‹‹አፕሳይክል ፋሽን›› – የወደፊት የፋሽን ኢንዱስትሪው ገጽታ

ሜቲ ኃይለማርያም ትባላለች፤ ዲዛይነር ናት። ‹‹ሜቲ አፕሳይክሊንግ›› የተሰኘ የራሷ ብራንድ አላት። ዲዛይነር ሜቲ ከተራረፉ ጨርቆች እና ፋሽናቸው አልፎባቸዋል ከተባሉ ሳይሸጡ ከቀሩ ልብሶች ጨርቆችን ወስዳ የራሷን ዲዛይን በመፍጠር አልባሳትን አዘጋጅታ ለደንበኞቿ ታቀርባለች።

የልብስ ዲዛይን ሥራ አንድን ጨርቅ ቀዶ ወደ አንድ ወጥ ልብስ ከመቀየር ያለፈ ነው ትላለች። ዲዛይነር መሆንን ከልጅነቷ ጀምሮ ትመኝ የነበረችው ሜቲ፣ ከልጅነቷ ጀምሮ ለሙያው ፍቅሩ እንዳላትና የተለያዩ ዲዛይኖችንም ትስል እንደነበርም ታስታውሳለች። ይሁንና የቤተሰቦቿ ፍላጎት የሆነውን የቀለም ትምህርት እንድትከታተል መደረጓን ትገልጻለች።

ሜቲ የ12ተኛ ክፍል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ግን ለስዕል የነበራት ፍቅር ጭምር ታሳቢ አድርጋ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአርክቴክት የትምህርት ዘርፍ ተከታትላለች። በዚህ ሙያዋም ሁለት አመት ከሰራችበት በኋላ ሁለተኛ ዲግሪዋንም እንዲሁ‹‹ በከተማ ዲዛይን ›› ተከታትላለች።

በእነዚህ የትምህርት ጊዜያት ግን የምትወደውን የዲዛይን ሙያ አልረሳችውም። የመጀመሪያ ዲግሪዋን እንዳጠናቀቀች ስሙን ለመጥቀስ የማትፈልገው አንድ የዲዛይን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እውቀቷን ለማሳደግ ብትገባም፣ እንደምትፈልገው በቂ እውቀት አላገኘችበትም። ስለዚህ ሌላ የተሻለ ትምህርት ቤት መፈለግ ነበረባት። የዲዛይን ትምህርትን ለአንድ አመት ያህል አሰልጥኖ የሚያስመርቀውን ትምህርት ቤት ምርጫዋ አድርጋ ስልጠናውን ወሰደች።

ይህን የዲዛይን ትምህርቷን የተከታተለችው ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር ሆና ነበር፤ ትምህርቱንም አብረዋት ሲማሩ ከነበሩ 75 ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች። በትምህርት ቤቱ የቀሰመችው እውቀትም የዲዛይን ሙያዋን አሳድጋ ስራዋን በተሻለ መልኩ እንድትጀምር እንዳስቻላት ትናገራለች። ስራውን ለመስራት የአንድ አመት ትምህርት በቂ እንዳልሆነ ተናግራ፣ ፍላጎት ካለ በጥረት ራሳችንን ማሳደግ እንችላለን ስትል ትገልጸለች።

‹‹የዲዛይን ትምህርቱን ከጨረስኩ በኋላ የራሴን ሱቅ ከፍቼ ለመስራት ሙከራ አድርጌያለሁ›› የምትለው ሜቲ፣ እንደ ሌሎች ዲዛይነሮች የተሻለ ገቢ ያስገኝልኛል ያለችውን የሀበሻ ልብስ ዲዛይን መስራት ጀምራም እንደነበር ታስረዳለች።

‹‹አንድ ስራ ያበላል ስለተባለ ብቻ መስራት በስራዬ ደስተኛ እንድሆን አላደረገኝም ›› ስትል ገልጻ፣ አንድን ስራ ገንዘብ ስለሚያስገኝና ሌላው ሰው ስለሰራው ብቻ መስራቱ ብዙም አያስደስታትም። በሙያዋ የራሷ የምትለው የምታበረክተው አስተዋጽኦ እንዲኖራት ትፈልግም ነበር።

ለእዚህም ስትል የአርክቴክት ስራዋን ትታ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲዛይን ትገባለች። ለእዚህም ስለ ብራንዲንግ እና የተለየ ሀሳብ ስለማምጣት የወሰደቻችው ስልጠናዎች ጥሩ እይታ ፈጥረውላታል። ‹‹የወሰድኩት ስልጠና ምን ልስራ የሚለውን የውስጤን ጥያቄ ለመመለስ አግዞኛል›› ብላለች።

የተራረፉ ጨርቆችን፣ ጊዜያቸው አልፎባቸዋል የተባሉ ፋሽኖችን እና ሳይሸጡ የቀሩ ልብሶችን ወደ አዲስ ፣ ውብ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊለበሱ ወደሚችሉ አልባሳት መቀየር ሜቲ ራሷን የምትገልጽበት መጠሪያዋ ሆኖ አግኝታዋለች ።

ወደ እዚህ ሀሳብ እንድታመራ የገፋት የራሷ የህይወት አጋጣሚ ወይንም መንገድ አላት። አስቀድማ ትመራው የነበረው ትዳር መፍረስ የዚህ አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቁማለች። በማህበረሰባችን ውስጥ አንዲት ከትዳሯ የተለየች ሴት ዋጋ እንደሌላት፣ እንደተሳሳተች እና እንደ ጥፋተኛ ተደርጋ የምትቆጠርበት ሁኔታ አለ›› ስትል ገልጻ፣ ህይወቱን የተሻለ ማድረግ የግለሰቡ ኃላፊነት መሆኑንና የተሻለ ህይወት መፍጠር እንደሚቻልም ትናግራለች።

እሷ እንዳለችው፤ የአፕሳይክሊንግ የተጣሉ ጨርቆችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሀሳብ አያስፈልጉም በተባሉ ጨርቆች እንዲሁም ተፈላጊነት የላቸውም በተባሉ ልብሶች ላይ እንደገና ህይወት በመዝራት እና አዲስ ስታይል በመፍጠር ለገበያው ተወደው እንዲቀርቡ ማድረግ ላይ ይሰራል።

በፋሽን ኢንዱስትሪው የተቆራረጡ ጨርቆችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ጽንሰ ሀሳብ በዓለም ላይ እየተዋወቀ እና ትኩረት የተሰጠው ነው ። ይህም ሰርኩላር ኢኮኖሚ በመባል ይታወቃል። ይህም ውጋጅ ጨርቆችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ወደ መሬት የሚጣሉ ተረፈ ምርቶችን አልያም ከጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ውጋጆችን መቀነስ አልያም መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል በዓለም ላይ በእጅጉ እየተስፋፋ ያለ ሀሳብ ነው።

ይህ አሰራር ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣውን ጭስ፣ ውጋጅ ኬሚካሎችን በመቀነስ አካባቢን፣ አየርን የሚበክሉበት መጠን እንዲቀነስ ማድረግ ያስችላል። አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት ኢንዱስትሪው የሚጠይቀውን ጥሬ እቃ እና ግብዓት ላይ ያለው ፍላጎት እንዲቀንስም ይረዳል።

ከተለያዩ ጨርቆች ድጋሚ ለተሰሩ ልብሶች የእኛ ማህበረሰብ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ነው የምትለው ሜቲ፣ በኑሮ ውስጥ ግን ሀሳቡ አዲስ እንዳልሆነ ትናገራለች። ‹‹በኑሯችን ልብሶች ሲያጥሩን ለታናናሾቻችን በመስጠት ቤት ውስጥ በመጠገን አልያም ለሌላ አገልግሎት በማዋል እንጠቀምባቸዋለን። ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው ሲመጣ ግን እንደ ፋሽን የመቀበል አስተሳሰባችን ያን ያህል አይደለም›› የምትለው ሜቲ፣ እንደ ሀገርም ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ጠቀሜታ ለመረዳት ብዙ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል።›› ስትል ትገልጻለች።

‹‹አሁን ላይ ሰዎች ያላቸውን አመለካከት ለመቀየር ከተረፈ ጨርቃጨርቆች ሌሎች አልባሳት ቢሰሩም፣ ጨርቆቹን ከሌሎች ጨርቆች ጋር በመደባለቅ ውበት እንዲኖራቸው በማድረግ ሰዎች ያላቸውን አመለካከት መቀየር ያስፈልጋል›› ትላለች።

ሜቲ ‹‹ሀብ ኦፍ አፍሪካ›› በተሰኘ የፋሽን ትርኢት ላይ የራሷ ዲዛይን ያረፈበትን የአፕሳይክሊንግ ዲዛይን ይዛ መቅረቧንም ጠቅሳ፤ እሱም ከፋብሪካዎች የወጡ ጅንስ ጨርቆችን ከሀበሻ ጨርቆች ጋር በመደባለቅ ይዛ የቀረበችው ዲዛይን መሆኑን አብራርታለች።

‹‹ሜቲ አፕሳይክሊንግ ፋሽን›› ጨርቆችን መልሶ የመጠቀም ሀሳቧ አድጎ ብራንዷ ሆኖ እንዲታወቅ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሯን ወክላ በፋሽን ትርኢቶች ላይ የማቅረብ ሀሳብም አላት። የሀበሻ ልብስ ብራንድ በመስራት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ጠቅሳ፣ በዲዛይን ትምህርት ቤቶች የዲዛይን ትምህርት ትሰጣለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You