የማይበገር የ‹‹ሚድዋይፎች›› አገልግሎት

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ላለፉት 32 ዓመታት የሚድዊፍሪ ነክ አገልግሎቶችን በማሳደግ የእናቶችን እና የሕፃናትን ጤና ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል:: ዓለም አቀፍ የሚድዋይፎች ማህበር አባል እና የአፍሪካ ሚድዋይፎች ማህበር መስራች ነው:: በዚህም ሚድዊፍሪን እንደሞያ እያስተዋወቀ የሚገኝና የሙያውን ደረጃ ለማሻሻል ከመንግሥት ጋር እየሠራ ያለ ማህበርም ነው::

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ዓለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀንን በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ እንዲሁም 32ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን “የሚድዋይፎች እንክብካቤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የጤና ሥርዓት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ከመላው ኢትዮጵያ በተሰባሰቡ 200 ሚድዋይፎች፣ እንግዶችና ሌሎች የጤናው ዘርፍ ባለስልጣናት በተገኙበት በቅርቡ አክብሯል:: በዚሁ ክብረ በዓል ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል:: ለዘርፍ መሻሻል አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል:: በሚድዊፍሪ ነክ ልምምዶች መሻሻል ላይ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎትን ለማረጋገጥም ውይይት ተካሂዷል::

የሚድዋይፎች እንክብካቤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የጤና ሥርዓት ግንባታ ሚናው ትልቅ መሆኑ ይታወቃል:: ሚድዋይፎች የእናቶችንና አራስ ሕፃናትን ጤና እና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያደርጉት አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም:: የአየር ንብረት ለውጥ የዘመኑ ዋነኛ የጤና ፈተና መሆኑም ይታወቃል:: በእናቶች እና ሕፃናት ጤና ላይ የሚያስከትለው መዘዝም ከፍተኛ ነው። እንዲያም ሆኖ በዚህ ቀውስ ውስጥ ሚድዋይፎች የተስፋ ብርሃን ሆነው ቆመዋል።

ሚድዋይፎች የጾታ እና የሥነ ተዋልዶ ጤናን ትምህርት፣ የወሊድ መከላከያ እና አጠቃላይ የውርጃ እንክብካቤ፤ ሴቶች ቤተሰብ ሲጀምሩ እና እንዲጀምሩ ብሎም እንዲመርጡ ማበረታታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያላቸውን ብቃት ያሳድጋል:: ለዛም ነው የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን ትኩረቱን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አተኩሮ የተከበረው::

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ኃይለመስቀል እንደሚናገሩት፣ ዓለም በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ጉዳቶች እያስተናገደች ትገኛለች:: በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሙቀት መጨመር፣ የበረዶ መቅለጥ፣ የሰዎች መፈናቀል፣ በግጭቶች ምክንያት የሰዎች መፈናቀል ሲያጋጥም የመጀመሪያ ተጎጂዎች እናቶችና ሕፃናት ናቸው:: ለእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት መስጠት ቀድመው የሚገኙት ደግሞ ሚድዋይፎች ናቸው:: ስለዚህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በቀጥታ የሥነ-ተዋልዶ፣ የእናቶችና የሕፃናት ጤና ላይ ጉዳት ያሳድራል::

ሚድዋይፎች ደግሞ ከሚሰጡት መደበኛ አገልግሎት ውጪ እንዲህ ዓይነት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ዘላቂ የሆነና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የጤና አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል:: ለዛም ነው የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን ‹‹የሚድዋይፎች እንክብካቤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የጤና ሥርዓት ግንባታ›› በሚል መሪ ቃል የተከበረው:: አላማውም ሚድዋይፎች የሚሰጡት የእናቶችና የሕፃናት ጤና አገልግሎት በቀውስ ጊዜም ጭምር የማይበገር እንዲሆን ነው::

ሚድዋይፎች የሚሰጡት የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት ሁሉም ነገር ጤናማ በሆነበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት በሚፈጠሩ ቀውሶች ውስጥም ያልተቋረጠና የማይበገር አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል::

እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ብቸኛ የሞያ ማህበር ነው:: በሀገሪቱ ያሉ ከ22 ሺ በላይ የሚሆኑ ሚድዋይፎች አሉ ተብሎ ይገመታል:: እነዚህ ሚድዋይፎች በተለያዩ ጤና ተቋማት ውስጥ ይሠራሉ:: ከትንሽዋ ጤና ማዕከል አንስቶ እስከ ትልቁ ሪፈራል ሆስፒታል ድረስ እነዚህ ሚድዋይፎች ይሠራሉ:: ከ63 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው:: በትምህርት ደረጃም ሲታዩ ከዲፕሎማ እስከ ዲግሪና የማስትሬት ብሎም የ ፒ ኤች ዲ ዲግሪ የደረሱ ናቸው ሚድዋይፎቹ::

ይህን ሁሉ በማድረግ የእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሻሻል የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ከፍተኛ ሚና የተጫወተ የሞያ ዘርፍ ነው:: የዛሬ ሃያና ሰላሳ ዓመት የእናቶች ሞት ከ100 ሺ እናቶች 1 ሺ እንደነበር ይታወሳል:: አሁኑ ጊዜ ግን የእናቶች ሞት ከ100 ሺ እናቶች ወደ 267 ወርዷል:: በተመሳሳይ የጨቅላ ሕፃናት ሞትም ሲታይ ከሚወለዱ 1 ሺ ሕፃናት ወደ 27 ዝቅ ብሏል:: ለእናቶችና ሕፃናት ሞት መቀነስ ደግሞ ሚድዋይፎች ከጀርባ ሆነው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል::

ይህ ሁሉ ስኬት ሲመጣ ግን በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል:: ከነዚህ ውስጥ አንዱ የትምህርት እድል አለማግኘትና ሞያን ለማሳደግ ያለመቻል ነው:: 57 ከመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ዲፕሎማ ያላቸው ናቸው:: ስለዚህ ዲግሪ መሥራት ይፈልጋሉ:: ራሳቸውን ማሳደግና መማር ይሻሉ:: ውስን የትምህርት ተደራሽነት መኖር አሁንም የሚድዋይፎች ፈተና ሆኖ ቀጥሏል:: በሌላ በኩል ደግሞ የሚድዋይፎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ሌላው ተግዳሮት ነው::

አሁን ላይ ያሉት 22 ሺ የሚጠጉ ሚድዋይፎች ቁጥርም አገልግሎቱን ከሚፈልጉ እናቶች ቁጥር ጋር የሚመጣጠንና የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ስታንዳርድ ጋር የሚሄድ አይደለም:: ስለዚህ በርካታ ሚድዋይፎችን ማሰልጠንና መቅጠር ያስፈልጋል:: በተለያዩ ምክንያቶች ግን እነዚህ ነገሮች ሲፈፀሙ አይታይም:: በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሥራ ጫና በጤና ተቋማት ውስጥ ይታያል:: በሚሰሩት የሥራ መጠን ልክ ተከፋይ ያለመሆን ችግሮችም ይታያሉ:: በሕይወታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮች ለምሳሌ የጤና እክል ቢያጋጥማቸው አጥጋቢ የሆነ የጤና መድህን ያለማግኘት ችግርም አለባቸው::

የሚሰሩበት የሥራ አካባቢ አመቺ አለመሆን፣ በተለያዩ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ሚድዋይፎች በበቂ ሁኔታ ያለመመደብና አለመወከልና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ሚድዋይፎች ያሉባቸው ችግሮች ናቸው:: ከነዚህ ችግሮች በመነሳት ከመንግሥትና ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን በየጊዜው ችግሮቹን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ:: በዚህም መሻሻሎች ይመጣሉ ተብሎ ተስፋ ይደረጋል:: በነዚሁ ችግሮች ውስጥም ሆነው ግን የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ለእናቶችና ሕፃናት ጤና መሻሻል የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ::

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት ማህበሩ ሚድዋይፎች እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የመጀመሪያው እያደረገ ያለው ነገር ሚድዋይፎቹን ወክሎ ለእነርሱ ድምፅ መሆን ነው:: ትልልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችንና ደጋፊ ድርጅቶችን በመጋበዝ ሚድዋይፎቹን ችግርና የሚፈልጉት ነገር ምን እንደሆነ የማሳወቅና የማስገንዘብ ሥራ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ስታንዳርዶች እንዲሻሻሉ፣ የሚድዋይፎች የትምህርት እድል እንዲሰፋ፣ የትምህርት ሴክተሩ ለሚድዋይፎች ካሪኩለም እንዲቀርጽ የመወትወት፣ የማስልጠኛ ተቋማት ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ረገድም ማህበሩ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነ ይገኛል::

የሚድዋይፎችን እውቀትና ክህሎት ከመጨመር አንፃር ደግሞ አንዳንዶቹ በገፅ ለገፅ ሌሎቹ ደግሞ በኦንላይ ትምህርት እንዲወስዱና እውቀታቸውን በማሳደግ የሚሰጡት አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው:: እንዲህም ሆኖ ግን ማህበሩ የራሱ ክፍተቶች ይኖሩታል:: ከነዚህ ውስጥ አንዱ የተደራሽነት ችግር እንዳለ ሆኖ የሀብትና የገንዘብ ውስንነት ነው:: ክፍተቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ማህበሩ ሚድዋይፎችን መወከል፣ ችግሮቻቸውን ማወቅ፣ የታወቁ ችግሮችን ደግሞ ለሚመለከታቸው አካላት በትክክለኛው ጊዜና ቦታ ማስረዳትና ማሳወቅ ማህበሩ ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ የሚሰራው ነው::

በጤና ሚንስቴር የጤና ዘርፍ የሰው ሀብት ልማትና ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሰግድ ሳሙኤል እንደሚናገሩት የጤና ሚንስቴር በዋናነት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል:: የጤና አገልግሎት ጥራት መለኪያው ብዙ ነው:: አንዱና ዋነኛው ግን የጤና አገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ የሚቻለው በተቋማት የባለሞያዎችን ቁጥር በሚፈለገው የምጣኔ ደረጃ ሲሆን ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ስታንዳርዶች አሉ:: በተለይ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት የሚባለውን እ.ኤ.አ በ2030 ለማሳካት 44 ነጥብ 5 ባለሞያ ለ100 ሺ ሕዝብ ያስፈልጋል::

አሁን ላይ እንደሀገር አጠቃላይ ሁሉም የጤና ባለሞያ ተደምሮ 17 ነጥብ 8 ባለሞያ ለ100 ሺ አካባቢ ይደርሳል:: ይህም የሰለጠነ የጤና ባለሞያ ማምረት ላይ በብዛት መሥራት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል:: ከዚህ አንፃር ጤና ሚንስቴር በልዩ ትኩረት ከትምህርት ሚንስቴር፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል:: ለዚህ ደግሞ የተሻለ ማስፈፀሚያ የሚሆን በቅርቡ የጤና ዘርፍ ሰው ሀብት ልማት ስትራቴጂክና ኢንቨስትመንት እቅድ ተዘጋጅቷል:: ይህም ከ2030 የዓለም የጤና ተደራሽነት ግብ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚሄድ ነው::

እነዚህ ሥራዎች ማለትም አንደኛ ባለሞያዎችን በጤና ተቋማት በሚፈለገው ልክ፣ ደረጃና ቁጥር ብቻ ሳይሆን ዓይነት ማሟላት ሲቻል ታካሚዎች ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እድል ይሰጣል:: በዚህ ረገድም በጤና ሚንስቴር በኩል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ::

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚያስረዱት ሚድዋይፎች እንደ ሀገር እየሠሩ ያሉትን ሥራ መዘከርና ሥራዎቻቸውን ማበረታታት ያስፈልጋል:: በሚድዋይፎች የሚሰሩ ጥናቶችንና ሌሎች ተግባራትን በጋራ በገምገም መንግሥት ላስቀመጣቸው እቅዶች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን መሰብሰብ ይገባል:: የጤና ሚንስቴርም የሚድዋይፎች ማህበርን ጨምሮ ከሌሎች የጤና ማህበራት ጋር ተቋማዊ በሆነ መንገድ ይሰራል:: ለዚህም ከሁሉም ማህበራት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል::

በዛ ስምምነት መሠረት የጤና ሚንስቴር የሞያ ማህበራቱን ከመደገፍ አንፃር ያለው ሚና ምንድን ነው ሞያ ማህበራትስ ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን በዝርዝር በማውጣት ይሰራል:: የሞያ ማህበራት ባለሞያዎችን አስተባብረው እንደሀገር የተቀመጡ የጤና ዘርፍ እቅዶችን ለማሳካት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጤና ሚንስቴር ድጋፍ ያደርጋል:: የባለሞያዎችን አቅም ከመገንባት አኳያም በርካታ ሥራዎችን ያከናውናል:: የሞያ ማህበራትም በሥራቸው የሚገኙ ባለሞያዎች በተለይ አሁን የጤና እውቀት በየጊዜው የሚለዋወጥ እንደመሆኑ ባለሞያዎቹ ተከታታይነት ባለው መልኩ ሞያዊ እውቀታቸውንና ችሎታቸውን እንዲያጎለብቱ በርካታ ሥራዎችን ይሰራሉ::

ለዚህ ጤና ሚንስቴር የፖሊሲ ድጋፍና የተለያዩ የፖሊሲ ማዕቀፎችን እያዘጋጀ ለማህበራቱ ይሰጣል:: እነርሱ ደግሞ ፖሊሲውን የማስፈፀም፣ የባለሞያዎችን አቅም መገንባት ላይ በርካታ ሥራዎችን ይሰራሉ:: በዚህ መልኩ ጤና ሚንስቴርና የሞያ ማህበራቱ ተቀናጅተው የጋራ ሥራዎችን ይሰራሉ::

እንደመሪ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ጤና ሚንስቴር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ እንዱ የእናቶችና ሕፃናት ጤና ነው:: የእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ መሥራት ደግሞ የቀጣይ ትውልድ ላይ መሥራት ነው:: በሶስት ዓመቱ የጤና ዘርፍ የልማትና የኢንቨስትመንት እቅድ ውስጥ ከተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱና ዋነኛውም የእናቶችና የሕፃናት ጤና ማሻሻል ነው:: እንደ ሀገር በተለይ ከእናቶች ሞት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቁጥር አንፃር አሁን ላይ በብዙ መቀነስ ተችሏል:: ይህም ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ትልቅ መሻሻል ነው:: ዋናው ጉዳይ ግን እናት ሕይወት በሰጠች መሞት ስለሌለባት በመንግሥት ደረጃ በልዩ ትኩረት ለእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት ድጋፍ ላይ በርካታ ሥራዎች ይሰራሉ::

በዚህ አገልግሎት ውስጥ ታዲያ የሚድዋይፎች ሚና ትልቅ ነው:: ስለዚህ ሚድዋይፎች እናቶች ጥራቱን የጠበቀ ቅድመ ወሊድ፣ በወሊድ ወቅትና ድህረ ወሊድ እንክብካቤ እንዲያገኙ፣ በወሊድ ወቅት ሊሰጥ የሚገባውን እንክብካቤ ከሌሎች ባለሞያዎች ጋር በመሆን ይሰራሉ:: ይህም ትልቅ ሥራ ነው:: የዚህ ሥራ ሂደት የራሱ የሆነ ተግዳሮት አለው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ በአንዳንድ ተቋማት የሕክምና መሳሪያዎች እጥረቶች አሉ:: ነገር ግን ደግሞ የእናቶችና የሕፃናት ጉዳይ እንደ ሀገር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ስለሆነ በተቻለ መጠን በልዩ የትኩረት አቅጣጫ የሚሰራ ነው::

በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት መፈናቀል ሲኖር ደግሞ በተለይ የእናቶችና የሕፃናት ጤና ላይ ትልቅ ጉዳት ያስከትላል፤ ትልቅ ተፅእኖም አለው:: ከዚህ ጋር በተያያዘም ይህን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተለይ ከክልሎች ጋር በመሆን እየተሠራ ነው::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You