ሕይወት ከነሰንኮፉ …

ዕድገት ውልደቱ ከለምለሙ የገጠር መንደር ውስጥ ነው:: ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ:: ሱሌማን እንደ ሀገሬው ባሕልና ወግ በሥርዓት ተኮትኩቶ አድጓል:: ለእናት አባቱ ታዛዥ ለቃላቸው ተገዢ ሆኖ:: እሱ ወላጆቹ ያሉትን ይሰማል፣ የተባለውን በአክብሮት ይፈጽማል:: በቤተሰቡ ዘንድ ተ ወዳጅ ነውና ም ርቃትና ምሥጋና በ ረከቱ ና ቸው::

ሱሌማን ግዛው መልካም ገበሬ ነው:: አርሶ ማደርን፣ ዘርቶ ማፈስን ከልጅነቱ ያውቀዋል:: ዕድሜው ሲደርስ ወላጆቹ ሊድሩት፣ ጎጆ ሊያወጡት ፈለጉ:: ‹‹እምቢኝ›› አላለም:: ለቃላቸው ታዛዥ፣ ለሀሳባቸው ተገዢ ሆነ:: ግዜው ሲደርስ የልባቸውን መሻት ሞላ:: በወግ ማዕረግ ተድሮ የሦስት ጉልቻን ወግ ጀመረ::

አባወራነት…

አሁን ሱሌማን በቤቱ የወላጆቹ ልጅ አይደለም:: ከልጅነት ዓለም ወጥቶ የጎጆው አባወራ ሆኗል:: ባለቤቱ መልካምና ቅን ሴት ነች:: ቤት ትዳሯን አክባሪ፣ ባሏን ወዳድ መሆኗ በእሱ ፊት ሞገስ ሰጥቷታል:: ጥንዶቹ ከዚህ ቀድሞ ሌላ ሕይወት አያውቁም:: ሁለቱም ለትዳር ዓለም አዲስ መሆናቸው ኑሮን በመልካም እንዲመሩት ምክንያት ሆኗል::

ፍቅርና ሠላም ካለ ትዳር በልጅነት መልካም ነው:: በእኩል ይዘው በጋራ ያድጉበታል:: በመተሳሰብ በመግባባት ይኖሩታል:: የጥንዶቹ ሕይወትም እንዲሁ ሆኖ ተገንብቷል:: ለጎጇቸው፣ ለኑሯቸው መዝለቅ ሁለቱም ዋልታ ማገር ሆነዋል:: ‹‹አንተ ትብስ እኔ ›› ይሉት ብሂል በእነሱ ጎጆ እውነት ሆኖ ዓመታትን ተሻግረዋል::

አሁን የባልና ሚስት ጎጆ በልጆች በረከት ታድሷል:: ልጆች ሲመጡ የቤተሰብ ቁጥር ሲጨምር፣ ኃላፊነት ይበዛል:: እንዲያም ሆኖ የሁለቱ ትዳር ክፍተት የለውም:: በፍቅር በመተሳሳብ ዘልቋል:: ልጆች ትምህርት ቤት ሲገቡ፣ አባወራው ስለእነሱ መኖር አቅም ጉልበቱን ይከፍላል:: ከእርሻው ሲውል ስለነጋቸው እያሰበ፣ አርቆ እያለመ ነው:: ተምረው ተለውጠው ራሳቸውን እንዲለውጡ፣ ወገናቸውን እንዲጠቅሙ ይሻል::

አራተኛው ልጅ…

ሀሊድ የሱሌማን አራተኛ ልጅ ነው:: እናት አባቱ እንደ ያስቡለታል:: ትምህርት ቤት ውሎ ሲመጣ የተማረውን ይነግራቸዋል፣ ያየውን ያጋራቸዋል:: ተወዳጁ ሀሊድ ልጅነቱ ብሩህ ሆኖ ተጀምሯል:: ከባልንጀሮቹ፣ ከእኩዮቹ ሲውል ደስተኛ ነው:: አንደኛ ክፍልን ተሻግሮ ሁለተኛውን ከጀመረ ሰነባብቷል::

ከቀናት በአንዱ ሀሊድ ትምህርት ቤት ውሎ ሲመለስ በፊቱ ላይ ድካም ታየ:: ይህን ያስተዋሉ ቤተሰቦች ጠጋ ብለው ምክንያቱን ጠየቁ:: እየጨነቀው ልብሱን ገልጦ አሳያቸው:: ሆዱ ላይ ከተለመደው ውጭ የተለየ ዕብጠት አለ:: አሁንም በድንጋጤ ምክንያቱን ደግመው ጠየቁት:: ትንሹ ልጅ ስለሆነበት ነገር አንዳች ምላሽ መስጠት አልቻለም:: ሁኔታው እንዳስጨነቃቸው ቀናትን በ ዝምታ አለፉ::

ስለትንሹ ልጅ የሆድ ዕብጠት አባት ሀሊድ አልሰማም:: ሚስቱን ጨምሮ መላው ቤተሰብ እሱ እንዳያውቅ በምስጢር ይዘውታል:: ይህ ዝምታ ግን እንደነበረው አልቀጠለም:: አንድ ቀን አባት የልጁን የሆድ ላይ ዕብጠት ሊያየው ግድ ሆነ:: ይህ አይነቱ ለውጥ ለእሱ አዲስ ነው:: እየደነገጠ ልጁን ደጋግሞ ጠየቀው:: ሀሊድ ትምህርት ቤት ሲጫወት ስለመውደቁ ተናገረ::

ሱሌማን ስለልጁ ጤና ውሎ አላደረም:: በአካባቢው ከሚገኝ ጤና ጣቢያ ወስዶ አስመረመረው:: የጤና ባለሙያዎቹ ለትንሹ ልጅ ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ሁሉ አደረጉ:: ተገቢውን ምርመራ ሲያጠናቅቁ ግን ሀሳባቸው በአንድ ቃል ተደመደመ:: ሁኔታው በእነሱ አቅም የሚቻል ባለመሆኑ ከፍ ወዳለ ሆስፒታል መሄድ እንዳለበት አሳወቁ::

ወሊሶ ላይ…

አባትናልጅ ከጤና ጣቢያው የተጻፈላቸውን ማስረጃ ይዘው ወሊሶ ሆስፒታል ደርሰዋል:: አሁንም ትንሹ ልጅ ተኩረት አግኝቶ እየታከመ ነው:: ቀን በቀን ተገቢው ምርመራ በሚገኘው ውጤት እየታገዘ ጥረቱ ቀጥሏል:: ሀኪሞቹ የስምንት ዓመቱን ሕጻን የጤና ችግር ለማወቅ እየታገሉ ነው:: ከቀናት በኋላ አባት ሱሌማን ስለምርመራው መልስ አገኘ:: አሁንም የልጁ ሕመም ከሆስፒታሉ አቅም በላይ መሆኑ ተነገረው:: አባት ግራ ተጋባ ይሻላል ብሎ በመጣበት ስፍራ አሁንም ለውጥ አላገኘም:: ቢደነግጥም የሚባለውን ለመቀበል ራሱን አዘጋጀ::

የአባትና ልጅ ቀጣይ አማራጭ ወደሌላ ከፍ ያለ ሕክምና ማምራት ሆነ:: ለምርመራው ከቆዩበት ወሊሶ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተላኩ:: አባት ሱሌማን ከዚህ ቀድሞ አዲስ አበባን አይቶት፣ ረግጦት አያውቅም:: ጉዳዩ የልጅ ነገር ቢሆንበት ፊቱን ሳይመልስ ለመንገዱ ተዘጋጀ::

ከሆስፒታሉ ሲደርስ የተጻፈለትን አሳይቶ ልጁን ሐኪም ዘንድ አቀረበ:: በሀሊድ ላይ አስፈላጊው ምርመራ አንድ በአንድ ቀጠለ:: ከልጁ የተገኙ ናሙናዎች ወደ ውጭ አገር መላክ ነበረባቸው:: እንደታሰበው ሁሉም በግዜው ተከወነ:: የምርመራው ውጤት እስኪደርስ በትዕግስት መጠበቅ ግድ ሆኗል::

የምርመራው ውጤት…

ከጊዜያት በኋላ ወደውጭ አገር የተላከው የሀሊድ የምርመራ ውጤት ለሚመለከተው ክፍል ደረሰ:: አባት የሚባለውን ሊሰማ ሐኪሞች ፊት ቀረበ:: የልጁ ችግር ምን እንደሆነ ለማወቅ በጭንቀት ቀናት ሲቆጥር ቆይቷል:: ሐኪሙ አባትን ከፊት ለፊቱ አስቀምጦ በእጁ የሚገኘውን የምርመራ ውጤት አሳወቀው:: አሁን ትንሹ ሀሊድ የደም ካንሰር እንዳለበት ተረጋግጧል::

ሱሌማን ከዚህ ቀድሞ ስለማንኛውም አይነት የካንሰር ሕመም ሰምቶ አያውቅም:: ዛሬ በልጁ ላይ ተገኘ ስለተባለው የደም ካንሰርም ግንዛቤ ይሉት የለውም:: የሚነገረውን ሁሉ አንድ በአንድ በትኩረት አዳመጠ:: ስለሕመሙ ምንነት ባያውቅም የልጁ ችግር በሕክምና መለየቱ አስደሰተው ::

አባት ወደ ጆሮው ከደረሱ እውነታዎች መሐል ሕክምናው ዓመታት ይፈጃል መባሉ አስደንግጦታል:: እስከአሁን ቤቱን ትቶ ፣ ሥራውን ፈቶ ለልጁ ጤና ብዙ ተንከራቷል:: መድኃኒቱ ተገኝቶለት፣ ድኖ ቤቱ ይገባል ያለው ሀሊድ በሕክምና ዓመታትን ሊዘልቅ ነው:: ይህኔ አቅሙን አሰበው:: ለሕክምናው ጥቂት የማይባል ገንዘብ ያስፈልጋል:: ይህን ሲታየው በጭንቀት አንገቱን ደፋ:: መጪው የእንግልት ግዜ ይበልጥ አሳሰበው::

በድንጋጤ ክው ያለው አባት ከሐኪሞቹ ቀርቦ አወጋ:: ሁሉም ለልጁ የሚደረገው የዓመታት ሕክምና ግድ መሆኑን አስረዱት:: ይህ ካልሆነ የሀሊድ በሕይወት መቀጠል አሳሳቢ መሆኑን ሲያውቅ ወደራሱ ተመልሶ ከውስጠቱ ተስማማ :: ከልጁ ማንም፣ ምንም እንደማይበልጥበት ገባው ::

ሱሌማን ቀጥሎ ስለሚጠበቅበት ግዴታዎች በግልጽ ተነገረው:: ለእሱ በወጉ ያልተረዳውን የደም ካንሰር ሕክምና ለመጀመር ጊዜ የሚያሻው አልሆነም:: ሀሊድ ሂደቱ በፍጥነት ተጀመረለት:: ፈታኙ የኬሞ ቴራፒና የጀርባው ላይ ናሙና እሱን ጨምሮ ሲያስጨንቅ፣ ሲያስለቅሰው ከረመ::

ያለፉትን ፈታኝ ቀናት ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስበው አባት ዓይኖቹ በዕንባ ይሞላሉ:: በእነዛ የጭንቅ ጊዜያት ሕመሙን በእኩል ተጋርቷል:: ልጁ ሲደክም እሱም ዝሏል፣ ሲታመም፣ ሲጨነቅ ቀድሞ ውድቋል:: ከሁሉም ግን ከማደንዘዣው አልነቃ ባለ ግዜ የሆነውን ሁሉ አይረሳም:: እንደእሱ ሕክምና ላይ ከሆኑት ልጆች ጥቂቶቹ የመትረፍ ዕድል አልነበራቸውም:: በሕይወት አለመኖራቸውን ሲያውቅ ሰማይ ተደፍቶበታል:: ስሙ በተጠራ ግዜም የልጁን አስከሬን ሊቀበል መስሎት መፈጠሩን እስኪጠላ አንብቷል::

በወቅቱ ማንም ከጎኑ አልነበረም:: እነዛን የጭንቅ ቀናት ያለፋቸው እሱ ብቻውን ከተሰጠው ፅናት ጋር ነበር:: ዛሬ ሀሊድ በመልካም ቁመና ላይ ይገኛል:: ቀድሞ አልራመድ ያሉት እግሮቹ መፍጠን ጀምረዋል:: መላወስ የማይችለው አንደበቱ ለማወራት ታድሏል:: ፊቱን በሳቅ ሞልቶ እስትንፋስ የሰጠው ኃይል ስለነገው ተስፋን እያመላለሰ ነው:: አሁን ያማረውን ለመብላት፣ ያሻውን ለመጠጣት፣ ከልካይ የለውም::

አባት ሱሌማን ይህን ለውጥ ሲመለከት የትናንቱን ስቃይ በ ‹‹ነበር ›› ያስበዋል:: ዛሬም ቢሆን ከባዱን የሕይወት ሸክም እንዳዘለ ነው:: በአዕምሮው ያለ ጥያቄ ምላሽ ሳይኖረው ቀናትን መግፋት ይዟል:: ብርቱው አባወራ የተበተኑት ቤተሰቦቹ የእሱን ድምፅ እየናፈቁ ነው:: ካሉበት የመከራ ሕይወት ይታደጋቸው ዘንድ ይጠብቁታል:: ‹‹አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ›› የሆነበት ሱሌማን ስለነእሱም ዕንቅልፍ የለውም:: ልቡ ለሁለት ተከፍሎ አርቆ ያስባል::

የእሱ ማንነት መልሕቋ እንደራቃት ጀልባ ይመስላል:: ከወዲያ ወዲህ የሚዋልለው ልቦናው ማረፊያውን እስኪያገኝ ከድካሙ አያርፍም:: አንድ ቀን ግን ሁሉም ሞልቶ ችግሩ እንደሚወገድለት አያጣውም:: ለዛሬው ግን ሕይወትን ከነሰንኮፉ ተቀብሎ የነገውን ዓለም በተስፋ ይጠብቃል:: ይህ ይሆን ዘንድ የትናንት ክፉና በጎ አጋጣሚዎች አስተምረዋታል::

የመጀመሪያው ቆይታ እንዳበቃ ሀሊድ የታዘዘለትን መድኃኒት ይዞ ወደሀገርቤት ተመለሰ:: ከወራት በኋላ ለተጨማሪ ምርመራ ሆስፒታል ተገኝቶ ሕክምናውን ይቀጥላል:: በሆዱ ላይ የታየው ዕብጠት መፍትሔ ካገኘ ወዲህ የቤተሰቡ ሠላም ተመልሷል:: የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ቢሆንም ትምህርቱን በአግባቡ መቀጠል አልቻለም::

ሱሌማን ስለልጁ ጤና በብዙ ተፈትኗል:: በእሱ ትከሻ የሚያድረው ጎጆ እስኪራቆት ገንዘቡን አሟጦ ጉልበቱን ጨርሷል:: ለመንገድ ምልልስና ለመድኃኒቶች ግዢ የሚያስፈልገው ወጪ የዋዛ አልነበረም:: ይህን ሁሉ ለመሸፈን የእሱ ጥረት ግድ ነበር:: አይቶት በማያውቀው ከተማ የታመመ ልጅ ይዞ መዞር ቀላል አይደለም:: ይህ ይሆን ዘንድ በዚህ መስመር ማለፍ በሻካራማው መንገድ መራመድ ግድ ሆኗል::

በፈተናዎች መመላስ…

የእነ ሱሌማን አካባቢ ሠላም ከራቀው ቆይቷል:: በየምክንያቱ የሚነሳው ግጭት መንድ ላሰበ ሰው የሚሆን አይደለም:: ‹‹ኮሽ›› ባለ ቁጥር መድረሻው የሚጠፋቸው ነፍሶች ሁሌም በጭንቀት ውለው ያድራሉ:: በየአጋጣሚው ቤቶች ይቃጠላሉ፣ ንብረቶች ይዘረፋሉ፣ ሰላም የለሽ ቀናት ዕንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፣ በአካባቢው ከነገሰ ቆይቷል::

ይህ እውነት ለአባትና ልጅ እጥፍ መከራ ነው:: ቀጠሮ ባለ ግዜ የነደደውን አመድ ረግጦ መውጣቱ ይከብዳል:: በቅርቡ በእነሱ መኖሪያ አካባቢ ድንገቴ ግጭት ተነሳ:: ሁኔታው ከወትሮው ባስ ያለና የጠነከረ ነበር:: አጋጣሚ ሆኖ ሱሌማንና ልጁ ወደ ሀገርቤት ተመልሰዋል::

ሌሊቱን የተነሳው ከባድ ግጭት ለመላው ቤተሰብ እንደዋዛ‹‹አልፏል›› ተብሎ የሚወራ አልሆነም:: ሕይወት አጥፍቶ ቤታቸውን አውድሟል፣ ንብረት አዘርፎ፣ በዱር በጫካው አሰድዷል:: ንጋት ላይ ሱሌማን ልጆቹን ለማሸሽ ብዙ ታገለ:: እነሱን ከአንዱ ዘንድ ደብቆ አባቱን ለመፈለግ ተሯሯጠ::

በድንገት ያየው እውነት ግን ከአዕምሮው በላይ ሆነበት:: የሚወዳቸው አባቱ የግጭቱ ሰይፍ አላጣቸውም:: የቆመበት ቦታ የእሳቸውን መገደል በዓይኑ አሳየው:: ሱሌማን አምሮ እያለቀሰ የአባቱን አስከሬን አነሳ:: ሲረጋጋ ወደቤቱ አማተረ ::ንብረቱ ወድሟል:: መኖሪያው ተቃጥሏል:: ውስጡ እየጋየ አባቱን አፈር አለበሰ::

አሁን የሱሌማን ልብ ለብዙ ተከፍሏል:: ቤት ይሉት የለውም:: ሚስት ልጆቹ ከጫካ ናቸው:: የሀሊድ የሕክምና ቀጠሮም ደርሷል:: ክፉኛ ተጨነቀ፣ ሆድ ባሰው፣ ኀዘንና መከራ የዋጠው አባወራ የቱን ይዞ የቱን እንደሚለቅ ግራ ገባው::

አይቀሬው መንገድ…

አባቱን ቀብሮ፣ ሙሉ ቤተሰቡን ከጫካ ጥሎ ሀሊድን በእጁ የያዘው አባት ለአይቀሬው መንገድ ተዘጋጅቷል:: የቤተሰቡ ሕይወት በትግል ቢተርፍም:: ስለ ትንሹ ልጅ ደግሞ እያሰበ ነው:: ስለእሱ ብዙ ደክሟልና ጤናው ስብራት እንዲያገኘው አይሻም:: በቀጠሮው ለሕክምናው ለማድረስ አዲስ አበባ ላይ ተገኝቷል::

አሁን ስለሚስቱና ስለሕጻናት ልጆቹ በቂ መረጃ የለውም:: እግሩ ካሰበው ቢያርፍም ልቡ ደግሞ ርቆ ሄዷል:: ሚስቱ ተመልሳ የምትገባበት ቤት የለም:: አለፍ ብሎ ለመራቅም አቅም አላገኘችም:: ሱሌማን በየአፍታው እነሱን እያሰበ ይጨነቃል:: የሱሌማን ጭንቀት ተጋብቶብኛል:: ስለ ቆመበት መንታ መንገድ እያሰብኩ ጫካ ስለተደበቁት ሚስት ልጆቹ ምን እንደሚያስብ ጠየቀኩት:: ዕንቅልፍ አልባው አባወራ በእጅጉ ከፍቶታል:: ከጥቂት ቀናት በፊት ወላጅ አባቱን አፈር አልብሷል:: ዛሬም ትኩስ ኀዘንተኛ ነውና ሆድ እየባሰው ነው::

ሱሌማን ሀሊድን እያሳከመ ቢሆንም ስለ ቀሪው ቤተሰብ መጨነቁ አልቀረም:: እነሱን ወደሌላ ሀገር ጥግ አስይዞ ለየልጁ ሕክምና ዳግም ይመለሳል:: ነገ ምን እንደሚሆን አያውቅም:: የእሱ መቆም ግን ለሌሎች መኖር ግድ መሆኑን ተረድቷል:: እነሱን ሳይታደግ ቀርቶ ጉዳት ቢያገኛቸው እሱ ቆሞ መሄድ አይችልም:: እንዲህ ከሆነ ደግሞ የትንሹ ሀሊድ ሕይወት አደጋ ላይ ነው::

ጠንካራው አባወራ በፈተናዎች መሐል እየተመላለሰ የነገን መልካም መሆን ያስባል:: ትናንት የሀሊድ እኩዮች በሞት ሲለዩ አይቷል:: ልጁ ደግሞ ፈጣሪና ሕክምናው አግዞት በታላቅ ለውጥ ውስጥ ነው:: እሱና ቤተሰቦቹ ትናንት ከሞቀ ጎጆ መልካም ሕይወት ይመሩ ነበር:: ዛሬ ደግሞ ድንገቴ የግጭት አጋጣሚዎች ለይቷቸዋል:: እሱ የትናንት ክፉ ታሪክ በዛሬው መልካም ገጽታ እንደሚተካ ተስፋ አለው::

የእሱ ማንነት መልሕቋ እንደራቃት ጀልባ ሆኖ ይመሰላል:: ከወዲያ ወዲህ የሚዋልለው ልቦናው ማረፊያውን እስኪያገኝ ከድካሙ አያርፍም:: አንድ ቀን ግን ሁሉም ሞልቶ ችግሩ እንደሚወገድለት አያጣውም:: ለዛሬው ግን ሕይወትን ከነሰንኮፉ ተቀብሎ የነገውን ዓለም በተስፋ ይጠብቃል:: ይህ ይሆን ዘንድ የትናንት ክፉና በጎ አጋጣሚዎች አስተምረዋታል::

አሁን ሱሌማንና ልጁ ‹‹ቤት ለእንግዳ›› ብሎ በተቀበላቸው የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እልፍኝ ውስጥ ይገኛሉ:: ካገር ቤት ሲመጡ እንደቤታቸው ያርፉበታል:: ወደ ከሕክምና ሲሄዱና ሲመለሱም አድርሰው የሚመልሷቸው አሳቢዎች ብዙ ናቸው::

አባትና ልጅ እንደትናንቱ ስለ ልብስ ማረፊያና ትራንስፖርት አይጨነቁም:: ‹‹አይዟችሁ›› ብለው የሚያበረቷቸው ከጎናቸው አሉ:: ሱሌማን ጠንካራው፣ አባወራ ተንከራታቹ አባት ስለሕይወት ሲል ሕይወቱን ከነሰንኮፉ ተቀብሏል:: ነገ ሌላ ቀን ነውና ተስፋው አይጨልም:: ዛሬን እየተራመደ ስለነገው መልካምነት ያስባል::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You