መሬት የማይተካ ሀብት ነው። በአግባቡ ካልተጠቀሙት ይባክናል። እንደ ልብስ ያልቃል። ካለቀ ደግሞ አይተካም። እንደ ወረቀት ልናባዛው አንችልም። ከሞላ ጎደል የአዲስ አበባን መሬት ጨርሰን ወደ አጎራባች ወረዳዎችና ከተሞች መቀላወጥ ከጀመርን ሰነባበትን። መሬት እንደ ልብስ እንደሚያልቅ በደንብ በተለይ የታዘብሁት ባደግሁባት የፍኖተ ሰላም ከተማ ነው። ሁላችንም ያደግንባቸውን ከተሞች ወይም የገጠር ቀበሌዎች 30 እና 40 ዓመት መለስ ብለን ብናስታውስና ዛሬ ላይ ከሚገኙበት ሁኔታ ጋር ብናነጻጽር መሬት አላቂ ሀብት መሆኑን እንረዳለን።
ወደ እኔዋ ፍኖተ ሰላም ስመለስ፤ የከተማዋ ወሰኖች ላህና አራራ የሚባሉ ወንዞች ነበሩ። ከእነዚህ ወንዞች ማዶ የገጠር ቀበሌዎች ነበሩ። በከተማዋ በስተሰሜን እና በስተደቡብ ለዛውም በከተማዋ የቅርብ ርቀት የገጠር ቀበሌዎች ነበሩ። በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎችም ሰፋፊ እርሻዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ከፍኖተ ሰላም በቅርብ ርቀት የከተማው ከብቶች የሚሰማሩበት፤ እኛም እንጨት የምንለቅምበት ጥቅጥቅ ያለ “ገዎቻ” የተባለ ደን ነበር። ከ30ና ከ40 ዓመት በኋላ ከተማዋ በአራቱም አቅጣጫ ተለጥጣ ወንዞችን ተሻግራ የገጠር ቀበሌዎችን እየሰለቀጠች ነው።
ገዎቻ በሚያሳዝን ሁኔታ ደኑ ሙሉ በሙሉ ተጨፍጭፎ ወደ መንደርና የእርሻ ቦታ ተቀይሯል። ልጆች ሆነን እንኮይ የለቀምንበት ደን ዛሬ ለምልክት እንኳ የቀረ ዛፍ የለም። ዶቅማ እንለቅምበት፤ በዓል በመጣ ቁጥር የሚጎዘጎዝ ቤርቤንዝና ቄጤማ እናጭድበት የነበረው የባከል ረግረግና ደን ዛሬ ተመንጥሮ እርሻና መንደር ሆኗል። ከተማዋ ከአምስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው ሆዳንሽ ጋር የተገናኘች ሲሆን በዚሁ ከቀጠለች በጥቂት ዓመታት ጅጋንና ማንኩሳን መጠቅለሏ አይቀርም። በነገራችን ላይ ማንኩሳ የዘመን ተሻጋሪው የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” ታሪክ መነሻ፤ የዋናው ገጸ ባህሪ የበዛብህ አባት ቦጋለ መብራቱና የእናቱ ውድነሽ በጣሙ ሀገር ናት።
ከፍኖተ ሰላም ከተማ ዳርቻ የሚገኙት እነዛ እየዋኘን ያደግንባቸው ወንዞች ዛሬ እየነጠፉ መሆኑን ስመለከት መሬት ለካ እንደ ልብስ ያልቃል ስል ለራሴ እጠይቃለሁ። አዎ መሬት እንዲህ የሚባክንና ከተፈጥሯዊ ሚዛኑ ውጭ ጥቅም ላይ ከዋለ አላቂ ነው። ከተማዋ ገበሬውን እያፈናቀለች የተፈጥሮ ሀብትን እያመናመነች መሬትን እየበላች መሆኗን ስታዘብ መሬት አላቂና የማይተካ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ናት እላለሁ። የመሬት አጠቃቀማችንን መለስ ብለን በመገምገም መላ ልናበጅ ይገባል። መሬትን ስለመጠቀም ብቻ ሳይሆን ስለመቆጠብና በአግባቡ ስለማስተዳደርና ስለማልማት ቆም ብለን ማሰብ አለብን። ሰሞኑን የጸደቀው አዋጅ በአንድም በሌላ መልኩ ለዚህ ስለሚያግዝ ሲሆን፤ ለዛሬው መጣጥፌ መነሻ ሆኗል።
የመሬት ተጠቃሚነት መብትን የሚያሰፋው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ ገብቷል። አዋጁ የአርብቶ አደሩን የመሬት አያያዝና አጠቃቀም እውቅና የሚሰጥ ነው። በግብርና ሚኒስቴር የመሬት ሕግ ባለሙያ አበባው አበበ፤ የረቂቅ አዋጁን ዓላማ፣ ይዘት፣ አስፈላጊነትና አጠቃላይ ድንጋጌዎችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ረቂቅ አዋጁ ለሴቶችና ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመሬት ላይ መብት የሚሰጥ፣ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ በመሬት ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የአርብቶ አደሩን መብትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ተቃኝቶ የተዘጋጀ ነው። በዚህም የተጠቃሚነት መብትን ማስፋት፣ የከፊል አርብቶ አደርና አርብቶ አደሩን የመሬት አያያዝና አስተዳደር ያካተተ፣ የገጠር መሬት ምዝገባና ቅየሳ ሕጋዊ ማዕቀፍ ያለው ሲሆን፤ አርብቶ አደሩ የሚገኝባቸው ክልሎች የአርብቶ አደር የመሬት አስተዳደር ሕግ የማውጣት ግዴታ እንዳለባቸው በአዋጁ ተመልክቷል።
አዋጁ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትን ለብድር ዋስትና ማስያዝ፣ የገጠር መሬትና ቅየሳ፣ የገጠር መሬት የመረጃ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ መሠረታዊ ለውጥ ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ማንኛውም ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ያለውን የመጠቀም መብት በማስያዝ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት ይችላል። ብድሩ በሚመለስበት ጊዜ ባይመለስ የመጠቀም መብቱ አበዳሪው ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚወስደው? የሚለውን መቀመጥ እንዳለበት፤ ውል በሚደረግበት ወቅት ከአሥር ዓመት በላይ ሊሆን እንደማይገባ የሕግ ባለሙያው ረቂቁ ላይ በተደረገ ውይይት ማሳሰባቸው አይዘነጋም። አዋጁ መሬት የሌላቸው ወጣቶችም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመስማማት የቤተሰቦቻቸውን መሬት በማስያዣነት በመጠቀም ብድር የመውሰድና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች መሰማራት ያስችላል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት በማንሳት በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየት አንስተዋል። በረቂቅ አዋጁ የተካተተው የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀትን ለብድር ዋስትና ማስያዝ የሚለው ድንጋጌ በጥንቃቄ መታየት ካለባቸው ጉዳዮች ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን ምላሽ ተሰጥቶበታል። የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ፤ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በሀገሪቱ አለመኖሩ የአካባቢ መራቆትና የደን መጨፍጨፍ በማስከተሉ ወጥነት ያለው አዋጅ አስፈልጓል። ሚኒስትር ዴኤታው የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ መብቶችን ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ላይም ግዴታዎችን እንደሚያስቀምጥ ጠቅሰዋል። የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ሰለሞን ላሌ፤ በአስረጅዎች መድረክ፣ ከባለድርሻ አካላትና ሌሎች ሃሳብ መስጫ መንገዶች ለአዋጁ ጠቃሚ ሃሳቦች መሰብሰባቸውን ገልፀዋል። ከዚህ ሂደት በኋላ ነው እንግዲህ አዋጁ ሰሞኑን ጸድቆ ወደ ሥራ የገባው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባው አዲሱን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሳምንት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል። የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ በንባብ ያቀረቡ ሲሆን፥ የረቂቅ አዋጁን መሻሻል አስፈላጊነት እና በምርመራው ሂደት የተከናወኑ ተግባራትንም በዝርዝር ለጉባኤው አስረድተዋል። አዋጁ የአርሶና አርብቶ አደሩን እና ከፊል አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ሀገሪቱ ከደረሰችበት ዘርፈ ብዙ እድገት ጋር እኩል ለማራመድ የሚያስችል ሲሆኑ፤ ረቂቅ አዋጁ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት በመጠበቅና በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑም ተመላክቷል።
ረቂቅ አዋጁ በምክር ቤት አባላት ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ምክር ቤቱ አዋጅ ቁጥር 1324/2016 አድርጎ አፅድቆታል። የመሬት ነገር ከተነሳ ደግሞ መሬት ላራሹን ያዋለደውን የ1966ቱን አብዮት በአለፍ ገደም ማንሳት ተገቢ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ማግሥት ጀምሮ እንደሆነ በርካታ የታሪክ መዛግብት አስፍረዋል። ለሺህ ዓመታት የቆየውን ዘውዳዊ መንግሥት መነቅነቅ የጀመሩ የፖለቲካ ቡድኖች የተነሱት በፋሺስት ወረራ ማግሥት ነው ይባላል።
በግለሰብ ደረጃ ዜጎች የፖለቲካ ለውጥ ሲጠይቁ መታየት የጀመሩት በዚሁ ወቅት መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። በተናጠል ከሚነሱ ጥያቄዎች እስከ ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ ጥያቄ በብዙ መንገዶች የሕዝብ ብሶቶች መስተጋባት የጀመሩት ከፋሽስት ወረራ በኋላ መሆኑ በስፋት ይወሳል። ይህ ዑደት ደግሞ ወደ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እስኪሸጋገር ድረስ በነበሩት ዓመታት፣ በግልም በቡድንም ሆነው ነፃነትን የጠየቁና መስዋዕትነት የከፈሉ የታዩበት እንደሆነ በብዙ ጸሐፍት ተከትቧል።
ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983›› በሚለው መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ ታሪክ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ ተቃውሞ በማንሳት እንደ ብላታ ታከለ ወልደ ሐዋሪያት ዓይነት ሰዎች ቀዳሚ እንደሆኑ ያወሳሉ። ከአልጋ ወራሽነታቸው ጀምሮ የንጉሡ አገልጋይ የነበሩት ብላታ ታከለ በጣሊያን ወረራ ወቅት ንጉሡ ከሀገር መሸሻቸው እንዳስከፋቸው ታሪክ ፀሐፊው ይጠቅሳሉ። በዚህ ያቄሙት ብላታ ታከለ ከድል በኋላ የንጉሡን መመለስም ተቃውመዋል። በተለይ ሀቀኛ አርበኞች ወደ ጎን ተብለው ባንዳ የነበሩትን ንጉሡ መሰብሰባቸው እንዳስቆጣቸው ይነገራል። በህቡህ ተቃውሞ ሲያደራጁ እየተያዙ በተደጋጋሚ ታሰሩ። ከእስር ባለፈ መንግሥት ተቃውሞ እንዲተው በሹመትና በጥቅም ሊደልላቸው ሞከረ። ሆኖም ንጉሡን አምርረው የጠሉት ብላታ ታከለ በ1962 በንጉሡ ላይ ቦምብ በመወርወር የግድያ ሙከራ አደረጉ በማለት መጽሐፉ ይተርካል። በዚሁ ንጉሡን የማስወገድ ጥረታቸው በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የሚገልጸው መጽሐፉ፣ ብላታ ታከለ ለ30 ዓመታት ንጉሡን በመቃወም እንደኖሩ ነው የሚተርከው።
በግለሰብ ደረጃ በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ ከተደረጉ ተቃውሞዎች መካከል በሁለቱ ወንድማማቾች ግርማሜ ነዋይና መንግሥቱ ነዋይ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም እንደ አብነት ይጠቀሳል። መንግሥት የመገርሰስ ሙከራው በቀጣይ ለመጡ የፖለቲካ ለውጦች አርዓያ በመሆን የሚያክለው እንደሌለ ይነገራል። የጦርም የቀለምም ትምህርት የቀሰሙት ወንድማማቾቹ ጥቂት ቁልፍ የሚባሉ ባለሥልጣናትን አሰባስበው፣ በታኅሣሥ 1953 ዓ.ም. የንጉሡን ለጉብኝት ከሀገር መውጣት ተገን አድርገው በመሩት የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ውጤቱ ባይሰምርም ሥርዓቱን በደንብ መነቅነቃቸው ይወሳል። ሁለቱ ወንድማማቾች የቆሰቆሱት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ሥርዓቱን መለወጥ አልቻለም።
ይሁን እንጂ የመፈንቅለ መንግሥቱ አስተባባሪዎች ሙከራ የንጉሡ ሥርዓት አይነኬ ነው የሚለውን ጥላ መግፈፉና ቀጥለው ለመጡ የነፃነት ትግሎች አርዓያ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ሥዩመ እግዚአብሔር ተብሎ የሚጠራውንና አይነኬውን ሥርዓት ደፍሮ በመቃወም ቀዳሚ ከሆኑ ሌሎች ሰዎች መካከል የብርሃኑ ድንቄ (አምባሳደር) ታሪክ በብዙዎች ይነሳል። በንጉሡ መንግሥት በተለያዩ ኃላፊነቶች ተመድበው የሠሩት ብርሃኑ (አምባሳደር) በሳዑዲ ዓረቢያና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል። እ.ኤ.አ. በሰኔ 1965 አድሏዊና የነቀዘ ያሉትን የንጉሡን መንግሥት በይፋ ከድተው በአሜሪካ ጥገኝነት መጠየቃቸው ይነገራል።
የንጉሡን መንግሥት አላገለግልም ብለው ከአምባሳደርነታቸው መልቀቃቸው በጊዜው ታላቅ ድፍረት እንደነበር፣ ‹‹አይ ስታንድ አሎን›› ብለው በጻፉትና ‹‹ብቻዬን ቆሜያለሁ›› በሚል ርዕስ በተተረጎመው ግለ ታሪካቸው በሰፊው ከትበውታል። የዚያን ጊዜውን መንግሥት ተቃውሞ በአሜሪካም በመደበቅም ቢሆን ከባድ መስዋዕት ሳይከፍሉ ማምለጥ እንደማይቻል የሚገልጹት ብርሃኑ (አምባሳደር)፣ የመጣው ይምጣ ብለው ለንጉሡ በቀጥታ በጻፉት ደብዳቤ ተቃውሟቸውን አስተጋብተዋል። አምባሳደሩ በዚህ ደብዳቤያቸው ከማስመሰልና ከመሸንገል ይልቅ፣ በሥርዓቱ ላይ እሳቸውም ሆኑ ብዙ ሕዝብ በሆዱ የቋጠረውን ያሉትን ብሶት በጠንካራ ቃላት አስተጋብተውታል።
‹‹ሁሌም እንደምነግርዎት ለግርማዊነትዎ በቃላት የምንገልጽልዎና ህሊናችን ውስጥ የሚመላለሰው ሐሳብ እንደማይጣጣም ነው። አንዳንድ ሰዎች በአስመሳይነት ቢገፉበትም ውስጣቸው ላለው ግጭት እኔ አንድ ምስክር ነኝ። በነፃ ህሊናዬ አሁንም ለግርማዊነትዎ ማሳወቅ የምፈልገው ነገር ቢኖር ሀገራችን የምትድነው በከፍተኛ ሞራልና ነፃነት እንጂ እርስዎን በማሞገስና በማሞካሸት አለመሆኑን ነው። ሀገሪቱ ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ በእርስዎ ትዕዛዝ በሚንቀሳቀሰው የጽሕፈት ሚኒስቴር እንደምትመራ የማያውቅ ሰው አለ ብለው ይገምታሉ? ሕዝቡም ነፃ ሆኖ እንዲናገር ከተፈቀደለት ሊነግርዎት ይችላል።
የፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ያለውን ብልሹ አሠራርና ግርማዊነትዎ በወንጀለኛና በፍትሐ ብሔር መቅጫ ሕግ ጠቅላይ ዳኛ ሆነው ፍትሕን እንዳሻዎ እንደሚነዱት የማያውቅ ያለ ይመስልዎታል? የፀጥታ ኃይሎችዎ በማናለብኝነት የሚፈጽሙት ተግባር የሌሎችን መብቶች እንደሚዳፈር የታወቀ ነው። በዚህ ደብዳቤዬ በግርማዊነትዎ አገዛዝ ዘመን የተፈጸሙትን በደሎችና ሥቃዮች ዘርዝሬ መጨረስ ያስቸግረኛል። ከሁሉ በላይ ግርማዊነትዎ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለው እንቅስቃሴ በተለይ የብሔሮች ጥያቄ አንድ ወቅት ፈንድቶ አደጋ እንደሚያመጣ እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ።
ግርማዊነትዎ አቤቱታዬ እንደ ፊተኞቹ ደብዳቤዎቼ ያነጣጠረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለሥቃይና ለእንግልት የዳረጉትን ጭቆናዎችና ስህተቶች እንዲያስተካክሉና አሁንም ቢሆን ጊዜው እንዳልመሸ ለማሳሰብ ጭምር ነው፤›› በማለት ነበር አምባሳደሩ ለንጉሡ በጻፉት ደፋር ደብዳቤ ቀድመው ያስጠነቀቁት። በቀጥታ ሥርዓቱን ለመቃወም ከደፈሩ ሰዎች በተጨማሪ ሀገሪቱ ሊገጥማት የሚችለው አደጋ ቀድሞ የታያቸው ግለሰቦች በእነዚህ ጊዜያት ለንጉሡ መንግሥት ሲያሳስቡና ሲወተውቱ መቆየታቸው ይነገራል። ይሁን እንጂ የንጉሡ መንግሥት እነዚህን ማሳሰቢያዎችም ሆነ ማስጠንቀቂያዎች ተቀብሎ ማስተካከያ እንዳልወሰደ ብዙዎች ይናገራሉ።
በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩትና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ የንጉሡ መንግሥት የማይሰማ መንግሥት እንደነበር ገልጸዋል። ‹‹አፄ ኃይለ ሥላሴ በፍጹም ማንንም የሚሰሙ መሪ አልነበሩም። አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ብቻ ሳይሆኑ ለሥርዓቱ በጣም የቀረቡ አራት ታዋቂ ሰዎችም ከእነ መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ደብዳቤ ጽፈውላቸው ነበር።
ጄኔራል ዐቢይ አበበ፣ ሀዲስ ዓለማየሁና ተክለጻዲቅ መኩሪያ ያሉበት አራት ሰዎች ሆነው በሀገሪቱ ሊደረግ የሚገባውን ለውጥ ጽፈው ለንጉሡ ሰጥተዋቸዋል። በሀገሪቱ የፖለቲካ ማሻሻያ ተደርጎ ልክ እንደ እንግሊዞቹ ሕገ መንግሥታዊ ዘውዳዊ ሥርዓት ተፈጥሮ ሙሉ የመንግሥት ሥራው በጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመራ ጠይቀዋቸው ነበር። እሳቸው ንግሥናቸው ሳይሻር መንግሥታዊ ሥራውን እንዲያስረክቡ ተጠይቀው ነበር። ንጉሡ ግን ይህን ሁሉ ውድቅ ነው ያደረጉት፤›› በማለት የንጉሡ መንግሥት ከአብዮቱ መፈንዳት ቀድሞ ያልተጠቀማቸው ብዙ ዕድሎች እንደነበሩ ተናግረዋል። ጽሑፉን ሳዘጋጅ መረጃዎቹን ከመጻሕፍት፣ ከሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎችም ምንጮች ተጠቅሜያለሁ!
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም