ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝ ግዙፍ ሀገር ነች። ግዙፍነቷ ከሕዝብ ብዛት እስከ ኢኮኖሚ ጥንካሬ ድረስ ይገለጻል። ከዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እስከ ጠንካራ መከላከያ እና የጸጥታ ተቋማት ግንባታ ድረስ ይዘልቃል። የነጻነት ተጋድሎዋና እና የጥቁር ሕዝቦች አለኝታ መሆኗም ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ያጎላዋል።
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ እምብርትና የስበት ማዕከል ናት። ሀገሪቱ ሁሉንም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች በማዕከልነት በማስተባበር አካባቢያዊ ጥምረት እንዲፈጠር የበኩሏን አስተዋጽኦ ማበርከት ከጀመረች ውላ አድራለች። በተለይም በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውም የህዳሴ ግድብን በመገንባት በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር እያደረገች ካለችው ጥረት ጎን ለጎን በዓለም ላይ ከነዳጅ ቀጥሎ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የስንዴ ምርት ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ቀጣናዊ ትስስሩ ተጨባጭ እንዲሆን አየሠራች ነው።
ለቀጣናው ሀገሮች ዘላቂ የሆነ ታዳሽ ኃይል ከማቅረብም በተጨማሪ፣ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ ጭምር ለቀጣናዊ ትስስሮቹ ጉልህ አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ እያደረገች መሆኑንም ብዙዎች በስኬት ያወሱታል። የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ቀጣናውን በማስተሳሰር ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት መፍጠር ከቻሉ፣ ሰላምም ሆነ ዳቦ ለቸገረው ክፍለ አህጉር ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ ከ13 ዓመታት በፊት የጀመረችው ታላቁ የዓባይ ግድብ ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቋል። ግድቡ ከወዲሁ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የኃይል ምንጭ በመሆን ምሥራቅ አፍሪካን በማስተሳሰር ላይ ይገኛል። ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የቀጣናውን ሀገራት በኃይል በማስተሳሰር የጋራ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ በር ይከፍታል።
እንደ ዓባይ ግድብ ሁሉ ኢትዮጵያ በግብርናው ረገድም ቀጣናዊ ትስስሩን የማጠናከር ሥራ በስኬታማነት በማከናወን ላይ ትገኛለች። በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ ስንዴ ምርት ነው። ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት እራሷን በመለወጥ ታሪክ ሠርታለች፤ ለቀጣናው ሀገራትም ኩራት ሆናለች።
በ2015/16 የምርት ወቅትም ኢትዮጵያ 129 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት ታመርታለች ተብሎ ይጠበቃል። 97 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ነው። 32 ሚሊዮን የሚጠጋውን ወደ ውጭ ልካለች። አብዛኛውም ምርት ወደ ጎረቤት ሀገራት የሄደ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም “ETHIOPIAN AID” በሚል በችግርና በጦርነት ውስጥ ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት እርዳታ የመስጠት ዕቅድ እንዳላት በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ይህቺ የስዕበት ማዕከል እና የቀጣናው ትስስር ማሳያ የሆነችው ሀገር ሰፊ ሕዝብ ያላትና ከባሕር ከ60 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ርቀት ቢኖራትም ባሕር አልባና ወደብ አልባ ሆና ላለፉት 33 ዓመታት ቆይታለች። ይህ ደግሞ ሀገሪቱን ለፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲ ውጣ ውረድ ዳርጓታል። ይህቺ ሰፊ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ችግሮቿ እየሰፉና እየከፉ ከሄዱ ችግሮቿ ከሀገር አልፎ ለቀጣናው የሚደርስ ነው።
ይህ ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን በማንገብ የባህር በር ጥያቄዎቹን ለቀጣናው ሀገራት አቅርባለች። በብቸኝነት ጥያቄውን የተቀበለው ሶማሊ ላንድ ብቻ ናት። ይህን መሠረት በማድረግም ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ በመሪዎቻቸው መካከል የመግባቢያ ሰንድ ተፈራርመዋል።
ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል።
የአፍሪካ ቀንድ የበርካታ ኃያላን ሀገራትን ትኩረት የሚስብ ስትራቴጂክ ስፍራ ነው። በተለይም አካባቢው በቀይ ባህርና በናይል ውሃ ተፋሰስ መሀል መገኘቱ የበርካታ ሀገራትን ቀልብ ሊስብ ችሏል። የቀይ ባሕርና የናይል ፖለቲካ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በማወዳጀትም ሆነ በማራራቅ ከፍተኛ ሚና ያለውን ያህል አካባቢውን በቁጥጥራቸው ለማዋል ህልም ያላቸውም ሀገራት የሚራኮቱበት ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በር እና የወደብ ባለቤት መሆኗ በግጭትና አለመረጋጋት የሚታመሰው የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ የተሻለ መረጋጋትና ሰላም እንዲሰፍንበት ያደርጋል። ሰፊ የሕዝብ ቁጥርና ጠንካራ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የሚታየውን የሽብር እንቅስቃሴ፣ የመርከቦች ጠለፋና እገታ፣ሕገወጥ ስደትና የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ሕገወጥ የመሳሪያ ዝውውርን በመቆጣጠር ረገድ አይነተኛ ሚና መጫወት ትችላለች።
ይህም አስተዋጽኦዋ ከቀጣናዊው ሀገራት አልፎ ለዓለም ሰላምና መረጋጋት አይነተኛ ሚና የሚጫወት ነው። ይህንኑ በመረዳት ኬንያን የመሳሰሉ የቀንዱ ሀገራት ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የምትሆንባቸውን አማራጮች በማፈላለግ ላይ ናቸው። ከአንድ ወር በፊትም ኬንያ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ያስችላል ያለችውን ቀጣናዊ የባሕር ጠረፍ አገልግሎት አጠቃቀም ስምምነት አማራጭ አቅርባ ነበር።
ያቀረበችው አማራጭ በቀጣናው የሚገኙ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በንግድ ስምምነት መሠረት የባሕር መተላለፊያ አገልግሎት እና ጥቅም የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም ተገልጿል። ኬንያ የጀመረችው ጥረት የሚበረታታ ነው። ቢያንስ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት ዕውቅና የሚሰጥና የቀጣናውም ሀገራት ከፉክክርና ግጭት ወጥተው የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ያሳየ ነው።
በአጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከመተባበር ውጪ አማራጭ የላቸውም። አካባቢው በኃያላን ሀገራት ተጽዕኖ ስር የወደቀ በመሆኑ ደካማ መንግሥታት ወይም መንግሥት አልባ ሀገራት ሲፈጠሩ እናስተውላለን። ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ዘልቃለች። አሁን ሱዳን ለሁለት ተከፍላ ወደ መንግሥት አልባነት እያመራች ነው።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር የአካባቢውን ሀገራት ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅና የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ቀጣና ለማድረግ ከቀጣናው አልፋ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ያላትን ኢትዮጵያ በአካባቢው ላይ አሻራዋን እንድታሳርፍ ማድረግ ይገባል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም