የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከኢትዮጵያ መውጣት

የኢሠፓ ሊቀመንበር እና የደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል። ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ያስወገደው የደርግ መሪ ናቸውና ወደፊትም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ ይጠራል።

የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለምን ከሀገር ወጡ? እንዴት ወጡ? ከወጡ በኋላ ምን ተከሰተ? እርሳቸውና በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ምን አሉ? የሚለውን በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን እናስታውሳለን።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከ33 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያ በመውጣት ወደ ዝምባቡዌ ኮበለሉ። የደርግን ሥርዓት የገረሰሰው ኢህአዴግ በወቅቱ ‹‹ፈረጠጠ›› በሚል ቃል መግለጹ ይታወሳል። ከዚያ በኋላም በየጊዜው የኢህአዴግ አመራሮች ‹‹ሀገር ጥሎ ፈረጠጠ›› የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ ለሕዝብ ደህንነት ሲባል ኮሎኔል መንግሥቱ ሀገር ጥለው መኮብለላቸውን በበጎ ያዩታል። እንደተናገሩት ‹‹አንድ ጥይት እና አንድ ሰው እስከሚቀር..›› ቢዋጉ ኖሮ አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ እልቂት ይፈጠር ነበር።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የ44 ዓመት ጎልማሳ እና የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ነበሩ። ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የነበረውን ክስተት ‹‹ሕብር ሕይወቴ መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፤ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ምናልባትም ከቤተ መንግሥቱ ዙሪያ በስተቀር አዲስ አበባ ውስጥ በደርግ እና በኢህአዴግ ተዋጊዎች መካከል ጥይት አልተተኮሰም። ከዚያ ይልቅ የነዋሪው ሥነ ልቦና ፍርሃትና ጥርጣሬ የተሞላበት ስለነበር መሳሪያ ያላቸው ሰዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ተኩሰዋል። ማን እንደሚተኩሰው የማይታወቅ የተኩስ ድምጽ አልፎ አልፎ ይሰማ ነበር፤ ከዚያ ውጭ መንግሥትን ያህል ነገር በትጥቅ ኃይል ሲገለበጥ ሊኖር የሚችለው ጦርነት አልነበረም። ስለዚህ ምናልባትም የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀገር ለቆ መሄድ አዲስ አበባ ውስጥ ሊኖር ይችል የነበረውን እልቂት ቀንሷል ብሎ ለመሞገት ያስችላል። ለመሆኑ እርሳቸው ይህን አስበው ነው ከሀገር የወጡት ወይስ የራሳቸውን ሕይወት ለማዳን ነበር? የሚለው እንደየፖለቲከኞቹ አተረጓጎም ይለያያል።

ፈረጠጡ ወይስ ለፖለቲካዊና ወታደራዊ ዓላማ ነበር የሄዱት? የሚለውን በራሳቸው አንደበት የተባለውን እና በወቅቱ ጓዶኞቻቸው የተባለውን እንጥቀስ።

‹‹…በመሠረቱ ለጉዞዬ ምክንያት የተደረገውና እውነትም የነበረው የብላቴን ጉዞ ነው። ብላቴን ልሄድ ነው፤ ኬንያ የሄድኩበት ምክንያት ሌላ የውጭ መገናኛ በር በማግኘትና በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በደቡብ ተደራጅቶ ለመልሶ ማጥቃት ድርጅት ለእኔ ምሥጢራዊ ተልዕኮ አስረድቼና ሁኔታውን አመቻችቼ እንዲመጣ ነው ተልዕኮዬ። እነርሱ እንግዲህ እንደሚመስለኝ ለእኔ መውጫ ያደረጉት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ገና ኬንያ ስሄድ እኔ በሁለት ሰዓት ከሃያ በረራ ስጀምር ሦስት ሰዓት ላይ እነርሱ ስብሰባ እንደጀመሩ፤ እዚያ እንደደረስኩኝ በሰባት ሰዓት የኔ ከሥልጣን መውረድ ዜና ተነገረ፤ ይሄው ነው! እና በዚህ ሁኔታ ነው፤ እኔ አልኮበለልኩም…››

ይህን የኮሎኔል መንግሥቱን ንግግር ግን ደርግን ከሥልጣን ያስወገዱት ብቻ ሳይሆኑ ከራሳቸው ጓዶችም የማይቀበሉት አሉ። በደርግ ዘመነ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በሌሎች ኃላፊነቶች ያገለገሉት ብርሃኑ ባይህ ‹‹የሀገር መሪ ከመቼ ወዲህ ነው መሳሪያ ሊገዛ የሚወጣው?›› ሲሉ ሞግተዋል። በቅርቡ (ከሁለት ዓመት በፊት) ረጅም ቃለ መጠይቅ የሰጡት እና ‹‹የሻምላው ትውልድ›› የሚለውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ የጻፉት ጓድ ፋሲካ ሲደልል ‹‹ከፍርጠጣው የሽምጠጣው›› በማለት ነገርየው ኮሎኔል መንግሥቱ እንዳሉት ሳይሆን የምርም ፍርጠጣ ነበር የሚል ይዘት ያለው ገለጻ አድርገዋል። ያም ሆነ ይህ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኢህአዴግ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኃይል የሚመሯትን ሀገር ለቀው ዚምባቡዌ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት አባላትን

ይወክላሉ የተባሉና ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ድረስ ማዕረግ ያላቸው 120 የጦሩ አባላት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ያቋቋሙት ‹‹የጦር ኃይሎች፣ የክብር ዘበኛ፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ›› መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አውረደ። ስያሜውንም ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› ብሎ በመለወጥ ስልጣን ይዞ ኅብረተሰባዊነት (Socialism)ን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መርሁ አድርጎ ሀገር መግዛት ጀመረ።

የመሠረተ ልማት አውታሮችን በተለይ ደግሞ ትምህርትን ለማስፋፋት ከተደረገው ጥረት ባሻገር የእርስ በእርስ ጦርነት፣ እሥራትና ሥርዓት አልበኝነት የአገዛዙ መለያዎች ሆኑ። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ያለው ጦር ሲሸነፍ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚወስዱት ርምጃ፣ የሊቀመንበሩ የአቋም ግትርነት (ድፍረት እንጂ ዲፕሎማሲ አይችሉም እየተባሉ ይታማሉ) እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ተደምረው የጦሩ መሪዎች በሊቀመንበሩ ላይ ጥርሳቸውን ነከሱባቸው፡፡

መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግም ሞክረው (ባለፈው ሳምንት ያስታወስነው) ሳይሳካ ቀረ። የሀገሪቱ ችግርም ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ።

ከዚህ ሁሉ ችግር ለማምለጥ ከሀገር መውጣትን ምርጫቸው ያደረጉት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኬንያ በኩል አድርገው ዚምባብዌ ገቡ። ኮሎኔል መንግሥቱ ከሚመሩት መንግሥት ጋር ሲዋጉ ከነበሩት አማፂያን መካል ‹‹ሻዕቢያ›› ኤርትራን ገነጠለ፤ ሕወሓትና አጋሮቹ ደግሞ ግንባር ፈጥረው ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ።

ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከመንግሥት ምክር ቤት የሚሰጥ መግለጫ እንዳለ እየደጋገመ ሲገልጽ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ «ጦርነቱ ያስከተለው ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም። ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል። ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቀርና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጭ ሄደዋል። ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን በመውረድ ሀገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ተክተው ይሰራሉ» የሚል አጭር መግለጫ ተላለፈ። በዚያው ኢህአዴግ ሀገሪቱን ተቆጣጠረ። የዚህን ዝርዝር በግንቦት 20 ታሪኮች እናየዋለን፡፡

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግንቦት 13 ቀን ከሀገር ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት የነበሩትን ሁነቶች ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚለው መጽሐፋቸው ያስታውሱናል።

ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በመኖሪያ ቤታቸው ለከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው የእራት ግብዣ አደረጉ። ግብዣው ሲጠናቀቅ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ሁሉንም ተጋባዥ እንግዶች እበራፋቸው ላይ በመሆን አንድ በአንድ እየጨበጡ ሸኟቸው።

ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም፤ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ መሉውን ቀን የተለያዩ ወረቀቶችን ቢሯቸው ውስጥ ሲቀዳድዱ ዋሉ ፤ አመሻሽ ላይ ግን ወደ ዘመቻ መምሪያ በማምራት ለከፍተኛ የጦር አ ዛዦቻቸው ንግግር አ ደረጉ።

ማክሰኞ ግንቦት 13 የፕሬዚዳንቱ ልዩ ረዳት ሻምበል መንግሥቱ፤ ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ ደርሶ ከዚያም ወደ አስመራ ደርሶ መልስ የሚበቃ ነዳጅ የሞላ አንድ ዳሽ 5 አውሮፕላን እንዲዘጋጅ ትእዛዝ አስተላለፈ።

በዚያው ዕለት ከጠዋቱ ወደ 2 ሰዓት ገደማ ፕሬዚዳንቱ ከተመረጡ አጃቢዎቻቸው እንዲሁም ከሶስተኛ ክፍለ ጦር የመጣና የቅርብ አጃቢያቸው ከነበረው ከሻምበል ደመቀ ባንጃው ጋር በመሆን በኮሎኔል ተስፋዬ መሪነት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመድረስ ተዘጋጅታ ትጠብቅ ከነበረችው አውሮፕላን ተሳፈሩ።

ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ፕሬዚዳንት መንግሥቱ የ17 ዓመት ስልጣናቸውን ለቀው ከኢትዮጵያ ወጡ፤ እነሆ እስከ አሁን ድረስም በዚምባቡዌ ሐረሬ ይኖራሉ።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You