ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየተመዘገቡበት ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይ በቱሪዝም በመዳረሻ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የዘርፉን መፃኢ እድል በበጎ መልኩ እንደሚያሻሽሉ ታምኖባቸዋል።
ለዚህም መንግሥት በዘርፉ የፖሊሲ ማሻሻያ ማደረጉ ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በሚገባ ያሳየበት አንዱ አስረጂ ነው። በሆስፒታሊቲ በኩልም ቢሆን በተመሳሳይ በሆቴል፣ ቱር ኦፕሬተርስ እና ሌሎች መሰል ንዑስ አገልግሎት ዘርፎች ላይ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ ከዓለም የቱሪዝም ገበያ ያላትን ድርሻ በበቂ ሁኔታ እንድትጋራ መሠረት ይጥላሉ ብሎ መውሰድ ይቻላል። በመላው ሀገሪቱ ባለኮኮብ ሆቴሎች መስፋፋታቸው፣ በመስህብ ስፍራዎች አገልግሎት ሰጪ ሎጆች፣ ሪዞርቶች እና የቱሪዝም ምርት አቅራቢዎች እየተስፋፉ መምጣታቸውም ለእዚህ በምሳሌነት ማንሳት ይችላል።
ቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፉ ኢትዮጵያ ባላት እምቅ ሀብት ልክ ተሻሽሎ ውጤት እንዲያሳይ ከላይ የተመዘገቡት ውጤቶች ብቻ በቂ አይደሉም። ከእነርሱ መሳ ለመሳ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በጥራትም ሆነ በብዛት መቅረብ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማት ኃላፊነት ይወስዳሉ።
የጥራቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ፖሊ ቴክኒኮችና ሌሎች የግልና የመንግሥት ማሰልጠኛዎች በርካታ የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲ ዘርፍ ባለሙያዎች እየወጡ ናቸው። ይህም ከመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ከማስተዋወቅና ከገበያ ልማት እንዲሁም ከፖሊሲ ማሻሻያው ጋር ተደምሮ ሚዛኑን የጠበቀ እድገት እንዲመጣ ምሰሶ በመሆን ያገለግላል። ዘርፉን ባልሰለጠነ አሊያም ሰልጥኗል በተባለ ጥራት በሌለው ኃይል ማደራጀት ያለ መሪ መኪና እንደማሽከርከር ይቆጠራል። በዚህ ምክንያት የሰለጠነና የተማረ የሰው ኃይል ለዘርፉ የጀርባ አጥንት ነው።
በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ማፍራት ስለሚገባ የሰለጠነ የሰው ኃይል ሲታሰብ ከ50 ዓመታት በላይ ባለሙያዎችን በማብቃት ወደ ኢንዱስትሪው በማቀላቀል የሚታወቀውን የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መነሳቱ አይቀርም። ይህ መንግሥታዊ ማሰልጠኛ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመንግሥት ልዩ ተልዕኮ ተሰጥቶት እየሠራ ይገኛል። በተለይ በሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ በተግባር፣ በፅንሰ ሃሳብ እንዲሁም ሙያው በሚጠይቀው ሥነ ምግባር የታነፁ ብቁ ባለሙያዎች የማብቃት ኃላፊነትም ተሰጥቶታል። ይህን ኃላፊነቱን በመወጣት በኩልም በትኩረት እየሠራ ይገኛል። በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው ተግባሮችም ለእዚህ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ተክሌ ተቋሙ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አኳያ በዘጠኝ ወራቱ ያከናወናቸውን ውጤቶች አስመልክተው እንዳሉት፤ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ በመንግሥት የተሰጡትን ተልዕኮዎች እያከናወነ ይገኛል። ከተልዕኮዎቹ መካከል ትምህርትና ስልጠና ዋናው ነው። ሌላው የጥናትና እና ምርምር፣ የማማከር ሥራ እና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ነው።
እነዚህን ኃላፊነቶቹን ይዞ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ ብቁና በሥነ ምግባር የታነፀ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሠራ መሆኑን ወይዘሮ አስቴር ይናገራሉ። ኢንስቲትዩቱ በስልጠና በመደበኛ በቀንና በማታው መርሀ ግብር፣ በእረፍት ቀናት (ቅዳሜና እሁድ) እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን ሙያቸውን ለማሳደግ ለሚፈልጉ ሠራተኞች እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዳይሬክተሯ በዘንድሮው በጀት ዓመት ኢንስቲትዩቱ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ በተለያዩ ሙያዎች ስልጠናዎችን ለመስጠት በማቀድ ካለፉት ዓመታት በተሻለ የሰልጣኞችን ቁጥር ማሳደጉን ይናገራሉ። በዚህም በሆቴል ማኔጅመንትና በቱሪዝም ማኔጅመንት በቀን ፕሮግራም በዲግሪ ማስተማር መጀመሩን ይገልፃሉ። ቅበላው እንዲጨምር ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎች ላይ ፍላጎት አሳድረው እንዲገቡ ግንዛቤ የመፍጠርና ቅስቀሳ የማድረግ ሰፊ ሥራዎች ማከናወናቸውን ያብራራሉ። በዚህም ካለው ውስን ቦታ አንፃር 720 የሚደርሱ አዲስ ሰልጣኞችን መቀበሉን አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከዘርፉ ካሉ ኢንዱስትሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ የስልጠና ፍላጎታቸውን ታሳቢ ያደረጉ የሙያ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ አንዳንድ ስልጠናዎች ተዛማጅነት እንዳልነበራቸው በዳሰሳ ጥናት በመረዳት በዚያ ላይ ማስተካከያ በመውሰድ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ስልጠና መስጠትም ተጀምሯል። በዚህም በስምንት የሙያ ዘርፎች ላይ በዲግሪና በደረጃ ገበያውን ታሳቢ ያደረገ ጥናት ተደርጎ ነው ስልጠናው የተጀመረው። በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎችም በስፋት እየተፈጠሩ ናቸው።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሰልጣኞቹ 70 በመቶ የሚሆነውን ስልጠናውን በሥራ ላይ በተግባር እንደሚያሰለጥን ዳይሬክተሯ ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም ባለሙያዎቹን የሚቀጥሩ ኢንዱስትሪዎች ከጥራት ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለ ለተቋሙ ግብረ መልስ የሰጡ እንደነበር አስታውሰው፣ ያንን ችግር ለመፍታት መሠራቱንም ይናገራሉ። የአሰለጣጠን ዘዴውን በማሻሻል ተማሪዎች በተማሩት የክፍል የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ላይ ብቻ የተግባር ልምምዱን እንዲያደርጉ የሚያስችል ስምምነት ከኢንዱስትሪዎቹ ጋር በማድረግ ጥራት ላይ ታይቷል የተባለውን ክፍተት ለመሙላት እየተሠራ መሆኑን ያመለክታሉ። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥም ይህ አካሄድ መልካም ለውጥ ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።
‹‹አንድ ሺህ 400 የሚሆኑ የሁለተኛና የሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች በ98 ሆቴልና የቱሪዝም ተቋማት ውስጥ የተግባር ልምምድ እያደረጉ ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ ተማሪዎቹ በክፍል ውስጥ በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ልምምድ በበቂ ሁኔታ እየወሰዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ኢንዱስትሪዎቹም የተለማማጆችን ውጤት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመሙላት ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ። አብዛኞቹ ተማሪዎችም በልምምድ ወቅት የሚያሳዩት ሥነ ምግባር፣ አቀባበልና አጠቃላይ ሙያዊ ብቃት መልካም ውጤት እንደታየበት ያስረዳሉ። በተለይ በዘንድሮው የተግባር ልምምድ መርሀ ግብር ሸራተን አዲስ፣ ኃይሌ ግራንድ፣ ሀያት ሬጀንሲ እና ሂልተን ሆቴሎች በርካታ ተማሪዎችን ማሳተፋቸውን ይናገራሉ። ከዚህ አኳያ የግል ዘርፉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ዳይሬክተሯ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ከተሰጡት ተግባሮችና ኃላፊነቶች መካከል ጥናትና ምርምር ማድረግ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ መስኮች አምስት ጥናትና ምርምር ውጤቶችን ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ወይዘሮ አስቴር እንዳብራሩት፤ የመጀመሪያው ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የስልጤ ዞን የባሕል ምግብ ላይ የተሠራ (ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባሕላዊ ምግቦችን ለዓለም አቀፍ ጎብኚው ለማስተዋወቅና የሀገሪቱን የምግብ ስብጥር ሀብት ለማጉላት) ጥናት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የዘርፉን የሰው ኃይል ስምሪት (በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ላይ ምን ያህል የሰው ኃይል እንዳለ ለመለየት) የተመለከተ ሲሆን፣ ሶስተኛው በትምህርት ተቋሙ ተመርቀው ከወጡ ባለሙያዎች ምን ያህሎቹ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንደሚገኙ ለመለየት የተሠራ (ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ያሉትን የሚሸፍን) ነው። አራተኛው ጥናት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ያላቸውን ፋይዳ የተመለከተው ሲሆን፣ አምስተኛው ደግሞ በስልጠና ሂደት ላይ ኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያለውን አቅም የሚመለከት ነው።
ቀጣይ ሶስት ወራት ያልተገባደዱ የኢንስቲትዩቱ ሥራዎች የሚጠናቀቁበት መሆኑንም ወይዘሮ አስቴር ይናገራሉ። በያዝነው የግንቦት ወር ውስጥ የሰለጠኑ ተማሪዎችን ከኢንዱስትሪው ቀጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ መድረክ (Job Fair) እንደሚካሄድ ይገልፃሉ። ሌላው ማሰልጠኛው በየዓመቱ የሚያካሂደው እና ዘንድሮ ለ11ደኛ ጊዜ የሚያካሄደው የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ሳምንት መሆኑን ያነሳሉ። በዚህ ዝግጅት ላይ በተለይ በክልሎች ያሉ ባሕላዊ ምግቦችን ለማስተዋወቅ ያለመ መርሀ ግብር እንደሚካተትበት ያስረዳሉ።
‹‹ኢንስቲትዩቱ ሰልጣኞችን የሚያሳትፍ የክህሎት ውድድር ያካሂዳል›› የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ ውድድሩ የቋንቋ ችሎታን የሚመዝን እንደሆነ ይገልፃሉ። ማሰልጠኛው ጀርመንኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን እንደሚያስተምር ጠቁመው፤ ተማሪዎች ያላቸውን ችሎታ እንዲያሳዩና እንዲበረታቱ ለማስቻል ውድድሩን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ይናገራሉ። ሂደቱም በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሙያዎች የቋንቋ ተግባቦት ክህሎታቸውን ደረጃ ለመለየት እድል እንደሚሰጥም ያስረዳሉ። በተጨማሪም በሆቴል ምግብና መስተንግዶ ዘርፍ የሚሰለጥኑትም በተመሳሳይ ሙያዊ ውድድሮችን እንደሚያደርጉ ይገልፃሉ።
ኢንስቲትዩቱ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ያከናወናቸው አምስት ጥናቶች ለሕትመት እንደሚበቁ የሚገልፁት ዳይሬክተሯ፤ ይህም በማጠናቀቂያ ምዕራፉ ላይ ከሚተገበሩ ሥራዎች ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ ይናገራሉ። ጥናቶቹ ለማህበረሰቡ የሚኖራቸውን ፋይዳ በተመለከተም በመገናኛ ብዙሃን ግንዛቤ ለመስጠት የሚያስችል መርሀ ግብር በእነዚሁ ቀሪ ጊዜያት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሚያከናውናቸው ሥራዎች ሲገመገሙ ከአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥራዎች የማይተናነሱ (የሚበልጥ) መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በተለይ ሙያና ሥራ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ሙያተኛን በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግብ እንደሆነም ይናገራሉ። ስልጠናን ለመስጠት የሚያስችል ምቹ ስፍራን ማግኘት ላይ ውስንነቶች እንደሚታዩበት አመልክተው፣ በዚህ የተነሳ ያለውን ፍላጎት ያህል ተደራሽ መሆን እንዳልቻለም ይገልፃሉ። የማሰልጠኛ ስፍራው ምቹና የግሉ ቢሆን ከዚህም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል ይናገራሉ።
ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ የራሱን ማሰልጠኛ ስፍራ ለመገንባት ከተቋራጭና አማካሪ ድርጅት ጋር ስምምነት ማድረጉን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፣ ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ መሆን ከቻለ ውስንነቶቹን ቀርፎ ለቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፉ ብቁ፣ በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ ባለሙያዎችን የማፍራት፣ የምርምር ውጤቶችን በስፋት የማውጣት እንዲሁም ማህበረሰቡን የማገልገል ኃላፊነቶቹን እንደሚወጣ ያስረዳሉ። የማሰልጠኛ ሞዴል የነበረው ገነት ሆቴል አሁን ባለቤትነቱ ወደሌላ አካል መዘዋወሩን በማንሳትም በዚያ ስፍራ ላይ ሌላ ግንባታ ማከናወን እንዳልቻለ ይገልፃሉ። በዚህ ምክንያት ሌላ አማራጭ በመውሰድ ግንባታ ለማከናወን ሥራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከሚያሰለጥናቸው ተማሪዎች ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር (65 በመቶ የሚሆነውን) የሚይዙት ሴት ሰልጣኞች መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፣ ይህም ለሴቶች ከፍተኛ የሥራ እድል በመፍጠር በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ላይ የአካታችነት ሚዛኑ የተጠበቀ እንዲሆን ድርሻው ላቅ ያለ እንዲሆን ያደረገው መሆኑን ተናግረዋል። ችግሮችን የሚፈታበት አንዱ መንገድ ሴቶችን ማስተማር መሆኑን በማንሳትም ማህበረሰባዊ ቀውሶችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ላይ የሴቶች ሚና ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይም ተመሳሳይ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ማሰልጠኛውም ይህንን ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም