የፀሐይዋ ድምቀት በእድሳት ላይ ላለችው አዲስ አበባ የተለየ ውበት ሰጥቷታል:: በየቀኑ የሚሠራውን የሚከታተለው ገብረየስ ገብረማሪያምም በየቀኑ እያየ የተለየ የደስታ ስሜት እየተሰማው ሞቅ እያለው፤ እያላበው ልብሱን በየቀኑ መቀየር ከጀመረ ውሎ አድሯል:: ተሰማ መንግሥቴ ደግሞ የሚያየውን ለማመን የተቸገረ ይመስላል:: ከአድናቆት አልፎ ልዩ ፈንጠዝያ ውስጥ ገብቷል:: ነግቶ በመሸ ቁጥር በደስታ ወደ እንቅልፉ ያመራል:: ቀን በእውኑ ብቻ ሳይሆን ሌሊት በህልሙም የሚያስደስት ነገር እያየ ያደረ ይመስላል::
ተሰማ እንደወትሮ ቢሆን ኖሮ በእግሩ በጭራሽ አይራመድም ነበር:: እንኳን በመንግሥት መኪና መጓዝ ጀምሮ ቀርቶ ለአጭር መንገድም ቢሆን በታክሲ ነበር የሚሳፈረው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እያየ ለመደሰት በእግሩ መራመድን እንደልማድ ወስዶታል:: አንዳንዴ ገና ከሥራ እንደወጣ ወደ ግሮሰሪ እየሄደ በየቀኑ የሚጎነጨውን ቢራ አቁሟል:: ጓደኞቹ እነገብረየስ ካልጠሩት ጎዳና ላይ መንጎማለልን እየጠጡ ከመዝናናት የተሻለ አስደሳች አድርጎለታል::
‹‹ቀን ከመንግሥት ሥራ በኋላ እየጠጣሁ ከማመሽ በአንድ ባለኮከብ ሆቴል ዕቃ አጣቢነት ብገባ ይሻለኛል::›› እያለ ደጋግሞ ሥራ ወዳድነቱን የሚገልፀው ገብረየስም፤ የሚሰራውን መንገድ እያየ በየቀኑ ከፒያሳ፣ በአራት ኪሎ አልፎ መገናኛ ድረስ በመጓዝ ብቁ እግረኛ መሆኑን አረጋግጧል:: ገብረየስ ምንም እንኳን በመሠራት ላይ ያለው መንገድ ለመራመድ ባይመቸውም፤ የሚያየው ነገር ሁሉ ያስደስተዋል::
በተቃራኒው ዘውዴ መታፈሪያ ግን እንደተለመደው ከደስታ ይልቅ መከፋት ይነበብበታል:: ፀጉሩ አቧራ ጠግቦ፣ ልብሱ እና ጫማው ቆሽሾ፣ ሰውነቱ በድካም ዝሎ በቀጠሮ ቦታ ደረሰ:: ከሌላው ቀን በተለየ ሁኔታ ሶስቱም በማምሻ ግሮሰሪ በር ላይ እኩል ተገናኙ:: በእጃቸው ተጨባብጠው ትከሻቸውን እያጋጩ ሰላምታ ተለዋወጡ:: ገብረየስ ለዘውዴ ‹‹ኧረ አንተ ሰው እንደው አንዳንድ ቀን እንኳ ፈካ የሚያደርግህን ነጭ ወይም ሌላ ደመቅ ያለ ልብስ ልበስ:: ሁልጊዜ ጥቁር እና ግራጫ የምትለብሰው ምን ሆነህ ነው?›› እያለ እየጠየቀው ወደ ውስጥ ዘለቁ::
ጥግ ያለች ጠረጴዛ መርጠው ክብ ሰርተው ተቀመጡ:: የማምሻ ግሮሰሪ አስተናጋጅ ይርጋ፣ ጠጋ ብሎ ቀድሞም የፀዳውን ጠረጴዛ በፎጣ እየወለወለ፤ ‹‹ ምን ልታዘዝ?›› አለ:: ተሰማ፤ ‹‹ ምን በመጣን ቁጥር ሁልጊዜ ምን ልታዘዝ ትላለህ? ሁላችንም ምን መጠጣት እንደምትፈልግ ታውቃለህ::›› ሲለው፤ ይርጋ በፈገግታ እሺ ብሎ ሮጠ:: ለዘውዴ ጓደኞቹ ምን እንዳጋጠመው ጠየቁት:: ምሬቱን ሊሰሙት በሚችሉት ድምፅ ሳይሆን ማጉተምተም በሚመስል መልኩ አንገቱን አቀርቅሮ ግንባሩን ቋጥሮ በግድ ቀና እያለ ከንፈሩን አንቀሳቀሰ::
ተሰማም ሆነ ገብረየስ ገብቷቸዋል:: ተሰማ፤ ‹‹ያልታደልክ!›› ብሎ ሳቁ አመለጠው:: ገብረየስ ምንም እንኳ የተሰማን ያህል ባይሆንም እርሱም ዘውዴን እያየ እንደመሳቅ አለ:: ዘውዴ እርሱ እየከፋው እነርሱ በመሳቃቸው ተሰማው:: ‹‹እንደውም ዛሬ ደክሞኛል ወደ ቤት ብገባ ይሻለኛል::›› ብሎ ከተቀመጠበት ተነሳ:: ገብረየስ ‹‹ በፈጣሪ ዛሬስ እውነትም ከፍቶሃል::›› ብሎ የተነሳውን ዘውዴ እጁን ጎትቶ አስቀመጠው:: ተሰማ ሂድም ተቀመጥም አላለውም:: ነገር ግን ሁልጊዜ ዘውዴ ‹‹ተጎጂ ነኝ›› እያለ በተከፋ ፊት ከእነርሱ ጋር መቀላቀሉ ሰልችቶታል::
ገብረየስ ለተሰማ፤ ‹‹ያስከፋህ ምንድን ነው?›› ሲል ጠየቀው:: ያልተጠየቀው ተሰማ ‹‹በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ስለ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሰጡት መግለጫ አበሳጭቶት ነው::›› በማለት ተናገረ:: ዘውዴ ትንሽ እንደማምረር አለ:: ‹‹ነገሩ አንተን ደልቶሃል::›› ብሎ በተቆጣ ዓይን ተሰማን ገላመጠው:: ገብረየስ ፤ ‹‹አይ! ነገር ማክረር ደግ አይደለም:: የከረረ ይበጠሳል:: ለምን ብለን እናከራለን?›› አለ:: ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ለኢትዮጵያ ብለንማ ማክረር አለብን:: ስለሀገራችን ያላከረርን ስለምን እናከራለን?›› ሲል ምላሽ ሰጠ::
ዘውዴ ምላሽ አልሰጠም:: ተሰማ ግን ‹‹የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ውንጀላ አቅርበዋል:: መንግሥት ሀገሪቱን እንዴት መምራት እንዳለበት ለመምከር ሞክረዋል:: በእጅ አዙር ከሚገቡት ጣልቃ ገብነት አልፈው በአደባባይ፤ ‹ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት ላይ ያሉ ወገኖች ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።› ይሄ ደግሞ የእርጎ ዝምብነት ነው:: ይሄ ዘውዴን ቢያበሳጭ የሚያስገርም አይደለም::›› ሲል ተናገረ:: ዘውዴ ምንም ማለት አልፈለገም:: ገብረየስ ትንሽ ግራ ተጋባ::
ዘውዴ የታሠረው አፉ ተፈታ:: ‹‹እኔ ጉዳዬ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን ጥቅም እና ፍላጎት ጋር የተገናኘ ነው:: በርግጥ በፍፁም የውጭ ጣልቃ ገብነትን አልደግፍም:: የአሜሪካን ኤምባሲም ሆነ የአሜሪካን መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያዝዙም ሆነ እንዲያስፈራሩ አልፈልግም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሀገሬ ነች:: ቤተሰብ የመሠረትኩባት እና ልጆች ያፈራሁባት ነች:: አሜሪካን ኢትዮጵያን ስትንቅ እኔን ናቀች ማለት ነው:: አንድ አሜሪካዊ በማያገባው ገብቶ ኢትዮጵያን ለማስፈራራት ሲሞክር ደሜ ይፈላል:: ይህ ቀልድ ሳይሆን እውነት ነው::›› አለ::
ገብረየስ መገረም በተቀላቀለበት መልኩ አንገቱን ወደ ኋላው ሳብ አድርጎ ‹‹እና ያስከፋህ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ መግለጫ ነው? ›› ሲል ጠየቀ:: ‹‹ በርግጥ እውነት ለመናገር መግለጫው አላስደሰተኝም:: ነገር ግን እንደተሰማም አልተበሳጨሁም:: ኢትዮጵያ ብዙ የውጭ ጠላቶች እንዳሏት እና ብዙዎች እንደሚዶልቱባት አውቃለሁ:: ቀድሞም ቢሆን በሰሜን አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እንዲጀመር ያደረጉት የውጭ ጠላቶች ናቸው የሚል እምነት አለኝ:: ሰላማዊ ምክክር እንዳይኖር ይሠራሉ የሚል ስጋት አለብኝ::
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት ላይም መነጋገር፣ በቂና ጠንካራ መተማመን እንዳይፈጠር ሲሠሩ እንደነበር አውቃለሁ:: በኢትዮጵያ ያለመግባባት ሁኔታ እንዲፈጠር ውጥረት እንዲኖር እንደሚሠሩ እረዳለሁ:: ሰው እንዳይሞት ሰላም እንዲሰፍን አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ የማቀጣጠል ዝንባሌ እንዳላቸው አስተውያለሁ:: መፍትሔው መገኘት ያለበት ከራሳችን ከኢትዮጵያውያን ነው:: አሜሪካ ቀድሞም ቢሆን በማያገባት እየገባች ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀቦችን ለመጣል መሞከሯን አልዘነጋም:: የእነርሱ መግለጫ አያስደስተኝም:: ይህ ማለት ደግሞ የተከፋሁት በዚህ ምክንያት ነው:: ለማለት እቸገራለሁ::›› በማለት በትክክል ያስከፋውን ጉዳይ ሳይገለፅ በመግለጫውም መበሳጨቱን ጠቁሞ አለፈ::
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ በርግጥ መጀመሪያ የአምባሳደሩ መግለጫ አበሳጭቶታል ያልኩት ለመቀለድ ነው:: ነገር ግን በርግጥ በትክክል ማድመጥ ጀምረሃል ማለት ነው:: ቀድሞ ደርሰህ ዕልህ ይቀናሃል:: ስለኢትዮጵያ የጦርነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አላግባብ ያለውን ጣልቃ ገብነት አስመልክቶ የሚተላለፉ መግለጫዎችን አዳምጥ:: ማዳመጥ ብቻ አይደለም ከመላው የኢትዮጵያውያን ሕዝብ ጎን ቁም:: የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያ እንድታድግ አይፈልጉም:: ጦርነት ቢኖር እንኳ ጦርነቱ እንዲቆም ከመሥራት ይልቅ፤ ማስቀጠልን ማዕከል አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ ማወቅ አለብን:: የሚያስቡት የመሳሪያ ሽያጫቸውን ወይም በተዘዋዋሪ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚጠቅማቸውን ጉዳይ ብቻ ነው::›› ሲል ምላሽ ሰጠ::
ገብረየስ ጥቂት ትንፋሽ ሳብ አድርጎ፤ ‹‹ በርግጥም ለሁሉም ነገር ደርሶ መቸኮል አይገባም:: በፍፁም ለውጭ ጣልቃ ገብነት ፈቃደኛ መሆን የለብንም:: የሚጠቅሙን መስሎን ስንቸኩል ሁሉንም እናጣለን:: የጅብ ችኩል፤ እንደተባለው ቸኩለን አንገት ማነቅ እያለብን ቀንድ ከነከስን ሁሉም ነገር ያመልጠናል:: እነርሱ የሚያደርጉት እያንዳንዱ ነገር ሁሉም ትርጉም አለው:: ትርጉሙም የራሳቸውን ጥቅም መሠረት ያደረገ ነው:: ለራሳችን እራሳችን ካላሰብን እና በተቃራኒው እነርሱ እያሰቡልን እኛ መኖር ከፈለግን ገደል እንደምንገባ መረዳት አለብን::›› ሲል እርሱም የሚያምንበትን ተናገረ::
ተሰማ ለገብረየስ፤ ‹‹በእውነቱ እጅግ ድንቅና የተቀደሰ ሃሳብ ተናገርክ:: ለራሳችን እራሳችን ማሰብ አለብን:: ለእኛ ሌሎች እንዲያስቡልን መጠበቅ ሞኝነት ነው:: ራሳቸው እንደሚሉት ነፃ ምሳ የለም:: ለሚሰጡን ነገር ለእያንዳንዱ ከእጥፍ በላይ አትርፈው ይቀበሉናል:: የሚሰጡን ነገር እንዲበዛ የግጭት ድግስ ይደግሱልናል:: ይህንን እኛ ነቅተን ማወቅ አለብን:: ግጭት ደግሰው መልሰው አዛኝ መስለው እናስታርቃችሁ ይሉናል:: አንዱ ሌላውን እንዲያኮርፍ፤ አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ እና ጫና እንዲፈጥር፤ መንግሥት እንዲዳከም፤ ከልማት ይልቅ በጦርነት እንዲጠመድ አቅደው ይሠራሉ::›› አለ::
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ እውነት ነው:: ይሄ ሆነ ያ ሆነ ብሎ የሌለውን የጦርነት ወሬ ማቀጣጠል ማንንም አይበጅም:: የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር መፍቀድም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አይጠቅምም:: ማንኛውም ሰው ሲሰራ ማድነቅ፤ እንደሥራው የሚገባውን እውቅና መስጠት እንጂ፤ ገና ለገና አንድ አምባሳደር መግለጫ ሰጠና መበሳጨት የትም አያደርስም:: ጥያቄዬ፤ ለምን በውጭ ጣልቃ ገብነት ላይ ያለንን አቋም ተመሳሳይ አናደርግም የሚል ነው:: ሀገር እወዳለሁ፤ የኮራሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ እያሉ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚጥሩትን፤ ኢትዮጵያን ንቀው እና አዋርደው የሚያዩትን መደገፍ ምጸት ነው::›› አለ::
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ የእኛ የኢትዮጵያውን ነገር እኮ አስገራሚ ነው:: ብዙዎቻችን መደገፍ የሌለበትን እንደግፋለን:: መነቀፍ የሌለበትን እንነቅፋለን:: ዛሬ የምንደግፈው ሰው የሚያስነቅፍ ሥራ ቢሠራ አንነቅፍም:: የምንነቅፈው ሰው የሚያስደግፍ ሥራ ቢሠራም አንደግፍም:: ነገራችን ሁሉ በተጨባጭ ምክንያታዊ ነው ለማለት እቸገራለሁ:: ዛሬ የደገፍነው ሰው በውጭ ኃይል ወይም በውጭ ጠላት ከተነቀፈ ተከትለን መንቀፍ ብቻ ሳይሆን ከነቃፊው ጋር አብረን እስከ መሰለል እንደርሳለን:: አላማችን የሀገራችን ጉዳይ ነው ለማለት እቸገራለሁ:: ምክንያቱም አጭበርባሪው እና ሌባው ብዙ ነው:: ›› አለ::
ዘውዴ ምንም አላለም፤ ገብረየስ ግን ከተሰማ ቀጠለ:: ‹‹ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ምንም ሊካድ በማይችል መልኩ ሞኝነት አለ:: ሞኞች ነን:: ስለዚህ የዓለም ጭራ ሆነናል:: ትንሽ ማደግ ስንጀምር በዚህ እና በዚያ እያሉ ሊያዳክሙን ይሞክራሉ:: አንዱ ዝም ሲል ወይም በውጭ ጠላት ላለመታለል ጥረት ሲያደርግ በተቃራኒው ሌላው ይታለላል:: በሚተላለፍለት ትዕዛዝ መሠረት ክብሪት ይጭራል:: የተጫረው ክብሪት ተቀጣጥሎ እሳት ሆኖ ኢትዮጵያውያንን ሲበላ፤ በውጭ ኃይል ተታልለው ክብሪት የጫሩትም በእሳቱ ይበላሉ:: ሞኞች ይበዙና ሀገር ያፈርሳሉ::›› በማለት ተናገረ::
ዘውዴ፤‹‹ እኔ የተለየ ሃሳብ አለኝ›› አለ:: ‹‹ ዋናው የኢትዮጵያ ችግር ስግብግብነት እና ለራስ የሚሰጥ የተሳሳተ ግምት ነው:: እኔ ብቻ ሃብታም፣ እኔ ብቻ ባለስልጣን፤ እኔ ብቻ አዋቂ ማለታችን ሁላችንንም ዋጋ እያስከፈለን ነው›› ሲል፤ ተሰማ በበኩሉ፤‹‹ የለም የለም የኢትዮጵያውያን ችግር ስንፍና ነው:: የተፈጥሮ ሀብት እያለን ስንፍናችን እንድንራብ እያስገደደን ነው:: ተግተን ሀገር በሚቀይር ጉዳይ ላይ ከመጠመድ ይልቅ፤ በትርኪ ምርኪ ፍሬ በማያመጣ ነገር ላይ ጉልበታችንን እና ገንዘባችንን እናባክናለን:: ጭራሽ የሚሰራውን እናጣጥላለን::›› ሲል ተናገረ::
ገብረየስ ደግሞ፤ ‹‹ በእኔ እምነት በትክክል ሚናችንን አላወቅንም:: በዚህ ምክንያት ብዙ ዋጋ እየከፈልን ነው:: ኢኮኖሚስት ኢኮኖሚስት ነው:: አናፂም አናፂ ነው:: ግንበኛም ግንበኛ ነው:: ትኩረታችንን የየራሳችን ሙያ ላይ ብናደርግ ጥሩ ነበር:: ነገር ግን ይህ ሊሆን ባለመቻሉ እና ሁላችንም ፖለቲከኛ እና ባለስልጣን ለመሆን በመፈለጋችን ሀገር ለማፍረስ ጫፍ ደረስን:: የውጭዎቹ መጫወቻ ሆንን::
ለውጭ ኃይል እራስን አሳልፎ መስጠት አይገባም:: ለሀገራችን በየተጠራንበት መስክ በመሰለፍ በራሳችን ዕውቀት እና አቅም መሥራት ይበጀናል:: ይህንን ሁሉም መገንዘብ አለበት:: ታሪክ የሚያሳየው ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን ነው:: ማንም ሊይዘን እና እጃችንን ሊጠመዝዝ አይችልም:: ለዚህ ፈቃደኛ አይደለንም:: ›› አለ::
ተሰማ ደስ አለው፤ ‹‹ አንጀቴን አራስከው ወንድሜ›› ብሎ በቀኙ በኩል የተቀመጠውን ገብረየስን ቀኝ ትከሻውን ጨመቅ አደረገው:: ዘውዴ ምንም ዓይነት ቃል አልተናገረም:: ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ አላሳየም:: ምክንያቱ ደግሞ እርሱም ቢሆን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በፅኑ ይቃወማል:: ኢትዮጵያን እስከ አሁን የጎተታት የውጭ ጣልቃ ገብነት ነው ብሎ ያምናልና ዝምታን መረጠ:: የተከፋበትንም ሳይገልጽ አለፈ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም