የአምራች ዘርፉ መሻገሪያ መላ

ዛሬ በከተሞቻቸው እድገት፣ በሕዝቦቻቸው ስልጣኔ፣ በቴክኖሎጂያቸው መዘመን፣ በሀብት መጠናቸውና በሌሎች በማሳያነት የሚቀርቡ ሀገራት ከትላንታቸው ረሀብ፣ ጦርነት፣ ወረርሽኝ፣ ያልዘመነ ቴክኖሎጂ፣ያልሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ድህነትና መሰል ችግሮች ይመዘዛሉ። በበረታ ህብረት፣ በስኬታማ የፖሊሲ ጉዞ፣ በጠንካራ የሥራ ባህል ድህነትን፣ ኋላቀርነትን በመፀየፋቸው ከከፍታቸው ደርሰዋል።

በተለይ የሀገር ውስጥ ምርቶቻቸውን በማሳደግ፣ ጥራታቸውን በመጠበቅ ከሀገሬው አልፈው ለሌሎች ሀገራት ተመራጭ እንዲሆኑ በማድረግ ዛሬያቸውን አሳምረዋል። ሩቅ አስበው የመጪውን ትውልድ አደራ ሳይዘነጉ ከትላንታቸው የችግር አረንቋ ለመላቀቅ በብዙ ዳክረዋል። እንደልፋታቸው ተሳክቶላቸው አዳፋቸውን አጥበው በፀዳ ገፅ በኩራት ቆመዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የምጣኔ ሀብት እድገት መሠረት በመጣል የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ይወሳል። በሰው ጉልበት ተንጠልጥሎ የነበረውን የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ሜካናይዜሽን፣ በእጅ ከማምረት በፋብሪካ መታገዝ እንዲሻገሩ ድርሻው የጎላ ነበር። የተጠቀሙበት ያተረፉበት የምጣኔ ሀብታቸውን እድገት ያፋጠኑበት፣ የማምረት አቅማቸውንም ያሳደጉበት ጭምር ነው። የውስጥ ፍላጎታቸውንም አሟልተዋል። ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በማምረት የወጪ ንግድ ላይ አተኩረው መሥራትም ችለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ለያዘችው የእድገት ውጥኗ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለመጨመርና አቅምን ለማሳደግ በዘርፉ የሚታዩትን ተግዳሮቶች ለማስወገድና የዜጎቿን የሥራ እድል ለማሟላት አልማ እየሠራች ትገኛለች። የገቢ ምርትን ለመቀነስና የወጪ ንግድን ለማሳደግ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በሀገር አቀፍ ደረጃ ገቢራዊ እየተደረገ ይገኛል። ለአስር ዓመታት የሚቀጥለው ይህ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ከፍ በማድረግ ሀገሪቱ በ2022 ለወጠነችው እድገትም ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ ተገምቷል።

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ ያስቀመጣቸውን ግብ ለማሳካት በኢንዱስትሪ የተሳካላቸው ሀገራት ተሞክሮን በመቀመር የተጀመረም እንደነበር ይታወቃል። ሜዲኢን ቻይና፣ ሜዲኢን ኢንዲያ የመሰሉ ዓለም አቀፍ ገበያን መቆጣጠር የቻሉ ሀገራት የኋላ ታሪክ ይሄው ቅድሚያ ለራስ፣ በራስ፣ ከራስ ሲባል የተፈጠሩ የሀገር ውስጥ የምርታማነት አብዮት የመጣ ለውጥ መሆኑ ግልፅ ነው።

ከሰላሳ እና አርባ ዓመታት በፊት የውጭ ገበያን ሊፈነጩበት ቀርቶ የራሳቸውን ፍላጎት አምራች ተቋሞቻቸው መሸፈን ብርቃቸው ነበር። ይህ ሁሉ ስኬቶቻቸው በእነዚህ ሶስት አስርት ዓመታት የበረታ ክንድ የመጣ እመርታ ነው። ቻይና፣ ህንድና ሲንጋፖር ይህንን ተግባራዊ በማድረግ የሚገለፁ የዓለም ሀገራት ናቸው። የራሳቸውን ምርት በመጠቀም ተጠቃሽ ሀገራት ለመሆን በቅተዋል።

በኢትዮጵያም የተጀመረው ንቅናቄ በዋናነት በሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻን አሁን ካለበት 30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ማድረስ አቅዷል። የኢንዱስትሪዎችን ሙሉ የማምረት አቅማቸውን ለመጠቀም የሰው ኃይል፣የፋይናንስ አቅርቦት፣ የተሟላ መሠረተ ልማት፣ ግብዓት በወቅቱና በጥራት ማቅረብ ያስፈልጋል። እነዚህን አካቶ አሁን ላይ ያለውን የማምረት አቅምን ወደ 56 በመቶ አካባቢ ማድረስ ተችሏል። ይህንን በሂደት ወደ 70 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዟል።

ታዲያ እንደ ሀገር የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የፋይናንስና ጉምሩክ ክላስተር፣ የግብዓት አቅርቦትን ለመቅረፍ ግብርና ሚኒስቴር የሚመራው ክላስተር፣ የሰለጠነና የበቃ ሰው ኃይል ለማቅረብ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር የሚመራው ክላስተር፣ ኢንቨስትመንትና የግል ዘርፉ ለማጎልበትና ከዛ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚመራ ክላስተር፣ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁ የመሠረተ ልማት ክላስተር ተቋቁሟል፡

እነዚህ ክላስተሮች በሥራቸው ደግሞ የቴክኒክ ኮሚቴዎች አሏቸው። በፌዴራል ደረጃ የሚመራ ስትሪም ኮሚቴ አለ። በእነዚህ መሀል ያለውን ሥራ ለማቀላጠፍ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አለ። ይህ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ክላሰተሮቹን በየደረጃው ከፌዴራል እስከ ክልል የማደራጀት ሥራ አከናውኗል። የተተኪ ምርት ስትራቴጂ፣ የአቅም ግንባታ ስትራቴጂ፣ የቆዳ ስትራቴጂና የመሳሰሉ ስትራቴጂዎችን መሥራትና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራዎች ተሰርተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የምርታማነት አብዮት ነው። አምራች ኢንዱስትሪን ማነቃቂያ፣ በራስ አቅም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የመተካት ወሳኝ እጥፋት ነው። በኢትዮጵያ የተሠራ በኢንዱስትሪዎቿ የተመረቱ ምርቶችም ገበያውን ይቆጣጠሩት ዘንድ መስፈንጠሪያ የሆነ የሥራ አብዮት ነው ማለት ይቻላል።

በተግዳሮቶች እግር ከወርች የተያዘው የአምራች ዘርፉን ፍጥነት መቀነሻዎች መሻገሪያ የሆነው ንቅናቄ ከሁለት ዓመት በፊት ሲጀመር ውጤቱን ቀድሞ ለመለካት አዳጋች ነበር። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት አቅምን ለማሻሻል፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ፣ የገቢ ምርትን ለመተካትና የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማስተካከል እንዲሁም የሥራ እድልን ለመፍጠር የተወጠነ ትልቅ ፕሮጀክት ነው።

ለስኬቱም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን ከማምረት አንፃር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለምሳሌ ምግብና መጠጥ፣ የምግብ ዘይት እዚሁ ሀገር ውስጥ ምርቶቹን ለመተካት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ጨርቃጨርቅና አልባሳት ከመከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ ጀምሮ የተማሪዎችን ዩኒፎርም እዚሁ ሀገር ውስጥ የመተካት ሥራዎች ተጀምረዋል። ብረታ ብረት ተሳቢዎችን፣ የፈሳሽ ቦቲዎችን እዚሁ ሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

እስካሁን በነበሩት ጊዜያት በትንሹ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንደተቻለ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተጨማሪም ንቅናቄው ለበርካታ ዜጎች ሥራ እድል ፈጥሯል። በመካከለኛ፣በአነስተኛና በከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ 170 ሺህ ዜጎች አካባቢ የሥራ እድል ተፈጥሯል።

እንደ ሀገር ያሉ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀምና ኢንዱስትሪንና ኢንቨስትመንትን ለማዘመን የተጀመረውን እቅድ ለማሳካትም ከመሬት፣ ከመሠረተ ልማትና ከሌሎችም ጉዳዮች ጋር ተያይዘው በባለሀብቶች የሚነሱ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል።

ትልቁ የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ቅንጅታዊ አሠራሩ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች በተለይ ወደ ክልል ወርዶ ከክልል ደግሞ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው አደረጃጀት መሠረት የሚመጡ ችግሮችን እየፈቱ መሄድና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው።

ከዚህ አኳያ የመሬት አቅርቦት ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ 57 ሺህ 589 ሄክታር አካባቢ መሬት ለኢንዱስትሪው ብቻ የሚሆን መሬት በተለያዩ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተዘጋጅቶ ከዚህ ውስጥ 12 ሺህ ሄክታር አካባቢ ከሶስተኛ ወገን ነፃ ሆኖ ለኢንዱስትሪዎቹ መተላለፍ ችሏል። ለጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች ወደ 763 ሺህ ሼዶች ተዘጋጅተው በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና በአራት ክልሎች ማስተላለፍ ተችሏል። ከኃይል መቆራረጥ ጋር ከኃይል እጥረት ጋር እንዲሁም ከአዲስ መስመር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ የተፈቱ ችግሮች አሉ።

በዚህም ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ገልጿል። ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተኪ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በተለይም መድኃኒትን ጨምሮ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ወጪ ያስወጡ የነበሩ ምርቶች በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች በዓለም ተወዳዳሪና ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን እያገዘ ይገኛል።

የሀገራችን የዘወትር ችግር የሆነው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ትንሽ ተራመድን ባልን ቁጥር ወደ ኋላ እየጎተተን ለኢኮኖሚያችን የጭን ቁስል ሆኖበታል። እንደ ኢትዮጵያ አርሶ አደር የሚደክም፣ የሚለፋም በዓለም ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው። ከአፍሪካ ውጭ ያለው አርሶ አደር የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ስለሆነ ትንሽቱ እስራኤል የአውሮፓ የፍራፍሬ መጋቢ ስትሆን ከሷም ብዙ የማትበልጠው ጃፓንም ከ125 ሚሊዮን ሕዝቧ የሚተርፍ ሩዝ አምራች ነች።

ከኢትዮጵያ ሶስት ጊዜ የምታንሰው ዩክሬንም ዓለምን በስንዴ ስታጠግብ ነበር። ከኢትዮጵያ ውጭ ያለው የአፍሪካው ዓለም ወይ በነዳጅና በማዕድን ይተዳደራል አሊያ አፈሩ ገና ያልተነካ ለም ነው። ኢትዮጵያ ግን እንደጥንታዊነቷ መሬቷን 3 ሺህ ዓመታት አርሰዋለች። ተራራማነቷም ለም አፈሯ በጎርፍ እንዲሸረሸር አድርጎታል።

ስለዚህም የዙር ድምሩ በየዓመቱ ለገበያ የምናቀርበው ምርት ወይ መጠኑ ይቀንሳል አሊያም ዋጋው ይቀንሳል። ይሄ ሲገለበጥ የውጭ ምንዛሬያችን ግኝት ከውጭ ንግዳችን ይልቅ በርዳታ፣ በብድር፣በዲያስፖራ ዜጎች ገቢ ላይ እንዲንጠለጠል ያደርገዋል እንደማለት ነው።

እነዚህ ሶስቱም መንገዶች ደግሞ አስተማማኝ አይደሉም። ርዳታው እንደጥንታዊው ዘመን ስገዱልኝ አለበት፤ ብድሩ ደግሞ የገንዘባችሁን የመግዛት አቅም ዜሮ አድርጋችሁ ተራ ወረቀት አድርጉ የሚል እጅ ጥምዘዛ አለበት፤ ሬሚታንስ ወይም ከዲያስፖራው የሚገኝ ገቢ ደግሞ እየሞቀና እየቀዘቀዘ ይለዋወጣል።

ለዚህ ደግሞ ኢኮኖሚስቶች መላ ዘይደውለታል። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ወጪና ገቢን ማመጣጠን፣ፍላጎትን መገደብ፣ ቁጠባን መጨመር፣ ሙስናን መታገል፣ ተተኪ ምርቶችን ማጠናከር ዋና ዋና ዘዴዎች ናቸው። ሁሉም ጋር ሙከራና ትግል ቢኖርም የሞት ሽረት አድርጎ መጓዝ ላይ መንጠባጠቦች አሉ። ያለመሰልቸት እነዚህን መጠበቅ ግን ምንም ዓይነት የተሻለ መፍትሔ የለም።

ባለፉት ወራት የተመለከትነው የኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ ብዙ የተኙና የሞቱትን ነፍስ ዘርቶባቸዋል። ለውጦችም ታይተዋል። ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን እዚሁ ለማምረት የተደረገው ትግልም በኃላፊዎቹ እንደተነገረን እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ድረስ አድኗል። እሰየው ነው ሁለቱም ተጠናክረው ይቀጥሉ ያስብላል።

በኢትዮጵያ ታምርት ባለፉት ዓመታት የታዩ ተስፋ ሰጪ እመርታን ማጠናከር ይገባል። ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያ ስታመርት እኛም መሸመት ይጠበቅብናል። የሚሰሩ እጆችን ከሥራ እያገናኘን፣ የሚፈጥር አእምሮን ወደ ተግባር እያስገባን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ማድረግ ይጠበቃል።

አሁንም የአምራች ዘርፍ ፈተናዎች አሉ። የጥሬ እቃ እንደልብ አለማግኘት፣ የፀጥታ ችግር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ እጥረትና መቆራረጥ ችግር፣ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት፣ የሠራተኛ ክህሎት ማነስ፣ የማኔጅመንት የማስፈፀም ልምድ ደካማነትን መፍታት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በርግጥ ከሁለት ዓመት በፊት በተለየ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገራችን የማምረት አቅም በማሳደግ ከእኛ የተሻገረ ለሌሎች የተረፈ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እየተሰራበት ነው። አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መፍታት ዘርፉንም ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ በሌሎች ሀገራት ላይ የተንጠለጠለውን የምርት ፍላጎት እዚሁ ሀገር ቤት በተሻለ ጥራት በማቅረብ ደጅ ተመልካቹን ወደ ሀገር ውስጥ ምርት እንዲመለስ ማድረግ ይጠበቃል።

በሀገሩ ምርት የሚኮራ ያንንም በተገኘበት አጋጣሚ የሚያስተዋውቅ ትውልድ መፍጠርም ይጠይቃል። እዚህ ደረጃ ለመድረስ ግን አስቀድሞ አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በገንዘብ፣ አስፈላጊ መሠረተ ልማት በማሟላት፣ ውጣ ውረዱን በተቀላጠፈ አሠራር በማዘመን ብዙዎች በዘርፉ እንዲሰማሩና የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ ይጠበቃል።

አሁን እየታዩ ያሉ ለውጦችን በመጠቀም ከክፍተቶች በመማር ያለመታከት ስለነገ ዛሬ በመሥራት ጉዞ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You