ተጣጣፊ እና ተንቀሳቃሽ ዘመናዊ ሊስትሮ ፈጣሪው ወጣት

ወጣት ሙሀባ ረዲ ይባላል። በቴክኒክና ሙያ ተቋም በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ትምህርት ዘርፍ ትምህርቱን ተከታትሏል። ‹‹አዲስ ባለታንከሯ ሊስትሮ›› የተሰኘ ዘመናዊ የጫማ ጽዳትና ውበት (የሊስትሮ) ቁሳቁስን አሟልቶ የያዘ የፈጠራ ሥራ ባለቤት ነው። ይህ የፈጠራ ሥራ የጫማ ማሳመርን /የሊስትሮ ሥራን / በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ ያሟላ ከመሆኑ ባሻገር የመንገድ መሠረተ ልማት እንዳይበላሽ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

የሊስትሮ ሥራ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ሥራው ግን የመንገድ መሠረተ ልማት እንዲበላሽ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆነ ወጣት ሙሀባ ይናገራል። አንድ ሊስትሮ በየቀኑ እስከ 36 ሊትር ውሃ ስለሚጠቀምና ውሃም በመንገድ ላይ ስለሚያፈስ መንገዱ እንዲበላሽ ያደርጋል። በመኪናና በሌሎች ምክንያቶች ከሚበላሸው መንገድ ባልተናነሰ በሊስትሮ ሥራ ወቅትም መንገድ የሚበላሽበት ሁኔታ ይፈጥራል። መንገዱ የሚፈለገውን ጥቅም ሳይሰጥ ቶሎ እንዲበላሽ ምክንያት እየሆነ ነው ሲል ያስረዳል።

ወጣት ሙሀባ እንደሚለው፤ አንድ ሊስትሮ አነሰ ከተባለ ሁለት ካሬ ሜትር ቦታ ሊይዝ ይችላል። ሥራው ደግሞ በአብዛኛው በመንገድ አካል ላይ የሚከናወን ነው፤ ሥራው የሚካሄድበት የመንገድ አካል የሆነ ቦታ በየቀኑ ውሃ ስለሚደፋበት ውሃ ይጠግብና ማበጥ ይጀምራል። ይህም የመንገድ ላይ ንጣፍ ከቦታው እንዲንቀሳቀስ ስለሚያደርገው አንዱ አንዱን እንዲነሳ እያደረገ እስከ መቶ ካሬ ሜትር ርቀት ድረስ ያለውን ንጣፍ ሊያስነሳው ይችላል። በተጨማሪም ውሃ ወደ ውስጥ እየሰረገ ሲመጣ መጥፎ ሽታ ይፈጥራል። ይህ የፈጠራ ሃሳብ ደግሞ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ የሚሆን ነው።

በተለይ አዲስ አበባ ከተማ እየተዋበች እንደመሆኑ ይህን መሠረተ ልማት በመጠበቅ ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ እና ከከተማ ስታንደርድ ጋር አብሮ የሚሄድ አሠራርን መከተል ያስፈልጋል ሲል ገልጾ፣ በሌላ በኩል ፈጠራው የሊስትሮ ሥራ ማንም ሰው ዝም ብሎ የሚገባበት ሳይሆን የተከበረ ሙያ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል ይላል።

‹‹አዲስ ባለታንከሯ ሊስትሮ›› የፈጠራ ሥራ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የተሰሩ የሊስትሮ ቁሳቁስን አሟልቶ የያዘም ነው። ሊስትሮዎች በሥራቸው እንዲተማመኑ እንደሚያስችላቸው ወጣት ሙሀባ ይናገራል። ሊስትሮ መሥራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አማራጭ አጥቶ የሚገባበት ሳይሆን ሥራዬ ብሎ አምኖ የሚሠራው እንዲሆንም ያደረጋል ይላል።

የፈጠራ ሥራው፣ ተጣጣፊና ተንቀሳቃሽ በመሆኑ በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳቀስና ማዘዋወር ይቻላል። ወደጎን 61 ሳንቲሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ቁመቱ ደግሞ 2ሜትር ነው፤ 60 ሳንቲሜትር ወደፊት የጥላ ከለለ አለው። መቀመጫም አለው። የመቀመጫው ከፍታ 12 በ30 ሳንቲ ሜትር ሲሆን፤ ስፋቱም 20 ሳንቲሜትር ነው። በተጨማሪም የውሃ ማፍሰሻ ታንከር፣ የሊስትሮ እቃዎች (ብሮሾችና ሌሎች) ፣ የልብስ ማስቀመጫ እና የራሱ የደንብ/ የሥራ/ ልብስ (ዩኒፎርም)እንዲኖረው ተደርጎ የተሠራ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት አብሮት የሚሄድና እሱን የሚመጥን የሊስትሮ አገልግሎት መስጠትን እንደሚፈልግ ተናግሮ፣ ይህ የፈጠራ ሥራ ደግሞ በትክክል አብሮ የሚሄድና፤ ዘመናዊ የሊስትሮ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ አስታውቋል።

ሙሀባ፤ በከተማዋ በሚሰጡ የሊስትሮ አገልግሎቶች ላይ ጥናት ማድረጉንም ይናገራል። በጥናቱም ሥራ ላይ ያለው የሊስትሮ አሠራር አሮጌ መንገዶች እንዲበላሹ ምክንያት የሚሆን ብቻ አይደለም፤ አዲስ መንገዶችን ጭምር ለማበላሸት እንደሚችሉም ይገልጻል። አዲሱ የፈጠራ ሥራ መንገዶችን ይታደጋል፤ መንገዱ ሳይጎዳ ከተማዋን ስታንደርድ በጠበቀ መልኩ የሊስትሮ ሥራ ለመሥራት ይመቻል ብሏል።

በአንዳንድ የከተማ ቦታዎች በተለያዩ ድርጅቶች የተሠሩ ማስታወቂያ የተለጠፈባቸው የሊስትሮ ሥራ የሚካሄድባቸው ግንባታዎች፣ ለባለሊስትሮው ጥቅም ሊሰጡ ቢችሉም መንገዱን ግን እያፈረሱ ነው ሲል ይጠቁማል። የመንገዱም ሆነ የከተማዋን ጽዳትና ውበት በጠበቀ መልኩ ሥራው እንዲቀጥል ከተፈለገ ደግሞ ዘመናዊ ሥራ ማምጣት ያስፈልጋል ሲል አስገንዝቦ፣ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት የፈጠራ ሥራውን መሥራቱን ይናገራል።

‹‹የፈጠራ ሥራው ከአልሙኒየም እና ከብረት የተሠራ ሲሆን ለሊስትሮ የሚያስፈልጉ ሙሉ እቃዎችንም እንዲይዝ ተደርጓል። የሊስትሮ ሥራ እንደ ሌሎቹ (የጸጉር እና መሰል) የሥራ ዘርፎች ዘመናዊና የውበትና የጽዳት ማሰልጠኛ ተቋም ኖሮት ሊሠራ የሚችል እንዲሆን እፈልጋለሁ።›› ያለው ሙሀባ፣ ‹‹በርግጥ ሥራው ቀላል ቢሆንም በባለሙያ ቢሰጥ ከከተማ ስታንደርድ ጋር አብሮ የሚሄድ ስልጡን የሊስትሮ ባለሙያ እንዲኖር ያስችላል›› ይላል።

ሙሀባ እንዳብራራው፤ የፈጠራ ሥራው ስምንት ዓይነት ዲዛይኖች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ያሉት በፕሮቶታይፕ ደረጃ ተሰርተዋል። ዲዛይኑ ሲዘጋጅ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ መቀመጥ እንዲችል ተደርጎ ነው፤ ሁሉንም ደረጃዎች የሚይዝ ከሆነ የሚፈለገውን አገልግሎት በሚፈለገው ቦታ ለመስጠት በእጅጉ አመቺ ይሆናል።

የፈጠራ ሥራውን በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› ኤክስፖ ላይ አቅርቦት ብዙ ሰዎች እንደወደዱትና ጥሩ ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶች እንዳገኙበትም ሙሀባ ተናግሯል፤ በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላትም እንዲሁ ሥራውን በጣም እንደወደዱት እና እሱ ያላያቸውን ገንቢ አስተያየቶች እንደሰጡትም አመላክቷል።

ከአዲስ አበባ ጽዳትና ውበት ቢሮ የሚመለከታቸው አካላት የፈጠራ ሥራውን አይተው አብረውት ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን እንደገለጹለትም ነው ሙሀባ የሚናገረው። ‹ብድር አግኝተህ የምትሠራ ከሆነ አሁን ቦታውን ለመፍቀድ ዝግጁ ነን› እንዳሉት ገልጿል። አዲሱ የፈጠራ ሥራ ‹‹የጸዱ ኢትዮጵያን›› አላማ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ጠቅሶ፣ በሰዎች መጎብኘቱ እንዳበረታተውም አመልክቷል። ‹‹ሰው የሰጠኝን አቀባባል ስመለከት እኔ የሰራሁት ሥራ እያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ እንዳለ ነው የተሰማኝ፤ ይህም ተስፋዬ እንዲለመልምና ወደፊት እንዲቀጥል ብርታት ሆኖኛል፤ ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶችንም ማግኘት አስችሎኛል›› ይላል።

በውበትና ጽዳት ላይ የፈጠራ ሥራ ለመሥራት የያዘውን መነሻ ሃሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ መሥራት ከጀመረ ስምንት ወራት እንዳስቆጠረ ነው ሙሀባ የሚያስረዳው። ከሰባት ዓመት በፊትም ይህን የሊስትሮ ፈጠራ በሌላ ዲዛይን መሥራቱን አስታውሶ፤ ‹‹ሥራ በሀገራችን፣ በክልላችን፣ በወረዳችን፣ በቀበሌያችን ፣ በቤታችን ፣ በውስጣችን አለ›› የሚል መሪ ቃል ይዞ በቀላሉ አካባቢው ላይ ሥራ ማግኘት እንደሚቻል ለማሳየት ሞክሮበት እንደነበር አስታውሶ፣ ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ እንደተወው ያስታወሳል። አሁን ላይ ጊዜው ደርሶ የአስተሳሰብ ለውጦች በመምጣታቸው ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ አሻሽሎ በማቅረቡ ቶሎ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደቻለ አስታውቋል።

ወጣት ሙሀባ፤ ቀደም ሲል ሌሎች ችግር ፈቺ የፈጠራ ሃሳቦቹን በመጠቀም አዲስ የመማሪያ ወንበር ፈጠራ ሰርቶ እንደነበር ያስታውሳል። ከኤል ኬጂ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚማሩበት እና አካል ጉዳተኞች ጭምር ታሳቢ ያደረጉ ዘጠኝ ዓይነት ዲዛይን ያላቸው አዲስ የመማሪያ ወንበሮች መሥራቱን ይገልጻል። ይህን ለመሥራት የተነሳሳበት ዋነኛ ምክንያት የትምህርት ጥራት ላይ የሚነሱ ችግሮችን ሙያው በሚፈቅደው መሠረት የሚጠበቅበት ለመወጣት በማሰብ እንደሆነ ያመላክታል። በዚህ የፈጠራ ሥራው ከአእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት መብት ማግኘቱንም አስታውቋል ።

የፈጠራ ሥራው ካለው ተፈላጊት አንጻር ሲታይ በሚፈለገው ልክ ገበያ ውስጥ መግባት እንዳልቻለም ይገልጻል። ለዚህ ምክንያቱ ለፈጠራ ሥራሠቀደም ሲል እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱ መሆኑን ይገልጻል። ከሁለት ዓመት ወደፊት ግን ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሶ፤ የፈጠራ ሥራው ወደ ገበያው እንዲገባ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑን አመላክቷል።

ሙሀባ፤ አዲሱ የፈጠራ ሥራ ከተሠራበት ቁሳቁስ ሁሉንም አካትቶ የያዘ በመሆኑ በዋጋ ደረጃ እንደየዲዛይኑ ዓይነት የተለያየ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ከ18ሺ እስከ 21ሺ ብር እንዲሸጥ ይፈልጋል። ይህ ዋጋ አዋጭ ሆኖ ሳይሆን አገልግሎት ከሰጠው በማንኛውም መልኩ ገቢ ማግኘት እንደሚችል አስቦ ነው።

ችግሩን አግኝተነዋል፤ እንዴት አድርገን ህብረተሰቡ ዘንድ እናድርሰው የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት። አንድ ፍሬ ከመሸጥ ከብዛት ላይ የሚገኘው ትርፍ ተመራጭ ነው ሲል ገልጾ፣ ‹‹በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንዲውል እፈልጋለሁ። ከአንዱ 50 ብር ከማገኝ ከብዛት ላይ ሁለት ብር ባገኝ እመርጣለሁ ሲል አስታውቋል።

ዓላማው ህብረተሰቡ ሲጠቀም ማየት መሆኑን ጠቅሶ፣ የዚያን ጊዜ እኔም ተጠቃሚ እሆናለሁ፤ ይህ ካልሆነ ግን ፈጠራው ሰው ሊያደንቀው ቢችልም፤ ተቆልፎበት ከተቀመጠ ገበያው ውስጥ ካልገባ በከንቱ ይቀራል›› ሲል ያስረዳል።

በፈጠራው ሥራው ከተሰሩት ስምንት ዲዛይኖች ውስጥ ሰዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ታስቦ ክፍት የተደረጉ መኖራቸው ያነሳው ሙሀባ፤ ሰዎች ይህን ብታሻሽለው፤ እንዲህስ ብታደርገው በማለት የሰጡት አስተያየት እሱ ልብ ብሎ ያላያቸውን እንዲመለከት እድል እንደፈጠሩለት አመላክቷል።

በቀጣይም የከተማ ጽዳትና ውበት ዲዛይኑን በሚገባ ከገመገመ በኋላ የተሰጠውን አስተያየት ጨምሮ ብዙ ሳይደክም በቀጣይ ለሚሰራው ሥራ እንዲያስብበትና በዚያ መልኩ እያስተካከለ ተደራሽ እንደሚያደርግ አስረድቷል።

በፕሮቶታይፕ ደረጃ የቀረቡት ሦስቱ ዲዛይኖች ተገምግመው በተሰጠው አስተያየት መሠረት የተወሰኑ ነገሮች ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ እንደሚችል ጠቅሶ፤ የተቀሩት ክፍት የተደረጉት ዲዛይኖች ደግሞ በከተማ ጽዳትና ውበት አስተያየት ተገምገመው እንዳለቁ ወደ ሥራ እንዲሚገቡ አስታውቋል።

ሙሀባ እንደሚለው፤ አዲሱ የፈጠራ ሥራ በሁለት ዓይነት መልኩ ተግባር ላይ እንዲውል ታስቧል። አንደኛው ጽዳትና ውበት መንግሥት የያዘው የራሱ የሆነ ነገር እንደሚኖር በማመን አብሮ ለመሥራት ዝግጁ የሆነበት ነው፤ በየመንገዱ ዳር ማስታወቂያ የሚያስለጠፉ ድርጅቶች ወጣቶችን የሚረዱበት ሁኔታ ለማመቻቸት አስቧል። ሁለተኛው ስፖንሰር ማድረግ የሚፈለጉ አካላት ድጋፍ በመጠየቅ በስፖንሰር እንዲሸፈን የሚደረገበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ነው።

ይህ ሊስትሮ ተንቀሳቃሽ እንዲሆን የተደረገበት ዋንኛ ምክንያት ቦታው እንዲጸዳና ንጽህ እንዲሆን ታስቦ ነው። አንድ ቦታ ላይ የተተከለ ከሆነ ግን የተለያዩ ነገሮች ስለሚጣልበት ሊቆሽሽ ይችላል ፤ በዚህ የተነሳም ማራኪነቱንና የቦታውን ውበትም ሊያሳጣው ይቻላል። ሊስትሮው የሚሰራው ሰው የሊስትሮ ሥራውን እንደጨረስ ቢፈልግ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ሊያስቀምጠው ይችላል፤ ካልሆነም ደግሞ እንደሻንጣ የሚተጣጠፍ በመሆኑ አጣጥፎ ወደ ቤቱ ይዞት ሊሄድ ይችላል።

እንደ ዲዛይኖቹ ዓይነት አሠራራቸው የተለያየ በመሆኑ የሚቀመጡበትን ቦታ ሊመጥን የሚችል ዲዛይን ለመፍጠር ታስቦ የሁሉም ዲዛይን እንዲለያይ መደረጉን ተናግሯል። ሊስትሮ የሚሠራው ሰው ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንደልቡ እንዲንቀሳቀስ ያስችለዋል። ለአብነትም እንደ ሸራተን አዲስ፣ መስቀል አደባባይና ቦሌ አየር መንገድ አካባቢ ሊቀመጥ የሚችል ሊስትሮ የተለየና የአካባቢውን ደረጃ የሚመጥን መሆን አለበት›› ይላል።

ሙሀባ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በወረቤ ከተማ ዲጆ ኢንተርፕራይዝ የተሰኘ ድርጅት መስርቶ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። አሁን ላይ በዲጆ ኢንተርፕራይዙ አማካኝነት 15 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። ይህ የፈጠራ ሥራ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ተመዝግቦ የባለቤትነት መብት ለማግኘት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሶ፤ አዲሱን የፈጠራ ሥራ ወደ ተግባር ለመቀየር ጊዜ በመስጠት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ያመላክታል።

የፈጠራ ሃሳብ ሁሉም ሰው ዘንድ በተለይ ወጣቱ ጋር አለ የሚለው ሙሀባ፤ ሃሳብ አውጥቶ ወደ ተግባር መለወጡ ላይ እንጂ የፈጠራ ሃሳብ እያንዳንዱ ሰው በአእምሮ ውስጥ እንዳለው ያነሳል። በአሁኑ ወቅት ለፈጠራ ሃሳብ መነሻ የሚሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች እንዳሉም ይገልጻል። አብነትም ሲጠቅስ፤ ‹‹‹‹የሌማት ቱሩፋት›› የሚለው ርዕስ ጉዳይ ሲነሳ የኔ ድርሻ ምንድነው እዚህ ላይ ምን ልሰራ እችላለሁ የሚለውን በማሰብ ከእኔ ጋር አብሮ የሚሄድ ሥራ ለመሥራት አስባለሁ፤ ይህም በፈጠራ ሥራ ሂደት ውስጥ የፈጠራ ሥራ ሃሳብን መሸጥና መለወጥ ይቻላል ብዬ እንዳምን አድርጎኛል›› ይላል።

ቴክኖሎጂ ዕለት ተዕለት በፍጥነት እየተለዋወጥ እንደሚሄድ ጠቅሶ፣ ከዚህ ጋር አብሮ ለመጓዝ የሚያስችል የፈጠራ ሃሳብ እንዲኖር ማድረግ የግድ እንደሚልም ያመላክታል። ለዚህም የወጣቱን የፈጠራ አቅም ተጠቅሞ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል ሲል ተናግሯል።

በቀጣይም ዲጆ ኢንተርፕራይዝን ደርአርባ ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ እንዲሸጋገር እንደሚደረግ አስታውቆ፣ ደርአርባ ማለት እስከ አርባ ድረስ የሚደርሱ አዳዲስ ፈጠራዎችን እየፈጠሩ መሥራት የሚችል እንዲሆን ማድረግ ነው ሲል ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ሃሳቡን አጠቃሏል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You