አረንጓዴ አሻራ ለኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለሰላም ግንባታም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው -አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ

የአየር ንብረት ለውጥ ከሚፈጥረው ተጽዕኖ ለመውጣት፣ ዓለምን ከመጥፋት የመታደግ ዓላማን በማንገብ በየሀገሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ይከናወናሉ። ይሄንኑ በሰፊው እያከናወኑ ካሉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ኢትዮጵያ ለዓለም ማህበረሰብ 22 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንዲያገግም እሠራለሁ ብላ ቃል ገብታለች። ይህንን ማዕከል አድርጋ መሥራት ከጀመረች ሰነባብታለች። በተለይ የክረምት መግባትን ተከትሎ በሚካሄድ የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ ሥነሥርዓት መሰረት በመላው ሀገሪቱ ተከላው ይከናወናል።

በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ ይሄው የሚቀጥል ሲሆን፤ የእዚህ ዓመት የችግኝ ተከላ ከሌሎቹ ዓመታት በምን ይለያል? በሚሉ እና በሌሎችም ከአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ እንግዳ ይዘንላችሁ ቀርበናል። የዕለቱ የወቅታዊ ገፅ እንግዳችን አደፍረስ ወርቁ (ዶ/ር) ናቸው።

እንግዳችን በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ባለሙያ፤ በፎረስት ሴክተር ትራንስፎርሜሽን ክፍል የፕሮግራም አስተባባሪ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሔደውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ናቸው። በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ በየቀኑ የሚሠራውን ቴክኒካል እንቅስቃሴ ይከታተላሉ፤ ይመራሉ። እኛም ከአደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንሆ ብለናል። መልካም ንባብ፤

አዲስ ዘመን፡-የዘንድሮ ችግኝ ተከላ መቼ እና እንዴት ለማስጀመር ታስቧል?

ዶ/ር አደፍርስ፡– የችግኝ ተከላው የማስጀመሪያ ሥነሥርዓት የሚካሄደው እንደተለመደው በየዓመቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መሪነት ነው። የአረንጓዴ አሻራ ዓብይ ኮሚቴ እና የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋማት አሉ። ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት፣ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽን ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎችም ሚኒስቴሮች ያሉበት ዓብይ ኮሚቴ አለ። በዓብይ ኮሚቴው ሥር ደግሞ የቴክኒክ ኮሚቴዎች አሉ። እነርሱም እየደገፉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ዓመታዊ የተከላ መርሃ ግብር ማስጀመሪያውን ያካሂዳል። በዚህ ጊዜ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ለኢትዮጵያውያን ጥሪ ይቀርባል።

ሁሉም ክልሎችም ዜጎቻቸውን ይዘው የኢትዮጵያን ወዳጆች አንድ ላይ አቀናጅተው የተከላ መርሃ ግብሩን ይጀምራሉ። ይህ አሁን ባለው ሁኔታ ሰኔ 3ኛው ወይም 4ኛው ሳምንት አካባቢ ይጀመራል ተብሎ ታቅዷል። ቀኑ ጊዜው ሲቀርብ ይፋ ይደረጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካስጀመሩ በኋላ፤ ዘንድሮ የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ሁሉም ክልሎች ክልላቸውን እየመሩ የተቀናጀ ዓመታዊ የተከላ መረሃ ግብር ማስጀመሪያ ፕሮግራም ይካሄዳል።

የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች በማስጀመሪያው ላይ የተዘጋጀው ችግኝ በአግባቡ በተዘጋጀለት ቦታ መተከል እንዲችል ለክልሉ ሕዝብ ጥሪ ያቀርባሉ። ይህ የሚሆነው ወዲያው ነው። ምክንያቱም ዘንድሮ ዝናቡ ቀድሞ ስለጀመረ ክልሎች ደግሞ በተከታታይ ዓመታዊ የማስጀመሪያ ቀን ያውጃሉ። በሌላ በኩል የአንድ ጀምበር የተከላ ፕሮግራምም እየታሰበ ነው። የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤትን ጨምሮ የአረንጓዴ አሻራ ዓብይ ኮሚቴ የበለጠ መግለጫ የሚሰጡበት ይሆናል። ይህ ትንሽ ለየት ባለ መልኩ እንዲከናወን ታስቧል።

በሁሉም የችግኝ ጣቢያዎቻችን ለአምና ተከላ ያልደረሱ ችግኞችን ተንከባክበን ለዘንድሮ የተከላ መርሃ ግብር ካደረስናቸው በኋላ ተጨማሪ ችግኞችን አዘጋጅተናል። በአጠቃላይ ከ115 ሺህ በሚበልጡ የችግኝ ጣቢያዎች ለዘንድሮ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ አዘጋጅተናል። የችግኝ ጣቢያዎቹ የተለያዩ ሲሆኑ፤ የመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች፣ የግለሰብ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ፣ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ባለቤትነት ችግኝ እያፈሉ ያሉ የፕሮጀክት ችግኝ ጣቢያዎች አሉ። የማህበራት እና የማህበረሰብ ችግኝ ጣቢያዎች አሉ። እነዚህ ተደማምረው 115ሺህ ሆነዋል። ስለዚህ ከማስጀመሪያ ሥነሥርዓቱ በኋላ በስፋት ማህበረሰቡን ይዘን ወደ ተከላ እንሰማራለን።

አዲስ ዘመን፡- የማስጀመሪያ ሥነሥርዓቱ እስኪደርስ የክረምቱ ወቅት ቀድሞ የገባባቸውና ቶሎ የሚወጣባቸው አከባቢዎች ላይ የሚከናወነው ተከላ በምን መልኩ ይፈጸማል?

ዶ/ር አደፍርስ፡- እስከ አሁን ተከላ እየተካሔደ ያለባቸው ክልሎች አሉ። ቀድሞ ዝናብ የገባባቸው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያም በተወሰነ መልኩ፣ ኦሮሚያም በተለይ ቆላማዎቹ አካባቢዎች ላይ ተከላ ሲካሄድ ቆይቷል። እስከአሁን 141 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። ይህንን እናበረታታለን፤ ምክንያቱም ዝናብ ካለ ቀድሞ ቢተከል መልካም ነው። እንደሰብል በስለው መሰብሰቢያ ጊዜ እናጣለን የሚል ስጋት የለብንም። እንደውም በቂ የዝናብ ጊዜ አግኝተው የፅድቀት መጠናቸው ከፍ ይላል።

የማስጀመሪያ ፕሮግራሙ በፌዴራል ደረጃ ይፋ ከመደረጉ በፊት ክልሎች ይፋ ማድረግ ባይኖርባቸውም፤ ዝናብ ቀድሞ ከገባ ተከላውን ቢያካሂዱ መልካም ነው። የችግኝ ተከላ በአንድ በኩል ዘር እና ጉልበት መሻማትን ይፈልጋል። ሰኔ እና ሀምሌ ላይ የገበሬውን ጊዜ እና ጉልበት የሚፈልጉ በርካታ ስራዎች አሉ። በተለይ የሰብል ልማቱ ጊዜ እና ጉልበት መውሰዱ የሚታወቅ ነው። ስለዚህ ዝናቡ እና መሬቱ ካለ መትከሉ ችግር የለውም።

ሌላው የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ከአምና ጀምሮ መሬት እንዲለይ ሲሰራ ነበር። ለተለየው መሬትም ተመጣጣኝ ችግኝ እንዲዘጋጅለት በሚል በጣም ብዙ ጥረት ስናደርግ ነበር። ምክንያቱም ከባለፉት ዓመታት እያየነው እና እየተሻሻለ የመጣው በደን ልማት እና በተፈጥሮ ሀብት ሥራ መጀመሪያ መሬት መለየት እንዳለበት አውቀናል። መሬት ከተለየ በኋላ ችግኝ ይዘጋጃል። ላልተዘጋጀ መሬት ችግኝ ቢፈላ መሬት ፍለጋ አስቸጋሪ ነው። ይህ ደግሞ በጣም በርካታ ችግር እያስከፈለ አይተነዋል።

አንድን ችግኝ ተስማሚ ባልሆነ ቦታ የመትከል ችግር እየተከሰተ ነበር።ይህንን ለማስቀረት ቀድሞ የመሬት ልየታ ተካሂዷል። የታወቀ መሬት ባለቤት አበጅተንለት፤ ባህሪውንም ለይተን ማለትም ይህ መሬቱ የሚያዋጣው ለፍራፍሬ ነው ወይስ ለቀርከሃ? ለሚዘገይ ዛፍ ነው ወይስ በፍጥነት ለሚያድግ ዛፍ? ለየትኛው ይመቻል? የትኛው ዝርያ የቱ ጋር ቢሆን ግብርናውን ይደግፋል? የተፈጥሮ ሀብቱን እና የውሃ ሀብት ልማቱን የኢነርጂ አቅርቦቱን ይደግፋል? የሚለውን ለማወቅ እና ከልማቱ ጋር የተዛመደ ሊሆን የሚችለው ቀድመን መሬታችንን ስንለይ ነው በማለት በጣም በስፋት በመሔድ በድምሩ በሀገር ደረጃ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ ተለይቷል።

ይህ መሬት የተፈላውን ችግኝ ሊይዝ የሚችል ነው። በእርግጥ የክልሎች ችግኝ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዳንዶቹን ችግኞች ቢያድሩ ብለን ይዘናል። ምክንያቱም ለዘንድሮ መርሀ ግብር ለአቅመ ተከላ ያልደረሱት ቢከርሙ እና ለከዱ ችግኞች መተኪያ ይሆናሉ በሚል ነው። ከተለየው 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ ደግሞ 700ሺህ ሔክታሩን ካርታ ለማዘጋጀት ማለትም ለመሬቱ ባለቤት የማበጀት (የጂኦ ሪፈረንሲንግ) ሥራ ለማከናወን እቅድ ተይዞ በስፋት ሲሰራ ነበር። የተከላ ቦታ የጂኦግራፊያዊ ልኬት የመሥራት ሥራ በየዓመቱ በጣም በከፍተኛ ተግዳሮት የተከናወነ ነበር። ነገር ግን በጣም ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ሆኗል።

መሬት ሊለይ ይችላል። ለምሳሌ፣ በአንድ ቀበሌ ውስጥ በዚህ ተፋሰስ ላይ ይህን ያህል መሬት ለአፍር እና ውሃ ጥበቃም ሆነ ለተፋሰስ ሥራ ለችግኝ መትከያ በአጠቃላይ ለአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ይህን የሚያህል መሬት አለ ተብሎ ሊለይ ይችላል። ያ የተለየ ቦታ ግን ካርታ ካልተዘጋጀለት እና ፌዴራል ላይ በማዕከል ደረጃ እዚህ ክልል ውስጥ፣ እዚህ ቀበሌ፣ እዚህ ተፋሰስ ውስጥ ይህን የሚያህል ሔክታር ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር መተግበሪያ መሬት አለኝ ማለት ካልተቻለ በስተቀር ሥራውን አስቸጋሪ ያደርገዋል። በተለይ የተጠያቂነት ጉዳይ ማንሳት አዳጋች ነው። አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሔ ጥያቄ በጣም እየጠበቀ መጥቷል።

አረንጓዴ አሻራን የምንሠራው መጀመሪያ ለራሳችን ነው። ነገር ግን ደግሞ የምንሠራው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ነው። ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንዲት ሀገር ዛፍ ተክያለሁ ስትል ከብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እና ከበረሃማነት መስፋፋት ጋራ ይያያዛል። በተጨማሪ እንደአንዲት ጥንታዊ ሀገር እና አካባቢዋም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆነች ሀገር አንፃር ለዓለም ቃል የገባናቸው በርካታ ውሎች አሉ። ለምሳሌ 22 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዲያገግም እናደርጋለን ብለን ቃል ገብተናል። ይህ ቃል የተደገፈ እና በሌሎች ሀገሮች የሚታወቅ ነው። ስለዚህ አንድ ጊዜ ለዓለም የተገባ ቃል የሚያስከስስ ባይሆንም የሚያስወቅስ ውል ነው። የሚያመጣው የራሱ ጉዳት አለው።

ችግኞችን በመትከል እና የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን፤ ነባር ደኖች እንዲያገግሙ በማድረግ ይህንን ሥራ እንሠራለን። መጀመሪያ የራሳችንን አርሶ አደር እና የከተማ ነዋሪ የአየር ንብረት ለውጥ ያለውን ተጋላጭነት እንቀንስለታለን፤ በሀገራችን ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ እንዲሁም ኢኮኖሚውን እንዲደግፍ እናደርግበታለን። እግረ መንገዳችንን ዓለም አቀፍ ኃላፊነታችንን እንወጣበታለን።

የዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ እንዲቀየር፣ የዓለም ብዝሃ ሕይወት እንዲጠፋ እና እንዲመናመን መሬት እንድትጎሳቆል እና በረሃማነት እንዲስፋፋ የኢትዮጵያ እጅም የእኛም አስተዋፅኦ አለበት። ‹‹ዓማቂ ጋዝ የመልቀቅ መጠናችን ትንሽ ነው፤›› እንላለን። በእርግጥ እርሱ እውነት ነው። ግን ደግሞ ትንሽ የሆነው ከሌሎቹ ትልልቅ በካይ ጭስ ለቃቂ ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር ነው። ከእነ አሜሪካ፣ ከእነቻይና እና ከእነሕንድ ጋር ሲነፃፀር እንጂ፤ በተነፃፃሪነት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ከታየ የእኛም ትንሽ አይደለም።

አሁን የአረንጓዴ ልማትን ተወት ካደረግነው የዓለም ቅርስ የሆነውን ብዝሃ ሕይወት እንጎዳለን። የባሌ ደን የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። የኮንጎ ደን የኮንጎ ሕዝብ እና መንግሥት ብቻ አይደለም። አማዞን ላቲን አሜሪካ ቢሆንም የሌሎች ሀገሮች መኖር የእርሱ መኖር አስፈላጊ ነው። ሳይንሱ የዓለምን የኢኮሎጂ ትሥሥር ይበልጥ እያወጣው ነው። የኢትዮጵያ የክረምት ወቅት ዝናባችን ከኮንጎ ደን ጋር የተያያዘ ነው።

ምዕራብ ላይ ያለው የኮንጎ ደን ባይኖር ኢትዮጵያ በክረምት ይህን ያህል ዝናብ ላታገኝ የምትችልበት ዕድል እንዳለ በርካታ ጥናቶች አሳይተዋል። ስለዚህ የኮንጎ መንግሥት ያንን ደን እንዲጠብቀው እና በዘላቂነት እንዲይዘው የኢትዮጵያ መንግሥት ይጠይቃል። ጥያቄው ሉዓላዊነትን በጠበቀ እና የጋራ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ መልኩ ነው። በዲፕሎማሲዊ መንገድ እናንተም ለእኛ ጠብቁልን እኛም ይህንን እየሠራን እንላለን።

እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት እንዳይጎሳቆል ሌሎች ሀገሮችም ይፈልጋሉ፤ የእኛን ሥራ ይጠብቃሉ። በተለይ ከእኛ ተፋሰስ የሚሄድላቸው የታችኛዎቹ ሀገሮች አባይ ብቻ ሳይሆን ባሮ እና አኮቦ የሚሄድላቸው፤ እነመረብ እና እነሸበሌን የሚቀበሉ ሀገሮችን ካየን ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚደርስላትን ጅቡቲን ከተመለከትን ብዙ ኃላፊነት አለብን። ምክንያቱም ይሔ ውሃ ትናንት እየፈሰሰ እንደነበረው ዛሬም ነገም መቀጠል አለበት። ያ የሚሆነው ደግሞ የኢትዮጵያ ከፍተኛ አካባቢዎች ላይ በቂ ዝናብ ሲዘንብ ነው። ይሄ የሚሆነው ደግሞ ተፋሰሱ ሲጠበቅ ነው።

ተፋሰሱ በረሃ እየሆነ እየተጎሳቆለ የሚመጣ ከሆነ አንደኛ በቂ ዝናብ ኢትዮጵያ ውስጥ አይመጣም። ይህንኑ እያየን ነው። በአንድ ወቅት ዝናብ ይዘንብባቸው የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ ዝናብ የለም፤ ትናንት ለምለም የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ ደርቀዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህንን ሥራ የመሥራት፣ ደኗን የመጠበቅ የተጎዱ ደኖች እንዲያገግሙ የማድረግ ተጨማሪ ደን የመፍጠር የተጎዱ አካባቢዎችን ወደ አረንጓዴነት እንዲመለሱ የማድረግ እና አጠቃቀሙን እንዲሁም የሥርዓት ምህዳር አገልግሎቱ ቋሚ እና የሚገመት እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋታል። ይህ መጀመሪያ ለራሳችን ብለን የምንሰራው ሲሆን፤ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የእኛ ባለብዙ ደን መሆን ከእኛ አልፎ ለጎረቤት ሀገሮችም የሚጠቅም መሆኑም መታወቅ አለበት።

አዲስ ዘመን፡-የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራው በእርግጥ በዓለም ምን ያህል እውቅና አለው?

ዶ/ር አደፍርስ፡- በእርግጥ ሥራውን ሠራን ብቻ ብለን መናገራችን በቂ አይሆንም። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ ይህን ሥራ ከሰራችሁ እንየው ብለው ይጠይቃሉ። የዘመኑ ቴክኖሎጂ አውሮፓ ቁጭ ብሎ የተቆፈሩ የችግኝ ጉድጓዶችን መቁጠር ያስችላል። ይህ የተዓማኒነት ጉዳይ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገሮች ላይም ይነሳል። እውነት ነው ብለን እንድንደጋገፍ የቱ ጋር ነው የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ይኸው ኦሮሚያ ውስጥ ወይም አፋር ውስጥ እዚህ ተፋሰስ መሬት ላይ፤ በዚህ ያህል ሄክታር ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ሠርተናል ብለን ማሳየት ይጠበቅብናል። ይህንን ማድረጋችን ማለትም የጂኦ ሪፈረንሲንግ ሥራ ሌሎች ሀገሮች እንዲያምኑን ብቻ ሳይሆን ነገ ወደ ገንዘብ እንድንቀይረው ቢባል እንኳ ለይቶ ማወቅ ያስፈልገናል።

ከአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ሥራችን ነገ ማህበረሰባችንን ከካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ ለማድረግ እንፈልጋለን፤ ይህ ደግሞ በትንሹ ውጤት ሲያመጣ የታየ ነው። ነገ ደግሞ ይንን አስፍተን ሀገር ደን በመጠበቅ አፈሯን በማልማት ግብርናዋን፣ የውሃ አቅርቦቷ እና የኢነርጂ አቅርቦቷን በመጨመር የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከፍ ታደርግበታለች እንደምንለው ሁሉ፤ ሌላ ተጨማሪ ምንጭ እንዲሆን እንፈልጋለን።

ከዓየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ ከካርበን ሽያጩ ገቢ ይገኛል። እርሱ ደግሞ መጀመሪያ የሚፈልጉት የቱ ጋር ምን ተደረገ? የሚለውን ነው። እኛ ደግሞ መልሳችን ኮኦርድኔታቸውን ለይተን እዚህ ቦታ ላይ ነው፤ ካርታው ይኸውና ባለቤቶቹ እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱ ጋር የለማ ይህን ያህል መሬት አለ። እዛ ላይ የተሠራው ሥራ ይሔ ነው። ከዚህ በፊት ካርበኑ ይህን ያህል ነበር፤ ይህ ሥራ ከተሠራ በኋላ በባለፉት አራት አምስት ዓመታት እና ወደ ፊት በምንሠራቸው ሥራዎች ደግሞ የካርበን ክምችት መጠን እዚህ ደርሷል ብለን ያንን በመረጃ ማቅረብ እስከ ቻልን ድረስ መሸጥ እንችላለን። በዚህም ተጨማሪ የካርበን ፋይናንስ ለሀገራችን የምናገኝበት ዕድል ይኖራል።

ስለዚህ የጂኦ ሪፈረንሲንግ ሥራ ከክልሎች ጋር በጣም በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ እና የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንድንሰራ ስንጥር ቆይተናል። አሁን ጥሩ እየተሠራ መጥቷል። እኛ የተለየው መሬት በሙሉ ጂኦ ሪፈረንሲንግ እንዲሆን እንፈልጋለን። አሁን 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታር ተለይቷል። ለምን የመንገድ ዳር ተከላ የሚካሄድበት መሬት አትሆንም? መገኛዋ ታውቆ ነጥብ ኖሯት ለምሳሌ የወልቂጤ ከተማ ውስጥ መንገድ አካፋይ ላይ መገኛቸው ይሔ ነው፤ ይህን ያህል ችግኝ በዚህን ያክል መሬት ላይ ተተክሏል። የተተከለበት ምክንያት መንገድ ለማካፈል ነው። የተተከሉት የችግኝ አይነቶች ደግሞ እንደዚህ የሚባሉ እና ዝርያቸውም ይሔ ነው። የሚተዳደሩት በዚህ መልክ ነው። ተብሎ እንዲመጣልን እንፈልጋለን።

ሁሉም የተለየ የተከላ መሬት ላይ ጂኦሪፈረንሲንግ እንዲሠራ እንፈልጋለን። በዛ መጠን ግን እየተሠራ አይደለም። ምክንያቱም ዓቅም የሚፈልግ ነው። የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋል። ጂፒኤስ ይፈልጋል፤ በተጨማሪ መረጃውን ለመሰብሰብ ሰዎች መሠልጠን ይኖርባቸዋል። መሻሻል ይፈልጋል፤ ስለዚህ አጠናክረን መሔድ ብንፈልግም ቀሪ ሥራዎች አሉ። በአጠቃላይ አሁን መሬት ተለይቷል። የተለየው መሬት ደግሞ ጂኦሪፈረንሲንግ ተሠርቶለታል። 115 ሺ የችግኝ ጣቢዎች ላይ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል።

አዲስ ዘመን፡- የሚተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዲኖራቸው አቅዶ ከመስራት አኳያስ የዘንድሮው ዝግጅት ምን ይመስላል?

ዶ/ር አደፍርስ፡- ከዚህ በፊት ከነበረው አንፃር የችግኞቹ ዝርያዎች ዓይነት የተለያየ ነው። የፍራፍሬ ችግኝ ቁጥሩ ከፍ እያለ እንዲመጣ በየዓመቱ እየተሠራ ነው። ከክልሎች ጋር በተደረገው ርብርብ ቀርከሃ መጠኑ በጣም ከፍ እንዲል ሠርተናል። የማስጀመሪያ ቀኑ እየደረሰ ሲመጣ በዓይነት እየለየን ቁጥራቸውን እንናገራለን። የመኖ ዝርያዎችንም በማስፋት እንደዚሁ የችግኙ ቁጥር ከፍ እንዲል እያደረግን ነው።

ይሄንኑም ለክልሎች ይበልጥ የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራን ሲሆን፤ ክልሎች ደግሞ ማህበረሰቡን ወጣቱን በወጣት ሴቱን በሴት፤ ገበሬውን በገበሬ፤ አርብቶ አደሩን በአርብቶ አደር፤ የከተማ ነዋሪውን በከተማ ነዋሪ፤ የመንግሥት ሠራተኛውን በመንግሥት ሠራተኛ እያደራጁ በተለይም ወጣቶች ይበልጥ ኃላፊነቱን ወስደው በየቀበሌው እያንዳንዱ ተፋሰስ ድረስ ያሉ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው።

ይህ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝን ባልተደራጀ እና ባልተቀናጀ መንገድ መትከል አይቻልም። በሌሎች ሀገሮች ያለው እንቅስቃሴ ሲታይ አስር እና አስራ አምስት ሀገሮች ተቀናጅተው የማይተክሉት ነው። ለዛ ነው፤ አሁን አሁን አንዳንድ ሀገራትም ተቀብለው የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ላይ ትልቁን የመሬት ማገገም ሥራ እየሠራ ነው ብለው እነርሱም እውቅና እየሠጡ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ሀገራት ቀድሞም የደን ሽፋናቸው 30 በመቶ የሆኑ ሀገሮች በዚህ መጠን ችግኝ እንዲያፈሉ አይጠበቅም። ነገር ግን ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ተከላ እያካሔድን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሚዘጋጁ ችግኞች ቁጥር እና የማድረግ አቅምን አጣጥሞ ከመስራት አኳያ ያለው ጉዳይስ በምን መልኩ የሚገለጽ ነው?

ዶ/ር አደፍርስ፡- አዎ ቁጥሩን በማሰብ በምን አቅማችን ልንተክል ነው? የሚሉ ሰዎች አሉ። ተቋሞቻችን በዚህ መጠን አልጠነከሩም፤ በቂ ፋይናንስ ማግኘት አይቻልም የሚሉ በርካታ ኢትዮጵያኖች አሉ። ሌሎችም በርከት ያሉ ከጎረቤት ሀገሮች የሚመጡ ጥያቄዎች አሉ። የሀገር አመራሩ፣ ዓብይ ኮሚቴውም ሆነ የቴክኒክ ኮሚቴው ሁላችንም በተለያየ ጊዜ ስናነሳ የነበረው ዋናው ጉዳይ በትንንሽ የመትከል ሥራ ትልቅ ውጤት ማምጣት አይቻልም የሚል ነው።

ኢትዮጵያ ለሰባት ሺህ እና ከዛ በላይ ለሆኑ ዓመታት የታረሰች ሀገር ናት። በተለይ ማዕከላዊው እና ሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተጎድቷል። ደህና ነው ብዙ አልተጋጋጠም የምንለው የሀገሪቱ ክፍልም እንዲዚሁ ደቡቡ እና ደቡብ ምዕራብ በተለይ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በጣም በፍጥነት መሬቱ እየተጎሳቆለ ደን እየጠፋ ብዝሃ ሕይወት እየተጎሳቆለ ነው። አፈሩ እየደኸየ ነው። በዚህ በደኸየ አፈር ላይ ደግሞ በዚሁ መጠን የሕዝቡ ቁጥር እየጨመረ ነው። አጨማመሩ በጣም ፍጥነት ያለበት ነው።

የሰው ቁጥር ሲጨምር ኢንዱስትሪው አድጎ ወጣቱን ወደ ሥራ የማይወስድልን ከሆነ (እንደምናየው በሕዝቡ መጠን ኢንዱስትሪው እያደገ አይደለም፡)፤ ብዙ ወጣት መሬት ላይ ሥራ መሥራት አለበት። በዛው በተወለደበት ቀዬ ምርትና ምርታማነቱ ከፍ ብሎ ሳይሰደድ ትምህርቱን እየተማረ መቆየት አለበት። ኢንዱስትሪ እና ከተማው ሲያድግ አዲስ አበባ መጥቶ ጎዳና ላይ አይቆምም። ጉልበቱ እና ጤናው እንዳይጎዳበት የሚያቀው ተፋሰስ ውስጥ እና የሚያውቀው ቀበሌ ላይ መቆየት መቻል አለበት።

ይሔ እንዲሆን ደግሞ ወጣቱ የሚሠራው ሥራ መኖር አለበት። አብዛኛው ሊሠራ የሚችለው መሬት ላይ ነው። ግብርና ፣ የእንስሳት እርባታ፣ የደን ልማት ሊሠራ ይችላል። ነገር ግን ለእነዚህ ሥራዎች መሰረቱ መሬት ነው። እኛ ሀገር መሰረቱ ተጎድቷል። አፈሩ ተጎድቷል፤ ውሃው ተጎድቷል፤ ዝናቡ ተዛብቷል፤ እርሱን መልሰን ማስተካከል ይኖርብናል። ይሔንን ለማድረግ አፈራችንን እና መሬታችንን ውሃችንን ለማከም አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ውስጡ ብዙ ቢሆንም መሳቢያው እና ማዕከሉ ችግኝ ተከላ ነው።

ይሁን እንጂ ችግኝ ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ መሆኑ መታወቅ አለበት። አፈር እና ውሃ ይጠብቃል። የወጣቱን አቅም ይጠብቃል። ሴቶችን ያግዛል። ሴቶች ከትምህርት ቤት መጥተው ብዙ ሩቅ ሳይሔዱ እዛው ቅርባቸው ውሃ እንዲያገኙ ያመቻቻል። የሥራ ዕድልም ይኖራል። ስለዚህ የሚዘጋጀው ችግኝ እና ያንን የመትከል ድርጊት አቅም የሚመጣው በዚህ ሁሉ አስፈላጊነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሥራውን ከችግኝ ማዘጋጀት ጀምሮ ከሥራ ዕድል አኳያ ምን ያህል ማየት እንችላለን?

ዶ/ር አደፍርስ፡- የችግኝ ማፊያዎች አንዳንዶቹ ትንንሾች ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ መካከለኛ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ትልልቆች ናቸው። በእያንዳንዳቸው ችግኝ ጣቢያ ሥራውን የሚያከናውኑ ሰዎች አሉ። በእያንዳንዱ ችግኝ ጣቢያ በትንሹ አስር ሰው ይቀጠራል ብለን ብናሰላው በተለይ ትልልቆቹ የችግኝ ጣቢዎች እስከ 500 ሰው ይቀጥራሉ። በተለይ ወደ ቀበሌ ወረድ ብለን ምንም ዓይነት የሥራ ዕድል በሌለባቸው አካባቢዎች እንደቀላል የሚታይ አይደለም።

አረንጓዴ አሻራ ይህንን እያደረገ ነገር ግን አለፍ ብሎ ትልቁ ነገር የግብርና ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ የሩቅ ጊዜ ሳይሆን አሁኑኑ በአረንጓዴ አሻራ የምርትና ምርታማነት መጨመር አንድ ማዕከላዊ መዳረሻችን ነው ብለን እየሠራን ነው። አረንጓዴ ልማቱ በቂ ዝናብ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘንቦ በእያንዳንዱ ወንዞቻችን፣ ኩሬዎቻችን እና ግድቦቻችን ውስጥ በቂ ውሃ ኖሮ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማቅረብም ሆነ፤ ከውሃ በቂ የኃይል ምንጭ ማግኘት የሩቅ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ነው ብሎ አስቀምጧል።

አረንጓዴ አሻራ እዚህ መሬት ላይ የሚሠራው ሥራ ከዛም ተርፎ ጎኑ ላይ ያሉ መክፈቻዎችንም በመጫን ሞተሩን ለማስነሳት ነው። ሀገሪቷ ያላት የተፈጥሮ ሀብት በአረንጓዴ አሻራ የበለጠ በማጉላት ኢኮኖሚውን ማሳደግ ነው። ኢኮኖሚን በማሳደግ ሂደት የተፈጥሮ ሀብትን ማጥፋት አያዋጣም። የተፈጥሮ ሀብቱ ለምንፈልገው ዕድገት ግብዓት እየሆነ እንዲሁም የሚያድገው ኢንዱስትሪ እና ኢኮኖሚ ከሚያገኘው ላይ መልሶ መሬት ላይ ኢንቨስት በማድረግ ዘላቂ የሆነ የዕድገት ሽክርክሪት ውስጥ እንድንገባ ነው። ካለንበት የድህነት አዙሪትም በአስቸኳይ እንድንወጣም ጭምር አልሞ የሚሠራ ነው። ስለዚህ አረንጓዴ አሻራን ከፍ አድርገን ካየነው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ቲዎሪ ብሎ መውሰድ ይቻላል። ስለዚህ ማህበረሰቡ ችግኝ ሲተክል ይህንን እሳቤ ይዞ ሊሆን ይገባል።

ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች ናቸው ። ነገ ግን ዛፍ፣ ፍራፍሬ፣ ኢንዱስትሪ ወይም ዝናብ ናቸው። ብለን ማመን አለብን። ነገ ዘላቂ ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት፤ ሕዝቦቿ እርስ በራሳቸው የሚከባበሩባት እና የሚዋደዱባት፤ የተረጋጋች ሀገር የምትሆነው ዛሬ በሠራነው ነው። በአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ እርስ በእርስ በመሬት የማይጣሉባት እና የማይገፋፉባት ሀገር ማድረግ እንችላለን ብለን ተነስተናል። አረንጓዴ አሻራ ለኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለሰላም ግንባታም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ምክንያቱም የሕዝቡ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ በተለይ በገጠር የደኸየ መሬት የያዘ ሰው ቤተሰቡን መመገብ አይችልም። በዚህ ጊዜ የመሬት ሽሚያ ይፈጠራል። በኋላም ይሔ መሬት ታሪካዊ ሥሪቱ የኔ ነበር ወደሚል ቅሬታ ይደረሳል። ማህበረሰባችንን እያጋጨ ያለው አንዱ የመሬት ማነስ ብቻ ሳይሆን የመሬት መደህየትም ጭምር ነው።

ስለዚህ መሬት እየደኸየ፣ ከብቶች አብረው ውሃ የሚጠጡበት ቦታ እየደረቀ ሲመጣ፤ የእኔ ከብት ቀድሞ ይጠጣ፤ የአንተ ከብቶች ብዙ ናቸው ቀንሳቸው የሚል ጥል ይነሳል። በኋላም ጉዳዩ የሕልውና ጉዳይ ሆኖ ግጭት ያስከትላል። ስለዚህ ይህ ችግር እንዳይፈጠር በአረንጓዴ አሻራ ደናችንን ብናክም እና የአፈር ለምነቱን ብናሻሽል እንዲሁም ሥራ ብንፈጥር በአጠቃላይ የሥነምህዳር አገልግሎቱን ብናሻሽል ዛሬ እንኳን ባይሆን ነገ ወደ መቻቻል እና ወደ መከባበር እንሔዳለን። አሁንም ይህ እየታየ ነው።

የአንዱ ክልል አመራር ሌላ ክልል ሔዶ እየተከለ ነው። መልዕክትም እያስተላለፉ ነው። ይህ ክልሎችን ከክልሎች ጋር የሚገናኙበት እና የሚግባቡበት ነው። ይህ ቀላል አይደለም፤ ችግሩ መገናኛ ብዙኃኑ ይህንን ሃሳብ አያቀርበውም እንጂ አረንጓዴ አሻራ እያደረገ ያለው በጣም ብዙ ነው። እንደውም ባለፉት ዓመታት ግጭቶች ቢኖሩም አረንጓዴ አሻራ ባይሠራ ኖሮ ኢትዮጵያ ስሟ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ያዳግታል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በጦርነት እየታመሰች ነው ይሉና በተቃራኒው በአረንጓዴ አሻራ እየተሠራ ያለውን ሲያዩ መለስ ይላሉ። በትልልቅ የዓለም መድረኮችም ይዘን እየቀረብን ያለነው የአረንጓዴ አሻራ ነው። ስለዚህ በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ ለኢትዮጵያ እንደቀላል የሚታይ አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

ዶ/ር አደፍርስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You