በጂቡቲ የወባ ስርጭትን ለመከላከል ዘረመላቸው የተሻሻሉ የወባ ትንኞች ተለቀቁ

በጂቡቲ የወባ በሽታን በከፍተኛ ሁኔታ እያዛመቱ ያሉ ወራሪ የወባ ትንኞችን ለመግታት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በዘረ መል ምህንድስና የተሻሻሉ የወባ ትንኞች ተለቀቁ።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ባደረገው ኦክሲቴክ ባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ ዘረመሉ የተሻሻለው እና የማይናደፈው ወንዱ አኖፌሌስ ስቴፈንሲ የተሰኘው የወባ ትንኝ ከሱ የሚፈለፈሉት የወባ ሴት ትንኞች በሽታውን ማሰራጨት ከሚችሉበት ጊዜ ቀደም ብሎ የሚገድል ዘረ መል ይዟል።

ሴት የወባ ትንኞች ብቻ ናቸው በመንደፍ ወባን እና ሌሎች በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎችን የሚያስተላልፈው። በምስራቅ አፍሪካ እንደዚህ አይነት የወባ ትንኞች ሲለቀቁ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በአፍሪካ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ በብራዚል፣ በካይማን ደሴቶች፣ በፓናማ እና በህንድ በተሳካ ሁኔታ ጥቅም ላይ ውሏል ሲል የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ገልጿል።

እ.አ.አ ከ2019 ወዲህ በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዘረመላቸው የተሻሻሉ የወባ ትንኞች መለቀቃቸውን ሲዲሲ ተናግሯል። የመጀመሪያዎቹ የወባ ትንኞች በጅቡቲ ከተማ ዳርቻ በምትገኘው አምቡሊ አካባቢ ሐሙስ ዕለት ተለቀዋል።

ይህ ሙከራ በኦክሲቴክ ሊሚትድ፣ በጂቡቲ መንግሥትና መንግሥታዊ ድርጅት ባልሆነው ማህበር ሙትዋሊስ አጋርነት የተተገበረ ነው።

“የማይናደፉ፣ በሽታን የማያስተላልፉ ጥሩ ትንኞች አዘጋጅተናል። እነዚህን ትንኞች ስንለቅ ከሴት ትንኞች ጋር ግንኙነት ይፈጥራሉ” ሲሉ የኦክሲቴክ ኃላፊ ግሬይ ፍራንድሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቤተ ሙከራ የሚመረቱት እነዚህ የወባ ትንኞች ከሴት ወባ ትንኞች ጋር ግንኙነት ካደረጉ በኋላ ከነሱ የሚፈለፈሉት ሴት ወባ ትንኞች እንዳያድጉ የሚያደርግ “ራስን የሚገድብ” ዘረ መል ይዘዋል።

ከፕሮጀክቱ በስተጀርባ ያሉት የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ በሕይወት የሚተርፉት ወንድ የወባ ትንኞች ብቻ ናቸው። እ.አ.አ በ2018 በቡርኪና ፋሶ ከተለቀቁት እና መሃን ወንድ ትንኞች በተቃራኒ በጅቡቲ የተለቀቁት ዘራቸውን ማስቀጠል የሚችሉ ናቸው።

ትንኞቹ የተለቀቁት የጅቡቲ ፍሬንድሊ ሞስኪቶ ፕሮግራም አካል የሆነው ሲሆን ይኸውም በሀገሪቱ በ2012 ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩትን አኖፌሌስ ስቴፈንሲ የተባሉትን የወባ ትንኝ ስርጭት ለመግታት ነው።

ሀገሪቱ ወደ 30 የሚጠጉ የወባ በሽተኞችን ብቻ በመዘገበችበት ወቅት በሽታውን ለማጥፋት ከጫፍ ላይ የደረሰች መስላ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የወባ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዶ በአውሮፓውያኑ 2020 ወደ 73 ሺህ ከፍ ብሏል። አፍሪካ ውስጥ ዝርያው በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ናይጄሪያ እና ጋና ይገኛል።

ስቴፈንሲ የተባለው ዝርያ መጀመሪያ የተገኘው በእስያ ሲሆን ለመቆጣጠር በጣም ፈታኝ ነው። ከባህላዊ የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች ማምለጥ የሚችል የከተማ ትንኝ ተብሎም ይጠራል። በቀንም ሆነ በሌሊት የሚናደፉ እና ፀረ-ተባይ መድሃኒቶችን የሚቋቋሙ ናቸው።

የጅቡቲ ፕሬዚዳንት የጤና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አብዱሊላህ አህመድ አብዲ ለፋይናንሺያል ታይምስ እንደተናገሩት ከሆነ የመንግሥት ዓላማ “ባለፉት አስርት ዓመታት በጅቡቲ የተከሰተውን የከፋ የወባ ስርጭት በአስቸኳይ ለመቀልበስ” ነው።

ቡህ አብዲ ካይሬ (ዶ/ር) “ከረዥም ጊዜ በፊት ወባ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ነገር ነበር። አሁን በመላው ጅቡቲ የወባ ህሙማን በየዕለቱ እያየን ነው። በአስቸኳይ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል” ብለዋል።

አዲሱን የወባ መከላከል ፕሮጀክት ለማስፈጸም የተወሰነው ጅቡቲ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ትንሽ ከተማ በመሆኗ በቀላሉ መጀመሩን አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

“ወባ ጤንነታችንን የሚጎዳ ከባድ በሽታ ነው። እነዚህ ትንኞች እንዴት እንደሚረዱን ለማየት ሰዎች እየጠበቁ ናቸው” ሲሉ በህብረተሰቡ በማዘጋጀት ሲሳተፉ የነበሩት እስማኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዘረመል ልውጥ ህያዋን ፍጥረታት አፍሪካ ውስጥ አወዛጋቢ ናቸው። የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች በሥነ-ምህዳር እና በነባር የምግብ ሰንሰለት ላይ መዘዝ ሊኖረው ይችላል በሚል አስጠንቅቀዋል። የኦክሲቴክ ኃላፊው ፍራንስደን ግን ከ10 ዓመታት በላይ በአካባቢ እና በሰው ጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለማሳደራቸው አልተመዘገበም ይላሉ።

“የእኛ ትኩረት በአካባቢ ውስጥ የምንለቀው ማንኛውም ነገር ደህንነቱ የተጠበቀ እና በጣም ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ምንም የአካባቢ ተጽዕኖ የላቸውም። መርዛማ ያልሆኑ እና አለርጂ የማያስከትሉ ልዩ ዝርያዎች ናቸው” ብለዋል።

ከተሳካ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ በሰፊ ቦታ ላይ ሙከራዎችን በማድረግ ትንኞቹን ወደ ተግባር ማሠማራቱ ይቀጥላል።

ወባ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ቢያንስ 600 ሺህ ሰዎችን ይገድላል። ከሚሞቱት ሰዎች ከአስሩ ዘጠኙ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ እንደሚገኙ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

  በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You