አዲስ አበባ ከተማን ለነዋሪዎቿ፣ ለእንግዶቿ፣ ለጎብኚዎቿ ምቹ በማድረግ ሂደት በእጅጉ የሚያስፈልጓት ምንም ቀራቸው የማይባሉ ግዙፍና ውብ ሕንጻዎች፣ ሰፋፊ መንገዶች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች ብቻ አይደሉም፤ ከተማዋ ያረጁ ያፈጁ መንደሮቿ መታደሳቸውን፣ በአዲስ መልክ መገንባታቸውን፣ የውሃ የአሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎቶቿ የተሳለጡ መሆናቸውን ብቻ አልነበረም የምትናፍቀው::
ከተማዋ መንገደኞቿ፣ እንግዶቿ በአጠቃላይ ሕዝቦቿ በአንቅስቃሴ ወቅት የሚገለገሉባቸው መፀዳጃ ቤቶችን በእጅጉ ሲፈልጉ ኖረዋል:: ሰውና ናቸውና ያሰቡት ቦታ ሳይደርሱ በፊት የሚያስፈልጋቸውን የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ባለማግኘት ተቸግረው ኖረዋል:: በዚህ ችግር የተነሳም ሳይወዱ በግድ የማይፈልጉትን አድርገዋል:: በየጥጋ ጥጉ ተፀዳድተዋል፤ የፍሳሽ መውረጃ ቦዮችን የአረንጓዴ ስፍራዎችን ላልተገባ ተግባር አውለዋል::
እነዚህ ዜጎች ማኅበረሰቡ ወይም መንግሥት የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በበቂ ሁኔታ ባለማዘጋጀታቸው/በአንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ ጨርሶ ባለማዘጋጀታቸው/ሳቢያ ይህን አይነት ችግር ብቻ አልደረሰባቸውም:: ጥፋተኞቹ እነሱ ብቻ ተደርገው ተወቅሰዋል፤ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ እዚህ አካባቢ መሽናት … ብር ያስቀጣል የሚል ማሳሳቢያ ተላልፋችኋል ተብለው የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸውም ጥቂት እንዳይደሉ ይገለጻል:: ከተማዋ በተከለከለ ስፍራ መፀዳዳትን በሚከለክሉ ማስታወቂያዎች ብትሞላም፣ መፀዳዳቱን ስትከለክል ኖራለች::
በአንድ ወቅት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በሆነ አንድ ከተማ የገጠመኝን ላንሳላችሁ:: በአንድ ግቢ ውስጥ የቤቱን ባለቤት ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች ቤቶችን ተከራይተው ይኖራሉ:: ተከራዮች የሆነ ሰዓት ላይ ግቢ ውስጥ ተሰባስበው ይጫወታሉ:: አንድ ቀን ያንን ጨዋታቸውን ሞቅ አርገው ይዘዋል:: የግቢው አጥር በቀርከሃ ወይም ሽንበቆ የታጠረ ነው /ይህ አይነት አጥር በአካባቢው የቅርጮ አጥር ተብሎ ይጠራ ነበር/:: በጨዋታቸው መሐል አንድ ሰው ወደ አጥሩ ተጠግቶ/ ወደ እነሱ አቅጣጫ/ መሽናት ይጀመራል::
ከመካከላቸው አንዱ ወደ ሰውዬው ፊቱን መልሶ አንተ እዚህ ለምን ትሸናለህ ሲል በቁጣ ይጠይቀዋል:: ሰውዬም ‹‹ አሞኝ ነው›› ሲል ይመልሳል:: ‹‹ ቢያምህስ ለምን ትሸናለሀ የሚል መልስ ያገኘው ያ ግለሰብ ‹‹ያመመ ጊዜማ አልጋ ላይስ ይሸና አይደል›› ያለውና ሁሉኑም አድማጭ አስቆ ከቁጣቸው የመለሰው ገጠመኝ ታወሰኝ::
ሰዎች ሰዎች ናቸውና በመንገድ ላይ እያሉ መፀዳጃ ቤት ሊያስፈልጋቸው ይችላል:: መንገድ ላይ መፀዳዳትን አንዳንዶች ችግሩን ለጠጪዎች ብቻ ይሰጡታል:: እነዚህ የማኅበረሰበ ክፍሎች በዚህ በኩል ብዙ ስማቸው ሊጠራ ቢችልም፣ ሽንት መቋጠር የማይችሉ፣ መቋጠርም የሌለባቸው፣ የታመሙ መንገድ ላይ የሚሸኑበት ሁኔታ ሊገጥም ይችላል:: ሰው በፕሮግራም አይታመም::
በዚህ ላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሆቴል ቤቶችንና መሰል ተቋማትን ልገልገል ቢሉ የማይፈቀድላቸው፤ የከተሞችን መውጫ መግቢያ የማያውቁ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ:: ሆቴል ቤቶች አገልግሎቱን እንዲሰጧቸው መጠየቅ የሚቸገሩ በርካታ ናቸው:: ሆቴል ቤቶችስ ቢሆኑ ከደንበኞቻቸው ውጪ ያለውን ሕዝብ ማስተናገድ ያለባቸውም አይመስለኝም::
በተለይ ሰዎች በብዛት በሚንቀሳቀሱባቸው የከተማ ክፍሎች መፀዳጃ ቤቶች በበቂ ሁኔታ የግድ ማስፈለጋቸው ጥርጥር የለውም:: በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የመፀዳጃ ቤቶች ጨርሶ አልነበሩም አይደለም የምለው:: በየዘመኑ መፀዳጃ ቤቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ስለመሞከሩ ብዙ አሻራዎችን መጥቀስ ይቻላል፤ ግን ጥቂትና የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ነው የነበሩት::
የከተማዋን ስፋት ታሳቢ ያደረጉ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች አልነበሩም:: በከተማዋ መልሶ ልማትና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች መስፋፋት ሳቢያ እንዲፈርሱ የተደረጉ መፀዳጃ ቤቶች በርካታ ናቸው:: እነዚህ መፀዳጃ ቤቶች የተተኩበት ሁኔታ ግን የለም፤ አገልግሎቱ በስፋት እንዲኖር ለማድረግ ይጀመራል፤ ግን ዘላቂ ተደርጎ አይሠራበትም::
በአንዳንድ ታክሲ ተራዎች አካባቢ ተንቀሳቃሽ መፀዳጃ ቤቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርገው እንደነበር አስታውሳለሁ:: እነዚያ መፀዳጃ ቤቶች ሊስፋፉ ቀርቶ ጨርሶ ተጠርገው የጠፉበት ሁኔታ ነው የተመለከትነው::
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በመቶ ሚሊዮኖች በሚገመት ብር በከተማዋ የተለያዪ አካባቢዎች በርካታ የሚባሉ መፀዳጃ ቤቶችን፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ጭምር የተካተተባቸው መፀዳጃ ቤቶችን ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቶም ነበር:: ያ ወቅት በመፀዳጃ ቤት ግንባታ ትልቅ ሥራ የተሠራበት ወቅት ነበር:: አብዛኞቹ የተገነቡት በመንገድ ክልል ላይ እንደመሆኑ ከመንገድ ማስፋፋት ጋር ተያይዞ እየተነሱ ናቸው:: እሱም ቢሆን ግን በአንድ ወቅት በዘመቻ ተሠራ፤ ከዚያ በኋላ የከተማዋን መስፋፋት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሥራው እንዲስፋፋ ሲደረግ አልታየም::
እነሱም ቢሆኑ ታዲያ እንደ መፀዳጃ ቤትነታቸው ፀድተው ብዙ ርቀት አልተጓዘም:: መፀደጃ ቤት ተብለው ራሳቸውም ያልፀዱ ሆኑ:: ተገቢው እድሳት በወቅቱ የማይከናወንላቸው በመሆናቸው በጣም የቸገረው ካልሆነ በቀር የሚገለገልባቸው አይደሉም::
የችግሩ ስፋት ሌላ አማራጭ እንዲመጣ አድርጓል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ጀሪካኖችን በመቁረጥ መንገደኞች አገልግሎቱን ሲፈልጉ ገንዘብ እየከፈሉ የሽንት አገልግሎት ብቻ እንዲያገኙ እያደረጉ ይገኛሉ:: ይህ የሆነ ጥግና ዞር ያለ ስፍራ ላይ ጀሪካኖቹን በማስቀመጥ የሚሰጥ አገልግሎት አገልግሎቱ ግን ወንዶችን ብቻ ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ሌላው ችግሩ ነው::
እነዚህ አገልግሎት ሰጪዎች በባሊ /በጀሪካን/ ያጠራቀሙትን ፍሳሽ የት ሊደፉት እንደሚችሉ ሲታሰብ ችግሩ የበለጠ አሳሳቢ መሆኑን እንረዳለን:: የሚደፉት በየፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮቹ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፤ የፍሳሹ ቀጣይ መዳረሻ ደግሞ ወንዞች መሆናቸው ሲታሰብ የፅዳት ጉዳይ በዋናዋ የሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ከሚያመላክቱት መካከል ይጠቀሳል::
ከተሞቻችን በተለይ ዋና ዋና ከተሞቻችን ይህን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት ዘላቂ ሥራ መሥራት ሲጠበቅባቸው ግን አልሠሩም:: በዚህ የተነሳ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማን ገጽታ በእጅጉ አበላሽቶታል::
መንግሥት እጅግ በርካታ ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እያሉት የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መግባቱ ትክክልና ወቅታዊ ነው፤ ይህ ብቻም አይደለም፤ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥም መሠረት የሚጥል ይሆናል::
በእዚህ ንቅናቄ ኅብረተሰቡን ለማሳተፍ በአንድ ጀምበር በዲጂታል ቴሌቶን በተካሄደ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ 154 ሚሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰብ ተችሏል:: በማግስቱ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ደርሷል:: ገንዘብ የማሰባሰቡ ተግባር አሁንም ድረስ እየተካሄደ የሚገኝ ይመስለኛል::
በእዚህ ንቅናቄ ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገነቡ ይጠበቃል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራውን ከማስጀመርም በላይ ብዙ ርቀት እንዲደርስ ማድረግ የሚያስችል ሥራ አስጀምረዋል:: እነዚህ መፀዳጃ ቤቶች በቂ ማሳያዎች ናቸው ሊሆኑ የሚችሉት::
በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት፣ ክልሎች ከተማ አስተዳደሮች ባለሀብቶችን፣ መላ ኅብረተሰቡን፣ በጤና በከተማ ልማትና በመሳሰሉት ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር ይህን ሥራ የላቀ ደረጃ ላይ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል::
ይህም ሥራ የሥራው የመጀመሪያው ምዕራፍ እንጂ የመጨረሻው አይደለም፤ ሥራው ዘላቂ መደረግ ይኖርበታል:: በከተማዋ ለቤቶች ልማት፣ ለገበያ፣ ለመናኸሪያ፣ ወዘተ ራሱን የቻለ ቦታ እንደሚዘጋጀው ሁሉ ለመፀዳጃ ቤቶችና አብረውት ለሚገነቡ አረንጓዴ ስፍራና ዕረፍት መውሰጃ ስፍራ የሚውል ቦታ በፕላን መመላከት፣ በካርታ ደረጃ መዘጋጀት ይኖርበታል::
በከተማዋ የት የት አካባቢ ላይ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ሊኖሩ እንደሚገባ መለየትም ይኖርበታል፤ ንቅናቄው ለመፀዳጃ ቤት የሚያስፈልጉ ቦታዎች ተለይተው እንዲቀመጡ፣ ደረጃቸውም የተጠበቀ እንዲሆን የሚያደርግ ዐሻራ ያኖራል ብዬ አምናለሁ::
እስመ ለዓለም
አዲስ ዘመን ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም