ስፖርትን ከቱሪዝም ያጣመረው ታላቁ የበቆጂ ሩጫ

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስመጥር ከሆኑ አትሌቶች መካከል በርካቶቹ የበቀሉት በቆጂ ምድር ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊና ተተኪ አትሌቶችን አሁንም እያፈራ የሚገኘው ይህ የአትሌቲክስ ማዕከል የአየር ሁኔታው፣ የቦታ አቀማመጡ እንዲሁም የሕዝቡ አኗኗር ሁኔታ ለስፖርቱ ምቹ በመሆኑ አትሌቲክስን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ እንዲኖር አድርጎታል፡፡

‹‹የሯጮቹ ምድር›› በሚል ስያሜ የሚታወቀው በቆጂ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ቤተሰብ ዘንድ በስፋት የሚታወቅና የሚጎበኝም ጭምር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስፍራው በሚገባው ልክ ያልተሰራበት አትሌቶችና ነዋሪዎቹም የሚገባቸውን ጥቅም ያላገኙበት ነው፡፡

ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በየዓመቱ የታላቁ በቆጂ ሩጫን በማዘጋጀት የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ለየትኛውም የስፖርት ዓይነት ምቹ የሆነ የአየር ሁኔታ እንዲሁም መልክዓ ምድራዊ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ በዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ በመላው ዓለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ ዘርፎች መካከል አንዱ ስፖርት ቱሪዝም ሲሆን፤ ውድድሮችን በማዘጋጀት፣ ስታዲየሞችንና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በመገንባት እንዲሁም በስፖርቱ አዝናኝና ሳቢ ክንውኖችን በማሰናዳት በርካታ ሀገራት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እንደ ታላቁ ሩጫ ያሉ ስፖርታዊ ተቋማት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ያለውን ሁኔታ በማነቃቃት ላይ ይገኛሉ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ባላት ሀብት ልክ ተጠቃሚ ልትሆን አለመቻሏን እንደ በቆጂ ካሉ ተሞክሮዎች መረዳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ስም በበጎ እንዲነሳ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የአትሌቲክስ ስፖርት ነው፤ አትሌቲክስ ሲነሳ ደግሞ በቆጂ የማትዘነጋ ስፍራ ናት፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረኮች ተሳትፎዋ ከሰበሰበቻቸው 58 ሜዳሊያዎች መካከል 18 የሚሆኑት (10የወርቅ፣ 3 የብር እና 5 የነሐስ) ሜዳሊያዎችን ያስመዘገቡ የኮከብ ሯጮች ምድር በቆጂ ባፈራቻቸው አትሌቶች በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት በአጠቃላይ በመድረኩ ከተመዘገቡት 23 የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል የ10 መነሻ ከአዲስ አበባ ከተማ 220 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው በተራሮች የተከበበችውና ለምለሟ በቆጂ ናት፡፡ ከሩጫ ባለፈ እንደ ብስክሌት እና ተራራ መውጣት ላሉ ስፖርቶችም በእጅጉ አመቺ መሆኗን ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡

በታላቁ ኦሊምፒክ በሴቶች ዘርፍ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ፋጡማ ሮባ፣ እጅጋየሁ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ ቲኪ ገላና፣ መስታወት ቱፋ፣ ትዕግስት ቱፋ፣ ለሜቻ ግርማ፣… የመሳሰሉት የኦሊምፒክ፣ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች የአትሌቲክስ ቻምፒዮን የሆኑ አትሌቶች ከዚችው መንደር ነው የተገኙት፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ስፍራውን የአትሌቲክስ እና የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ‹‹ታላቁ የበቆጂ ሩጫ›› በሚል የሩጫ ውድድር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ዘንድሮም ለ3ኛ ጊዜ በመጪው እሁድ ግንቦት 18/2016 ዓ.ም ውድድሩ የሚደረግ ሲሆን፤ 1ሺ500 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም የአትሌቲክስ ወዳድ የሆነውን ነዋሪ ጨምሮ ጀማሪና ታዋቂ አትሌቶች ይሳተፉበታል፡፡

የሩጫ መርሀ ግብሩን ተከትሎም የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ ሩጫው የሀገር ውስጥና የስፖርት ቱሪዝምን ለማሳደግ ከማስቻሉ ባለፈ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችንም ለመሳብ የሚጠቅም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከስፖርታዊ ሁነቱ ባለፈ ሌሎች የዞኑን የቱሪዝም ሀብትና ባህሎች ለማስተዋወቅም ጠቀሜታ አለው፡፡ ለዚህም የቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ ከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡ ለአትሌቶች ምቹ በሆነው ምድር በሚዘጋጀው የበቆጂ ሩጫ ላይ ታዋቂ አትሌቶች ጭምር ተሳታፊ እንዲሆኑና እንዲጎበኙም አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የበቆጂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ብርሃኔ ነገሰ፤ በቆጂ ከሯጮች መፍለቂያነቷ ባለፈ በርካታ የተፈጥሮና ባህላዊ የሆኑ ቱሪስቶችን መሳብ የሚችሉ ሀብቶች ያላት መሆኑን ገልፔዋል፡፡ የበቆጂን ታሪካዊ ስፍራነት ለማሳየት እንዲሁም ይበልጥ እንዲታወቅ ለማድረግ ለሚካሄደው ሩጫ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል፡፡ ሩጫው ወደፊትም የሀገርን ሰንደቅ የሚያጎሉ ተተኪ አትሌቶችን ለመፍጠር ከመፍጠሩም ባለፈ በቱሪዝም እንዲሁም በከተማዋ ኢንቨስት እንዲያደርግ የሚጋብዝ በመሆኑ ሁሉም የራሱን ተሳትፎ እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You