እና የበለጠ መተሳሰሪያ ገመድ በመሆንም ዛሬ ላይ አድርሰውናል።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በአንድ በኩል ከብዝሀ ማንነት የሚመነጭ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄንን ብዝሀ ማንነትና እሳቤ በልኩ ተገንዝቦ ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት ካለመፈጠሩ ጋር ተያይዘው የሚታዩ የግጭትና አለመግባባቶች ተፈጥረዋል።
እነዚህ በአንድ በኩል የአንድነት አውዶችን የሚያጎሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአንድነት መንገዱን ሊፈትኑ የሚችሉ ሁነቶች ደግሞ እንደየጊዜው እየተመዘዙ፤ የሕዝረታችን ማጽኛም፣ የሕብረታችን መበተኛም እንዲሆኑ ሲመነዘሩና ሲተረኩ ተመልክተናል።
በዚህ በኩል በተለይ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከአንድነቱ ይልቅ ልዩነቱ፤ ከመልካም ትርክቱ ይልቅ የታሪክ ስብራቶችን የበለጠ በሚያጎሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር የተለመደ ሆኗል። አሁን አሁን ደግሞ ሀገርን በብዙ እየፈተነ ሕዝቧንም ከኖረበት፣ ከተጋመደበት አንድነት ለመነጠል የሚዳዳው የተሳሳተ በወል እውነት ላይ ያልተመሰረተ ትርክት የበለጠ ፈተና እየሆነ ይገኛል።
ይሁን እንጂ በማንኛውም መልኩ ቢታይ በከፍታ የምትገለጽ ሀገር እውን ማድረግ የተቻለው የብዙዎች የጋራ ውጤት ነው። ኢትዮጵያም የታሪክ ገናናነቷ፤ የስልጣኔ መንገዷ፤ የነፃነትና አልደፈር ባይነት እውነቷም በዚሁ የወል መንገድ የተገኘ ነው። የዛሬዋ የኢትዮጵያ ማንነትም እንደ ትናንቱ በሁሉም አቅጣጫ በሚዋጣና በአንድነት በጠነከረ፣ አላማው በገዘፈ ጠጠር የሚገነባ ነው።
ይሄ እንዲሆን ደግሞ ዛሬም እንደትናንቱ የምንሰባሰብበትና በአንድ የምንቆምበት እሴት አለን። ምክንያቱም እኛ በአራቱም ማዕዘናት ስለሀገር ሲሉ የተዋደቁ፣ ደምና አጥንታቸውን ባፈሰሱ በቅድመ አያቶቻችን አፅም የፀና፣ ማህበራዊ መስተጋብሩ የጠነከረ፣ ባህላዊ ዕሴቶች ያዳበሯት፣ ትውልድ በማፍራት ሂደት የራሳቸው ድርሻ ያላቸው፣ የኛ የምንላቸው፣ በኛነት የገነባናቸው፣ በአብሮነት የምንዘልቅባቸው ትርክቶች ባለቤቶች ነን።
እናም ለትናንቱ ከፍታችን እኩል ድርሻ አለን ካልን፤ እንደ ሀገር ደግሞ ደንቀፍ ሲያደርገንም ለሚፈጠረው ችግር ድርሻውን በጋራ መወስድ ይጠበቅብናል። እኔ የቤት ሥራዬን ባለመወጣቴ የመጣብን ችግር ነው ብሎ ሁሉም ኃላፊነቱን መውሰድም ይኖርበታል። በመገፋፋት ‹‹እሱ ነው፣ እሷ ናት›› በሚል በመጠቋቆም የበለጠ ወደ አዘቅት መግባት ውጪ ከአርንቋ መላቀቅን አያስከትልም፤ ሰላምንም አያሰፍንም።
ሰላም ደግሞ የሁሉም ጉዳዮች ማጠንጠኛ ቋጠሮ ነው። ያለሰላም ምንም ነገር ማከናወን አይቻልም። ሰላም የሁሉም ነገር ዋስትና በመሆኑ ዋጋው ከፍ ብሎ ይነሳል። ካለ ሰላም ነገ የለም። ምክንያቱም ግጭትና ጦርነት ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ይወስድብናል። ሰላም ከሌለ ሰርቶ መለወጥ፣ ተስፋ ብሎ ነገርም የለም።
ይህንን የሰላም አየር ለማደፍረስ ደግሞ እዛም እዚህም ፀብ የሚጭሩ አይጠፉም። በዚህ ምክንያት በሚከሰቱ ግጭቶች ደግሞ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ከሰፈራቸውም ይፈናቀላሉ። በአንጻሩ የግጭትና ጦርነት ጫሪዎች በንጹሃን መከራ ላይ ኑሯቸውን ያደላድላሉ።
እነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጠሩትና ሰላምም ዋጋ የምታጣው ደግሞ፤ ለግጭትም ሆነ ጦርነት ገፊ በሆኑ ምክንያቶች እና አለመግባባቶች ላይ ቀድሞ ለመነጋገር ባለመፍቀድ ነው። በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት የፖለቲካ አለመጋባባቶች በፈጠሩት እና በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ አለመነጋገር በወለዳቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች በርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ንብረትም ወድሟል፤ ብዙዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ብዙ ልጆቿንም፤ ሀብቷንም አጥታለች።
መቅደም የሚገባቸው ሰላማዊ ውይይቶች እየዘገዩ መሆንና መፈጠር ያልነበረባቸው ጦርነቶች እየፈጠኑ ሀገር በማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ እንድትጓዝ ሆኗል። ይሁን እንጂ ዛሬ ይሄንን የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ስቃይ ለመግታት እድል አለ። ዛሬ ጠመንጃን ጥሎ ወደ ጠረጴዛ በመምጣት እስካሁን ያለፍንበትን ውድመት እንዲበቃ ማድረግ ይቻላል።
ለዚህም መንግሥት በተደጋጋሚ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደ ውይይት እንዲመጡ፣ ችግሮች በአፈ ሙዝ ሳይሆን በንግግር እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ ነው። ኢትዮጵያ በምክክር ስር የሰደዱ ችግሮቿን ነቅላ እንድትጥል መንገዱን ለመጥረግ እየሠራ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየተሳተፉ ያሉ መሳሪያ የታጠቁ አካላት ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ እያደረገ ነው።
በሀገር ደረጃ ባለፉት ዓመታት ሰላምን ለማስፈን መንግሥት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ያነሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግበው ጠመንጃ ይዘው ጫካ የገቡም አሉ። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ/ዶ/ር/ በነቀምቴ በነበራቸው ቆይታ “ጦርነት፣ እርስ በርስ መገዳደልና መበላላት ይብቃን” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። በባህር ዳር የፕሮጀክት ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተውም ይህንኑ ጥሪ በድጋሚ አስተላልፈዋል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ይበል የሚያሰኝ ነው። መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አካል ቁርጠኝነቱ እስካሁን ካደረገው በላይ ማድረግም አለበት። አንድ ርምጃ ወደፊት መሄድ ኃላፊነቱ የሰጠው ግዴታ ነው። በተለይ መሳሪያ የያዙ በየቦታው፣ በየጫካው ያሉ አካላትን በተለያየ መንገድ አሳምኖ እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ አሁንም መሥራት አለበት። መንግሥት የማሳመን ሥራውን በሌሎች ሶስተኛ አካላት አማካኝነትም አምነው ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ ያስፈልጋል። የቁርጠኝነቱ ልክ የሚጀምረውም እዚሁ ጋር ነው። ለሰላም የማይከፈል ዋጋ ስለሌለ ሁሉንም አማራጭ መጠቀም ተገቢ ነው።
ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ሕዝብ በሚገባ ያውቀዋል። ጦርነትም ከብዙ ዋጋ ማስከፈል በኋላ በመጨረሻ የሚቋቸው በድርድርና በስምምነት ነው። ከዚህ አኳያ እዛም እዚህም ጦርነት የሚጎስሙ አካላትን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምጣት ያስፈልጋል። በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች ደግሞ ትዕግሥትን ይጠይቃሉ። ምክንያቱም በአንድ ቀን የሚፈታ ችግር የለም። ሁሉም አካላት ለሀገርና ለዜጎች ሰላም ሲባል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ውይይትና ድርድርም ቢሆን በአንዴ ብቻ ችግሩን የሚፈታ አይደለም። ያለ መግባባታችንን አለዝበን ወደተሻለ መግባባት ለማምጣት መለያየት፤ ደግሞም ለመወያየት መዘጋጀት ከተቻለ ብዙ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል። ቀጥ ያለ አቋም ከመያዝ ይልቅ ነገሮች ቀለል አድርጎ ሀገርና ሕዝብን ማዕከል አድርጎ ‹አንተ ይሄን ተው፣ እኔ ይሄን ልተው› ብሎ በመነጋገር ሰጥቶ መቀበል መርህን ሁሉም ቢከተለው ችግሮቻችን የሚፈቱበት መንገድ ቀላል ይሆናል።
በተቃራኒው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተፅእኖ ከፍ ብሎ የሚነሳው የሰላም እጦት ሀገርንም ወደማትወጣው ቅርቃር ውስጥ ይከታል። መንግሥት ይህንን በመገንዘብ ለሀገር ሰላም ሲል በሩን ለድርድር ክፍት ቢያደርግም ታጣቂ ቡድኖች ግን ወደ ድርድር የመምጣት አካሄዳቸው ግን ችግር ያለበት ነው። ለዚህ የተለያየ ምክንያት ቢኖራቸውም አንዳንዶች ግን ጦርነቱ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ዋነኛ የገንዘብ ምንጫቸው ግጭት በመሆኑ ነው።
ይህም ለህብረተሰቡ መብትና ጥቅም እየታገልን ነው የሚሉት አካላት ለሚታገሉለት ህብረተሰብ በተቃራኒው ሆነው እንዲታዩ አድርጓል። ለሞት ለመፈናቀል ምክንያት ሲሆኑ ይታያሉ። ነገር ግን እታገልለታለሁ የሚሉት ማህበረሰብ ሁኔታው አስጨንቋቸው የራሳቸውን ጥቅም ወደጎን በመተው ወደ ድርድር መምጣት አለባቸው። ለህብረተሰብ የሚታገል አካል የህብረተሰብ እንግልት፣ ውድመት፣ ሞት እና ስቃይ ሊሰማው ይገባል። በራቸውን ከፍተው፣ ልቦናቸውን መልሰው ለውይይት ቀናኢ መልስ መስጠት አለባቸው።
በመሆኑም ሕዝብን ያስቀደመ ውይይት መደረግ አስፈላጊ ነው። መንግሥትም ይህንኑ እየሠራ መሆኑን ያነሳል። የዚህችን ሀገር ሰላም ከማረጋገጥ አንፃር በርካታ ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን መወጣት ከቻሉ የኢትዮጵያ ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ ይችላል። ለዚህ ቀዳሚው መንግሥት ሲሆን፤ ሆደ ሰፊ መሆንን እና እስካሁን እንዳደረገው በየትኛውም መልኩ ያሉ የሰላም በሮችና መስኮቶች ክፍት አድርጎ ለመነጋገርና ለመደራደር ፍቃደኛ መሆኑን በዘላቂነት ማሳየት አለበት።
ነገር ግን መንግሥት ብቻውን እዚህች ሀገር ላይ ያሉትን ችግሮች በሙሉ ሊፈታ አይችልም። ሁላችንም መተባበር አለብን። መሳሪያ ይዘው ጫካ የገቡ ኃይሎችም ለሕዝብ እታገላለሁ እስካሉ ድረስ ባለፉት ዓመታት ጫካ ውስጥ በመግባታችን ምን አተረፍን፣ ለሕዝባችን ምን ጠብ የሚል ነገር አመጣን የሚሉትን ጉዳዮች ቆም ብለው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።
እናም ስለሕዝብ እንታገላለን ስለኢትዮጵያዊያን ያገባናል ብለው ጫካ የገባ አካል ሁሉ ከማንም በፊት የሕዝቡን ፍላጎት ማስቀደም ስለሚገባው እነዚህን የውይይትና ችግሮችን በንግግር የመፍታት ጥሪዎችን መቀበል ይገባዋል። ቀድሞም ይህ ሁሉ ውድመት ከመፈጠሩ በፊት ሰላምን የሚያሰፍኑና የሚያፀኑ ንግግሮች ከዛሬ ይልቅ ትላንት ቢደረጉ መልካም ነበር። ከነገ ግን ዛሬ እጅጉን ይሻላል።
ቀን ቀንን እየተካ በመጣ ቁጥር በግጭት በጦርነት ውስጥ መቆየት በውድመት ላይ ውድመት፣ በኪሳራ ላይ ኪሳራ፣ በመከራ ላይ መከራ ከመጨመር ውጪ ማንንም አሸናፊ አያደርግም። የሚገኝ ትርፍም የለም።
በአንጻሩ በእያንዳንዱ የሰላም ቀን እያንዳንዱ ዜጋ ተጠቃሚ ነው። የህዝብ ፍላጎት ደግሞ ሰላም ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ እንዲሳካ ሰላምን ለማፅናት ብቸኛው መፍትሄ ውይይትና ንግግር ቦታቸውን መያዝ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካላት ሰላምን ለማፅናት ሀገርን ከውድመት ለመታደግ ቀናኢና ተባባሪ መሆን፣ የሕዝብን ፍላጎት ማስቀደም ይገባል።
የሰላም አየር የራቃቸው አካባቢዎች እንኳን ልማትና እድገት ሊያልሙ ቀርቶ ወጥቶ መግባት አዳጋች ሊሆን ይችላል። ሆኖም ከእጅ ስትወጣ የዋጋ ክብደቷ ከእንቁ በላይ የሚሆነው ሰላም እያለችን አናስተውላትም ይባላል።
በግጭትና ጦርነት የታመሱ ሀገራት የመጨረሻ ውጤታቸው መንኮታኮት እንጂ ልማትና ብልፅግና አይደለም። ለዚህም ነው ግጭት ከመጥመቅ ጠመንጃን ቁልቁል አድርጎ የብእር ጫፍ መጠቀም፣ በክብ ጠረንጴዛ በሀሳብ መፋጨት ሁሉም የሚሻትን ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው። ስለሰላም መወያየት የንግግር ዲስኩር ማብዛት ጉንጫችን ሰላምንና ሰላምን እያነሳ ቢለፋ እናተርፋለን እንጂ የምናጣው ነገር የለም።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች ወደ መረጋጋት አውድ እየመጡ ነው። ቀድሞ ለመንቀሳቀስ ጥርጣሬ በነበረባቸው አካባቢዎች አሁን የልማት ስራዎችን ጭምር እየተመለከትን ነው። ህዝቦች ስለሰላም በህብረት ወጥተው የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ማሰብ ይከብድ በነበረበት ቦታ ሁሉ ወጥተው በጋራ ሰላማችንን ጠብቀናል፣ግጭትና ጦርነት ይብቃን፣ ልማትና እድገትን እንፈልጋለን እያሉ ነው። ይህም የግጭት ምርኮኛው ጥቂቶች መሆናቸውን የሚነግረን፤ በየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍ ያለ ሕዝብ ግን ሰላምና ልማት ብቻ የሚሻ መሆኑ አስረጂ ነው።
ሆኖም ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አሁንም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ውስጥም በተጨባጭ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የተፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚመለከት ህዝብም ሰላሙን በመጠበቅ ረገድ ሀላፊነቱን ወደ መንግስት ከመጠቆም መውጣትና እኔም ለአካባቢዪ ሰላም ዘብ ነኝ ማለት ይኖርበታል። እንዲህ ሲሆን ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ማፅናት ቀላል ይሆናል።
ለዚህም አንድነትን ማጠናከርና ሀገርን መገንባት የሁሉም ሀላፊነት መሆን አለበት። በተቃርኖ ያቆሙንን ችግሮቻችንን በማከም ልዩነታችንን ለማስፋት በዚህም በዚያም ወጥረው የያዙንን የተበተቡንን ገመዶች በጣጥሶ መጣል ይገባል። በዚህ መልኩ ለችግሮቻችን መፍቻ የሚሆኑን ውይይትና ምክክርም በእጃችን ላይ ያሉ ብቸኛ አማራጮቻችን በመሆናቸው አጋጣሚውን እንጠቀምበት። ባሉን ዘመናት በተሻገርንባቸው ሀገራዊ እውቀቶቻችን በመታገዝ፣ ስብራቶቻችንን በመጠገን ለነጋችን በፅናት ለመቆም በጋራ እንስራ!
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም