የፕሪቶርያው ስምምነትና የማዕከላዊ መንግሥቱ ጥረት

ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉዓላዊነትን፣ የግዛት አንድነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ዕልባት አግኝቷል፡፡ የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ እርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመርና የሀገሪቱን የድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ አላማ አለው።

በአጠቃላይ ሲታይ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እንዲሁም ይህንን ተከትሎ በኬንያ ናይሮቢ የተፈረመው ባለ 12 ነጥብ የማስፈጸሚያ ሰነድ የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች የያዘ ነው፡፡

የመጀመሪያው ጉዳይ ሕግ መንግሥታዊ ሥርዓትን ማስከበር ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሚመነጭ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲካሄድ የማድረግ ስልጣን ያለው የምርጫ ቦርድ እንደሆነ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ከዚህ ድንጋጌ በተቃረነ መልኩ በትግራይ ክልል ‹‹ምርጫ›› ተካሂዷል በሚል የትግራይ መንግሥት መቋቋሙን ስሁት በሆነ መልኩ ለማወጅ መሞከሩ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የተካሄደውን ‹‹ምርጫ›› እንዳልተካሄደ እንደሚቆጠር በመግለጽ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቆ ነበር፡፡

ይህንኑ ሃሳብ የሚያጸና ውሳኔ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ በተካሄደው ስምምነትም ሰፍሮ እናገኘዋለን። ምርጫው ሕገ ወጥ በመሆኑም በትግራይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋማል፤ በሂደትም ምርጫ ተካሂዶ ክልሉን የሚያስተዳድር መንግሥት ይጸናል፡፡ ስለሆነም አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ሕዝብን ሰላም የሚያስጠበቅውና ሕጋዊ ውክልና ያለውም የፌዴራል መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በትግራይ ሕዝብ ተመርጫለሁ የሚል ሕጋዊ አካል የለም፡፡ ስለሆነም ከዚህ ውጭ የሚቀርቡ ጉዳዮች በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ተቀባይነት የላቸውም፤ በዚህ ጉዳይ ሊቀመጥ የሚችል ቅድመ ሁኔታም እንደሌለ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡፡

በሌላ በኩል የፕሪቶርያው ስምምነት በግልጽ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ መከላከያ ሠራዊት ብቻ መኖር አለበት የሚለው ነጥብ ነው፡፡ በስምምነቱ ላይ ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን ትጥቅ ማስፈታትን በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ እንዳለ ከስምምነት የደረሱበት ጉዳይ ነው።

ይሄንን እውነታ ወደጎን ትቶ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ለማጓተት መሞከር አይችልም። በፕሪቶርያው ስምምነትም ሆነ በናይሮቢው የማስፈጸሚያ ሰነድ መሠረት ስምምነቱን ወደ ተግባር ከመለወጥ ውጭ ሊቀመጥ የሚገባ ቅድመ ሁኔታ አይኖርም፡፡

ሌላው በፕሪቶርያው ስምምነት የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ውሳኔ ካሳለፉባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን የማስጠበቅ ስልጣን የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ በተለይም ከውጭው ዓለም ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችና ስምምነቶች ሁሉ ሊከናወኑ የሚችሉት በፌዴራል መንግሥት ብቻ መሆኑ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ነጥብ ነው፡፡ ይህው ሃሳብም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 8 ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ የፕሪቶርያው ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸናና የዜጎችን ሰቆቃ የሚቀርፍ ስምምነት በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር ነው፡፡ ስምምነቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እፎይታ አጎናጽፏል፡፡

ከፕሪቶርያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው፡፡ በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችንና ሰብዓዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ለማድረስ መሠረት የጣለ ነው፡፡ በዚሁ መሠረትም በትግራይና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎቶች መልሰው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ አስችሏል፡፡ የሕዝቡን ችግር በፍጥነት ለመቅረፍም አሁንም ድረስ ሥራዎች በስፋት እየተሠሩም ይገኛሉ።

ሌላው የፕሪቶርያው ስምምነት የማዕዘን ድንጋይ ግጭትን በዘላቂነት ማስቆም ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ለ10 ቀናት ከመከሩ በኋላ በዘላቂነት ግጭት ለማቆም ተስማምተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ለማረጋገጥ በርካታ መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ ነው፡፡ በመስዋዕትነቱም የሀገሩን ሉዓላዊነት አጽንቷል፤ አንድነቱን አጠናክሯል፤ ዳር ድንበር አስከብሯል፡፡ የኢትዮጵያን መፍረስ ለሚመኙ ባዕዳን በቂ ትምህርት ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ወደማይፈልጉት ጦርነት ከመግባታቸው በፊት በርካታ የሰላም ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ሽማግሌዎችንና ታዋቂ ሰዎችን ጭምር በመላክ ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ አውዳሚው ጦርነት ውስጥ ሆና ‹‹የሰላም ያለህ›› ሲሉ ቆይተዋል። ለሰላም ሲባል የትም ቦታ፤ በማንኛውም ጊዜና ርዕሰ ጉዳይ ለመወያየት ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጥረቱም ፍሬ አፍርቶ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ታሪካዊ የሚባል የሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡

“በዘላቂነት የጦር መሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማ ለማድረግ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ግጭት እንዲቆም ተስማምተናል” ብለዋል ሁለቱ አካላት።

ሕወሓት እና መንግሥት በአንድ ድምጽ ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎችን አስከትሏል ካሉ በኋላ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ከግምት በማስገባት ግጭቱን ምዕራፍ ከኋላችን ትተን “በሰላም እና በመቻቻል ለመኖር” ተስማምተናል ማለታቸው የሚታወስ ነው። በዚሁ መሠረት አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ቆይቷል፡፡

የፕሪቶርያው ስምምነት ሌላኛው ማዕዘን ትጥቅ ማስፈታት ነው፡፡ የኢትዮጵን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ እና መጠበቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት ሕወሓት እና ኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትን ለማስከበር መስማማታቸው የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች “በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም የፌዴራሉን ተቋማትና አየር ማረፊያዎችንና አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ ዋነኛ መሠረተ ልማቶችን” ሙሉ ለሙሉ እንደሚቆጣጠሩ ተጠቅሷል።

ለተጎጂ ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታን ማቅረብ ሌላኛው የፕሪቶርያው ስምምነት አካል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የተፋጠነ ርዳታ እንዲያደርስ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

ከላይ የተዘረዘሩት ዋነኛዎቹ የፕሪቶርያው ስምምነት አካል ሲሆኑ ስምምነቱ ከተፈረመበት ከጥቅምት 23 ቀን 2015 ጀምሮ ያለው አተገባበር ግን የተሟላ ነው ብሎ ለመውሰድ አያስደፍርም፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው አንድ ዓመት በስምምነቱ መሠረት የተፈጸሙ ጉዳዮችን እና ቀሪ ቤት ሥራዎች ምንድን ናቸው የሚለውን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛው መፍትሔ የፕሪቶርያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን የኢፌዴሪ መንግሥት በጽኑ ያምናል። ይሄንንም በተመለከተ የፌዴራሉ መንግሥት ከመነሻው እስካሁን ያለው አቋም ወጥ እና የማይናወጥ መሆኑን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የፕሪቶርያው ከአቋም ባሻገር ተግባራዊ እንቅስቃሴም አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ ከስምምነቱ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተመራ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች ያሉበትን ቡድን ወደ ትግራይ የላከው የፌዴራል መንግሥት ነው።

የፌዴራል መንግሥት ተቋማትና ክልሎች ለትግራይ ሕዝብ ድጋፋቸውን ያሳዩት ወዲያው ነው። የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በመቀሌ ተገኝተው ለሕዝቡ ያላቸውን አጋርነት በማሳየት የሚቻላቸውን ድጋፍ በዓይነትና በገንዘብ አድርገዋል፡፡

በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት የገዢው ፓርቲ ሊኖረው የሚችለውን ድርሻ በመተው ሕወሓትና የታጣቂ አመራሮች ጊዜያዊ መንግሥቱን እንዲያቋቁሙ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ከልዩ ልዩ አካላት ተውጣጥተው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የሚካተቱ አመራሮች እስኪተዋወቁና እስኪግባቡ ድረስ የትግራይ ሕዝብ የችግር ወቅት እንዳይራዘም በማሰብ ነው። በዚህም ለትግራይ ሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝት ከፕሪቶርያው ስምምነት በላይ በመሄድ አረጋግጧል፡፡

በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን የትምህርት ሂደት ለማስቀጠል ልዩ ልዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የሰው ኃይልና የተቋም አቅም ግንባታ፣ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ሥልጠና፤ የዩኒቨርሲቲዎችን የአመራር ቦርድ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል፡፡ በትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም በኩል 165 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በዕቅድ ተካትቶ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ለአንደኛና ለሁለተኛ ሩብ ዓመታት ማስፈጸሚያ 517.9 ሚሊየን ብር በገንዘብ ሚ/ር በኩል ለክልሉ ተልኳል፡፡

በትምህርት ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት አንድ ነጥብ 46 ቢሊየን ብር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ በ2016/17 ዓ.ም በትምህርት ቤቶች ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች የ111 ነጥብ 08 ሚሊየን ብር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ የትምህርት ተቋማት መልሶ ግንባታ 441 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል።

የሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ተመልሷል። በፋብሪካና በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ አካላትን በመደገፍ ሥራ ጀምረዋል፡፡ ለወርቅ ሥራ የሚያገለግሉ ሁለት ከባድ ተሽከርካሪዎች በርዳታ ተለግሰዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የክልሉን የዘርፍ መሥሪያ ቤት ለማጠናከር ከተወሰዱ ርምጃዎች ባሻገር ለካፒታል በጀት አራት ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፤ ለመደበኛ በጀት 11 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር፣ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 400 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ 16 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በ2015/16 ለክልሉ ተሰጥቷል፡፡ በክልሉ ለሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በድምሩ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተላልፎላቸዋል፡፡ በልማት አጋሮች በኩል ደግሞ የአንድ ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ድጋፍ ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በቻናል አንድ አንድ ነጥብ 7 ቢሊየን እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር በክልሉ ባቋቋመው ጽሕፈት ቤት በኩል፣ በትግራይ ለሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እና ለአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ565 ሚልየን ዶላር በላይ ፈሰስ ተደርጓል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክትም 65 ሚሊዮን ብር ለክልሉ ተላልፏል።

በጦርነቱ ወቅት የተቋረጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም በልዩ ፕሮግራም የክልሉ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ለዘጠኝ ከተሞች የፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ከ409 ሚሊየን ብር በላይ እና ከ7 ሚሊየን ዶላር በላይ ለክልሉ ተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ እና ለመንገድ ፕሮጀክት ጥገና ከ418.6 ሚሊየን ብር በላይ ወደ ክልሉ ልኳል፡፡ ለትግራይ ገጠር መንገድ ጥገና ከመንገድ ፈንድ ከብር 107 ሚሊየን ብር በላይ፤ የ2026 በጀት ቅድመ ክፍያ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ተልኳል፡፡ በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል ደግሞ በጠቅላላው የ4.2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

የክልሉን የጤና ዘርፍ አቅም ለመገንባት እንዲቻል 164 ልዩ ልዩ ባለሞያዎች ተመድበው ድጋፍ እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ ሁሉንም በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት በመደገፍ ወደ አገልግሎት ለመመለስ የተቻለ ሲሆን፣ ሁሉም ሆስፒታሎች ተኝቶ የማከም አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ሁለገብ እንቅስቃሴ 217 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ተችሏል፡፡

በ2015/16 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለክልሉ የቀረበ ሲሆን፣ ለአንድ ሺህ 427 አርሶ አደሮች መጠቀሚያ የሚሆን አንድ ሺህ 720 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በዚሁ የምርት ዘመን ፕሮጀክቶች በኩል ለክልሉ ተገዝቶ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በ2015/16 የምርት ዘመን ክልሉ 80 ሺህ የተለያዩ ማዳበሪያዎች ጠይቆ ሁሉም ቀርቦለታል፡፡ ለ2016/17 ምርት ዘመን ደግሞ ክልሉ ከጠየቀው መካከል የ70 ሺ ቶን ማዳበሪያ ተገዝቷል፡፡

ለግብርና መገልገያ የሚሆኑ የትራክተሮች፣ የውኃ ፓምፖች ድጋፍ ለአርሶ አደሮች ተለግሷል፡፡ በአጠቃላይ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ለክልሉ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ይህ ድጋፍ ቀደም ሲል ለክልሉ ሲሰጥ ከነበረው አንጻር ከ5 ዓመታት በጀት በላይ ነው፡፡

በሕወሓት ወገን ግን አሁንም በበርካታ ሺ የሚቆጠር ታጣቂ ትጥቅ አልፈታም፡፡ ሠራዊት አልተበተነም፡፡ ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግሮች አልተቋረጡም። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ የፕሪቶርያውን ስምምነት የሚሸራርፍና በሂደትም ወደ ግጭት ሊያስገባ የሚችል ነው፡፡ ስለዚህም ለሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መሠረት የሆነውና የዜጎች ሰቆቃ እንዲበቃ ያደረገው የፕሪቶርያው ስምምነት ቅድመ ሁኔታ የለውም፤ ስለሆነም በስምምነቱ መሠረት መፈጸም ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ያለውም ብቸኛው አማራጭ ይህንን ስምምነት ማስፈፀም ነው።

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You