እንደ ሀገር ለቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ልማት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ በመንግሥት ይገለፃል። የዚሁ አካል የሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ዓውደ ርዕይ ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ስካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል። ለአምስት ቀን በዘለቀው ዓውደ ርዕይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎች አምራቾች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።
በዚህ አውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ነው። ትውልድና ዕድገቱ በሲዳማ ክልል መዲና ሀዋሳ ከተማ የሆነው ወጣት ኤርሚያስ ኃይሉ ይባላል። ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ከተማዋ የተከታተለው ኤርሚያስ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ምህንድስና በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
ከከፍተኛ ትምህርት መጠናቀቅ በኋላ የመንግሥት ሥራ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነበር የሚለው ኤርሚያስ፤ የአካባቢው ማህበረሰብና ቤተሰብ ደግሞ የመንግሥት ሥራ ብቻ አዋጭ እንደሆነ እንጂ የግል ሥራ ፈጥሮ በራስ መንቀሳቀስ አትራፊ እንዳልሆነ ስለሚታሰብ ይህንን አስተሳሰብ ታግሎ ወደ ሥራው ለመግባትና ውጤታማ ሆኖ ለማሳየት የተደረገው ትግል ቀላል አይደለም ይላል።
“እንደ ሀገር ያለው የሥራ ዕድል አነስተኛ በመሆኑ ከከፍተኛ ትምርህት ቆይታ በኋላ የራስን ሥራ ፈጥሮ የመሥራትን ዓላማ ነበረኝ” የሚለው ወጣት ኤርሚያስ፤ አንድን ነገር ማሳካት እችላለሁ ብሎ ሰው ከተነሳ የሚያቆመው ኃይል አይኖርም የሚል እምነት አለው።
በአሁኑ ወቅት (ኦሶ ማሽነሪ) የተሰኘ የግል ድርጅት መስራችና ባለቤት የሆነው ወጣት ኤርሚያስ ስለ ድርጅቱ ምርትና አገልግሎት ስናገር፤ በዋናነት ከውጭ የሚገቡ አነስተኛና መካከለኛ ግብዓቶችን ማምረት የሚችሉ ማሽኖች እንደሚሰራ፤ ከዚህ በተጨማሪ ከውጭ ሀገር ተገዝተው የሚገቡ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ማሽኖችን በመጠገን ደረጃቸውን በማሻሻል ላይ የተመሰረተ ድርጅት እንደሆነ ይናገራል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የሽንኩርት መፍጫ ማሽን በመሥራት ነው ወደ ኢንዱስትሪው የገባነው የሚለው ወጣት ኤርሚያስ፤ በመቀጠል የፈሳሽ ሳሙና መሥሪያ ማሽን፣ መበየጃ ማሽን፣ ከፍ ሲልም የስኳር፣ የጨውና የቡና መፍጫ ማሽኖችን በመሥራት አሁን ላይ ትላልቅ የደረቅ ሳሙና ማሽኖችን ጨምሮ የቡና ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በመሥራት ላይ እንደሆነ ይናገራል።
የምንሰራቸው ማሽኖችን ከጥራት አንፃር ከውጭ ከሚገቡ ማሽኖች ጋር አወዳድሮ መመልከት ቢቻል በብዙ መመዘኛ የተሻሉ ሆነው የሚገኙ ናቸው የሚለው ኤርሚያስ፤ በተለይ ከዋጋ አኳያ ከውጭ ከሚገቡ ተመሳሳይ ማሽኖች አንፃር ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ያላቸው እና በተመጣጠኝ ዋጋ ለገበያ የቀረቡ እንደሆኑ ይናገራል።
ወጣት ኤርሚያስ ለዚህ ማሳያ ይሆናል ያለውን ሲናገር፤ “እኛ አንድ የቡና ማቀነባበሪያና መውቅያ ማሽን ለገበያ ያቀረብነው በተለያየ መጠን ከአንድ መቶ አምሳ እስከ ሶስት መቶ ሺህ ብር ነው። ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጥ ይሄው ማሽን ግን ከውጭ ሲመጣ ከሶስት እስከ አራት ሚሊዮን ብር ነው የሚሸጠው” ከዚህ አንፃር ጥራት ያለው ምርት በተመጣጠኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሆነ ያስረዳል።
በጥናት ላይ የተመሰረተ በእውቀትና በልምድ የታገዘ ሥራ በመሥራት የማሽን ምርቱ የላቀ ጥረት እንዲኖረው ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ የሚናገረው ወጣት ኤርሚያስ፤ በተመጣጠኝ ዋጋ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖችን መሥራት እንጂ የሚያገኙትን ገንዘብ ብቻ በመመልከት ጥራት የሌለው ማሽነሪ ለገበያ እንደማያቀርቡ በአፅንኦት ይናገራል።
ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ማሽን ወደ ማምረት ስንገባ በሴክተሩ ውስጥ ያለው ችግር ምንድነው የሚለውን በቅድሚያ እንደሚያጠኑ ይናገራል። ለምሳሌ አንድ ሰው የደረቅና ፈሳሽ ሳሙና ወይም ሻማ ለማምረት ስያስብ የሚያስቸግረው ነገር ምንድነው? ገበያው ላይ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን በጥናት እየለየን ስንሰራ ቆይተናል።
በዚህም አብዛኛው ሰው ማሽን ከውጭ ሀገር በውጭ ምንዛሬ ነው የሚያስመጣው፤ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ደግሞ ረዥም ጊዜ ይወስዳል፣ ስለዚህም በሀገር ውስጥ ማሽን እስካልተመረተ ድረስ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ አይቻልም። ከውጭ የመጡትም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ በጣም ቀላል በሆነ ብልሽት ምክንያት መጠገን በቀላሉ ስለማይቻል ማሽን ተበላሽቶ ሰዎች ከገበያ የሚወጡበት አጋጣሚ አለ። ይህ ትልቅ ክፍተት በመሆኑ ሰዎች ወደ ሴክተሩ ለመግባት ይቸገራሉ፤ እነዚህን ክፍተቶች ለመቅረፍ ወደ ሥራ በመግባት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ይናገራል።
የሀገር ውስጥ ምርትን ከመጠቀም አኳያ የህብረተሰብ ግንዛቤ እየተቀየረ እንደሆነ የሚናገረው ኤርሚያስ፤ (ኦሶ ማሽነሪ) ከሽንኩርት ማሽን ጀምሮ የመበየጀ ማሽን፣ የፈሳሽና ደረቅ ሳሙና መሥሪያ፣ የዳቦ ማቡኪያና መጋገሪያ የቡና ማቀነባበሪያ ማሽኖችን እየሠራ እስከዛሬ ዘልቋል። እነዚህን ምርቶች ወስደው የተጠቀሙ ሰዎች አብዛኞቹ የሚሰጡት አስተያየት እንደተደሰቱ ወጣት ኤርሚያስ ይናገራል። ጥራት ያለው ምርት ማምረት ከተቻለም ህብረተሰቡ ለመሸመት እንደማይቸገር ማሳያ ነው ይላል።
የምንሰራቸው የማሽነሪ ምርቶች እንደ ሀገር የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው የሚለው ኤርሚያስ፤ ሀገሪቱ ከሌላት የውጭ ምንዛሬ አውጥታ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባቸውን የማሽነሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ከማዳን የፈጠራ ሥራን እንደሚበረታታ ይናገራል።
በኦሶ ማሽነሪ አማካኝነት የሚሰራው የቡና ማቀነባበሪያ ማሽንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የቡና ምርት እንዲሁ በጥሬው ለውጭ ገበያ ከመሸጥ ይልቅ እሴት ጨምሮ በመላክ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይናገራል።
በሁለት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ሥራውን የጀመረው (ኦሶ ማሽነሪ) ዛሬ ላይ ጠቅላላ የካፒታል መጠኑ ከአስራ አራት ሚሊየን ብር በላይ እንደደረሰ የተነገረው ወጣት ኤርሚያስ፤ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር በአምስት ሰዎች ሥራውን የጀመረው ድርጅቱ አሁን ላይ በጊዜያዊነት በቀን እየተከፈላቸው ሥራቸውን ከሚሰሩ ወጣቶች በተጨማሪ ለአስራ ሁለት ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለ ይናገራል።
መካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ መሆን በራሱ ወደ ማሽነሪ ማምረት ገብቶ ውጤታማ ለመሆን ዋስትና አይሆንም የሚለው ወጣት ኤርሚያስ፤ እራሱን ለማብቃት በየጊዜው እንደ ዩቲዩብ ያሉ ዲጂታል መንገዶችን በመጠቀም የብዙ ሀገራት ጥናታዊ ጽሑፎችን በማጥናት፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎችን የመመረቂያ ጽሑፎችን በሥነ ሥርዓት ትኩረት ሰጥቶ በማንበብ፣ እንዲሁም በተለያዩ የውጭ ሀገራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አማካኝነት የሚተላለፉ የንግድና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን በትኩረት በመከታተል እራስን ብቁ ለማድረግ እንደሚሰራ ይናገራል።
ወጣት ኤርሚያስ እንደሚናገረው፤ በኦሶ ማሽነሪ የሚመረቱ ምርቶች ከውጭ ከሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች አንፃር በገበያው ተወዳዳሪ ሆነው መውጣት እንዲችሉ ከዲዛይን፣ ከጥንካሬ አኳያ የተለያዩ መመዘኛዎችን በማውጣት ጥራት ያለው ማሽን ለገበያ ማቅረብ እንደቻሉ ይገልጻል።
ወጣት ኤርሚያስ በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ ስለነበረው ቆይታ ሲናገር፤ “ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች የነበሩበት አውደ ርዕይ በመሆኑ ከፍተኛ ልምድ ያገኘበት እንዲሁም አብረው የመሥራት ፍላጐት ያላቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች የተገናኙበት መድረክ ነው። በማሽን ምርት ሥራው ላይ በራስ አቅም መሟላት የማይችሉ የጥራት ጉድለት የሚቀርፍ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ከቀረቡ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት ለወደፊቱ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚሆን አቅም የተገኘበት ኤክስፖ ነው” ብሏል።
በተጨማሪም በዚህ ኤክስፖ ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር በመገናኘት የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ቃል እንደተገባ ከዚህ ውጭ ለኤክስፖው ለማሳያነት የቀረቡ ሶስት የቡና ማቀነባበሪያ ማሽኖችን ከመሸጥ በተጨማሪ ሌሎችን ከሃያ በላይ ማሽኖችን ሊገዙ የሚችሉ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻሉ ወጣት ኤርሚያስ ይናገራል። የዚህ ዓይነት ፕሮግራም ለኢንዱስትሪና አምራች ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ የሚያበረታታ በመሆኑ መቀጠል እንዳለበት ተናግሯል።
ቴክኖሎጂና ፈጠራ ከዚህ በኋላ ከፍተኛ የሀገር ሀብት መሆን የሚችሉ ነገሮች ናቸው የሚለው ወጣቱ፤ የተፈጥሮ ሀብት አላቂ በመሆኑ ወጣቱ ፈጠራ ላይ ማተኮር እንዳለበት ይናገራል።
ከዚህ ቀደም እንደነበረው ወደፊት ባሉት ጊዜያት ማሽኖችን ከውጭ እያመጡ መቀጠል አዳጋች ይሆናል የሚለው ወጣት ኤርሚያስ፤ ምክንያቱም ሀብት እያነሳ በሄደ ቁጥር ማሽን የሚሰራበት ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኪሳራ ይዞ ይመጣል። ይህ እንዳይሆን ከአሁኑ መሥራት መጀመር ያስፈልጋል፤ ከዚህ አኳያ መንግሥት ማሽን አምራች ኢንዱስትሪና ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የግል ድርጅቶችን በተለያየ መልኩ በመደገፍ የሚጠበቅበትን የላቀ ሚና ማዋጣት እንዳለበት ይናገራል።
መንግሥት ከንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ፣ የብድር አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ለውጦችን ማከናወን አለበት የሚለው ወጣቱ ለአብነት የማሽን ሊዝ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ለማሽን አምራች ኢንዱስትሪ ቅድሚያ መስጠት ከተቻለ ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻል ይናገራል።
ከቀረጥ ጋር ባሉ ጉዳዮች እንዲሁ ጀማሪ የማሽነሪ አምራች ድርጅቶች ማበረታታት ቢቻል እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲሁ ቅድሚያ ሰጥቶ የብድር አቅርቦት የሚሰጣቸው ዘርፎች አሉ የማሽነሪ ኢንዱስትሪውም በዚህ ማዕቀፍ ታይቶ ሊበረታታ ይገባል ይላል።
በዘርፉ ውጤታማ ሆኖ ለመውጣት ብዙ አስቸጋሪና ተስፋ አስቆራጭ አጋጣሚዎችን አሳልፈናል የሚለው ኤርሚያስ፤ ባጋጠሙን ውጣውረዶች ሁሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ነገሮችን በተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ ማሳካት እንደቻሉ ይናገራል። ‹‹ወጣቶች ብዙ እንቅፋት ሊያጋጥመቸው ይችላል ነገር ግን ለፈተናው እጅ ባለመስጠት ላሰቡት ነገር እስከመጨረሻው መስዋዕትነት በመክፈል መትጋት አለባቸው›› ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል።
አሁን ላይ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማሽኖች እየቀረብን ነው የሚለው ወጣቱ፤ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በምስራቅ አፍሪካ አቅም ያለው የማሽን አቅራቢ ኩባንያ መሆንና በረዥም ጊዜ ሂደት ደግሞ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ትልቋ ማሽን አቅራቢ ሀገር ማድረግ ዓላማ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ይህንን ዓላማ ለማሳካት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንዳለም ገልጿል።
መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ የሚናገረው፤ ኤርሚያስ ግን አሁንም በኢንዱስትሪው ዓለም ከደረሰበት የልህቀት ደረጃ አንፃር ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ብዙ መሥራት እንዳለባት ይናገራል። መንግሥት በተለይ በሀገር ውስጥ የማሽን ማምረት ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ ለምሳሌ በመንግሥት ግዥ ጨረታ ወቅት ለሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ቅድሚያ በመስጠት ማበረታት እንዳለበት ሃሳብ ይሰነዝራል።
በመጨረሻም ለወጣቶች ባስተላለፈው መልዕክት ችግሮች ሁልጊዜ መኖራቸው የማይቀር ነው። ችግሮች ሲያጋጥሙን ግን ‹‹በቃ አይሆንልኝም›› ወይም ‹‹በዚህ ሀገር ሥራ መሥራት አይቻልም›› ብሎ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በፅናት በመቆም የራሱንም የሀገሩንም ነገ የተሻለ ለማድረግ መትጋት አለበት ይላል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም