ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሯ በየአመቱ ብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል መታወቅ ችላለች። በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄም 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ለእዚህም እስካሁን የተዘጋጀው ችግኝ ለመትከል ከታቀደው በላይ እንደሆነ የሚኒስቴሩ መረጃ ጠቁሟል። ይህም የችግኝ ተከላውን ከእቅዱ በላይ ለመፈጸም ያግዛል ተብሎ ይታመናል።
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ፤ ለዘንድሮው ችግኝ ተከላ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል፤ ችግኞቹን ለመትከል የሚያስችለው የቦታ ዝግጅትም እየተደረገ ነው። ችግኞቹን በአንድ ነጥብ ሚሊዮን ሄክታር ላይ ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም ወደ 900 ሺ የሚሆነው ሄክታር መሬት ዝግጁ ሆኗል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ንቅናቄው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚቻልበት አማራጭ ላይም ትኩረት ተደርጓል። በዚህ ረገድም ዘንድሮ ሊተከል ከታሰበው 60 በመቶ የሚሆነው ችግኝ ፍራፍሬና መኖ እንደሆነም ነው ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለከተው። ይህም አርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበን አማራጭና ገበያን ማረጋጋት የሚቻልበትን ሁኔታም ይፈጥራል። በአብዛኛው የፍራፍሬ ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፤ የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ለማድረግ ፤ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማስገኘትና ወደ ውጭ ለመላክም ጭምር ከፍተኛ ጥቅም አለው።
ግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ እንደሀገር በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እስከአሁን በተሠራው የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ በአብዛኛው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ፍራፍሬዎች ላይ ትኩረት የተደረገ ሲሆን፣ በዚህ በተከናወነው ተግባርም ሀገሪቱ በአቦካዶ ምርት በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን መያዝ አስችሏታል። በሌሎችም ፍራፍሬዎች ተመሳሳይ ውጤት ለማምጣት እንደ ሀገር እየተሠራ ነው።
በተለይም ነሃሴ ወር ላይ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር ተከላ ኢትዮጵያ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ እንድስትሰፍር ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችም ተጀምረዋል። በዚህ ረገድም ሁሉም ክልሎች መርሃግብሩን በንቅናቄ ደረጃና በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።
ከእነዚህም ክልሎች መካከል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድንም በክልሉ በመርሃግብሩ እየተተገበሩ ካሉ ሥፍራዎች መካከል በምስራቅ ጉራጌ ዞን በተለይም በቡታጀራ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ሥራ ቦታው ድረስ በመሄድ ቅኝት አድርጓል። የችግኝ ማባዣ ማኅበራትንና ማዕከላትን ሥራንም ተመልክቷል።
ወጣት ያሬድ ከበደ በቡታጀራ ከተማ የጥምረት የችግኝ ማባዣ ማህበር መስራች አባል ነው። ወጣቱ እንደሚናገረው፤ ማኅበሩ ከተመሠረተ አምስት ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ አምስት አባላትም አሉት። ማህበሩ በዋናነትም የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትን መሠረት ያደረጉ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ እንደ አቦካዶ ያሉ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን በስፋት በማባዛትና ለአርሶአደሩ በማሰራጨት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
‹‹ችግኝ የማባዛት ሥራውን ስንጀምር ካፒታላችን 10 ሺ ብር ነበር፤ የከተማ እስተዳደሩ በሰጠን ቦታ ላይ በተለይም አቦካዶ፣ ፓፓያ ቡና፣ እንሰት፣ የተለያዩ አበባዎችና ቅመማ ቅመሞች ችግኞች በስፋት በማበዛት በከተማውና በዙሪያው ላሉ አርሶአደሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች በማሰራጨት ለመርሃ ግብሩ መሳካት ርብርብ ስናደርግ ቆይተናል›› ይላል። በዞኑ ግብርና ቢሮ ድጋፍ የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው መሆኑንም ገልጾ፤ በዚህም ምክንያት ከሌላ ዞንና ክልል ጭምር የሚመጡ ደንበኞች ማፍራታቸውን ያስረዳል።
እንደ ወጣት ያሬድ ማብራሪያ፤ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በዓመት አቦካዶ ብቻ 50 ሺ ችግኝ በላይ ለገበያ ያቀርባል፤ ቡና ሶስት ሺ፣ ፓፓያ ሁለት ሺ ችግኞችን በማፍላት ለተጠቃሚዎች ያደርሳል። ማህበሩ እስካሁን 15 ለሚሆኑ ወጣቶች በቋሚነት እንዲሁም በጊዜያዊነት ደግሞ እስከ 40 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል። ካፒታሉንም አንድ ሚሊዮን ያደረሰ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ በሚያደርግለት ድጋፍም ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ መሳካት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። ሥራዎቹን በማስፋፋት ለበርካታ የከተማዋ ወጣቶች የሥራ እድል የመፍጠር ራዕይም አለው።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ የፍራፍሬ ማባዣና ሥልጠና ማዕከል ኃላፊ አቶ አመልጋ መንጂ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ሲመሠረት ሶስት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ ነው። የመጀመሪያው የተሻሻሉ የአቦካዶ ችግኞችን ለአርሶአደሮቹ የማሰራጨት ሥራ ሲሆን ፣ የተለያየ ዝርያ ያላቸውን አቦካዶ ችግኞች ማባዛትና ቴክኖሎጂውን ለአርሶአደሮች ተደራሽ ያደርጋል፤ ለባለሙያዎች ስልጠናም ይሰጣል። ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ የአባካዶ ምርትን ለውጭ ገበያ የማብቃት ዓላማ ይዞ ሥራ የጀመረ ሲሆን ፣ እነዚህን ሶስት ዓላማዎች በማሳካት አርሶአደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።
‹‹አቦካዶ በማዕድን የበለፀገ በመሆኑ አርሶአደሮችም ሆኑ ሌሎች ተጠቃሚዎች በምግብነት ቢጠቀሙበት ጉልበት ይሰጣል። በሁለተኛ ደረጃ ምርቱን ለወጭም፤ ለሀገር ውስጥ ገበያም በመሸጥ አርሶ አደሮች በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም በማግኘት ላይ ናቸው›› ይላሉ። ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ጥቅም እያስገኘ ያለ ተቋም መሆኑንም ያመለክታሉ። እስከአሁን ባለው ሁኔታ በወረዳው ጥምረት የአቦካዶ አምራቾች የህብረት ሥራ ማህበር አማካኝነት ምርቱን በማህበራቱ አማካኝነት ተሰብስቦ ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ አካላት የሚያስረክብበት ሁኔታ እንዳለም ያስረዳሉ።
ማህበሩ ምርቱን ለአውሮፓ ገበያ እንዲሁም መካከለኛና ሩቅ ምስራቅ ሀገራት እንደሚልክም ይገልጻሉ። በወረዳ ደረጃም እስከአሁን 30 ቶን የሚሆን አቦካዶ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ገበያ ደግሞ እስከ 50 ቶን አቦካዶ እንደሚያቀርብ ያነሳሉ። ‹‹ይህም ምርት የተገኘው ከአራት ዓመት በፊት ከተተከሉ የአቦካዶ ችግኞች ሲሆን፣ ከአራት ዓመት ወዲህ ደግሞ የአቦካዶ ልማቱ በየአመቱ በእጥፍ እያደገ መጥቷል። በዚያው ልክ በቀጣይ ዓመት ወደ ምርት የሚገባው የአቦካዶ ዛፍ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል›› ሲሉም ጠቁመዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በአካባቢው ያሉት አብዛኞቹ የህብረተሰብ ከፍሎች በቋሚ ሰብል ደረጃ የተለያዩ እንሰት ምርቶች ተመጋቢዎች ናቸው። በተለይ በደጋ አካባቢ ያሉት የእንሰት ውጤቶችን ነው ለእለት ምግብ ፍጆታቸው የሚጠቀሙት። ወደ ቆላማ አካባቢ የሚኖሩት ደግሞ በቆሎ ተመጋቢዎች ናቸው። በመሆኑም የአባካዶ ምርትን ከእንሰት፣ ከበቆሎና ከስንዴ ጋር አጣምሮ በመመገብ ተመጣጣኝ የሆነ ምግብ ማግኘት ይችላሉ፤ እያንዳንዱ ሰው የሚያገኘውንም የምግብ ይዘት ከፍ ያደርገዋል። በተለይ ለህፃናት እድገትና አዕምሮ መበልፀግ አባካዶ ፋይዳው የጎላ ነው።
በሌላ በኩልም አርሶ አደሮቹ ደግሞ ምርቱን ብቻ ሳይሆን ለብዜት የሚያገለግለውን ቅርንጫፍ ጭምር በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ። ‹‹በዚህ ረገድ እኛም በዓመት እስከ 500 ሺ ብር ከአርሶ አደሮቹ እንገዛለን። ለምዕራብ ጉራጌ ከፍል፤ ለሃዲያ፤ ከንባታ፣ ስልጢ ዞን ለሚያባዙ አካላት ፍሬ ሰጪ ቅርንጫፉን በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነናል›› ይላሉ። ለአብነትም በአመት በወረዳው ብቻ እስከ 300 ሺ ቅርንጫፍ በመሸጥ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ነው የጠቀሱት።
ማዕከሉ ሥልጠና መስጠት ዋነኛው ሥራ መሆኑን አስታውቀው፣ ‹‹ከዚህ ማእከል ሥልጠና ያገኙ ወጣቶችና አርሶአደሮች ችግኝ በማባዛት በዚህ ወረዳ ብቻ ወደ አምስት አርሶ አደሮችና ሁለት ማህበራት ተሳትፈው በዓመት እስከ 10 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝተዋል›› ብለዋል። እነዚህ ተቋማት ቢያንስ ከአስር በላይ ሠራተኞችን ያቀፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል። በዚህ ደግሞ ማዕከሉ እስከ 18 ሠራተኞችን ተጠቃሚ ማድረጉንና ከመንግሥት ምንም ሳይጠብቅ ራሱን በራሱ እየደጎመ የሚኖር ተቋም መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
አቶ ሰይፉ መንጌ የቡታጀራ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ ናቸው። ቡታጀራ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን በስኬት እየተገበሩ ካሉ የክልሉ ከተሞች መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። በዋናትም የፍራፍሬ ችግኞችን በማባዛትና በመትከል ረገድ ውጤታማ የሚባል ሥራ ከውናለች። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የከተማ አስተዳደሩ በራሱ አቅም ከሚያባዛውና ከሚያሰራጨው በተጨማሪ ለሌሎች ማህበራትና የችግኝ ማህበራት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ የእነወጣት ያሬድ ጥምረት ማህበረም ድጋፍ ከሚደረግላቸው መካከል ይጠቀሳል።
‹‹እንደከተማችን ከ 12 በላይ በተመሳሳይ ደረጃ ያሉ የችግኝ ማፊያ ጣቢየዎች አሉ›› የሚሉት አቶ ሰይፉ፣ ጣቢያዎቹ የፍራፍሬና የደን ችግኖችን በማፍላትና በማሰራጨት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ አኳያ የከተማ አስተዳደሩ ለእነዚህ ተቋማት ቦታ ከመስጠት ጀምሮ የገበያ ትስስር በመፍጠርና የቴክኒከክ ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ያብራራሉ። አብነት አድርገውም ጥምረት የችግኝ ማባዣ ማህበርም የተደራጀው በከተማ አስተዳደሩ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
‹‹ማህበሩ በየአመቱ ከ70 ሺ በላይ የተለያዩ ችግኞችን በማፍላት ለተጠቃሚዎች እንዲያደርሱ የገበያ ትስስር ተፈጥሮለታል። በዋናነትም ለወጭ ገበያ የሚሆን ‘ሃስ’ የተባለ የአቦካዶ ዝርያ በስፋት እያመረቱ ነው›› ይላሉ። ከዚያ ባሻገር ሮዝመሪ ፣ ቡና እና የእንሰት ችግኞችንም በማፍላት የሚያሰራጩ መሆኑን ያመለክታሉ። በቀጣይም ለመርሃ ግብሩ መሳካት ማህበራቱ ምንም አይነት የቦታም ሆነ የገበያ ችግር እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አቶ ሰይፉ አስታውቀዋል። የገበያ ትስስር ሲባልም ከከተማዋና በዙሪያው ካሉ አርሶአደሮች እንዲሁም ከወረዳው ባሻገር እስከ ስልጤ ዞን፣ ኦሮሚያ ድረስ የሚላክበት ሁኔታ ይኖራል ብለዋል።
እንደአርሳቸው ገለፃ፤ በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ ማህበራትና ማዕከላት ችግኝ ከማፍላትና ከማሰራጨት ባለፈ እሴት የተጨመረበትን የፍራፍሬ ምርት ለወጭ ገበያ እንዲያቀርቡና ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ ሥራም እንደዲገቡ ይጠበቃል። ለእዚህም የከተማ አስተደደሩ ቦታና የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ድጋፍ ያደርጋል። የቴክኒክና የግብዓት ድጋፍ በማድረግም ሃላፊነቱን ይወጣል። በአሁኑ ወቅትም በዘርፉ ለመሠማራት በርካታ የከተማዋ ወጣቶች ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሥልጠና የመስጠትና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ይሠራል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አይችሉህም ሲጃ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዞኑ ዘንድሮ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ 24 ሚሊዮን ችግኞችን በማበዛት ለመትከል አቅዶ ሲሠራ ቆይቷል። እስከአሁን ወደ 19 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን፣ ከዚያ ውስጥ ከስድስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑት የአቦካዶ ችግኞች ናቸው። በዞኑ ችግኝ በማባዛትና በማሰራጨት ሥራ ላይ የተሠማሩ በርካታ ማህበራትና ማዕከላት ያሉ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል። ከእነዚህም መካከል ችግኝ ከማፍላትና ከማሠራጨት ባለፈ አቦካዶ አምርተው ወደ ውጭ እስከ መላክ የደረሱ ማህበራት አሉ።
‹‹በዞናችን በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ኢኒሼቲቭ በመከተል የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱን በሁሉም አካባቢዎች ላይ ለመተግበር ሰፊ ሥራ ሠርተናል። የሚባዛውም ሆነ የሚተከለው ችግኝ መጠንም በአየመቱ እየጨመረ ነው፤ አምና ሶስት መቶ ሺ ነበር፤ ዘንድሮ ስድስት መቶ ሺ ተመርቷል ይላሉ።
‹‹ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዞኑ በሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች ላይ መሬት በመስጠትና ሥራአጥ ወጣቶችን በማደራጀት በአረንጓዴ ልማት የሥራ መስክ ፈጥረው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው›› በማለት የሚናገሩት አቶ አይችሉህም፤ የወረዳው ችግኝ ጣቢያ መኖሩንና ከ80 ሺ ችግኝ በላይ የማፍላት አቅም እንዳለውም ያስረዳሉ። ይኸው ጣቢያ አሁኑ ወቅት በ 3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ነው የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በማፍላት ለተጠቃሚዎች እያደረሰ ነው። በተለይም 2 ነጥብ 5 ሄክታር በሚሆነው መሬት ላይ 2 ሺህ 800 የአባካዶ እናት ዛፍ (ማዘር ትሪ) እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህንንም ከተለያዩ የተሻሻለ ዝርያ ካላቸው አባኮዶዎች ጋር በማዳቀል ምርታማነቱን በእጥፍ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ያብራሩት።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ዞኑ በጥቅሉ ከ300ሺ በላይ የሚሆን ትላልቅ የአባካዶ ዛፎች አሉ፤ ለማዳቀል የሚያስፈልገው የእያንዳንዱ አቦካዶ ዛፍ ቅርንጫፍ ብቻ ከስምንት እስከ 10 ብር ይሸጣል፤ አምራቾቹ ከችግኝ ባሻገር በዚህም ተጠቃሚ ናቸው። ‹‹አምና ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለማዳቀል የሚችሉ ቅርንጫፍን ከአምራቾቹ ግዢ ፈፅመናል›› ያሉት ሃላፊው፤ ከዚህ በመነሳት በርካታ ወጣቶች በዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በቀጣዩ በጀት ዓመት በተለይም ተመርቀው ሥራ ላጡ የዞኑ ወጣቶች ቦታ የመስጠት ሥራ በስፋት ይሠራል። ቀድመው ተደራጅተው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱትን ማህበራት ደግሞ ወደ መካከለኛ ደረጃ በማሳደግ ከማምረት አልፈው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ እንዲከፍቱ ፤ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ወደ ውጭ እንዲልኩ ለማድረግ ርብርብ የሚደረግ ይሆናል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም